አሁን ባለንበት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ከዘመኑ ጋር እየዘመነ መሄድ ይጠበቅበታል። እየዘመነ የመጣውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ስለመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎችም ያስገነዝባሉ። ለእዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ማድረግ ላይ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል፤ ተደራሽነቱ ደግሞ በመሰረተ ልማት ብቻ አይደለም፤ መሰረተ ልማቱ የሚፈልጋቸውን ቴክኖሎጂዎች ቁሳቁስ ማቅረብ፣ ባለሙያዎችን ማሰልጠን ወሳኝ ጉዳይ ናቸው፡፡
ይህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለስራ፣ ለኑሮና ለመሳሰሉት አስፈላጊ የመሆኑን ያህል በጥንቃቄ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል። ሰዎች መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት የሚለዋወጡበት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በተለይም የኢንተርኔት ተደራሽነት እያደገና እየሰፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ አገልግሎት በሚውልበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግም ይገባል።
በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምዳችንም እጅግ ከፍተኛ አቅም ያለውና በእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ የሚገኘው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፋይዳ፣ ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ በሚውልበት ወቅት መከተል ስለሚገባ ጥንቃቄ ኢትዮጵያ በዘርፉ ስላለችበት ደረጃ ከዘርፉ ባለሙያ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል። ባለሙያው የአይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መርዕድ በቀለ ናቸው።
አቶ መርዕድ በቀለ የአይ ኢ ኔትዎርክ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተሰማርተው ወደ ሥራ ከገቡ 14 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ባንኮችን ጨምሮ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ትላልቅ የዳታ ማዕከላትን ከመገንባት ጀምሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅትን አቋቁመው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
በአሁን ወቅትም በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ ያለውን የዳታ ሴንተር በማሳደግና በማስፋፋት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ለመስጠት ስምምነት በማድረግ ወደ ሥራ ገብተዋል።
አዲስ ዘመን፡- ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በዚህ ዘመን ለአንድ ሀገር ያለው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?
አቶ መርዕድ፡– በአሁኑ ዘመን ሰዎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት የሚለዋወጡበት አንዱ መንገድ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ነው። በተለይም የኢንተርኔት ተደራሽነት እያደገና እየሰፋ የመጣ ሲሆን፣ ዓለምን ሙሉ ለሙሉ አንድ በማድረግ ሰዎች ከዚህኛው ጫፍ እስከ ወዲያኛው ጫፍ በቀላሉ እንዲገናኙና መረጃ እንዲለዋወጡ የሚደርግበት ቀልጣፋ አገልግሎት ነው፡፡
ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። በተለያየ ዘርፍ አስገብተን ብንጠቀመው አበርክቶው የጎላ ነው። ለአብነትም ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ለትምህርት ከሚሰጠው አበርክቶ አንጻር ብንመለከተው ትምህርት ላይ አስፈላጊ የሆኑ በርካታ መረጃዎችን ማግኘት ያስችላል። ትምህርት ቤቶች፣ መምህራንና ተማሪዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ትምህርትን በዘመናዊ መንገድ፣ በርቀትና በጥራት ለመስጠት ይጠቅማል።
በጤና ዘርፍም አገልግሎት መስጠት ይቻላል። በተለይም የጤና ባለሙያ እጥረት ባለበት አገር ውስጥ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ አቅም ያላቸውና ጥቂት ቁጥር ያላቸው የጤና ባለሙያዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም በርካታ ቁጥር ያላቸው ታካሚዎች ዘንድ መድረስ ይችላሉ። የመንግሥት አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ለመስጠት ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው። ከታችኛው መዋቅር ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ ቴክኖሎጂን መጠቀም ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡
ቀበሌ ላይ ፋይል ጠፋ ሲባል ይሰማል። ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን መጠቀም ከተቻለ በቀላሉ ፋይሉን መለየት ይቻላል። ውሃ፣ መብራትና ሌሎችንም ክፍያዎች ለመክፈል ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በትልቁ ያግዛል። የግብርና መረጃዎችንም እንዲሁ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል። ስለዚህ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማንኛውም የሰው ልጆች የሕይወት እንቅስቃሴ ውስጥ የተቀላጠፈ አገልግሎትን በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ የማድረግ ትልቅ አቅም አለው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በየትኛው ዘርፍ መጠቀም ቢቻል ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለው ያምናሉ?
