ወቅቱ እንደ አሁኑ የአማርኛ ፊልም እንደ አሸን የፈላበት አልነበረም:: እንዲያውም ፊልም ምን እንደሆነ የማይታወቅበት የገጠር አካባቢም ሊኖር ይችላል:: ምክንያቱም በወቅቱ ቴሌቭዥን በከተሞች ብቻ የተወሰነ ነበር፤ ሲኒማ ቤቶችም የሉም::
ከ28 ዓመታት በፊት በ1987 ዓ.ም ‹‹ፀፀት›› የተሰኘ ፊልም ተሰርቶ ነበር:: ይህ ወቅት በኢትዮጵያ የደርግ ሥርዓት ተወግዶ፣ ኢህአዴግ አገሪቱን ተቆጣጥሮ የሽግግር ጊዜውን ጨርሶ የአገሪቱ መንግሥት የሆነበት ነበር::
በዚህ ወቅት ዛሬ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ዘርፍ የእቅድና ፕሮግራም ኃላፊ ሆነው የምናውቃቸው፤ የያኔው ወጣት አለባቸው ደሳለኝ ‹‹ፀፀት›› የተሰኘ ፊልም ደርሰው፣ በተስፋዬ ስንቄ አዘጋጅነት፣ በእሩቅያ አህመድ ፕሮዲዩሰርነት ለዕይታ አበቁ:: የፊልሙ ደራሲ ዛሬ ደግሞ በዲያስፖራው ዘርፍ አገራቸውን እያገለገሉ ነው፤ ለዚህም መንግሥት በቅርቡ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል::
ወደ ፊልሙ ስንመለስ፤ ፊልሙ የፍቅር ፊልም ነው፤ የሁለት ሰዓት ርዝማኔ አለው:: መልካሙ ተበጀ፣ አበበ አዲስ፣ ቤተልሔም አሰፋ፣ ኩራባቸው ወልደማርያም፣ ተስፋዬ ሲማ፣ ፍቃዱ ተክለማርያም እና ቻቺ ታደሰ በተዋናይነት ተሳትፈውበታል::
ፊልሙ የአገራችንን ማህበራዊ ሕይወትና ልማድ የሚያሳይ ነው:: እንደ አሁኑ ብዙ አይነት ፊልሞች ከመሰራታቸው በፊት የኢትዮጵያን የበቀል ልማዶችም የሚያሳይ ነው:: ውስብስብ የፍቅር ታሪክ ነው::
በገሃዱ ዓለም እንደምናየው በፍቅር ግንኙነት ውስጥ፤ ከተለያዩ ፍላጎቶች አንፃር በቀሎች ሲፈጸሙ እናያለን:: በፀፀት ፊልም ውስጥ እነዚያን ክስተቶች እናያለን::
ለጊዜው የጽሑፋችን ዓላማ ይዘቱን መተንተን አይደለም:: ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዕይታ መምጣቱን እና ፊልሙ ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዕይታ ሲመጣ ዓድዋን ለመዘከር ይዞት የመጣውን ዓላማ ማሳወቅ ነው:: ፊልሙ ባለፈው ቅዳሜ በሀገር ፍቅር ቴአትር መታየት የጀመረ ሲሆን አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ አንፃር፤ መቼ መቼ እንደሚታይ በአዘጋጆች ይነገራል ተብሏል::
የፊልሙ ደራሲ በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው አገራዊ ሁኔታ ተገፍቶ ከአገር ወጣ፤ ከአገር ለመውጣቱ ግን የፊልሙ ይዘት ምንም ድርሻ አልነበረውም:: ዳሩ ግን ደራሲው ከአገር ከወጣ በኋላ ከፊልሙ ይዘቶች ውስጥ ፀጉር መሰንጠቅ ተጀመረ::
