መዳረሻዬ ሽሬ እንዳስላሴ ነው። ለዘገባ ሥራ ከባህርዳር- ጎንደር- ደባርቅ- ሽሬ መንገድ ከሚዲያ ባልደረቦች ጋር እየተጓዝኩ ነው። የጥምቀት ሙሽራዋ ጎንደር እየተኳኳለች ነበር። ደባርቅ ከመድረሴ በፊት ዳባት ትገኛለች-የደጃች አያሌው ብሩ ቁርቁር ከተማ። ደጃች አያሌው ትውልዳቸው በጌምድር ጋይንት ቢሆንም ግዛታቸውና ኑሯቸው ዳባት ነበር። ሞገደኛው ደጃዝማች አያሌው ብሩ በጎንደር ማኅበረሰብ ዘንድ ዝናቸው የናኘ ነው።
ደጃዝማች አያሌው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ (ከልጅ ኢያሱ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት) ታሪካዊ ክንውኖች ጉልህ ተሳትፎ አላቸው። አንዷን ብቻ ልምዘዝ። ራስ ተፈሪ ‘ንጉሠ-ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ’ ደጃች አያሌው የቅርብ ዘመዳቸውን ራስ ጉግሳ ወሌ ብጡልን (የንግሥት ዘውዲቱን ባለቤት) ወግተው የጎንደር ግዛት ‘ራስ’ ተብለው ለመሾም ቃል ቢገባላቸውም፤ ተልዕኳቸውን ተወጥተው ቃሉ ባለመፈጸሙ ደጃዝማቹ ከአጼው ጋር መቀያየማቸው አልቀረም። በዚህም:-
“አያሌው ሞኙ፣ ሰው አማኙ ሰው አማኙ፣
የአያል ጠመንጃ፣ ስሟን እንጃ ስሟን እንጃ…” በማለት የጎንደር አዝማሪ አዚሟል። ዛሬም ይህ ግጥም የብዙ ባህላዊ ዘፈኖች አዝማች ነው።
ደጃች አያሌው ብሩ ደፋር ናቸው ይባላል። ከአጼ ኃይለሥላሴ ጋር ቢቀያየሙም በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ሲመጣ ቅድሚያ ለአገሬ ብለዋል። ‘የተደበቀው ማስታወሻ’ በተሰኘው የዶክተር ሀራልድ ናይስተሮም (ትርጉም ገበየሁ ተፈሪ እና ደሳለኝ አለሙ) መጽሐፍ እንደተጠቀሰው ደጃች አያሌው “ንጉሡ እንደኛ ሰው ናቸው። ኢትዮጵያ ግን የሁላችንም ናት” ብለው ጦራቸውን መርተው በሽሬ ግንባር ዘምተዋል።
ጉዟችን ቀጥሏል። ደባትን እያለፍን ነው። ‘እንኳን ደህና መጡ፤ ወደ ጭና ታሪካዊቷ ሥፍራ’ የምትለዋን ታፔላን በስተግራ እያየን ወደ ደባርቅ ገሰገስን። የሰሜን ተራሮች የብርድ ወጨፎ ያረሰረሳትን ደባርቅን ከማለፋችን ሊማሊሞ ጠመዝማዛ ቁልቁለት ተቀበለን። አስፈሪ የሊማሊሞ መልክዓ ምድር የደጋው ሰሜን ውርጭ እና የተከዜ በርሃ ኬላ ነው። ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረመድህን
“የሰማይ የምድሩ ኬላ፣ የየብስ የጠፈሩ ዋልታ
አይበገር የዐለት ጣራ፣ አይመክተው መከታ
ሊማ-ሊሞ አድማስ ሰበሩ፣ በጎማ ፈለግ ይፈታ?
በትሬንታ እግር ይረታ?…” ብሎ የመኪና መንገድ ተገንብቶበት በማየቱ ግርምቱን የተቀኘለትም ለዚህ ይመስላል።
ከሊማሊሞ ቁልቁለት በኋላ አዲ-አርቃይ፣ ዛሪማ፣ ማይፀብሪ እና ሌሎች የጠለምት ወረዳ ከተማዎችን አልፈን፤ የዋልድባ ረባዳማ አካባቢዎችን ተሻግረን ተከዜ ወንዝ ደረስን። የዚህን መንገድ እና ተከዜ ወንዝን ሳስብ የሀዲስ ዓለማየሁ ትዝታ አስተከዘኝ። የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር የወገንን ጦር ፊት ለፊት መቋቋም ሲሳነው በሰው ልጆች ላይ ተደርጎ የማያውቅ መርዝ በጅምላ የፈጀበት አሳዛኝ ታሪክ ነበር። በተከዜ ወንዝ ውሃን በመመረዝ የወገን ጦር ያለቀበት ሥፍራ ነው። የተከዜ ሸለቆ በኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት ዋጋ የተከፈለበት ነው። ሀዲስ ዓለማየሁ በአንድ ዕለት የተመለከቱትን እንዲህ ጽፈውታል።
“የተከዜ ውሀ እመሻገሪያው ላይ ሰፊና ፀጥ ያለ ነው። ታዲያ ያ ሰፊ ውሀ፤ ገና ከሩቅ ሲያዩት ቀይ ቀለም በከባዱ የተበጠበጠ ይመስላል። “ምን ነገር ነው፤ ምን ጉድ ነው?” እየተባባልን ቀረብ ስንል መሻገሪያው በቁሙም በወርዱም ከዳር እስከ ዳር ሬሳ ሞልቶበት የዚያ ሬሳ ደምና ፈርስ ነው። የሰው ሬሳ፣ የፈረስ እና የበቅሎ ሬሳ፣ ያህያ ሬሳ፣ ያውሬ ሬሳ፣ ሬሳ ብቻ! እግር ከራስ ራስ ከእግር እየተመሰቃቀለ እየተደራረበ ሞልቶበት፥ የዚያ ሁሉ ሬሳ ደምና ፈርስ ነው”። ይሉናል። ቀጥለውም
“በእውነቱ እንዲህ ያለውን መሳሪያ ምንም ጠላት ቢሆን በሰው ላይ ለማዋል የሚጨክን ሰው፣ ሰብዓዊ ስሜት የሌለው፣ አለት ድንጋይ የተፈጠረበት መሆን አለበት፤ እንዲህ ያለውን መሳሪያ በሰው ላይ ማዋል ሰብዓዊ ህሊና ሊሸከመው የማይችል እጅግ ከባድ መሆኑን ዓለም ሁሉ ያወቀውና ያወገዘው በመሆኑ የኢጣሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ከማድረጉ በቀር “ሌላ መንግሥት በሌላ አገር ላይ አደረገ’ ሲባል ተሰምቶ የሚያውቅ አይመስለኝም” ብለዋል።
ከተከዜ ባህር ማዶ ጉዞዬ ያገኘኋት ሌላዋ ታሪካዊ ሥፍራ እንዳባጉና ናት። እንዳባጉና የወገን ጦር ትልቅ ገድል የፈጸመበት ነው። ጀግኖች አባቶቻችን የጠላት ታንክ ሳያስፈራቸው የጠላት ጅምላ ጨራሽ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ተቋቁመው ጠላትን ድባቅ የመቱበት፤ ወደ አክሱም እንዲያፈገፍግ ያደረጉበት ሥፍራ ነው። “የጠላት ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በጦር ሜዳው ትንንሽ ቦምቦች አውቶማቲክ ጠመንጃ ይተኩስ ነበር። አቢሲኒያኖች ደግሞ ከጠላት ጋር ግብግብ ገጥመው ጉዳይም አልሰጡትም ነበር…” ይላል ዶክተር ሀራልድ ‘የተደበቀው ማስታወሻ’ በተሰኘ መጽሐፉ።
ይህ አካባቢ በሀገር ፍቅር የነደዱ ኢትዮጵያውያን ደም ያፈሰሱበት፣ አጥንት የከሰከሱበት፤ ለኢትዮጵያ መስዕዋትነት የከፈሉበት ነው። ይህ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዋጋ የተከፈለበት ቀጣና ነው።
ቀኑ ተገባዷል። ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። እኔም የማሽላ ማሳዎችን ግራ ቀኝ እየተመለከትኩ ለዕለቱ መዳረሻችን ወደሆነችው ሽሬ ከተማ ገባን። ሽሬ በትግርኛ ‘ሽረ’ ሲሉት ይደመጣሉ። በእርግጥ ሽሬን ለመጀመሪያ ጊዜ መርገጤ ነው። ዕለቱም ጥር ሥላሴ ነው። ሽሬ በጥር ሥላሴ ትደምቃለች፤ ሙሉ ስሟም ሽረ እንዳስላሴ ነው።
የሽሬ ሥላሴ ጠበል
ሽሬ ደርሰን ማረፊያችንን ያዝን። ጊዜው በጣም አልመሸምና ከተማዋን በቀላሉ መቃኘት ይቻላል። ሽሬ ሰፊና ደማቅ የዞን ከተማ ናት። ከመካከላችን የአንደኛው ባለሙያ ቤተሰቦች ሽሬ ነበሩና አስጠሩን። ለሥላሴ ጠበል ግብዣ። ባል እና ሚስቱ ከልክ በላይ መስተንግዶ አደረጉልን። ‘ጠብ እርግፍ አድርገው አስተናገዱን’ ማለት ይቀላል። እንግዳ መቀበል ነባር ኢትዮጵያዊ እሴታችን ቢሆንም ጦርነት ውስጥ ለቆየ አካባቢ የተለየ መልክ ነበረው። እንግዳ አቀባበላቸው በእርግጥም የመሃል አገር ሰው የናፈቃቸው ይመስላል።
የተትረፈረፈ እህልና ውሃ አቅርበው በ’ብሉልን፤ ጠጡልን’ ተማጽኗቸው የተነፋፈቀ ቤተ-ዘመድ ግብዣ አስመሰሉት። የሥላሴው ጠበል የሽሬ ጠላ ቀረበ። የሽሬ ጠላ ሳስታውስ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ታወሱኝ። የወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምሀሩ ፕሮፌሰር ሽብሩ በዘመነ ደርግ በዕድገት በሕብረት ዘመቻ ተማሪዎቻቸውን ይዘው ሽሬ ዘምተው ነበር። በወቅቱ ታዲያ የሽሬ ጠላ ፍቅር ይዟቸው በየጊዜው ሲኮመኩሙ የተመለከቱ ሰዎች ‘ፕሮፌሰሩ ከጠፉ የሚገኙት ጠላ ቤት ነው’ ሲባሉ እንደነበር ‘ከጉሬ ማርያም እስከ አዲስ አበባ’ በተሰኘው ግለ ታሪካቸው አስፍረዋል።
ከግብዣ መልስ ከማረፊያ ሆቴል ላይ ሆኜ ከተማዋን ስቃኛት ከጦርነት ድባቴ የተላቀቀች ይመስላል። የአመሻሽ ሕዝቡ እንቅስቃሴም ሆነ እስከ ሌሊቱ አጋማሽ የሚሰሙ የመዝናኛ ቤቶች ሙዚቃዎች የከተማዋን አሁናዊ መልክ የገለጠልኝ ነበር።
ንጋት ላይ በቁርስና ቡና ሰዓታት ከሰዎች ጋር መስተጋብሬ ጀመረ። በጦርነት አዙሪት የከረመችው ሽሬና አካባቢው ኑሮ እጅጉን የከበደ ነበር። መልከ-ብዙ ማህበራዊ ቀውሶች አስተናግደዋል። አሁናዊ ምላሻቸው “ተመስገን፤ ያ ሁሉ አለፈ” የሚል ነው።
ገበያው ተረጋግቷል፤ ማህበራዊ ኑሮ ተመልሷል። ድህረ-ሰላም ስምምነት ለሽሬ ነዋሪዎች ሁለንተናዊ እፎይታን አንብሯል። ከቀናት በኋላ በአክሱም የታዘብኩትም እንዲህ ነው።
ኑሮን ያቀለለው የተቋማት አገልግሎት ጅማሮ
በመጀመሪያ ዘገባ ስራዬ መሰረተ ልማትን አገልግሎት ቃኘሁ። ባንክ፣ ቴሌ፣ ሆስፒታል… መሰሎቹን። ተጠቃሚዎችንም፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ ኃላፊዎችንም አነጋገርሁ። ከሰላም ስምምነቱ ማግስት ጀምሮ ተቋማቱ ወደስራ መመለሳቸው ከሁለንተናዊ ችግር እንደታደጋቸው ያነሳሉ። በትራንስፖርት እየተንቀሳቀሱ፣ በኤሌክትሪክ ስራዎቻቸውን እየከወኑ ነው። ለሁለት ዓመታት የተቋረጠው አገልግሎት አቅርቦት እና የአገልግሎት ፈላጊዎች ፍላጎት ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ የተጠቃሚዎችም፤ የአገልግሎት ሰጪዎችም ሃሳብ ነው።
በሽሬ ስሁል ሆስፒታል የተመለከትኳቸው፤ ያነጋገርኳቸው፤ ከታዳጊዎች እስከ አዛውንት ዕድሜ ያሉ ህሙማን የሰላም አየር ማግኘታቸው የሕይወታቸው ዑደት እንዲቀጥል አድርጓል። ድንገተኛም ሆነ ነባር ህመም ያለባቸው ሰዎች በነጻ እየታከሙ ነው ያገኘኋቸው። ሰላም ከሌለ መታከም ቀርቶ በቅጡ ማስታመም፤ በወጉ መቀበርም እንደማይቻል ገልጸውልናል።
የጤና፣ የባንክና የቴሌኮም አገልግሎት የግብዓት ክፍተቶች የማሟላት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም በፌዴራል ደረጃ በየተቋማቱ የተመደቡ አስተባባሪዎች አረጋግጠውልኛል። የጸጥታ አካሉና የህብረተሰቡ ትብብርም የሚያስቀና እንደሆነ ግለሰቦችም፤ የጸጥታ አካላትም ነግረውኛል። አክሱም ጺዮን ማርያም፣ ሽሬ ስላሴ ንግስ፣ የጥምቀት በዓላት ከሶስት ዓመታት በኋላ በአደባባይ ታቦት ወጥቶ ተከብሯል። የፌዴራል ፖሊስ ተወካዮችም ይህንኑ ነው ያረጋገጡልኝ። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከከተማ ነዋሪዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ቤተሰባዊ የሆነ ይመስላል። እንቅስቃሴያቸውም የሰላማዊ ቀጣና መልክ ያለው ነው፤ ዩኒፎርም ከመልበሳቸው በስተቀር ጀሌያቸውን ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ደግሞ መተማመን ከመፍጠር ባለፈ ጦርነት ውስጥ ለቆየ ማህበረሰብ ከስነ ልቦና ጫና እንዲላቀቅ አይነተኛ ሚና እንዳለው ይሰማኛል።
ኢ-መደበኛ የሽሬና አክሱም ወጎች
ያረፍኩበት ሆቴል ባለቤት ‘አደይ’ ተግባቢ ናቸው። ደግ እናት ይመስላሉ። ከገባን ጀምሮ ‘ጠላ ተጎንጩ፤ ቡና ጠጡ’ ጭንቃቸው ነው። ሁለት ቀን ቡና አስፈልተውልናል፤ ጠላ አቅርበው ዘክረውናል። ይህ ሁሉ ሲሆንም ለከተማው እንግዳ መሆናችንን እንጂ ስለሙያችንም ሆነ ስለሌላ ማንነታችን አያውቁም ነበር። ብዙ መጨዋወትና ውሎ አዳር በኋላ ነው ጋዜጠኛ ስለመሆናችን ያወቁት።
አደይ ተጫዋች ናቸው። አማርኛ ያዝ ቢያደርጋቸውም ጨዋታቸው ‘ኩርሽም’ ነው- ተሰምቶ የማይሰለች። በአጋጣሚ ‘ሰለክላካ’ ስለምትባለዋ ታሪካዊ ሥፍራ ጠይቄያቸው እያወጋን ነበር። ‘እንደእናንተ ወጣቶች ሳለን ‘ሰለክላካን ያላዬ ሸዋን ያመሰግናል’ ይባል ነበር። ታዲያ አንድ የሸዋ ሰው መጣና ሰለክላካን አየና ‘በቃ ይቺ ናት’ ሰለክላካ’ ብሎ ተገረመ” ብለው አሳቁን። (የፍቅር እስከ መቃብር መሪ ገጸ-ባህሪው ‘በዛብህ’ ወደ ዲማ ጊዮርጊስ ሄዶ ‘የዲማ መልኳ እና ዝናዋ’ ተጣርሶበት እንደተገረመበት ቅጽበት መሆኑ ነው)። አደይ የተጀመረው ሰላም ፍጹም ምሉዕ ሆኖ ወደ ቀደመ ኢትዮጵያዊ መልካችን የምንመለስበት ጊዜ እንዲመጣ ይሻሉ። ከጦር-ነት ወደ ሰላም-ነት!
ቆንጂዬዋ ፊዮሪ የኮሌጅ ተማሪ ነበረች። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ጀምሮ በኋላም በጦርነት ሳቢያ ትምህርቷን ካቆመች ሦስት ዓመታት ሆኗታል። ጦርነቱ ከቆመ በኋላ የጀበና ቡና ጀምራለች። ደንበኞቿ ሰብሰብ ብለን እንቀመጣለን። ፊዮሪ ከስኒ ማቅረቢያዋ ላይ አነስተኛ ጀበናዋን፤ የሚያማምሩ ስኒዎቿን እና መዓዛው ከሚያውድ የዕጣን ማጨሻዋ ጋር ሰድራ ይዛ ትቀርባለች። ከመካከላችን ካለው ጠረጴዛ ላይ ታስቀምጥና እርሷም ወንበር ይዛ ከመካከላችን ትቀመጣለች። ቡናው እስኪሰክን ጨዋታዋን ታስኮመኩመናለች።
ቡናው ከሰከነ በኋላ ቡናዋን ቀድታ ለእያንዳንዳችን በእጃችን እያነሳች ትሰጣለች። በሽሬ ቡና የሚቀርበው በዚህ መልክ ነው። ለፊዮሪ እና መሰሎቿ ጦርነቱ ክፉ ጠባሳ መጣሉ፤ ተስፋቸው ላይ መጥፎ አሻራ ማስቀመጡን ታነሳለች። አሁን ግን ብሩህ ተስፋ ሰንቃለች። ስለነገዋም “ሰላሙ ይዝለቅልን፤ ትምህርቴን ለመቀጠል እመኛለሁ” ትላለች።
አክሱም ከሽሬ በስተሰሜን 60 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ከሽሬ አክሱም ስንንቀሳቀስ ከጥምቀት ዕለት በስተቀር ገበሬው የግብርና ሥራዎቹን እየከወነ ነበር። አርሶ አደሩ ያርሳል፤ መስኖውን ያለማል። የተዘራውን ውሃ ያጠጣል። የበቀለ ቡቃያውን ይኮተኩታል። ከጦርነት ወደ ልማት መዞሩን ዐይኔ ታዝቧል።
በጥምቀት ዋዜማ፤ የከተራ በዓል ዕለት ሁለት ጎራማይሌ የረፋድ ትዕይንቶችን ላንሳ። ከአክሱም ከተማ ወደ አድዋ እና ሽሬ መገንጠያ አካባቢ ሰፊ የቀንድ ከብት ገበያ ነበር። እውነተኛ የዓመት በዓል ገበያ መልክ ያለው ትዕይንት ነበር። በተለይም የፍየል ዋጋ በተመጣጣኝ ዋጋ እየተገበያዩ እንደነበር ሰምቻለሁ።
ታሪካዊቷን አክሱም ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ የረገጥኳት/የተሳለምኳት ከአራት ዓመት በፊት በ2011 ዓ.ም ይመስለኛል። ከገበያው ቀጥሎ በታቦተ-ጽዮን መገኛዋ ርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ደጅ፣ በጥንታዊያኑ የአክሱም ሐውልት መገኛ አደባባይ ነበር። ከጽዮን በስተምዕራብ በአርባቱ እንሰሳ በኩል፤ በቅዱስ ያሬድ ዋርካ… አድርጌ በጽዮን ዋናው በር ደረስኩ። ማራኪ የአክሱም የኮብልስቶን መንገዶች ኦና ናቸው። የወትሮው ግርግር ናፍቋቸዋል።
ከጽዮን ቅጥር ግቢ በዋናው በር በስተውጭ አነስተኛ እና ብቸኛ ዋንዛ በኮብልስቶን መሃል ነበረች። ዛሬም ለምልማ አለች። በዚህ አካባቢ ድሮ የነጭ ጎብኚ ጋጋታ፣ የጽዮን ደጅ ጠኚ ምዕመን… የተጨናነቀ ነበር። እንደ ድሮው የፎቶ አንሺ ግርግር፣ የአክሱም መስቀል ቀርጸው የሚሸጡ ወጣቶች ጫጫታ የለም። ይልቁንም እርጥባን የሚሹ አቅመ ደካሞችና ህፃናት ነበሩ። ጦርነት የሥፍራዋን መልክ አጠይሞታል። ያም ሆኖ ከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በኩሉሄ ባይባልም ወደነበረበት እየተመለሰ ነው። የግልም ሆነ የመንግሥት ባንኰች ሥራ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ከአክሱም ሐውልት ወደ ሌላ ሰፈር አቀናሁ። ትርሐስ ገና ታዳጊ ልጅ ነች። ጠይም፤ ስርጉድ፣ ሳቂታና ተረበኛ አይነት ልጅ ነች። እንደ ሽሬዋ ፊዮሪ መንገድ ዳር የጀበና ቡና እየሰራች ነው። ከሩቅ የመጣን እንግዶች መሆናችንን ስታውቅ፤ ደስታዋ ከገጿ ይነበብ ነበር። ያለፉ ጊዜያትን ሰቆቃ አጫወተችን። ስለቀጣይ ዕጣ ፈንታዋ እና ዕቅዷ ስታወራ ትቆይና “የሰው ልጅ ግን በጣም ከሃዲ ነው። ከወራት በፊትኮ ስለቢዝነስ አላስብም ነበር። መቼ እሞታለሁ እንጂ” ብላ ራሷን ትወቅሳለች።
ወደ ሰማይ አንጋጣ ፈጣሪዋን ታመሰግናለች። ጦርነት ተራውንም ሕዝብ ለመልከ-ብዙ ቀውስ ዳርጎት እንደቆየ ታነሳለች። ዛሬ ሁሉ አልፎ ሰላም መውረዱ ለመጨዋወት መብቃቷ ለእርሷ ትልቅ ብሥራት ነው። ይህ ለትርሐስ ብቻ ሳይሆን ለመላው አክሱማዊያን መሆኑ እሙን ነው።
አክሱም ከተማ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ከዋለችበት ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ በሻለቃ አዛዥነት የተሰማራ የፌዴራል ፖሊስ አባልም ያጋጠመውን አሳዛኝ ገጠመኞች አጫውቶኛል። ጦርነቱ ቢራዘም ኖሮ በተራው ሕዝብ ላይ ምን ያህል የከፋ ጉዳት ይደርስ እንደነበር በአሳዛኝ ሁኔታ ገልጾልኛል። አክሱሞች ያን ሁሉ አልፈው ሰላም አየር ነፍሶ፣ ከስጋት ቆፈን ተላቀው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል።
የዛሬ ሳምንት ሰርክ(11 ሰዓት) ላይ አክሱም የከተራ በዓል በድምቀት አክብራለች። ታቦተ-ጽዮን ወደ ባህረ- ጥምቀቱ ስትወርድ፤ ወግና ሥርዓቱ ተጠብቆ፣ ሕዝቡ በሀበሻ ነጫጭ አልባሳት፣ ካህናት በልብሰ ተክህኖ ደምቀው … እየተከወነ ነበር።
አንዲት እናት ለአማርኛ ተናጋሪ በቀረበ አነጋገር እያለቀሱ ታቦት እየሸኙ ነው። ትኩር ብዬ ሳያቸውም ዕንባቸው ዱብ ዱብ ይላል። “ከዚያ ሁሉ መከራ አልፎ ለዚህ በቃን፤ ተመስገን” እያሉ እልልታውን ያቀልጡታል። በደስታ እያነቡ ነበር። ይህ ስሜት የብዙኃኑ አክሱማዊያን እናቶች እንደሆነ መገመት ቀላል ነው።
አክሱም በኮቪድ እና በኋላም በጦርነቱ ምክንያት ባህረ-ጥምቀት ታቦት ወጥቶ ሲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ከወትሮው በተለየ ድምቀትና ውበት በሰላምና በደስታ፤ በአደባባይ እልልታና ሆታ በማክበራቸው ልዩ ስሜት ፈጥሮባቸዋልና! እናም በአክሱም የከተራ ሆነ የበዓለ-ጥምቀት ክብረ-በዓላት በሰላም ስምምነቱ ማግስት በድምቀት ተከውኖ አለፈ።
የሃይማኖት አባቶቹም ሆኑ ምዕመኑ በሰጡት ቃለ መጠይቅም የዘንድሮው ክብረ-በዓል ካለፉት ዓመታት ነባራዊ ሁኔታ ጋር እያነጻጸሩ፤ ትልቅ ብሥራትና መልክ እንዳለው ገልጸዋል። ሰላም እንዲጸና፤ ነባር ኢትዮጵያዊ አንድነትና መተባበር እንዲመለስ ጽኑ መሻታቸውን ነግረውናል።
በበጎ ቀን የማውቃትን አክሱም፤ ከረዥም ጊዜ በኋላ አሁናዊ መልኳን ታዝቤ፤ የነገ ትዝታ ሰንቄ ተመለስኩ!!
ሰላም ለኢትዮጵያ!!
አየለ ያረጋል (ኢዜአ)
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015