በመዲናዋ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ

አዲስ አበባ፡ በመዲናዋ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሁለት ነጥብ 93 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 612 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ መሠረት ወልደማሪያም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተሻለ የኢንቨስትመንት አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡

የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ከባለፈው ዓመት ሩብ ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ13 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቁመው፤ በአብዛኛው አዲስ ፍቃድ የጠየቁ ባለሀብቶች በአገልግሎት ዘርፍ እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንደሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት ዘርፉ ሆቴልን፣ ቱሪዝምን እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎችን እንደሚያጠቃልል ገልጸው፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የኤሌክትሪክ፣ የብረታብረት፣ የእንጨት ውጤቶችን እና ጨርቃጨርቅን እንደሚያካትት ጠቅሰዋል፡፡

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለ8ሺህ 707 ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የተናገሩት ዳይሬክተሯ፤ አዲስ ፍቃድ ያወጡ ኢንቨስተሮችም ለ770 ሰዎች ቋሚ እና 490 ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

አዲስ ፍቃድ ያወጡ ኢንቨስተሮች ወደ ሥራ እንዲገቡ የመስክ ክትትል እንደሚደረግ የጠቆሙት ወይዘሮ መሠረት፤ በክትትሉ የታዩ ችግሮች ካሉ እንዲስተካከሉ እና በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ኢንቨስተሮች የሚያነሱት ትልቁ ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጥ በማምጣቱ ችግሩ እየቀነሰ መሄዱን ተናግረዋል፡፡

በኢንቨስተሮች በተደጋጋሚ የሚነሳው ሌላው ችግር የመሥሪያ ቦታ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን ኮሚሽኑ የሚፈታው ባለመሆኑ ወደ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንደሚልክ እንዲሁም በኪራይ እና በተለያየ መልኩ የሚሠሩበትን ሁኔታ ላይ ሙያዊ ድጋፍ እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

ሌሎች በኮሚሽኑ በኩል ሊፈቱ የሚችሉ የመሠረተ ልማት ችግሮች ግን ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር በትብብር እንደሚፈቱ ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት በሂደት የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር የተናገሩት ዳይሬክተሯ፤ መዲናዋ ንጹሕ እና ሠላም መሆኗ ለኢንቨስትመንት መበረታታት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

ኮሚሽኑ የኢንቨስተሮችን ጊዜ በቆጠበ መልኩ ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ መሠረት፤ ኢንቨስተሩ ባለበት ቦታ ሆኖ ፍቃድ እንዲያወጣ እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኝ የሚያስችል ዲጂታል ቴክኖሎጂ በሥራ ላይ ለማዋል ሂደቱ እየተጠናቀቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

Recommended For You