አዲስ አበባ፡- የማህፀን በር ካንሰር ክትባትን በሁሉም ክልሎች በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አሁንም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የመጀመሪያው የብሄራዊ የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተጀመረ፡፡
የክትባት መርሃ ግብሩ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በይፋ በተጀመረበት ወቅት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደገለፁት፤ ክትባቱን ተግባራዊ በሚያደርጉ ሃገራት በሙሉ የሚነዙ የተዛቡ ወሬዎች ክትባቱን ተግባራዊ ለማድረግ ችግር ሆኖ የቆዩ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይገጥሙ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ቢሰሩም አመርቂ ውጤት እንዳልተገኘ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ አሁንም በተለይ ከጤና ባለሙያዎች፣ ወላጆችና የትምህርት አካላት ጋር በመሆን ክትባቱ መካን እንደማያደርግ፣ የከፋ የጎንዮሽ ጉዳትም እንደማያስከትል ግንዛቤውን በተጠናከረና ተከታታይነት ባለው መልኩ ለህብረተሰቡ ማሳወቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ወላጆች፣ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ልጃገረዶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ክትባቱ ምንም አይነት የከፋ ጉዳት እንደማ ያስከትል በመገንዘብና ከሚነገሩት የተዛቡ ወሬዎች በመራቅ ለስራው ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው በአንድ ሀገር ክትባትም ሆነ ሌሎች የጤና ፕሮግራሞች ሲጀመሩ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ህብረተሰቡ የማይቀበልበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም ተናግረው፤ ክትባቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ችግሩ ሊያጋጥም እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ የክትባቱን አስፈላጊነት በማስረዳት ልጃገረዶቹ ክትባቱን እንዲያገኙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
«ከህመሙ አሰቃቂነትና አደገኛነት እንዲሁም ከሚያስወጣው ወጪ አንፃር ክትባቱን መከተብ አዋጭ በመሆኑ ወላጆች ልጃገረድ ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ሰፊ የቅስቀሳ ስራዎች መስራት አለባቸው፤ለክትባቱ ውጤታማነት ተከታታይ የሆኑ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህር ቶችም እንደዛው ያስፈልጋሉ» ብለዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ሮማን ገለጻ፤ህብረተሰቡ ምንም አይነት ጥርጣሬ ሳይገባውና ክትባቱ ከመካንነት ጋር የማይያያዝ መሆኑን በመረዳት ለውጤታማነቱ የበኩሉን መወጣት ይገባዋል፡፡
በክትባት መርሃ ግብሩ 14 ዓመት የሞላቸው 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ልጃገረዶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከተባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ እነዚሁ ልጃገረዶች ከስድስት ወር በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ዳግም ክትባቱን እንደሚወስዱም ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2011
አስናቀ ፀጋዬ