አቶ መርዕድ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ የተሻለ ነው። ምክንያቱም የሁሉም ነገር መሰረት ትምህርት ነውና ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም ያስፈልጋል። ጥራት ያላቸው ትምህርቶች ተቀርጸው በርቀት መስጠት ቢቻል የተሻለ ነው።
በአሁኑ ወቅት የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ለሙሉ ትምህርት የሚሰጡት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ነው። ተማሪው በፈለገውና ባመቸው ሰዓት እየፈለገ የሚጠቀምባቸውና መማር የሚቻልባቸው ቴክኖሎጂዎች ተሰርተዋል። በእኛ አገርም ይህንኑ ማዕከል በማድረግ ቢሰራ መልካም ነው። በአሁኑ ወቅት የስልክ አገልግሎት ብዙ ቦታ እየደረሰ ነው። ኢንተርኔት በየቦታው ተደራሽ እየሆነ ይገኛል።
ስለዚህ ገጠር ውስጥ ርቆ ያለውም ተማሪም ይሁን ከተማ ውስጥ ያለው ተማሪ ተመሳሳይና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ተማሪው ጥራት ያለው ትምህርት ይዞ ሲወጣ፤ ኢኮኖሚውን መቀየር ይችላል። የመንግሥት ኃላፊውም፣ የባንክ ሠራተኛውም፣ የጤና ባለሙያውም፣ ነጋዴ የሚሆነውም ሁሉም ከትምህርት ይዞት በሚወጣው ልክ ነው ሊሰራ የሚችለው። ስለዚህ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጀመሪያ ለትምህርት በሚገባ መጠቀም ቢቻል እጅግ በጣም ጥሩና የሚያመጣው ውጤትም ትልቅ ነው፡፡
ሁለተኛው የመንግሥት አገልግሎቶችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲደገፉ ማድረግ ያስፈልጋል። ብዙ ሰዎች በመንግሥት አገልግሎት ሲማረሩ ይሰማል። ለችግሩ የተለያየ ምክንያት ቢኖረውም ቴክኖሎጂ ብንጠቀምና መረጃዎች በሲስተም ተደራጅተው መቀመጥ እንዲችሉ ቢደረግ መረጃ ጠፋ አይባል፤ የመረጃ መፋለስ አያጋጥምም ባጠቃላይ ከቅሬታ የጸዳ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ይቻላል። ለዚህም ሠራተኞችን በትንሽ ስልጠና ማብቃት ይቻላል፡፡
ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት ተቋማት ይልቅ የግል ዘርፎች በበለጠ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ለአብነትም ባንኮችን መጥቀስ ይቻላል። ባንኮች ያለ ኮር ባንኪንግ አይሰሩም። በዚህም አንድ ቅርንጫፍ ላይ አካውንት የከፈተ ሰው ሌላ ቦታ ሄዶ ገንዘቡን ማውጣት ይችላል። በኤቲኤም ማሽን ገንዘብ ማውጣት ይቻላል። በሌሎችም ዘርፎች ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየሆነ ነው። ነገር ግን የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ትምህርት ላይ በስፋት ማየት አልተቻለም። ይህም ወደኋላ አስቀርቶናል፡፡
ግብርና ላይ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በደንብ መጠቀም ይቻላል። እንደሚታወቀው በአገሪቱ ያለው መሬት የአገሪቷን ህዝብ አጥግቦ ለውጭ ኤክስፖርት ማድረግ የሚያስችል አቅም አለው። ይሁንና አገሪቷ በተፈጥሮ የተሰጣትን ይህን ጸጋ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም አልሰራንበትም። ቴክኖሎጂን ብንጠቀም የት ቦታ ላይ ምን የተሻለ ምርት ማምጣት ይቻላል? በየአካባቢው ምን አይነት በሽታዎች አሉ? የአየር ሁኔታው ምን አይነት ነው? የትኛው ቦታ ላይ ነው ምርጥ ዘር መጠቀም ያለብን እና ሌሎች ጥያቄዎችንም ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም መመለስ ይቻላል። በስፋት ለሚያመርተውም ሆነ በትንሽ መሬት ላይ ለሚያመርተው አርሶ አደር መረጃው ጠቃሚ ነው። ስለዚህ እንደ አገር ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ትምህርት፣ የመንግሥት አገልግሎትና ግብርና ላይ በደንብ ብንጠቀምበት ውጤታማ በመሆን አገርን መቀየር እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ ምልከታ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ኢትዮጵያ በምን ደረጃ ላይ ናት ማለት ይቻላል? ችግሮቹና መፍትሔውስ?
አቶ መርዕድ፡- እውነት ለመናገር በጣም በብዙ ወደኋላ ቀርተናል። እርግጥ ነው ዘግይተን በመምጣታችን ያገኘናቸው ጥቅሞችም አሉ። ለአብነትም ስልክን ብንመለከት እንደሌሎች አገራት ከአናዶል ስልክ ተነስተው ከዛም ዲጅታል ስልክ፣ ፋክስና ሌሎችንም በሂደት ተጠቅመው ቀስ በቀስ ነው አሁን ላይ የደረሱት። እኛ ግን ዘግይተን ወደ ቴክኖሎጂው በመምጣታችን በአንድ ጊዜ ሁሉንም አልፈን አሁን የተደረሰበትን ቴክኖሎጂ ዛሬ ገዝተን ማምጣትና መጠቀም ችለናል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የማምጣት ዕድሉም አለን።
ቴክኖሎጂን በይበልጥ እየተጠቀምንበት ያለው ግን ለማህበራዊ ሚዲያ ለፌስቡክ እና ለዩቲዩብ ነው። ብዙ ሰዎች ዩቲዩብ ላይ ነው ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ፤ ዳታዎች ቢታዩ የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። ከዛ ይልቅ ግን ሰዎች ኑሯቸውን ለማሻሻል፣ ትምህርትን ለማሻሻል፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማሻሻልና ግብርናን ለማሻሻል እና ሌሎች ኑሯችንን ቀለል ማድረግ ለሚያስችሉ ተግባራት ብናውለው በአጭር ጊዜ ብዙ ነገሮችን መለወጥ እንችላለን።
በሌላው ዓለም ቴክኖሎጂን በመጠቀም በቤታቸው ተቀምጠው ሁሉንም ነገር ያገኛሉ። እኛ ግን ወደኋላ በመቅረታችንና በሚፈለገው መንገድና ልክ ቴክኖሎጂን ባለመጠቀማችን ምክንያት ዛሬም ለመብራት፣ ለውሃና ለሌሎች ክፍያዎች እንሰለፋለን። በዚህም ጊዜና ጉልበት እናባክናለን። ስለዚህ ቴክኖሎጂን በአግባቡ ጥቅም ላይ ልናውለው ይገባል።
እርግጥ ነው በትራንስፖርት ላይ እየታየ ያለ ለውጥ አለ። እሱ ጥሩ ነው ራይድ፣ ፈረስና ሌሎችም ቴክኖሎጂን በመጠቀማቸው ይህን አገልግሎት ማግኘት ችለናል። ነገር ግን ከዚህ በበለጠ የዕለት ተዕለት ኑሯችንን ማቅለል የምንችልባቸው ብዙ አይነት ቴክኖሎጂዎች ያሉ ቢሆንም የአብዛኛው ሰው ትኩረት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በመሆኑ ገና ብዙ ይቀረናል። አልተጠቀምንበትም።
ለዚህም አንደኛው ማነቆ በአገሪቱ የነበረው አንድ ቴሌኮም ብቻ የነበረ በመሆኑና የአገልግሎት አሰጣጡ ጥሩ ስላልነበረ ነው። አሁን ግን ተጨማሪ ቴሌኮም መጥቷል። ነባሩም አገልግሎቱን በደንብ እያሻሻለ ነው። በዚህም የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እየጨመረ መጥቷል። ሁሉም ሰው የኢንተርኔት ተደራሽ መሆን ችሏል። ነገር ግን ይህን ተደራሽነት ለፌስቡክና ለዩቲዩብ ብቻ መጠቀም ሳይሆን ልክ እንደፈረስና ራይድ ሁሉ ለውሃ፣ ለስልክ፣ ለግብር መክፈያና ለሌሎች አገልግሎቶችም መጠቀም ቢቻል ብዙ ለውጦችን ማምጣት ይቻላል። አንደኛ ሰውዬው ታክስ ለመክፈል ጊዜውን አያባክንም። ሁለተኛ መንግሥትም ተገቢውን ክፍያ በጊዜው መሰብሰብ ይችላል። ስለዚህ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷል ብለው ያምናሉ ካልሆነስ ለምን?
