ብልጽግናን ለማምጣት ራዕይ ሰንቃ ለምትጓዝ ሀገር ገቢ መሰብሰብ ላይ አተኩሮ መስራት ወሳኝ ነው። ያለ ሀብት፣ ያለ ገንዘብ አቅም የቱንም ያህል መፍጨርጨሩ ቢኖር፣ የትኛውም ፍላጎት ሊመለስ፣ እቅድም ስኬታማ ሊሆን አይችልም።
ኢትዮጵያ የመልማት፣ የማደግና የመበልጸግ ጽኑ ፍላጎት አላት። ፍላጎት ብቻም ሳይሆን ሰፋፊ እቅዶችን አዘጋጅታ እየተገበረችም ትገኛለች። ለእዚህ የሚያስፈልገውን ሀብት በማሰባሰብ ላይም እንዲሁ በትኩረት እየተሰራ ነው። መንግሥት ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት አንስቶ በገቢ አሰባሰብ ላይ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እያካሄደ ይገኛል።
ይህም በገቢ አሰባሰቡ በኩል የተያዙ እቅዶች ስኬታማ እየሆኑ የሚሰበሰበው ገቢም እየጨመረ እንዲመጣ አስችሏል። ያለፉት ዓመታት የገቢ አሰባሰቦችም ይህንኑ አመላክተዋል። በተያዘው 2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር ከተሰበሰበው ገቢ መረዳት የሚቻለውም ሀገሪቱ ገቢ ለመሰብሰብ ያስቀመጠቻቸው እቅዶች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው።
የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት 228 ቢሊዮን 229 ሚሊዮን 060ሺ 140 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ 225 ቢሊዮን 933 ሚሊዮን 008ሺ 025 ለመሰብሰብ ተችሏል። አፈጻጸሙም 99 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል ። ይህ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 54 ቢሊዮን 622 ሚሊዮን 624ሺ 687 ወይም በ31.89 በመቶ እድገት አሳይቷል።
ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ የሀገር ውስጥ ገቢው ድርሻ 138.82 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ከተያዘው የ 137 ቢሊዮን ብር ዕቅድ አንጻር የ 100.6 በመቶ ነው። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ በብር 33.4 ቢሊዮን ወይም የ 31.7 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
በገቢ አሰባሰቡ ለተገኘው ስኬት ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት፣ ሰራተኞቻቸው መላው ግብር ከፋይ ማህበረሰብ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። በቀጣይ ስድስት ወራትም ተመሳሳይ ርብርብ በማድረግ እንደ ሀገር ለመሰብሰብ የታቀደው ገቢ እንዲሰበሰብ እነዚህ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ጥሏቸው ያለፈ ጫናዎች ባሉበት ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ገቢ መሰብሰብ ባልተቻለበት ሁኔታ የተገኘ ገቢ እንደመሆኑም ትልቅ ሊባል የሚችል ነው።
እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ከሀገሪቱ የመልማት ፍላጎት አኳያም ሲታይ ግን በዘርፉ ገና ብዙ መስራት የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አኳያ ሀገራዊ ፍላጎቶችን በየጊዜው እየቃኙ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማጎልበት አስፈላጊ ነው።
አሁንም በርካታ ግብር ከፋዮች ተገቢውን ግብር እየከፈሉ አይደሉም ኮንትሮባንዲስቶችና ሌሎች በርካታ ሕገወጦች በዘርፉ አሉ። እነዚህን ስር የሰደዱ ችግሮች በመፍታት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ገቢን መሰብሰብ አሁንም የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች የቤት ስራ መሆኑ ይቀጥላል።
ለዚህም የግብር ከፋዮችን ግንዛቤ በማዳበር፣ በሕግና በመሳሰሉት መንገዶች በመጠቀም ተገቢውን ግብር ማስከፈል፣ ግብር ጨርሶ የማይከፍሉትን ወደ ግብር መረቡ ማስገባት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር ነው። የእነዚህ ሕገወጦች መበራከት ሌሎች ሕገወጦች እንዲፈለፈሉ ስለሚያበረታታ በሕግ አግባብ የግብር መሰረትን ማስፋት በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ከተለመዱት የገቢ መሰብሰቢያ መንገዶች በተጨማሪ ዘመኑ የሚጠይቃቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም አገልግሎቱን ማቀላጠፍ ያስፈልጋል። ዘርፉን በዘመናዊ ትክኖሎጂ ለማዘመን የሚደረጉ ጥረቶች እያስመዘገቡ ካለው ስኬት አንጻርም ፤ ትክክለኛ እና ፍትሀዊ ገቢ ለመሰብሰብ የሚደረገውን ጥረት የበለጠ ለማጠናከር ከቴክኖሎጂ እኩል መራመድም ይገባል። የሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታም ለዚህ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይገመታል።
አሁን ባለው የገቢ አሳባሰብ የእቅድ አፈፃፀም እየተመዘገበ ያለው ስኬት የሚያበረታታ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ገና ያልተሰበሰበ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ከመኖሩ አንጻር ብዙ የቤት ስራ እንደሚኖር መገመት አይከብድም። ለዚህ ደግሞ ራስን በሁለንተናዊ መንገድ ማዘጋጀት ተገቢና ወሳኝ ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015