በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው የግብርናው ዘርፍ አሁንም የመሪነቱን ሚና ይዞ ቀጥሏል። በ2015 በጀት ዓመት ስድት ወር በዋና ዋና ማክሮ ኢኮኖሚ እቅድ አፈጻፀም ላይ በተደረገ ውይይት ግብርናው በተሻለ አፈፃፀም ላቅ ያለ ሆኖ መገኘቱ መገለጹ ይታወሳል። ግብርናው እንዲሸጋገር (ትራንስፎርም) እንዲያደርግ መንግሥት በልዩ ትኩረት የሰራው ሥራ ውጤት እንደሆነም ከተከናወኑት ተግባራት መገንዘብ ይቻላል። ከዋና ዋና ተግባራቶች መካከልም ዘርፉ በግብርና ሜካናይዜሽንን እንዲታገዝ የተሰራው ሥራ አንዱ ሲሆን፣ ለተከታታይ አራት ዓመታት የተከናወነው የበጋ ቆላ መሥኖ ልማትም ግብርናው ከፍ እንዲል ካደረጉት ተግባራት ይጠቀሳል። የበጋ መስኖ ልማቱ ግብርናው እንዲነቃቃ ያስቻለ እንደሆነም ይታመናል፡፡
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ልክ በሰፊው አቅዷል። በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ በቅርቡ በተያዘው የሌማት ቱሩፋት እቅድ ደግሞ በእንስሳትና እንስሳት ውጤቶች፣በንብ ማነብ ሥራዎች እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል። የግብርናው ሥራ ክረምት ከበጋ እንዲከናወን በማድረግም በክረምት ላይ ብቻ ያተኮረውን የግብርና ሥራ ባህል በመቀየር የትኩረት ሥራው አስተዋጽኦ አድርጓል። በተለይም የግብርናው የመአራረት ዘዴ ኋላ ቀር ሆኖ መቆየት እንዲሁም ለልማቱ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ከመሆን ጋር ተያይዞ እየለማ ያለው መሬትም ካለው ለልማት ሊውል ከሚችለው የመሬት የሀብት መጠን ጋር የተጣጣመ እንዳልሆነ በማሳያነት ይነሳል፡፡
ዘርፉን በግብርና ሜካናይዜሽን ለመደገፍ የተጀመረው ሥራ ከልማት ውጭ ሆኖ የቆየውን መሬት ወደ ልማት በማስገባትም ድርሻ እንዳለው ከዘርፉ ባለሙያዎች ይሰማል። መሬትን ወደ ልማት ከማስገባት በተጨማሪ መንግሥት በሰፊው አቅዶ እያከናወነ ያለውን የግብርና ሥራ ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው የግብርና ሜካናይዜሽን ትግበራ ሲጠናከር እንደሆነ እሙን ነው። እኛም በጉዳዩ ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ሙያዊ ትንታኔ እንዲሰጡ ጋብዘናል፡፡
እንግዳችን ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ፣ እንደ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን፣ የግብርናውን ሥራ በተግባር ለማየትም ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የነገሩን። በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። እንደ ዶክተር ይፍሩ ገለጻ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያስፈልጉና ወሳኝ ከሆኑት ግብአቶች እንደ ትራክተር፣ ማጨጃና መውቂያ የመሳሰሉ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም በሰብልም ሆነ በእንስሳት ልማት የተሻሻለ ዝርያና አስፈላጊ ግብአቶች ያስፈልጋሉ።
በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልም ወሳኝ ነው። ሆኖም ግን የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እንዳይለወጥ (ትራንስፎርም) እንዳያደርግ ቀስፈው ከያዙት መካከል የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦት አለመኖር ነው። 90 በመቶ የሚሆነው የሰብል ልማት ሥራ የሚከናወነው በሬ በቀንበር ጠምዶ በማረስ ነው። ይህን ማነቆ ለመፍታት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት የግብርና ሜካናይዜሽንን ጥቅምና አስፈላጊነት በጥናት የተደገፈ አሳማኝ የሆነ ሰነድ አዘጋጅቶ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በማቅረብ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። በዚህ የጥናት ሰነድ መንግሥትን ለማሳመን የተሞከረው ቀረጥ የተከፈለበትና ከቀረጥ ነጻ በግዥ ወደ አገር ውስጥ በሚገባ የግብርና ሜካናይዜሽን በሚሰጥ አገልግሎት መካከል ሊገኝ የሚችለውን ትርፍና ኪሳራ በሂሳብ ስሌት በማቅረብ ነው። ጥናቱ በምንግሥት አመኔታ አግኝቶ ከሶስት አመታት በፊት ጀምሮ የግብርና ሜካናይዜሽን ከቀረጥ ነጻ ወደ አገር ውስጥ በመግባት ላይ ይገኛል፡፡
በተመቻቸው ነፃ ቀረጥ እድል የግብርና ሜካናይዜሽንን ተደራሽ ለማድረግ ክልሎች በስፋት ገዝተው ለማህበራት በማከፋፈል የግብርና ሜካናይዜሽንን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ በግላቸውም በመግዛት አገልግሎት የሚሰጡም ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። እንደ አገር ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግርና በተለያዩ ምክንያቶች የግብርና ሜካናይዜሽን ዋጋ ውድ ነው። ይህም በተደራሽነትና በአገልግሎት ዋጋ ላይ ውስንነት ይፈጥራል። በተለይም ለአገልግሎት የሚጠየቀው ገንዘብ ከአቅም በላይ ሲሆን አርሶአደሩ ሊጎዳ ይችላል። ለዚህ መፍትሄው አርሶአደሩ በሚቀርብለት የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን፣ ከሰብል ልማት በተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል። አብዛኛው የኢትዮጵያ አርሶ አደር ከአንድ ሄክታር በታች (ሰባት ነጥብ ሰባት) የመሬት ይዞታ ነው ያለው። ተጨማሪ ገቢ ከሌለው ያለው የመሬት መጠንና አቅም ትራክተር ለመጠቀም አያስችለውም፡፡
ሌላው መፍትሄ ኩታገጠም (ክላስተር) የግብርና ዘዴን መጠቀም ነው። መንግሥትም በአሁኑ ጊዜ በዚህ አቅጣጫ እየሰራ ይገኛል። አሁን ባለው አንድ ኩታገጠም (ክላስተር) 15 ሄክታር ነው። አርሶአደሩ በዚህ መንገድ ከተንቀሳቀሰ የግብርና ሜካናይዜሽን ለመጠቀም ያስችለዋል። ያዋጣዋልም። ይህ ዘዴም ወጭ ቆጣቢ በመሆኑ አርሶአደሩን ተጠቃሚ ያደርገዋል። የተደራሽነትንም ክፍተት ይሞላል። በዚህ መንገድ እየተበረታታ በመሆኑ የተፈለገውን በግብርና ሜካናይዜሽን መጠቀምን ማጎልበት ይቻላል፡፡
እንዲህ ባለው የተደራሽነትና ተጠቃሚነት አሰራር እንዲሁም መንግሥት በግብርናው ዘርፍ የያዘውን ሰፊ የልማት እቅድ በግብርና ሜካናይዜሽን የማከናወን ተግባር በምን ያህል ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ሊያሳካው እንደሚችልም ዶክተር ይፍሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከሶስት ዓመት በፊት በግብርና ሜካናይዜሽን ግብርናውን ለማሳለጥ እቅድ ነድፎ እንደነበር አስታውሰዋል። ይህም እኤአ በ2030 የተሻገረ ግብርናን ለማየት ታሳቢ በማድረግ ነው።
ቅድመ እቅድ ለማሳካትም የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም ስድስት ዓመት ነው የቀረው። በተለያየ አቅጣጫ በግብርና ሥራ ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው። በተፈጠረው መነቃቃትም በበጋ ቆላ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ ውጤት ተመዝግቧል። ወደ ትግበራ የገባው የሌማት ቱሩፋት ሥራ ሲደመር የግብርናውን ልማት ከፍ ስለሚያደርገው ቢያንስ መዋቅራዊ ሽግግር ላይ የደረሰ ግብርና ይኖራል የሚል እምነት አለ። ብዙ አምራች እንደሚፈጠርም ይጠበቃል፡፡
የግብርና ሽግግሩን ለማሳካት ከመንግሥት ድርሻ በተጨማሪ የተለያዩ አጋሮችን ተሳትፎ ይጠይቃል። የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት አቅርቦት የሚጠበቀው ከግሉ ዘርፍ በመሆኑ ይበረታታል። በዘመናዊ እርሻ ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶችም ያስፈልጋሉ፡፡
አርሶአደሩን በሬ ጠምዶ ከማረስ ስራው በማላቀቅ በግብርና ሜካናይዜሽን ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ከተቻለ በኋላ ወደ ኋላ እንዳይመለስ በቁጥጥርና ክትትል የመደገፍ ሥራ የመንግሥት ድርሻ እንደሆነም መዘንጋት የለበትም። በተለይም ከማን ምን ይጠበቃል የሚለው ሊሰመርበት ይገባል። ዶክተር ይፍሩ በዚህ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ አርሶአደሩ ያለምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ምርት ማምረት እንደማይችል ሁሉ የግብርና ሜካናይዝሽንን ጥቅም ሲገነዘብና ተጠቃሚነቱ ከፍ ሲል ግዴታ አድርጎ ነው የሚቀበለው። ፍላጎቱ አቅርቦቱን ይገፋዋል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡
አርሶአደሩንና የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪውን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በዚህ በኩል መንግሥት የግብርና ፖሊሲ ክለሳ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል። ተከልሶ ወደ ተግባር ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ፖሊሲ ችግሩን እንደሚፈታም ይጠበቃል። እየተከለሰ ስላለው የግብርና ፖሊሲም ዶክተር ይፍሩ በሰጡት መረጃ፤ የዛሬ 21 ዓመት በወጣ የግብርናና ገጠር ፖሊሲ ነበር ዘርፉ ሲመራ የቆየው። በቀደመው እና ሁን ላይ ባለው የግብርና ልማት ሥራ ብዙ ልዩነቶች ተፈጥረዋል። ይህንን ለማጣጣም እንዲሁም እኤአ በ2030 በግብርና ሊደረስበት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ለረጅም በቆየ ፖሊሲ ለመተግበር ስለሚያስቸግር ፖሊሲውን መከለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የማሻሻያ ፖሊሲውም በ10 መሠረታዊ መስኮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ዋና ዋናዎቹም የግብርና ቴክኖሎጂ ግብአት፣ የፋይናንስ (ገንዘብ) አቅርቦት፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ፣ የውሃ አጠቃቀም፣ አቅም ግንባታ ናቸው። ይህንም ኃላፊነት ተቀብሎ እየሰራ ያለው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት እንደሆነና ፖሊሲው ፀድቆ በቅርብ ጊዜ ወደ ትግበራ እንደሚገባም ዶክተር ይፍሩ ገልጸዋል። ቀደም ሲል የነበረው በፌዴራልና በክልሎች መካከል የነበረው ተቀናጅቶና ተናብቦ አለመሥራት ችግርም በዚህ ጊዜ በመሻሻሉ ለግብርናው ሥራ መሳለጥ መልካም ነገሮች ተፈጥረዋል። በበጋ ቆላ መሥኖ ልማት የተከናወነው የቅንጅት ሥራ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
በዚሁ ላይ ተጨማሪ ሙያዊ አስተያየታቸውን የሰጡን በግብርና ሙያ በማማከር ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ የነገሩን ዶክተር አበራ ደሬሳ ናቸው፡ ፡በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ የተጀመረው ልማትና በሌማት ቱሩፋት መርሃግብር ግብርናውን ከፍ ለማድረግ በመንግሥት የተያዘው እቅድ አስፈላጊነቱ አያነጋግርም ያሉት ዶክተር አበራ፤ እቅዱን ለማሳካት በግብርና ሜካናይዜሽን የታገዘ ሥራ መሥራት ግድ እንደሆነ ነው የገለጹት። አቅርቦቱንም በአገር ውስጥ የሚቻለውን በአገር ውስጥ በመሸፈን፣ በአገር ውስጥ የሌለውን ደግሞ ከቀረጥ ነጻ በማስገባት አገልገሎት ላይ የሚውልበትን መንገድ በማመቻቸት የተጀመረውን የልማት ሥራ በማጠናከር ማፋጠን እንደሚጠበቅ ነው ምክረ ሃሳብ የሰጡት፡፡