አቶ መርዕድ፡– በሃሳብ ደረጃ ቴክኖሎጂ ላይ መሥራት እንዳለብንና ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ይታመናል። በተግባር ግን ለዘርፉ በቂ ትኩረት ተሰጥቶታል ብዬ አላምንም። ዘርፉ መበረታታት አለበት። ቴክኖሎጂው እንዲያድግ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል። በዘርፉ ውስጥ ያሉት ኩባንያዎችም በራሳቸው ጥረት ነው እየተጓዙ ያሉት እንጂ ዘርፉን የሚደግፍና ግልጽ የሆነ ፖሊሲ የለም።
ለዚህም አንዱ እንቅፋት የሆነው ፍራቻ ነው። ምክንያቱም ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ከፍተኛ አቅም ያለው ነው። ዓለም በቴክኖሎጂ ብዙ ርቀት የተጓዘ በመሆኑ ሳይበር አታክ ቢያጋጥም ሙሉ ከተማን በአንድ ጊዜ መብራት ማጥፋት ይቻላል። ለምን ሙሉ ከተማው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተገናኝቷል። የሆነ አገር ላይ የተቀመጠ አንድ አጥፊ ሙሉ ከተማዋ ውሃ እንዳታገኝ ማድረግ ይችላል። ባንክ ላይ ያሉ ገንዘቦችን በአንድ ጊዜ ጠራርጎ ሊወስድ ይችላል። የዚህን ያህል አቅም አለው።
ስለዚህ ቴክኖሎጂ ጥቅም እንዳለው ሁሉ የሚያስከትለው አደጋም በዚህ ልክ ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ ያሻዋል። ቀዳዳዎች በሙሉ በአግባቡ መዘጋት አለባቸው። ለዚህም ሳይበር ሴኪዩሪቲ የሚባለው ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በመንግሥት ደረጃ የተቋቋመው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነትም (ኢንሳ) ዋና ሥራው ይህ ነው። እናም የሳይበር ደህንነት ልክ መከላከያ ብለን አገርን እንደምንጠብቀው ሁሉ ሳይበር የሚባለውንም መጠበቅ ካልቻልን ይዞት የሚመጣው አደጋ ከፍተኛ ነው። ይህ ሥራ መሠራት አለበት:: ነገር ግን ‹‹ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደረም›› እንደሚባለው የሚመጣውን አደጋ በመፍራት ኋላቀር ሆነን ልንቀር አንችልም። ስለዚህ ቴክኖሎጂውን እያለማን ጎን ለጎን ደግሞ ቴክኖሎጂው ሌላ አደጋ ይዞ እንዳይመጣ መጠንቀቅና መጠበቅ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
አቶ መርዕድ፡- ያለንበት ዘመን ያለጥርጥር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ዓለም እየተንቀሳቀሰች ያለችው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ነው። ሌላው ቢቀር ያለ ኢንተርኔት ሥራ መሥራት አይቻልም። ወደፊት ደግሞ የባሰ ቴክኖሎጂ አስገዳጅ እየሆነ የሚመጣበት ጊዜ ነው። ስለዚህ እንደ አገር አሸናፊ እንድንሆንና ቀድመን መጓዝ እንድንችል ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን። ለቴክኖሎጂ ትኩረት ከሰጠን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሌሎች ዘርፎችን ማለትም ግብርናን፣ ጤናንን፣ ትምህርትን፣ የባንክ ሥራን፣ ነጋዴውና መንግሥትንም ጭምር እናግዛለን። በተለይም አገር በቀል የሆኑ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲበረታቱና በየዘርፉ ገብተው ማገዝ እንዲችሉ መደገፍ ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂ እያደገ ሲመጣ የውጭ ባለሃብቶችን በቀላሉ መሳብና ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ለዳረጉልን ትብብር እናመስግናለን!
አቶ መርዕድ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም