ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑና ያልሆኑ የበርካታ ወንዞች ባለቤት መሆኗን ተከትሎ የውሃ ማማ እየተባለች ብትወደስም ስሟና ግብሯ ሳይገናኙ ዘመናትን አሳልፋለች:: አብዛኛዎቹ ወንዞቿ እንደዳቦ በሚገመጠው ለም መሬት መካከል ያለምንም ሥራ ሲገማሸሩ እና ሲተኙ የኖሩ በመሆናቸው አገሪቱ የወንዞቿን በረከት ለዘመናት ሳታጣጥም ኖራለች:: አባይን ጨምሮ አንዳንዶቹ እንደውም ከለም አፈሯ እየዛቁ ወደ ጎረቤት አገራት ሲያግዙ የኖሩ በመሆናቸው ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ሚዛን ደፍቶ ነበር::
የአገራችን አርሶ አደሮችም ቢሆኑ በዝናብ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ የግብርና ሕይወትን ስለሚመሩ የመኸሩን አዝመራ ከሰበሰቡ በኋላ የበጋውን ወራት በወንዞች ተጠቅመው የማምረት ልምድ አልነበራቸውም:: እንደውም ለአገራችን አርሶ አደሮች የበጋው ወራት እንደ እረፍት ጊዜ የሚቆጠር ነበር:: በበጋ ወራት ወንዞች ለአርሶ አደሩ ይጠቅማሉ ከተባለ ምናልባትም ለከብቶች ውሃ መጠጫነት፣ ለንጽህና መጠበቂያነት እና ለመጠጥነት ቢሆን ነው::
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሁኔታዎች እየተለወጡ መጥተዋል:: ይህ ዘመናትን ያስቆጠረው የወንዞቻችንና የመሬቶቻችን ተኳርፎ የመኖር ሁኔታ የስንዴ ፍላጎትን ለማሟላት በሚል ከተነቃቃው የበጋ ግብርና በኋላ መልኩን ቀይሯል:: ዛሬ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የመኸሩን አዝመራቸውን ከሰበሰቡ በኋላ እንደ ከዚህ ቀደሙ በበጋው ወራት እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡበት ሁኔታ የለም::
አርሶ አደሮቻችን የመንግሥትን አቅጣጫ ተከትለው ላለፉት ሶስት ዓመታት ወንዞችን እየጠለፉ የማልማት ባህላቸውን አሳድገዋል:: ይህ አዲስ የሥራ ባህል ጅምር ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ውስን ውሃ ገብ መሬቶችን ብቻ በማልማት አመርቂ ውጤት እንደተገኘ የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያመላክታሉ::
የበጋው ግብርና ገና በሚፈለገው ደረጃ ባልተስፋፋበት በዚህ አጭር ጊዜ ስንዴን ኤክስፖርት የማድረግ ቁመና ላይ ተደርሷል:: ለበጋው ግብርና አመቺነት ያላቸው ወንዞቻችን እና መሬቶቻችን ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ ሲውሉ ደግሞ አሁን የተገኘውን ውጤት በሁለት እና በሶስት እጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል መገመት አይከብድም:: ልክ እንደ መኸሩ የምርት ዘመን ሁሉ የበጋውም ወራት መደበኛ የግብርና ሥራ የሚከናወንበት ይሆናል:: ኢትዮጵያ በዓመት ሁለቴ የማምረት አቅም ታጎለብታለች:: በምግብ ራሷን ከመቻል አልፋ ኤክስፖርት የማድረግ ህልሟንም እውን ታደርጋለች::
አዲሱ የሥራ ባህላችን በዝናብ ጥገኝነት ላይ ተቸንክሮ የኖረውን ኋላ ቀር ግብርና አሠራር ነጻ የሚያወጣም ጭምር ነው:: የመኸሩ ወቅት አንዳንድ ጊዜ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ይፈተናል:: የዝናብ እጥረት ፣ በረዶ፣ ዋግ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ወዘተ በመኸሩ ግብርና ውጤታማነት ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አለ:: ከዚህ አንጻር የመስኖ ግብርና የመኸሩን ወቅት ያህል ፈታኝ ሁኔታዎች አይገጥሙትም::
