አንድ አገር ስኬትና ኪሳራን የምታወራርደው ባለመችው፣ እልምታም ባበቃችው ትውልድ ነው። ትምህርት ደግሞ ይህን ትውልድ እውን ለማድረግና ለአንድ አገር እድገት መሰረት፣ ዋልታና ማገር ነው። የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅና የተደራሽነት መጠኑን ማስፋትም የአገርን እድገት አንድ እርምጃ ወደፊት ለማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም።
ኢትዮጵያ፣ ‹‹የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም›› ፣ ተማር ልጄ… ተማር ልጄ…..ላልተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው››የሚለው የእናት አባት ምክር ከቃል አልፎ በሙዚቃ ተከሽኖ ትውልድ የተሻገረባት፣ ‹‹መማር ያስከብራል አገርን ያኮራል!››የሚለው ቃልም በዜማ ታጅቦ በዝማሬ ሲሰማ የቆየባት አገር ናት።
ትምህርትን በአግባቡ የተጠቀሙ እና ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት የተከተሉ የዓለም አገራት ቁሳዊና ሰብዓዊ እድገታቸው ጎልቶ የሚታይ ነው::እንደ አገር ለቅኝ ገዢ የማትመቸው አገር ኢትዮጵያ፣ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓትን ከተዋወቀችበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርት ስርዓቷን ነጻ ሳታደርገው ቆይታለች።ከዛም ሲሻገር ሥርዓተ ትምህርቷ ከውጪ አገራት ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውስጥ ፖለቲካ ጫናም ጸድቶ ያውቃል ብሎ ደፍሮ መናገርም አይቻልም።
ኢትዮጵያም የምትከተለው ሥርዓተ ትምህርት ለድህነቷና በየዘመኑ ለሚነሳው አገራዊ ግጭት እንደ መንስኤ ተደርጎ ይወሰዳል።የአገሪቱ ዋና ችግር እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ፖለቲካም የተበላሸው የትምህርት ሥርዓት ውጤት እንደሆነ ይነሳል።
የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ እንደሚደመጡት ከሆነ፣ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የቁልቁለት መንገዱ የፈጠነው የደርግን መንግሥት መውደቅ ተከትሎ ወደ ሥልጣን በመጣው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር(ኢሕአዴግ) የአገዛዝ ዘመን ነው::
በወቅቱ ትምህርትን ለሁሉም ዜጐች በስፋት የማድረስ ተልዕኮን እንደያዘ የሚያስበው ኢህአዴግ፤በማዳረስ ላይ የመተማመን ጉዞን በመራመድ የኢትዮጵያን የመማር ማስተማር ሂደት በማጥራት ሳይሆን በማብዛት በሽታ ሲገድለው ቆይቷል::
የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በሚል በሚከናወኑ ተግባራት የትምህርት አቅርቦቱ ሊያድግ ይችላል:: ይሁን እንጂ ከዚህ ጎን ለጎን የጥራቱን ጉዳይ ታሳቢ ያደረገ መንገድ ካልተከተሉ ዞሮ ዞሮ አተርፍ ባይ አጉዳይ ሆኖ መቅረት ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው::
የቀደሙት አመታት ለትምህርት ስርአቱ ሞት በተለይም ለጥራቱ ዝቅጠት ግንባር ቀደም መንስኤዎች ተብለው የተለዩ በርካታ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ::የፈተና አሰጣጥ ሂደት ከዝግጅት እስከ ስርጭት ዝርክርክ መሆንም ከብዙ ችግሮች መካከል በቀዳሚነት ይነሳል::
እንደሚታወቀው ትምህርት የነገ የአገር ተስፋ የሆኑ ተማሪዎችን በእውቀት፣ አመለካከትና ሥነምግባር ቀርጾ የማውጣት ቁልፍ ሲሆን ፈተና ደግሞ የዕውቀት መለኪያ ነው። ፈተና ተማሪዎች በትምህርት ወቅት በገበዩአቸው እውቀቶች ልክ የሚፈተሹበትና የሚለኩበት ሚዛን ነው።
ይሁንና በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በፈተና አሰጣጥ ሂደት በሚስተዋሉ ድክመቶች ተማሪዎች በተደራጀ ሁኔታ ኩረጃ ላይ ሲተጉ ተስተውሏል። ኩረጃ በዕለት ተዕለት የትምህርት ስርዓት ወቅት የሚያጋጥም ቢሆንም በተለይ በብሔራዊ ፈተናዎች ላይ የሚከወንበት መንገድ ዘመን ባመጣው ቴክኖሎጂ የተደፈገ መሆኑ ኪሳራውን ከፍ አድርጎታል።
ኩረጃው በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በፈተና ጣቢያ አስተባባሪዎች፣ በፈታኝ መምህራን፣ በመስተዳድር ኃላፊዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በተለይም ስማቸውን በመሸጥ ጥሩ ገቢ ለማግኘት በሚጥሩ ትምህርት ቤቶችም ጭምር መቀነባበሩም የኢትዮጵያን የትምህርት ስርአት ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎት ቆይቷል።በመንግስት በኩል ችግሩን ለመከላከል ለተከታታይ ዓመታት የተለያዩ ተግባራት ቢከናወኑም ውጤታማ መሆን ግን አልተቻለም።
ለአገሪቱ ትምህርቱ ጥራት ውድቀት እንደ ምክንያት ከሚነሱ ችግሮች መካከል ሌላኛው ተማሪዎችን ያለማውደቅ ዘይቤ (Zero Attrition Rate) የሚለው የተሳሳተ ሐሳብ በዋነኝነት ይነሳል::ይህ እሳቤ ተማሪዎች ‹‹ባናጠናም እናልፋለን›› በሚል አስተሳሰብ እንዲያድርባቸውና ሳይዘጋጁ ለፈተና መቅረብ የተለመደ እንዲሆን አድርጎት ቆይታል::
ከአገሪቱ ካስቀመጠችው አነስተኛ ማለፊያ ነጥብ እጅግ ያነሰ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ከመጀመሪያ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉት የትምህርት እርከኖች ቁጥራቸው እየበዛ መምጣቱ ሳያንስ፤ ወደ መሰናዶ ትምህርት የገቡት ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበት አሳፋሪ ሁኔታ ፈጥሯል።
ምንም እንካን በርከት ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠታቸው እሰይ የሚያስብል ቢሆንም ቀደም ባሉት አመታት አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚከፈቱት ለብዙሃኑ እንደሚታደል መሰረታዊ ሸቀጥ ተቆጥረው መሆኑም ሌላው ለዘርፉ ራስ ምታት እንደነበር ይታወሳል::የዩኒቨርሲቲዎቹን አቅምና ፍላጎት ከመዳሰስ ይልቅ ተማሪዎችን በገፍ ለማስመረቅና ለፖለቲካ ጥቅም እንጂ፣ለአካባቢው ሕዝብ ብሎም ለአገሪቱ ዕድገት በሚያስፈልግ መልኩ ተገቢው ጥናት ተደርጎባቸው አልነበረም::
በእነዚህና በሌሎችም ግዙፍ ችግሮች በአጠቃላይ በትምህርት ተግተው እውቀት ሸምተው ኢትዮጵያን ለመጥቀም የሚታትሩና ለትምህርት ትኩረት በመስጠት የሕይወት መስመራቸውን የሚያስተካክሉ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ እንዲሽቆለቆል አድርጎታል።
የትምህርት ሥርዓቱ በመሰል ሰንሰለቶች ተተብትቦ መስመር ሊይዝ ባለመቻሉ እና ተቆርቋሪ ባለቤት በማጣቱም አገሪቱ የተማረና የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል እያጣች፣ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችም በየጊዜው ሲባባሱ አስተውለናል::
ትምህርት በኢትዮጵያ እጅግ ውስብስብ ለሆኑ የፖለቲካ ቀውሶች መነሻ ሲሆን የታየበት አጋጣሚ ብዙ ነው:: ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በየጊዜው የሚያገረሸው የብሔር ፖለቲካ ውዝግብና የተማሪዎች ግጭት ከጥናትና ምርምር ይልቅ ዩኒቨርሲቲዎችን ዝነኛ ሲያደርግ ይታያል::ብሔራዊ ፈተናዎች ጊዜያቸው በደረሰ ወይም ውጤት በተለጠፈ ቁጥር፣ በአገሪቱ የሚነሳው የፖለቲካ ውዝግብ ደግሞ ከዓመት ዓመት እየጨመረ ሲሄድ ታዝበናል::
በመሰል መፍትሄ በራቃቸው ችግሮች ከአመት አመት ‹‹ያልተማሩ አባቶቻችን ያቆዩዋትን አገር የተማሩ መኃይማን ደርሰው አፈረሷት›› ሲባል መስማት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎም፣የዘርፉ ምሁራንም ሳይውል ሳያድር ጊዜና አቅም ሰጥቶ የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻል እስካልተቻለ ድረስ አገሪቱ አስከፊ ቀውስ ውስጥ ትገባለች በሚል በተደጋጋሚ ሲወተውቱም ቆይተዋል::
ይህ ውትወታ ታዲያ በተለይ ከኢሕአዴግ ከሥልጣን መወገድ በኋላ፣ ሰሚ ጆሮ ማግኘት የቻለ ሲሆን የለውጡ መንግስትም እንደ መፅሃፍ ቅዱስ ቃል ሳይነካ የቆየውንና የአገሪቱን ትምህርት እንዘጭ እንቦጭ ሲያደርግ የከረመውን ፖሊሲ ለመለወጥ ትኩረት ሰጥቷል::
ቀድሞ የነበረውን የትምህርት ዘርፍ ችግር ያስቀራል የተባለ የትምህርት ማሻሻያም ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ሲደረግ የቆየ ሲሆን፤ በዚህም የትምህርትና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ ከማዘጋጀት ጀምሮ አዳዲስ አሠራሮችን አስተዋውቃል::
አዲሱ ፍኖተ ካርታው ሙያው ላይ ባሉ ምሁራን የተዘጋጀ፣ ለበርካታ ዓመታት የተደረገን ጥናት መሠረት ያደረገ እንደመሆኑም ለግብረ ገብነት፣ለአገር በቀል ዕውቀት፣ለሙያና የቀለም ትምህርት፣ ለቴክኖሎጂ፣ ምርትና ተግባራዊ፣ ጥናትና ምርምር ትኩረት ተሰጥቷል::
በአዲስ ስርአት ትምህርት ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩና ዘርፉን ተብትበው ያሰሩ ሰንሰለቶችን ለመበጣጠስ ይረዳሉ በሚል ከተለዩ መፍትሄዎች መካከልም የፈተና ስርአቱን ፈር ማስያዝ ዋነኛ ሆኖ ይጠቀሳል::በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተማሪዎች ዘንድ እየተስፋፋ የመጣውን ኩረጃና የፈተና ስርቆት ለመግታት በተለይ ባለፈው ዓመት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።
በተለይ ኩረጃና የፈተና ስርቆት ለመከላከል፣ ኩረጃን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠርና በማህበራዊ ሚዲያው ከዕውቀት ይልቅ ጥፋትን ለሚዘሩ የጥፋት መልዕክተኞች እድል ላለመስጠት ዘንድሮ በፈተና አሰጣጥ ሂደት ላይ ስር ነቀር ለውጥ አድርጓል።ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርትና ማሰልጠኛ ተቋማት ብሄራዊ ፈተናው እንዲሰጥ ተደርጓል።
የብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን በየዩኒቨርሲቲው በመውሰድ ለኩረጃ ፍፁም አመቺ በማይሆን መንገድ እንዲፈተኑ የማድረጉ ዕርምጃ፣ ትምህርት ሚኒስቴርን ለብዙ ትችቶች ያጋለጠ ደፋር ዕርምጃ እንደነበር የሚታወስ ነው::ይሁንና በትግበራው ሂደት ከሌሎችም ነባራዊ ሃቆች ጋር ተዳምሮ የሚፈለገው ምት መምታት ችሎ አሳይቷል::ዘንድሮ የ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱት 996 ሺህ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ያለፉት 3 ነጥብ 3 ከመቶ ወይም 29 ሺህ 909 ብቻ መሆናቸው ለዚህ ምስክር ሆኖ መቅረብ የሚችል ነው::
እንደ እኔ እምነት በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና አሰጣጥና ዕርማት ሒደትን ትምህርት ሚኒስቴር በጥብቅ ሒደት እንዲካሄድ በማድረጉ በመጨረሻ የመጣው ውጤት የኢትዮጵያ ትምህርት የሚገኝበትን የጥራት ጉድለት ያለንበትን ቀውስ ብሎም የችግሩን ልክ በአግባቡ፣ በአሐዝ መረጃ ፍንትው አድርጎ አደባባይ አውጥቷል::
በሺህ የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪ እንኳን ለማሳለፍ ያልቻሉበት ሁኔታና የተማሪዎቹ መውደቅ በትምህርት ስርዓቱ ለረዥም ጊዜ ሲጠራቀሙ የመጡ ብልሹ አሠራሮች ውጤት ነው:: የተማሪዎቹ አስከፊ ውድቀት የቀድሞው ስርአተ ትምህርት ድምር ውጤት ነው::
ከተፈታኞቹ ሃምሳ ከመቶና ከዚያ በላይ ጥያቄዎቹን መልሰው ለማለፍ የቻሉት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ አናሳ መሆን ቀደም ባሉት አመታት ይሰጥ በነበረው ፈተና በአብዛኛው ተማሪዎቹ ውጤት እንጂ እውቀት እንደሌላቸው ፍንትው አድርጎ ያስመለከተ ነው::
የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ዛሬ የተፈተኑትን ተማሪዎች የሚያስተምሩ አስተማሪዎች ከተመለመሉበት፣ ከሠለጠኑበት መንገድ፣ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ ከተመራበት ፖሊሲና አቅጣጫ እና ከሌሎች ብዙ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ፤ ባለፉት አሥርት አመታት የሄድንበት የተንሻፈፈ ጉዞ ውጤት ነው።
ይህን ከመረዳት ይልቅ ከዚህ በተቃራኒ መንግሥት በትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ስም የብዙ ተማሪዎችን የወደፊት ሕይወት በፈተና እያበላሸ ነው የሚል ትችት የሚሠጡ ይሰማሉ::ይሁንና መራርም ቢሆን ሃቁን ልንቀበልና እየመረረንም ልናጣጥመው ይገባል::
የመንግስት የለውጥ ጉዞ እርምጃውም ኢትዮጵያ በቂ የተማረ እና ለውጥ የሚያመጣ ትውልድን እንድታገኝ ትልቅ አቅም የሚሰጥ ነው:: መሰል አሰራር በስርቆት መተማመንም ሙሉ በሙሉ ያስቀራል:: ከስርቆት ይልቅ በራሱ አቅም የሚተማመንና በእውቀት የላቀ ትውልድን ለመፍጠር አቅም ይፈጥራል::
በእርግጥ ከብዙ ጥናትና ሙግት በኋላ ኩረጃና ሥርቆትን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ተግባራዊ የተደረገው የተማከለ የፈተና ስልት ያስገኘው ውጤት ከፍተኛ ማኅበረሰባዊ መደናገጥን ሲፈጥር ታይቷል።ለረዥም ዘመን ሳይገለጥ፣ አልፎ ተርፎም እንደ ትክክለኛ ነገር ሲቆጠር የኖረን ማኅበራዊ ስብራት በሆነ አጋጣሚ ተገልጦ ፊት ለፊት ሲጋፈጡት በመጀመሪያ በድንጋጤ ተውጦ የሚያደርጉት ቢጠፋ እምብዛም አይደንቅም፤ ተፈጥሯዊ ምላሽም ነው።
ይሁንና ጉዳዩንና የነገሩን መሠረት ለመካድ መሞከር ወይም ሰንካላ ሰበብ እያስቀመጡ ማለፍ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉትም፣ለወባ በሽታ የወባ መድኃኒት እንጂ፣ ገና ለገና በሽታው እንደ ራስ ምታትና ብርድ ብርድ የማለት ምልክቶችን አሳየ ተብሎ የብርድና የራስ ምታት ማስታገሻ መድኃኒቶችን እንደ ዘላቂ መፍትሔ አይወሰድም። ችግሮች ሲገጥሙ ጣት መጠቆምና በቀዳዳ ሾልኮ ማምለጥ የሞኞችና የፈሪዎች መፍትሔ ሲሆን፤ ትክክለኛው የብልህና የጀግኖች መንገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ፊት ለፊት ተጋፍጦ በጥበብ ለመርታት መፍጨርጨር ነው።
ችግሩ በአንድ ሌሊት እንዳልተፈጠረ ሁሉ መፍትሔውም በአንድ አዳር ሊመጣ አይችልም። ዛሬ ከአበባ አልፎ ፍሬውን ያየነውን የትምህርት ችግር ቀልብሶ ለማስተካከል ረጅም ጊዜና ከባድ ዋጋ ይጠይቃል። የትናንት ስህተታችን የፈጠረውን የዛሬ ስብራታችንን ተረድተን ዘላቂ መፍትሔ ከሚፈጥሩት ወገን ለመሆን መዘጋጀት አለብን። አዲስ ሃሳብና ጉልበት ለመገስገስ ተስፋ ሰንቀን እንነሳ፤ ለላቀ ለውጥና ለተሻለ ነገ እንትጋ። እንደ ሀገርና እንደ ማኅበረሰብ የሚያዋጣን መንገድ ይሄ ነው።
ታዋቂው የሳይንስ ሊቅ አልበርት አንስታይን እንዳለውም አንድን ነገር በተመሳሳይ ዘዴ ደግሞ ደጋግሞ በመስራት የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው::በመሆኑም አዲሱን የለውጥ መንገድ የግድ ልንቀበልና በተለየ መንገድ በመራመድ ለችግሩ መፍትሄ ልንሰጠው ይገባል::መንግስት የአገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ መርምሮ አሳሪና ለትምህርት ጥራት መውደቅ ምክንያት የሆኑ ስንክሳሮችን ማውጣትና መሰል ደፋርና ውጤታማ ተጨባጭ ስራ መስራቱን ሊቀጥል ይገባል::
በመጨረሻም አንድ ነገር ብዬ ላብቃ:: አሁን ባለው ሁኔታ ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችል ትኬት የቆረጡት 30 ሺ የሚሆኑት ብቻ ናቸው::ይሁንና መንግስት የዘንድሮን የዩኒቨርሲቲ የመቀበል አቅም ታሳቢ ባደረገ እና ትግበራው በአገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ እንደመሆኑ ለአንድ ጊዜ በሚከወን መልኩ ለአንዳንድ ተማሪዎች እድል መስጠትን ታሳቢ ማድረግ ቢችል መልካም ነው::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም