ከለውጡ በፊት የነበረው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስብስብ በሆኑ ችግሮች የተያዘ፤ ሀገርን እንደሀገር የከፋ የህልውና አደጋ ውስጥ ሊከት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደነበር ይታወቃል፤ ከለውጡ ዋነኛ ገፊ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ይኸው በኢኮኖሚው ዘርፍ የነበረው ሀገራዊ ስብራት መሆኑም ይታመናል።
በመንግስት መዋቅር እስከ መደገፍ የደረሰ የከፋ ሙስና ፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ሳይቀሩ የሚሳተፉበት የኮንትሮባንድ ንግድ ፣ ምርት ላይ ሳይሆን ብድር ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ መንገድ፣ የዓባይ ግድብን ጨምሮ የነበሩ የፕሮጀክቶች መዘግየትና ጥራት መጓደል፣ በተለያየ ጊዜ የተወሰደና ሲንከባለል የመጣው ከፍተኛ የሀገር ዕዳ፣ ከሀገር በስፋት ሲሸሽ የነበረ ሀብት ወዘተ ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ስብራት ተጠቃሽ ምክንያቶች ነበሩ።
በወቅቱ አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ከውጪ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ በሙሉ አቅም ማምረት አለመቻላቸው ፤በምርት ሂደት ውስጥም ያሉት ቢሆኑ በሰላም እጦት አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከምርት ውጪ መሆናቸው፤ የሀገራዊ የኢኮኖሚ ስብራቱ መገለጫ እንደነበሩ ይታወሳል።
ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል የሚያስችል የውጪ ምንዛሬ ክምችት አለመኖር፤ መንግስት መንግስታዊ ስራውን ማከናወን የሚያስችል በቂ ሀብት በእጁ አለመኖሩ፤ ከዚያም ባለፈ በተጠና እና በተናበበ መንገድ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሲደረጉ የነበሩ አሻጥሮች ሌሎኞቹ የስብራቱ ማሳያ ነበሩ።
ይህን ተጨባጭ ተግዳሮት ሰብሮ ለመውጣት የለውጥ ኃይሉ /መንግስት/ አዲስ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምሮ ስትራቴጂክ በሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ፈጣን የማሻሻያ ርምጃዎችን በመውሰድ ሀገርን ከፍ ካለ ውድቀት መታደግ ችሏል።
በተለይም እንደ የዓባይ ግድብን የመሳሰሉ ሀገራዊ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ችግሮች ፈጥኖ በማጥናትና ፕሮጀክቶቹ ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚቀጥሉበትን አዲስ የቁጥጥርና የክትትል ስርአት በመንደፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭ ተግባራትን አከናውኗል።
በመንግስት መዋቅር ሲካሄዱ በነበሩ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዷል፤ ለከፍተኛ ሙስና የተጋለጡ ተቋማትን በመለየትም በአዲስ አደረጃጀትና አመራር ተስፋ ሰጪ ወደ ሆነ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ ማድረግ ችሏል።
ኢኮኖሚው በአንድ ወይም በሁለት ዘርፎች ሳይታጠሩ ዘርፈ ብዙ እንዲሆኑና በብዙ ተግዳሮት ውስጥ የነበረው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚነቃቃበትን የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም ኢኮኖሚው መንግስት ተገዶ የገባበትን ጦርነት መሸከም የሚያስችል አቅም እንዲፈጥር አድርጓል። በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋማት የተመሰከረለትን ዕድገትም በየዓመቱ እያስመዘገበ እንዲሄድ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ችሏል።
በእርግጥ ሀገራዊ ኢኮኖሚያቸው ረጅም መንገድ የተጓዘ ችግር ውስጥ ያሉ ሀገራት፤ ኢኮኖሚያቸውን ከውድቀት ታድገው ከፍያለ ሀገራዊ አቅም ለመገንባት የሚያደርጓቸው ጥረቶች በአንድ ምሽት ተጀምረው የሚያበቁ አይደሉም። የትናንት ስብራቶቻቸውን በሚገባ ተረድተው በአግባቡ ማከምን የሚጠይቅ ነው።
ከዚህ አንጻር መንግስት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ስብራት በአግባቡ አጥንቶ ስብራቱን ለመፈወስ እየሄደበት ያለው መንገድና የሚጓዝበት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ እሴቶች የሚበረታቱና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ድል ለማስመዝገብ መሰረት እየጣሉ ያሉ ናቸው።
ከዚህ አንጻር መንግስት ሰሞኑን ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያድግበታል ብሎ ያስቀመጠው የትንበያ ውጤት፤ተስፋ ሰጪ ነው፤ በቀጣይ የተጀመረው ሀገራዊ የሰላም ጥረት ተጨባጭ ፍሬ ሲያፈራ እውነታው ከዚህ የተለየ ገጽታ ሊኖረው እንደሚችልም ይታመናል።
ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያም ቢሆን ሀገሪቱ ካለችበት የተመራጭነት ደረጃ አንጻር፤ በቀጣይ ሊኖር የሚችለው የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ፍሰት ዓመታት ያስቆጠረውን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ስብራት ለማከም ትልቅ አቅም እንደሚሆንም አያጠራጥርም።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም