የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የጀግንነት መገለጫ ጥግ ነው፡፡ ሰራዊቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ ሁሌም ራሱን ለሕዝብና ለሀገር አሳልፎ ይሰጣል፤ የሀገሪቱን ሉአላዊነትን ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ መስዋዕትነትን ይከፍላል፡፡ በዱር በገደሉ ይዋደቃል፡፡ ደሙን ያፈሳል፤ አጥንቱን ይከሰክሳል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከጥንት እስከ ዛሬ በደምና አጥንታቸው ታሪክ ሲሰሩ፤ ሀገር ሲያቆሙና ኢትዮጵያን ሲታደጉ ኖረዋል፡፡ ሀገሬን አላስደፍርም፤ማንነቴን አላዋርድም፤ ሰንደቄን አላስረግጥም በማለት በዱር በገደሉ ደማቸውን ሲያፈሱ፤ አጥንታቸውን ሲከሰክሱ ኖረዋል፡፡ ዛሬም የዚሁ ውርስ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በደምና አጥንቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና አንድነት በማስከበር ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ ሁሉም በአንድ ድምጽ የሚስማማበት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር ጀግና ሰራዊት ነው፡፡ ሰራዊቱ ድል የሚፈጥር፣ ሞትን የሚያሸንፍ፣ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር፣ ፍላጎቱን ለዓላማው የሚያስገዛ፣ የነፃነትን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ የጨለማን ጊዜ ማሻገር የሚችል ልበ ሙሉ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ በጦርነት ወቅት ጀግና ሆኖ በስኬት በመራመድ ላይ ይገኛል፡፡
የአንድ መከላከያ ሀይል እምቅ አቅምና ጥንካሬ፤ የመለኪያ መስፈርቶቹ፤ የሰራዊቱ ብቃትና የውጊያ ዝግጁነት የታጠቀው ዘመናዊ የጦር መሳሪያና በታጠቀውም መሳሪያ በየትኛውም የመሬት ገጽ ላይ ለመጠቀም ያለው ችሎታና ብቃት ሀገርን ለመከላከል በውስጥ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሰልፎ ያስመዘገበው ድልና ስኬት ከዚህም አልፎ ድንበር ዘለል ተልእኮን በመወጣት ረገድ ያሳየው ወይንም የሚያሳየው ብቃት የአቅሙን ልኬት ሊያሳዩ የሚችሉ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሩን ዳር ድንበር ከማስከበሩም ባሻገር በጎረቤት ሀገራት ጭምር ተልዕኮ በመውሰድ ሰላምን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡ በሶማሊያ፤ በሱዳን፤ ቀደም ሲልም በላይቤሪያ፤ በሩዋንዳና ቡሩንዲ ሀገራት ተሰማርቶ ሰላም ማስከበር የቻለ የሕዝብ ልጅ ነው፡፡ ይህም ብቃት ሊገኝ የቻለው ከሰራዊቱ ተፈጥሯዊ ባህሪ በሻገር በየጊዜው እየተደረገለት በመጣው አቅም ግንባታ ስራዎች አማካኝነት ነው፡፡
በተለይም ባለፉት አራት አመታት ሰራዊቱን ለማዘመን በተሰሩ የለውጥ ስራዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ ራሱን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ በማጠናከር ሳይዋጋ የሚያሸንፍበት ብቃት ላይ ደርሷል፡፡
የምድር ኃይልን በሰው ኃይልና የውጊያ አፈጻጸም በማጎልበት ከአየር ኃይልና ከሌሎች አቅሞች ጋር ያለውን ቅንጅት የማሳደግ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በትጥቅና በመረጃ ግንኙነት አቅሙን በመገንባትም የማሸነፍ ብቃቱን አሳድጓል፡፡ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲና ከተለያዩ የደህንነትና የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የባህር ኃይልን አቅም የማሳደግና የሳይበር ጥቃት ዝግጁነት /የሳይበር ዋርፌር/ ብቃትን በማሳደግ ከተለመደው የውጊያ ስልት ወጣ በማለት የሚቃጡ ዘመን አመጣሽ ጥቃቶችን የመከላከል ብቃቶችን ተጎናጽፏል፡፡
መከላከያ ከለውጡ ወዲህ በሰራቸው የሪፎርም ስራዎች በቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ፣ በመከላከያ ምርምር ስራዎች፣ በባህር ኃይል ዝግጁነትና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን አከናውኗል፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት የተቃጡ ውስብስብ ጥቃቶችን የመመከት ብቃቶችን አዳብሯል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ለሀገሩ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገነቡ ድልድዮችና መሰረተ ልማቶችን በመገንባት፤ የግብርና ምርቶችን በመሰብሰብ፤ የአርሶ አደሩን ምርቶች ከተባይና ከተፈጥሮ አደጋ በመጠበቅ የዜግነት ግዴታውን የሚወጣ የሕዝብ ልጅ ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎንም የተፈናቀሉና ከቀያቸው የተሰደዱ ወገኖችን በመንከባከብና ካለው ላይ ለዕለት ጉርስ የሚሆን ገንዘብ በማዋጣትም ሕዝባዊነቱን የሚያሳይ ሰራዊት ነው፡፡
በአጠቃላይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተቋም ላይ እየተሰሩ ያሉ የለውጥ ተግባራት የሰራዊቱን ሀገር የመከላከል አቅም የሚጨምርና የሀገሪቱን ሉአላዊነትና አንድነት የሚያስጠብቅ ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም