ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ ይታወቃል:: የዚህ ምክንያቶቹም 83 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ የዕለት ጉርሱንና የዓመት ልብሱን የሚያገኘው እንዲሁም ቤተሰቡን የሚያኖረው ከዚሁ ከግብርና ዘርፍ በሚያገኘው ገቢ በመሆኑ ነው:: ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ከምታገኝባቸው ምርቶች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የግብርና ምርቶች ናቸው::
ከእነዚህ የግብርና ምርቶች መካከል በቀዳሚነት እየተጠቀሱ ከሚገኙት የቡና እና የአበባ ምርቶች በተጨማሪ የቅመማ ቅመም ምርትም ለውጭ ገበያ በመቅረብ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ይታወቃሉ:: ከግብርና ምርቶች መካከል በቅመማ ቅመም ዘርፍ ተጠቃሽ ከሆኑትና ወደ ውጭ ገበያ ከሚቀርቡት ውስጥ ዝንጅብል፣ በርበሬ፣ ኮረሪማ፣ ጥምዝ እርድ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ሄል፣ አብሽና ድንብላል ይገኙበታል::
ከቡናና ሻይ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ተቋም ተለይተው ከቀረቡት 109 ከሚደርሱ የቅመማ ቅመም ምርቶች፤ መዓዛማ ተክሎችና የቅመማ ቅመም ቤተሰቦች ከ50 በላይ የሚሆኑት በኢትዮጵያ የሚመረቱ ናቸው:: ከእነዚህ ውስጥም 23 የሚደርሱት ቅመማ ቅመሞች በጥሬያቸውና እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ለአገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ::
ለአገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ያለው ይህ የቅመማ ቅመም ምርት በአገሪቱ እንዴት እየለማ ነው፤ የግብይት ሂደቱስ ምን ይመስላል፤ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ሚና እንደምን ያለ ነው? በእዚህ ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቅመማ ቅመም ልማት ዴክስ ኃላፊ አቶ ሞገስ አሸናፊ የአገሪቱ እምቅ ሃብት የሆነው የቅመማ ቅመም ምርት በተለመደው የአስተራረስ ዘዴ እየለማ ውስን በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ያስታውሳሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህም ሲባል ታዲያ እናቶች በትንሽ ቦታና አጥር ጥግ ለመድሃኒት በሚል የሚያለሙት አሰራር ነው የተለመደው:: አሁን ላይ አርሶ አደሩን በማስተማርና ግንዛቤ በማስጨበጥ የቅመማ ቅመም ምርት በስፋት እንዲያለማ እየተደረገ ነው:: ምርቱን ወደ ውጭ ገበያ በመላክም አገሪቷ ከዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል እየተሰራ ይገኛል:: በዚህም መሰረት አርሶ አደሩ ግንዛቤውን እያገኘ ሰፊ በሆነ የእርሻ መሬት ላይ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችና መአዛማ ተክሎች በማልማት ከአገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ነው::
በአገሪቱ በስፋት ከሚመረቱት የቅመማ ቅመም ምርቶች መካከል በርበሬ፣ ድንብላል፣ አብሽ፣ ነጭ አዝሙድ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ኮረሪማ፣ እርድ፣ ዝንጅብልና ሌሎችም ተጠቃሽ እንደሆኑ ያነሱት አቶ ሞገስ፤ እነዚህ ቅመማ ቅመሞች ለውጭ ገበያ እንደሚቀርቡ ያመለክታሉ፤ የእነዚህን ቅመማ ቅመሞች ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የገበያ ተደራሽነታቸው እንዲሰፋ የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ይናገራሉ::
እንደ አብሽ፣ ድንብላል፣ ነጭ አዝሙድና ጥቁር አዝሙድ የመሳሰሉት በአገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች ማለትም ጎንደር፣ ሸዋና ባሌ አካባቢ በስፋት እንደሚለሙ ተናግረው፣ እንደ ዝንጅብልና እርድ የመሳሰሉት ደቡብ ላይ በስፋት የሚለሙ መሆናቸውን ይገልጻሉ:: ዝንጅብል በበሽታ ምክንያት በ2004 ዓ.ም አካባቢ ሙሉ ለሙሉ ጠፍቶ አደጋ ውስጥ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሞገስ፤ ካለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ወዲህ በሽታውን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት አርሶ አደሩም እያንሰራራ ይገኛል ይላሉ:: ለውጭ ገበያ ያለው ተደራሽነት እንደ ቀደመው ጊዜ የሚያበረታታ እንዳልሆነም ነው ያስታወቁት:: እንደ እርድ፣ በርበሬና የመሳሰሉት ቅመማ ቅመሞች ግን ጥሩ የገበያ ዕድል እንዳላቸው ተናግረዋል::