የመኸሩ ወቅት ግብርና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሲያጋጥሙትና ምርታማነት ሲቀንስ የበጋው ግብርና የሚያካክስበት እድል ተፈጥሯል:: ባለፉት ሶስት ዓመታት በበጋው ግብርና ከተገኘው በሚሊዮኖች ኩንታል የሚቆጠር የስንዴ ምርት ይልቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶአደሮች አዲስ የሥራ ባሕል ማዳበራቸው በመጪው የግብርና ሥራ ላይ ተስፋ እንድንጥል ያደርጋል::
የውሃ ማማ ተብላ የምትወደሰው ኢትዮጵያ በ1966 ዓ.ም እና በ1977 ዓ.ም በድርቅ ስትመታ የሕዝቦቿ ብዛት ከ40 አስከ 70 ሚሊዮን እንደማይበልጥ የዚያን ዘመን መረጃዎች ያመላክታሉ:: ያን ጊዜ በድርቅ ተመታን ብለን ለምጸዋት እጃችንን የዘረጋነው ከዛሬው የተሻለ አቅም ያላቸውና በለም መሬቶቻችን መካከል የተኙ ወንዞች እያሉን ነበር:: የተከማቸውን የውሃ ሀብታችንን ልክ እንደ አሁኑ ለግብርና ሥራ ሳናውል ቀርተን በድርቅ የተመታንባቸው እና ምጽዋት የጠየቅንባቸው እነዚያ ዘመናት ሊያስቆጩን ይገባል::
አሁን መንግሥት ወንዞችን ተጠቅሞ ማምረት እንደሚቻል በተግባር እያሳየን ይገኛል:: የአገራችን አርሶ አደሮችም አይናቸውን ገልጠዋል:: እንደበፊቱ የዝናብ ጥገኛ ሆነው ክረምትን ለሥራ በጋን ለእረፍት ሳይሉ ክርምት ከበጋ እያረሱ ማም ረትን ተለማምደዋል::
ውስን የውሃ ሀብት ያላቸው አንዳንድ የዓለማችን አገራት የመስኖ ግብርናን በማዘመን ሕዝባቸውን ከመመገብ አልፈው ለሌሎች አገራት የሚተርፍ ምርት ሲያመርቱ ስናይ ያለፈው የአገራችን የመሬትና የውሃ ብክነት ያስቆጨናል:: እስራኤል በውስን መሬቷ ላይ የመስኖ ግብርናን በማስፋፋት ኢኮኖሚዋን የምትደጉም ተጠቃሽ አገር ነች:: ጎረቤቶቻችን ሱዳን እና ግብጽም ከእኛው አገር የሚፈስላቸውን የአባይ ወንዝ ለመስኖ ሥራ በማዋል የተትረፈረፈ በረከት የሚያገኙ ምሳሌዎቻችን ናቸው::
ኢትዮጵያ እዚያው በዚያው መመጋገብ የሚችል የውሃና የመሬት ጸጋ የተቸራት አገር ሆኗ እስከዛሬ ድረስ በመስኖ ሥራ ስሟ አለመጠራቱ የሚያስገርም ነው:: ከዚህ በኋላ ግን በየወንዙ ዳርቻ ተንጣለው የተቀመጡ ሰፋፊ መሬቶች ያለሥራ የሚቀመጡበት ዘመን ያለፈ ይመስላል:: ወንዞቻችንም በራስጌ እና በግርጌያቸው በግራ እና በቀኛቸው ወደ ተንጣለሉት ለም መሬቶች እየፈሰሱ ምድሪቱን በልምላሜ የሚያፈኩበት፣ በረከታቸው ለአርሶ አደሩ የሚተርፍብት ዘመን ላይ ደርሰዋል::
እንደግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያለፉትን የሶስት ዓመታት ልምድና ተሞክሮ በመቀመር በዘንድሮው የበጋ ወራት አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር በዘር ለመሸፈን ታቅዷል:: የመኸሩ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ውሃ ገብ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች በሙሉ ወደ መስኖ ሥራ እንዲገቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል::
መንግሥት የበጋ ግብርናን በማበረታታት ዓመታዊ የምርት መጠንን ከዓመት ወደ ዓመት እያሳደገ መምጣቱ አዲስ ለውጥ ነው:: ይህን ልምድና ተሞክሮ በመላ አገሪቱ በማስፋፋት አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት አላቅቆ በግብርና ዘርፍ የታሰበው የእደገት ደረጃ ላይ ለመድረስ በእጅጉ የሚጠቅም ነውና ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም