‹‹ሁሉም ደራሲዎች ፀሐፊዎች ናቸው፤ ሁሉም ፀሐፊዎች ግን ደራሲ ላይሆኑ ይችላሉ›› የሚባል ማብራሪያ አለ:: የዚህ ማብራሪያ መልዕክት ጽሑፎችን አደራጅቶና ሰብስቦ በመጽሐፍ መልክ ያሳተመ ሁሉ ደራሲ ይባላል ማለት ነው:: በእርግጥ ይህን የሚለው የእንግሊዘኛው ማብራሪያ ነው:: ወደ አማርኛው ማብራሪያ ስንመጣ፤ ደራሲ ማለት ፀሐፊ ማለት ነው::
በአገራችን ልማዳዊ አተያይ ደራሲ የሚባለው የግድ ታዋቂና ዝነኛ ደራሲ ብቻ ይመስለናል:: የምንመዝነውም በቀድሞዎቹ ታዋቂ ደራሲዎች ስለሆነ በረጃጅም ልቦለድ ነው:: ከቅርብ ጊዜ የተለመዱት ግለታሪክ (አውቶ ባዮግራፊ) እና ወጎች እንደ ቀድሞዎቹ ረጃጅም ልቦለዶች አልሰረጹም::
በአጠቃላይ፤ ሳይንሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ በየትኛውም ሙያ ላይ የሚያተኩር ሙያዊ መጽሐፍ ሁሉ ፀሐፊው ደራሲ ተብሎ ነው የሚጠራ::
ይህን ለማለት የቻልኩበት ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ አይነት መጽሐፎች እየበዙ ስለመጡ ነው:: ከረጃጅም ልቦለዶች ይልቅ ሰዎች የሕይወት ገጠመኞቻቸውን እየጻፉ ነው:: ብዙ የፖለቲካና የማህበራዊ ሕይወት ውጣ ውረድ ያሳለፉ ደግሞ ግለ ታሪካቸውን እየጻፉ ነው:: እነዚህ ሰዎች የሚጽፉት ለስነ ጽሑፍ ብለው ሳይሆን ያጋጠማቸውን ነገር ለተደራሲያን ለማጋራት ነው::
ከእንዲህ አይነት መጽሐፎች በቅርቡ ‹‹ሥውር ወግ›› የሚል መጽሐፍ ከእጄ ገባ:: ደራሲው ያለምዘውድ ይታየው ይባላል:: መጽሐፉ የታተመበት ጊዜ ኅዳር 2015 ዓ.ም የሚል ነው:: የመጽሐፉ የገጽ ብዛት 330 ሲሆን የመሸጫ ዋጋውም 330 ብር ይላል::
የመጽሐፍ መግቢያ የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ‹‹ጥበብ ጠርታኝ ሳይሆን ሕይወት በፈተናዋ ገፍታኝ ብዕሬን አነሳሁ›› ይላል:: ደራሲው በሙያው የምህንድስና ባለሙያ ነው:: በልጅነቱም በስነ ጽሑፍ ዘርፍ ውስጥ አልፋለሁ የሚል ምኞት ኖሮት አያውቅም:: እንዲጽፍ ያስገደደው በልጅነት አስተዳደጉና ተማሪ እያለ ያሳለፋቸውን የሕይወት ውጣ ውረዶች ናቸው::
የመጽሐፉ ይዘትም የሚናገረው የደራሲውን አስተዳደግና ውጣ ውረድ ነው:: እንዲያውም ደራሲው በስነ ጽሑፍ ዘርፍ ውስጥ ስላላለፈ እንደ ስነ ጽሑፍ አልቆጠረውም እንጂ ሳያውቀው መጽሐፉ ስነ ጽሑፍ ሆኗል:: ምክንያቱም በትረካው ውስጥ የአገር ቤት የአነጋገር ዘይቤዎች፣ አካባቢያዊ (በተለምዶ ቀበሌኛ) ቃላት አሉ:: በስነ ጽሑፍ ውስጥ እንደ ንግግር ማጣፈጫ የሚያገለግሉት ምሳሌያዊ አነጋገሮችና ፈሊጣዊ ንግግሮች አሉበት::
መጽሐፉ የአገር ቤት ወጎችን ይነግረናል:: እነዚህን ወጎች የሚያውቃቸው ምናልባትም በገጠሩ የአገራችን ክፍል ያደገ ሊሆን ይችላል:: ደራሲው በቀጥታ ባደገበት ማህበረሰብ ውስጥ እያየውና እየሰማው ያደገውን ነው የጻፈው:: የመጽሐፉ መቼት በሰሜን ምዕራብ የአገራችን ክፍል ያለውን የጎጃም አካባቢ ወግና ልማዶች የሚያሳይ ነው::
የአንድን አካባቢ ማህበረሰብ ወግና ልማድ ማወቅ ወይም የአንድን ግለሰብ ውጣ ውረድ ማወቅ በዚያ ውስጥ የራሳችንንም ሕይወት እንዲናገኝ ያደርጋል:: በምን አይነት መንገድ ተምረው እዚህ እንደደረሱ ያሳያል:: ያ ደግሞ ለሌሎችም አርያ ይሆናል ማለት ነው::
የሕይወቱን ወጣ ውረድ አስተማሪነት ምናልባትም የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየቀረቡ ከሚናገሩት እናገኝ ይሆናል:: እንዲህ በመጽሐፍ መልክ ሲሆን ግን ተደራሽነቱ ይሰፋል:: ሌሎች ሰዎችም የየራሳቸውን እንዲጽፉ ያነሳሳል::
ስለዚህ እንዲህ አይነት ጀማሪ ፀሐፊዎችን ልናበረታታ ይገባል:: ደራሲ ሲባል የግድ ስመ ገናና የሆኑት ብቻ ከመሰለን ስህተት ነው:: በውጭው ዓለም በአንዲት ነጠላ ጉዳይ ላይ ብቻ ግዙፍ መጽሐፍ ይጻፋል:: በአገራችን ግን ይህ የተለመደ አይደለም:: ብዙዎች ‹‹መጻፍ አልችልም፣ እኔ ደራሲ አይደለሁም፣ እኔ የስነ ጽሑፍ ተማሪ አይደለሁም…›› በሚል መጽሐፍ ለመጻፍ አይነሳሱም::
ከዚህ ልማድ ልንላቀቅ ይገባል:: ሐኪሙም፣ መሐንዲሱም፣ የሕግ ባለሙያውም፣ ግንበኛውም ደራሲ
መሆን ይችላሉ:: ምክንያቱም እነዚህ የተጠሱ ሰዎች ሁሉ ሀሳብ አላቸው:: መጽሐፍ ደግሞ ሀሳብ እንጂ ሌላ አስማታዊ ነገር አይደለም:: ለቋንቋና ስነ ጽሑፍ ተመራቂዎች ብቻ የተተወ ሙያ አይደለም:: ማንም ሰው ያየውን፣ የሰማውን፣ ያጋጠመውን ሁሉ ቢጽፍ ሀሳቦች ይንሸራሸራሉ ማለት ነው::
ስለዚህ እንዲህ አይነት ከስነ ጽሑፍ ዘርፍ ውጭ ያሉ ሰዎች ሲጽፉ በርቱ እንላለን::
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015