የቅመማ ቅመም ግብይትን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡን በቡናና ሻይ ባለስልጣን የቅመማ ቅመም ገበያ ልማትና ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ገለታ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ ገበያ የሚላኩት የቅመማ ቅመም ምርቶች በመጠንና በጥራት እየጨመሩ ሲሆን፤ አገሪቷም ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እያደገ መጥቷል::
በዋናነት ወደ ውጭ ገበያ ከሚላኩት የቅመማ ቅመም ምርቶች በተጨማሪ በጉምሩክ መረጃ ውስጥ የሚካተቱ ሌሎች የቅመማ ቅመም ምርቶች መኖራቸውን ነው አቶ ካሳሁን የጠቆሙት:: በዚህም መሰረት በተያዘው በጀት ዓመት እንደ አገር በጥቅሉ 14 ሺ 896 ቶን መታቀዱን ጠቅሰው፣ ከዚሁ ምርት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ገቢም 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ተናግረዋል:: እስካሁን ባለው የገበያ ሂደትም ባለፉት ስድስት ወራት አራት ሺ 727 ሜትሪክ ቶን ቅመማ ቅመም መላክ የነበረበት መሆኑን አስታውሰው ሶስት ሺ 374 ሜትሪክ ቶን በመላክ የዕቅዱን 71 በመቶ ማሳካት ተችሏል ሲሉ ያብራራሉ:: ይህም ከገቢ አንጻር ሰባት ነጥብ 03 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት እንደተቻለና የእቅዱን 78 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው የተናገሩት::
አሁን ላይ የቅመማ ቅመም ምርት ግብይት አንዱ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እየተሠራበት ይገኛል ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ባለፉት ዘመናት የቅመማ ቅመም ዘርፉ ልክ የህግ ማዕቀፍ እንዳልነበረው ይገልጻሉ:: በዚሁ ምክንያትም በገበያ ውስጥ አነስተኛ ድርሻ እንደነበረው ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የቅመማ ቅመም ግብይት የሚመራበት የግብይት መመሪያ ወይም የህግ ማዕቀፉ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቀዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ እስካሁን በነበረው የገበያ ሂደት በተለይም ለዘርፉ የተዘጋጀና ግብይቱ የሚመራበት የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ችግሮች ነበሩ:: ይሁንና አሁን ላይ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫውን ሙሉ ለሙሉ በቅመማ ቅመም ላይ በማድረግ አምራች ክልሎችን ጨምሮ የግብይት መመሪያውን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው:: የግብይት መመሪያው ሥራ ላይ ሲውልም በውስጡ የሚይዛቸው በርካታ ፓኬጆች ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፤ ከፓኬጆቹ መካከልም የመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከላትን ጨምሮ የግብይት ተዋናዮች እነማን ናቸው፤ ከአምራቹ በቀጥታ የሚገዛው ማን ነው፤ ከእነሱ የሚረከቡትስ እነማን ናቸው የሚሉትና ሌሎችም ተካተውበታል ሲሉ ያብራራሉ::
በአገሪቱ በቅመማ ቅመም ግብይት ተሰማርተው ምርቱን ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩ ከ100 የሚበልጡ ላኪዎች ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፤ እነዚህንና ሌሎችንም የዘርፉ ተዋናዮች የማገናኘትና ህጋዊ የማድረግ ተግባር እንደሚከናወን አመልክተዋል:: የእስከ አሁኑ የገበያ ሂደት ችግሮች እንዳሉት በመጥቀስም አሁን ላይ ችግሮቹን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል::
አቶ ካሳሁን እንዳስታወቁት፤ ወደ ውጭ ገበያ በስፋት ከሚላኩት የቅመማ ቅመም ምርቶች መካከልም በርበሬ፣ ዝንጅብል፣ እርድ፣ ኮረሪማ፣ ነጭ አዝሙድ፣ ጥቁር አዝሙድ በዋናነት ይጠቀሳሉ::
የቅመማ ቅመም ምርት የገበያ ሂደትን በተመለከተ አምራቾቹ ምርቱን ለመሰረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት ያቀርባሉ:: መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ደግሞ ምርቱን አዘጋጅተው ወደ ውጭ ለሚልኩ ላኪዎች በማቅረብ ግብይቱ ይከናወናል::
እነዚህ ቅመማ ቅመሞች ከአገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ወደ ውጭ ገበያ ሲላኩ በጥሬያቸውና እሴት ተጨምሮባቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን፤ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ወደ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ካናዳ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኢንዶኔዥያ፣ እስራኤልና እንግሊዝ እንደሚላኩ ገልጸዋል:: የምርቶቹ መጠን ይብዛ አልያም ይነስ እንጂ 28 ለሚደርሱ የዓለም አገራት የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመሞች ተደራሽ መሆናቸውንም ያመለክታሉ::