በተለይም ገጸ ባህሪያቱ የያዟቸውን ስሞች በማውጣት ይህ ስም ይህን ብሔር የሚወክል ነው፤ ሀሳቡም እንዲህ ለማለት ነው በሚል የፖለቲካ ውክልና የሰጡትም አልጠፉም:: በነገራችን ላይ በንጉሣዊ ሥርዓቱና በደርግ ጊዜ በግልጽ መንግሥትን መተቸት አይቻልም ነበር ይባላል:: በዚህም ምክንያት በወቅቱ ይዘፈኑ የነበሩ ዘፈኖች በቅኔ ነው:: ለፍቅረኛ የዘፈኑ በማስመሰል ለሀገር ይዘፈናል::
በዚህ ልማድ ውስጥ የመጣው የወቅቱ ሥርዓትም ነፃነትን አጎናጽፌያለሁ ቢልም ዳሩ ግን መጠራጠሩና እንዲህ ለማለት ተፈልጎ ነው የሚል ትርጉም ፍለጋው ግን አልቀረም:: ያም ሆኖ ግን ደራሲው ራሱ እንደተናገረው ከአገር የወጣው ከፊልሙ ጋር በተያያዘ ጉዳይ አይደለም::
ፊልሙ የሚታየው የዘንድሮውን የዓድዋ በዓል በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች፣ እንዲሁም ከአገር ውጭ ደግሞ በአሜሪካና አውሮፓ ጎዳናዎች በኩራት ለማክበር ነው:: ዓድዋም ከመበሻሻቂያነት በማውጣት የሁሉም ጥቁር ሕዝቦች የኩራት አርማ መሆኑን ማሳየት ነው::
ደራሲው አለባቸው ደሳለኝ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዓድዋ የእገሌ የሚባል አይደለም:: እንዲያውም የጥቁር ሕዝቦች ብቻ እንኳን የሚባል አይደለም:: ለነጮች ሁሉ ነፃነትንና እኩልነትን ያስተማረ ነው:: እንደ ሰው ልጅ ማሰብን ያስተዋወቀ ነው:: በሰው ልጆች ውስጥ፤ ባሪያና ጌታ፣ ነጭና ጥቁር፣ የበላይና የበታች፣ ገዢና ተገዢ… የሚባል መደብ መኖር እንደሌለበት ያሳየ ነው::
ዓድዋ ነጩ ሕብረተሰብ ራሱን እንደገና እንዲያይ፣ ፖሊሲውን እንዲፈትሽ ያደረገ ነው:: ዓድዋ ዓለም አቀፍ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ ነው::
ስለዚህ ኢትዮጵያ ያገኘችው ይህ የዓድዋ ድል በዓለም አቀፍ ደረጃ መታየትና መመዝገብ ስላለበት የፀፀት ፊልምን ማየት ይህን የዓድዋን በዓልም እንደማሳየት ነው፤ አገርን ማስተዋወቅ ነው::
በ1987 ዓ.ም በታተመ ጦቢያ መጽሔት ላይ እንደተገለጸው፤ ፀፀት ፊልም በዚያን ወቅት ባለቀለም ፊልም ነበር:: በወቅቱ በእንግሊዝ አገር ታይቷል:: እዚያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ፊልሙን በማየት የአገራቸውን ሁኔታ በናፍቆት እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል:: ፊልሙን ለመጻፍ ሁለት ዓመት እንደወሰደበት ደራሲው በወቅቱ ለጦቢያ መጽሔት ተናግሯል::
እነሆ ከዚያ በኋላ እንግዲህ የፊልም አብዮቱ እየጎረፈ መጣ:: አሁን ላይ የጥራትና የይዘት ተመሳሳይነት ችግር እንጂ በአገራችን የፊልም ብዛት ችግር እንደ ወቀሳ ሲነሳ አይሰማም:: ስለዚህ ቀደም ሲል ፊልም ይሰሩ የነበሩና ለብዙ ዓመታት በብዙ አገራት ልምድ ያላቸው ትልልቅ ሰዎች ወደ ፊልሙ ኢንዱስትሪ ቢገቡ እንላለን:: ቢቻል ፊልም ቢሰሩ፤ መሥራት ባይችሉ (ባይፈልጉ) እንኳን ግን ቢያንስ ምክረ ሀሳብ ቢሰጡ እንላለን::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015