እንደ ዶክተር አበራ ገለጻ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም እንደየአካባቢው ሥነምህዳር የሚለያይና አብሮ መታየት ያለባቸው ሌሎች ነገሮች በመኖራቸው በግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም የሚደረስበትን ጊዜ ከወዲሁ ለመተንበይ ያስቸግራል። እድገቱ በአገር የገንዘብ አቅምና የግብዓት አቅርቦት ላይም ይወሰናል። በበቂ ገንዘብ መደገፍ ከተቻለ ይፋጠናል፡፡ካልሆነ ግን የእድገት ሂደቱ አዝጋሚ መሆኑ አይቀርም። ይህም ሆኖ የግብርና ሜካናይዜሽን ለመጠቀም ያለው ፍላጎትና ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች በመሆኑ ደረጃ በደረጃ የሚፈለገው ግብ ላይ መድረስ ይቻላል። የግብርናው እድገት አበረታች በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝና አሁን መንግሥት በያዘው አቅጣጫም ተስፋ ሰጪ የሆነ ነገር መኖሩን ነው እንደዘርፉ ባለሙያ የታዘቡት፡፡
እርሳቸውን ጨምሮ በዘርፉ ላይ የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች የግብርና ትራንስፎርሜሽን አስፈላጊነት በተለያየ አጋጣሚ እና መንግሥትም በዘርፉ ምክር ፈልጎ ሲጠይቃቸው እያገዙ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር አበራ። የምክር አገልግሎቱም የመንግሥትን የግብርና ፖሊሲና አቅጣጫ በመረዳት መሆን እንዳለበት፣ ይህን መሠረት አድርጎ የምክር አገልግሎት ሲሰጥም መንግሥት በዘርፉ ያወጣው ፖሊሲና ፕሮግራም አስፈላጊ ነው ወይንም አይደለም የሚል መከራከሪያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ከአማካሪው የሚጠበቁ ተግባራት እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡
የማማከሩ ተልእኮ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ወይንም እንዲያድግ ብቻ ሳይሆን የተመረተው ምርት ገበያ ላይ ውሎ በአርሶአደሩ ሕይወት ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችልበትን መንገድ እንዲሁም ፣ ኢንዱስትሪውንም የሚመግብና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን በሚያጎላ መልኩ የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ማመላከት መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የማማከር አገልግሎቱ ሙያን መሠረት ያደረገ ሲሆን ውጤቱም እንደሚያመረቃ ገልጸዋል። መንግሥትም የአማካሪዎችን ሙያዊ ድጋፍ ለመቀበል ዝግጁ ካልሆነ ማማከሩ ትርጉም እንደሚያጣ ነው የተናገሩት። መንግሥት የሙያ ምክሩን ካልተገበረ ችግሩ ከአማካሪዎች ወይንም የመንግሥት ተደርጎ እንደሚወሰድም ነው ያስረዱት። አማካሪና መንግሥት ተናብበው ከሰሩ ግን ውጤት ይገኛል የሚል እምነት አላቸው። ‹‹ግብርናው አዝጋሚ ሆኖ ሳይሆን በፍጥነትና ተጨባጭ በሆነ መንገድ ነው እድገት ማስመዝገብ ያለበት፡፡አሁን ካለው በእጥፍ መመረት ይኖርበታል። ይህ ሲሆን ነው ለውጥ መጣ የሚባለው›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ዶክተር አበራ እንደአአገር የመንግሥት የገንዘብ አቅም ውስንና ያለው የገንዘብ አቅምም ለተለያዩ የልማት ዘርፎች የሚውል ቢሆንም ግብርናው ላይ ግን የተለየ ትኩረት መሠጠት አለበት የሚል አቋም አላቸው። አሁን ላይ ለግብርናው ዘርፍ በመንግሥት እየተበጀተ ያለው በጀት ግብርናውን በፍጥነት ለማሳደግ የሚያስችል ነው የሚል እምነት የላቸውም። ለዘርፉ በቂ ፋይናንስ መመደብ አለበት ከሚሉ ወጎኖች መካከል ናቸው። ለዘርፉ የተሻለ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በበጋ ቆላ መስኖ ስንዴ ልማት የታየው የተናበበ እቅድና ክንውን በሌሎችም እንዲደገም ማድረግ እንደሚገባም ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም