ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተከሰተውን ወቅታዊ ሁኔታ የገመገመው የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አለመግባባቱን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሚፈጸም የጸና እምነት አለው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋራ ግብረ-ኃይሉ በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚሰራጩ ዘገባዎችና በመረጃ ስምሪቱ ባሰባሰባቸው ግብዓቶች መሠረት በእምነቱ አባቶች በተመሳሳይ ቀንና ቦታ ሕገወጥ የሰልፍ ጥሪ በማድረግ የዜጎች ህይወት የሚቀጠፍበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ቅስቀሳዎች እየተደረጉና ሌሎችም ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል።
ይህ አካሄድ ክስተቱን እንደ ሽፋን በመጠቀም ከውስጥና ከውጭ ተቀናጅተው ሀገራችንን ለማፍረስ ለሚሰሩ ፀረ-ሰላም ኃይሎች በር እየከፈተ መሆኑን መላው የሀገራችን ሕዝብና የዕምነቱ ተከታዮች ግንዛቤ ሊወስዱ እንደሚገባ የጋራ ግብረ-ኃይሉ አመልክቷል።
ትናንት ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በሀገራችን እንገነባለን ስንል “እኛ ካልፈቀድንላችሁ በስተቀር መገንባት አትችሉም” ሲሉን የነበሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ዛሬ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት አለመግባባቱን ለማባባስ ጊዜ አልወሰደባቸውም ያለው የጋራ ግብረ-ኃይሉ፤ እነዚህ የውጭ አካላት በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተፈጠረውን አለመግባባት እንደ እድል በመጠቀም ልዩነትን የሚያጎላ እና ችግሩን የሚያባብስ እንቅስቃሴ ውስጥ መገኘታቸውን የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።
ስለሆነም መላው የሀገራችን ሕዝብ፣ የዕምነቱ አባቶችና የዕምነቱ ተከታዮች ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከውስጥ የሽብር ኃይሎች ጋር እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ አንቂ ስም ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ከሚሹ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀናጅተው ሀገራችንን ወደማያባራ ብጥብጥ ለማስገባት እያደረጉ ያሉትን ቅስቀሳና እንቅስቃሴ በውል ተገንዝባችሁ የእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ እንዳትሆኑ የጋራ ግብረ-ኃይሉ በአጽንኦት አሳስቧል።
በሃይማኖቱ ሽፋን የሚደረጉ የሕገወጥ ሰልፎቹ ቅስቀሳዎች የተለያዩ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀምና በህቡዕ በመደራጀት የአፍሪካ ሕብረትን ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ከሚገኝበት ወቅት ጋር እንዲገጣጠሙ በማድረግ በሀገሪቱ የደኅንነት ስጋት እንዳለ በማስመሰል ጉባኤው እንዲስተጓጎል ሆን ተብሎ በዕቅድ እየተመራ መሆኑን የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ደርሶበታል።
ሕገወጥ እንቅስቃሴዎቹ ደም አፋሳሽ እንዲሆኑ ታቅዶ ችግሩ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የጦር መሣሪያዎች ሲዘዋወሩ የነበሩ ሲሆን ግብረ -ኃይሉ ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከአዘዋዋሪ የደም ነጋዴ እንዲሁም ሽብርተኞች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ይገልፃል።
በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ በሚመለከተው አካል የተፈቀደ ሰልፍ የሌለ መሆኑ ታውቆ ኅብረተሰቡ ከዚህ ሕገ ወጥ ሰልፍና ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት ራሱን እንዲጠብቅ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ መላው ሕዝብ፣ የዕምነቱ አባቶችና ተከታዮች ለሀገራችን ሰላምና ደኅንነት እንደወትሮ ዘብ በመቆም ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጋር ተቀናጅታችሁ እንድትሠሩ እና ማንኛውም አለመግባባት በሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ የበኩላችሁን እንድትወጡ ጥሪውን ያቀርባል።
የጋራ ግብረኃይሉ ከዚህ ውጪ ሰልፍ አደርጋለሁ ብሎ በሕገ- ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ኃይል እንዲሁም ሰልፎቹን ለማስተባበር እና ለመሳተፍ የሚሞክሩ አካላት ለሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት ተጠያቂ መሆናቸውን በማሳሰብ ግብረ – ኃይሉ ለዜጎችና ለሀገር ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ሲባል ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ከወዲሁ በጥብቅ ያሳውቃል።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ ለቤተክርስቲያኗ አባቶች እና ለዕምነቱ ተከታዮች የሚደረገውን የደኅንነት ጥበቃ ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ እንደሚቀጥል ጠቁሟል። በየክልሉ የምትገኙ የፀጥታ ኃይሎችም በአካባቢያችሁ ሕገወጥ ሰልፎች እንዳይካሄዱ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያኗ፣ ለእምነቱ አባቶች እና ተከታዮች በአጠቃላይ ለሕዝቡ ተገቢውን የደኅንነት ጥበቃ እንድታደርጉ የጋራ ግብረ –ኃይሉ ያሳስባል።
በመጨረሻም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ ዝግጅት ማድረግ በመጀመራቸው ኅብረተሰቡ እንደተለመደው ሁሉ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ከግብረ -ኃይሉ ጎን እንዲቆም በድጋሚ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረኃይል ጥሪውን ያቀርባል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና
የአዲስ አበባ ፖሊስ
የካቲት 01 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015