በስፋት ወደ ውጭ ገበያ እየቀረቡ ካሉትና ከላይ ከተዘረዘሩት ቅመማ ቅመሞች በተጨማሪ በቅርቡ በተለምዶ የስጋ መጥበሻ ቅጠል ወይም አዝሞሪኖ በስፋት እየለማና ወደ ገበያ እየገባ እንደሆነ ያነሱት አቶ ካሳሁን፤ ምርቱ በስፋት እየተመረተ ያለውም በስልጤ ዞን አካባቢ በኩታ ገጠም እርሻ መሆኑን ይጠቁማሉ፤ ይህ በክላስተር እየተመረተ ያለ ሰፊ የአዝሞሪኖ ምርት ገበያ ማግኘት እንዲችልና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል::
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በአገር ውስጥ የሚሸጠው ምርት እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት እንዲችል ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው:: ይሁንና ቻይና የአዝሞሪኖ ምርትን በስፋት እያመረተች የዓለም ገበያ ፍላጎትን ለማሟላት በስፋት እየሄደችበት ነው:: ከቻይና በተጨማሪም ሞሮኮና ሌሎች አፍሪካ አገራትም ምርቱን በስፋት የሚያመርቱ በመሆናቸው ኢትዮጵያም በአዝሞሪኖ ምርት የውጭ ገበያ ውስጥ መግባት እንድትችል ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ::
ተፎካካሪና ተወዳዳሪ ከሆኑ አገራት ጋር በመሆኑ ገበያውን ሰብሮ ለመግባትና በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም፣ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸውም ነው አቶ ካሳሁን የሚናገሩት:: ከዚህም ባለፈ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ምርቱን ወደ ውጭ ገበያ የላኩ እንዳሉም አንስተዋል:: ይሁንና ባለፉት ስድስት ወራት ብዙ ተልኳል ማለት ባያስደፍርም በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከተላኩ የቅመማ ቅመም ምርቶች መካከል ሶስት ኮንቴነር አዝሞሪኖ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ::
በጅምር ላይ ያለውን የአዝሞሪኖ ልማት በማስፋፋት ተፎካካሪ በመሆን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ብዙ ሥራ መሠራት እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ ካሳሁን፤ ምርቱን በጥራት በማምረት በውጭ ገበያው ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻልም ነው ያስረዱት::
የቅመማ ቅመም ምርት የሚመራበት የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ በማንሳት፤ የግብርና ሚኒስቴር የግብይት መመሪያውን በቅርቡ የሚያጸድቅ መሆኑንም አቶ ካሳሁን ጠቁመዋል:: መመሪያው እንደጸደቀም እስከ ታች ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል:: ወደ ውጭ የሚላኩ የቅመማ ቅመም ምርቶች የጥራት ደረጃቸው የተዘጋጀ በመሆኑም ከህግ ማዕቀፉና ከመመሪያው ጋር አዛምዶ እንደሚሰራ አስታውቀው፣ ይህንኑ አጠናክሮ በመቀጠልም የቅመማ ቅመም ምርቶችን ከሌሎች ተፎካካሪ አገራት ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል፤ በጥራትና በስፋት አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል::
እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፤ በአገሪቱ በርካታ የቅመማ ቅመም አይነቶች እየተመረቱ ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ ቆይተዋል:: ከውጭ አገርም በተመሳሳይ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የቅመማ ቅመም ምርቶች አሉ:: በመሆኑም በአገር ውስጥ የሚመረቱ የቅመማ ቅመም ምርቶችን እሴት በመጨመር ከውጭ የሚመጡትን የቅመማ ቅመም ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ይሰራል:: ለአብነትም የሮዝመሪ ዘይት ለማምረት ባለሃብቶች ማሽን በማስገባት ሂደት ላይ ይገኛሉ:: ይህም ከአገር ውስጥ ፍላጎት ባለፈ ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚደረግ ሂደት በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል::
አገሪቷ እስካሁን በነበረው ሂደት ከቅመማ ቅመም ምርት ማግኘት የሚገባትን ገቢ ማግኘት እንዳልቻለች የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፤ ለአብነትም ባለፈው በጀት ዓመት ከምርቱ የተገኘው ገቢ 16 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደነበር አስታውሰዋል:: ይሁንና በቀጣይ በደንብ መሰራት ከተቻለ ከዚህ በበለጠ ገቢ ማግኘት ይቻላልም ብለዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም