ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ- የሌማት ትሩፋቱ ቀጣይ አቅጣጫ

በኢትዮጵያ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥና በተለይ ለጤና፣ ለአእምሮ እድገትና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑ ታምኖበት ለአራት ዓመታት የሚዘልቅ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር እየተተገበረ ይገኛል። መርሃ ግብሩ እንደ ወተት፣ እንቁላል ስጋ፣ ዓሳ፣ ማር ያሉትን ገንቢ ምግቦች በቤተሰብ ደረጃ ከማረጋገጥ በተጨማሪ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንዲያስችልም ታስቦ ነው ወደ ትግበራ እንዲገባ የተደረገው።

መርሀ ግብሩ እነዚህ ገንቢ ምግቦች በየዕለቱ ከሌማት እንዳይለዩ በማሰብ የተቀረጸ ነው። የምግብ ዋስትናዋን ላላረጋገጠችው ኢትዮጵያ ምን ይመረት? ለምን ይመረት? እና መቼ ይመረት? በሚሉት ላይ ጥናት በማካሄድ እነዚህን የምግብ ዓይነቶች በስፋት ለማልማት የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ተቀርጸው ወደ ትግበራ ተገብቷል።

በ2015 ዓ.ም አካባቢ ወደ ሥራ የተገባበት ይኸው መርሀ ግብር፤ ጥሩ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። በልማቱ በቤተሰብ ደረጃ በሚካሄድ የሌማት ትሩፋት መርህ ግብር ልማት የተመጣጠነ ምግብ ከመመገብ አኳያ ለውጥ እየመጣ መሆኑ ይገለጻል።

በዚህ ልማት ወተት፣ እንቁላል፣ ሥጋ፣ ዓሳ፣ ማር ገበያ ላይ ይትረፈረፋሉ፤ ዋጋቸውም ይረጋጋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፤ ምርቱ በዝቶ ገበያ ይጠፋና ምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጠራል ተብሎም ተሰግቶም ነበር።

ይሁንና የምርቶቹ የገበያ ዋጋ ግን በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ስጋ በኪሎ ከ600 እና 700 ብር እስከ 2 ሺህ 600 ብር መሸጥ ተጀምሯል። ወተት በሊትር በቅርቡ ከነበረበት 100 ብር በቀናት ውስጥ ዋጋው ወደ 120 ብር አሻቅበዋል። እንቁላል ከ12 ብር የስድስት ብር ጭማሪ በማሳየት 18 ብር እየተሸጠ ይገኛል። ማር በኪሎ ከ600 ብር እስከ 900 ብር እየተሸጠ ሲሆን፤ አሳም በኪሎ ከ250 ብር ወደ 400 ብር ዋጋው አሻቅቧል። እነዚህ ዋጋዎች ከሕዝቡ አቅም ጋር በእጅጉ የተለያዩ በመሆናቸው ሕዝቡ ቅሬታውን ሲገልጽ ይሰማል።

ይህ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሌማት ትሩፋት ዕቅዱ እና አፈፃፀሙ እንዴት ይታያል? ምን ውጤት አስገኘ? እንደታቀደው በሌማት ትሩፋት መትረፍረፍ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው ? የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳንላቸው በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና የዓሳ ሃብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፅጌሬዳ ፍቃዱ እንዳሉት፤ በመርሀ ግብሩ በሰፊው እየተሠራ ሲሆን፣ በዚያው ልክም ውጤታማ መሆን እየተቻለ ነው።

የምርቱ መጨመር የምግብ ዋስትናን ለማሻሻልም የራሱን ድርሻ እየተጫወተ መሆኑን አስታውቀው፣ የአርሶ አደሩን ገቢ ከማሳደግ አንፃርም በርካታ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዲሁም ለብዙዎች የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን በስፋት ለማምረት የሚያስችል ምቹ የአየር ፀባይ አለ። ይህም የኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት ለሆነው የግብርናው ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ከግብርና ውስጥ አንዱ የእንስሳት ሃብት ነው። በሀገሪቱ ያለውን የእንስሳት ሃብት መጠቀም ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፤ መንግሥት የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ቀርፆ እየተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ፤ ፕሮግራሙ እንደ ሀገር የሚመራው በበላይ አመራር ወይም በሚኒስቴር ደረጃ ነው። በክልል ደግሞ በክልል ፕሬዚዳንቶች ይመራል፤ በእዚህም ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።

በከፍተኛ ኃላፊዎች የሚመራ በመሆኑ አመራሮች ለዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ የዘርፉ ችግሮች እየተቀረፉ ናቸው። የሌማት ትሩፋት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የእንስሳት ዘርፍ ሰፊ ትኩረት አግኝቷል፤ ሕዝቡም ግንዛቤው እያደገ ሲሆን፤ ብዙ ሴቶች እና ወጣቶች ወደ ዘርፉ እየገቡ ናቸው። በፊት መደገፍ የማይፈልጉ ፕሮግራሞች ለመደገፍ ወደ ዘርፉ እየመጡ ይገኛሉ።

በሌማት ትሩፋት በወተት፣ በዶሮ፣ በአሳ እና በማር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ ፕሮግራሙ ሲጀመር የነበረው አፈፃፀም አነስተኛ እንደነበረ እና አሁን ግን በሶስት ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ውጤት መምጣቱን በምሳሌ አስደግፈው ያስረዳሉ።

በሀገር ደረጃ የአንድ ቀን ጫጩት የማሰራጨት አቅም 26 ሚሊየን ነበር። ባለፈው ዓመት መጨረሻ 74 ሚሊየን የአንድ ቀን ጫጩቶችን ማሰራጨት ተችሏል። የዘንድሮው ዕቅድ ደግሞ 150 ሚሊየን ሲሆን፤ እስከ አሁን 90 ሚሊየን ጫጩቶች ተሠራጭተዋል።

የአሳ ጫጩት ሥርጭትም እንዲሁ እያደገ መጥቷል። በፊት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ጫጩቶች ይሰራጩ ነበር፤ አሁን ወደ ስድስት ሚሊየን የዓሳ ጫጩት ማሠራጨት ተችሏል። ሲሉ የሌማት ትሩፋቱን ተከትሎ የማሠራጨት አቅም ምን ያህል እንዳደገ አብራርተዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የማዳቀል አገልግሎት በዓመት 500 ሺህ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ አሀዝ አሁን ከሶስት ነጥብ አምስት ሚሊየን በላይ ደርሷል ብለዋል።

ፕሮግራሙ በብዙ ፈተና ውስጥ ሶስት ዓመታት ማስቆጠሩን አስታውሰው፤ በተለይ በተጀመረበት ወቅት የተወሰኑ ችግሮች ገጥመው እንደነበርም አመልክተዋል።

በመሪ ሥራ አስፈፃሚዋ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል አንደኛው የግብዓት አቅርቦት እጥረት ነው። ከዚህ በፊት በክልሎች ሥራው ባልተቀናጀ መልኩ ይካሄድ የነበረበት ሁኔታም ሌላው በችግርነት የሚጠቀስ ጉዳይ ነው። ብዙ ሰዎች ቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን የማስመጣት እና የማሠራጨት ሥራ ቢጀምሩም፤ እነዚህ ዶሮዎች ከውጪ የሚመጡት በውጭ ምንዛሪ እንደ መሆኑ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እና ምንዛሪ ለማግኘት ያለው ሂደት ከባድ በመሆኑ ብዙዎች ከዘርፉ መውጣታቸውንም ጠቁመዋል።

‹‹የቀድሞው የግብርና እና የገጠር ልማት ፖሊሲ የግል ባለሃብቶችን ታሳቢ ያደረገ አልነበረም›› ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ የመግባት ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ ሁኔታዎች ምቹ ናቸው ማለት አይቻልም ነበር ብለዋል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ ለተገለፁት ችግሮች የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችንም በተመለከተ አብራርተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ከበጀት ጀምሮ ያለውን እጥረት ለማቃለል በመንግሥት በኩል ጥረት ተደርጓል። በፌዴራል ደረጃ በፕሮግራሞች ውስጥ እየተካተተ ገንዘብ እንዲኖር ማድረግ ተችሏል። ክልሎችም ካላቸው ገቢ ላይ ለፕሮግራሙ እየመደቡ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

በክልሎች በተበታተነ መልኩ ይሠራበት የነበረውን ሁኔታ በመቀየር በመንደር ደረጃ ለመሥራት ሙከራ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ፤ በመንደር ደረጃ ሥራው መጀመሩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን እና ግብአቶችን ለማቅረብ እንዲሁም የሕክምና አገልግሎቶችን ለመስጠት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል። እየተሰበሰበ ላለው ምርት ገበያ ምቹ የሚሆንበት ዕድል መፈጠሩንም ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት ይተገበራሉ ተብለው ያልታሰቡ አንዳንድ ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውሰው፤ ቀደም ሲል በዶሮ ልማት ላይ የዶሮ ዝርያን በተመለከተ የሚሠራው ከውጭ አገር እንዲገቡ በማድረግ ነበር። አሁን ግን ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ ያጋጥም የነበረውን ችግር ለማቃለል፤ ቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን በማስገባት በቀላሉ ወላጅ ዶሮዎችን ማግኘት ተችሏል ብለዋል። ከዚህ ወር ጀምሮ ወላጅ ዶሮዎችን ማሠራጨት የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሚሆንም ጠቁመዋል። ቅድመ ወላጅ ዶሮዎች ወደ ሀገሪቱ በመግባታቸው ብዙዎች ወደ ዘርፉ ይሠማራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

እንደ መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ፤ ባለሀብት ሊያለማ ሲነሳ ምቹ ሁኔታ ካልተፈጠረ ባለሃብቱም አገርም ተጠቃሚ አይሆኑም። ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ባለሃብቶችን በተመለከተ በፖሊሲ በተደገፈ መልኩ በስፋት መሳተፍ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠርን ታሳቢ በማድረግ፤ ግብርና የራሱን ፖሊሲ ከልሷል። በአዲሱ ፖሊሲ ለባለሃብቱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ማሳተፍ የሚቻልበት ሁኔታ ተቀምጧል። በፖሊሲ ደረጃ ከማስቀመጥ ባሻገር፤ ማስተግበሪያ የሚሆኑ መመሪያዎች እየተዘጋጁ ናቸው፡፡

መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ እና የተትረፈረፈ ምርትን ከማግኘት አንፃር ምን ያህል ውጤታማ መሆን ተችሏል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የሌማት ትሩፋት አንደኛ ዓላማው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። ማሕበረሰቡ በልቶ እንዲያድር፤ የእንስሳት ምርቶችን ፕሮቲኖችን በቀላሉ እንዲያገኝ ሕፃናትም በተሟላ ሁኔታ እንዲያድጉ ታስቦ የመጣ ፕሮግራም ነው። የተያዘው ግብም በታቀደው መሠረት እየተሳካ ይገኛል።

ባለው አቅም ልክ ግብ መቀመጡን እና በዚህም ስኬታማ መሆን መቻሉን ጠቅሰው፣ ሆኖም ግን የሕዝብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣት እና ከዚህ ጋር በተመጣጠነ መልኩ በታሰበው ደረጃ መትረፍረፍ ላይ ባይደረስም፤ በሌማት ትሩፋቱ ምርት ከሚጠበቀው በላይ ጨምሯል የሚል ፅኑ እምነት አለ ሲሉ አብራርተዋል።

‹‹ምርቱ በሚፈለገው ደረጃ እንደልብ ተትረፍርፏል ለማለት ይቸግራል›› ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ፤ የምርት አቅርቦት እጥረት አለ ማለት እንደማይቻል አስረድተዋል። እንቁላልም ሆነ ዶሮ ገበያው ላይ ሳይጠፉ ዋጋቸው ውድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለእዚህ ምክንያቶቹ የተለያዩ ናቸው ብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በዶሮ እርባታ ላይ ከ70 እና ከ80 በመቶ በላይ ወጪ የሚወጣው ለመኖ ነው። የመኖ ዋጋ መጨመር የዶሮ ዋጋ እንዲጨምር አርጓል። ሌላው ቀደም ሲል መንግሥት አምራቾችን ለማበረታታት ሲል ከእንቁላል ላይ ቫትን አንስቶ ነበር። አሁን ግን ቫት ጨምሯል። ለዋጋው መወደድ ሌሎችም ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡

ይህ የመጀመሪያ ፕሮግራም በመሆኑ፤ ሁለተኛው የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ሲጀመር ውጤቱ እያደገ ችግሩ እየተቃለለ ይሔዳል ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ፤ በዚህ መልክ ከቀጠለ በሁለተኛው ደረጃ ላይ በእርግጠኝነት የተሻለ ነገር ማግኘት እንደሚችል አመላክተዋል። በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሕበረሰቡ እንዲቀርብ መሥራት ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ዋጋ ክልል ላይ እንደ ከተማ ውድ አይደለም። ምክንያቱም ክልል ላይ ሕብረተሰቡ በየቤቱ ስለሚያመርት ገዢዎች ጥቂት ናቸው። በከተማም በቤተሰብ ደረጃ ሕብረተሰቡ በየራሱ ቢያመርት የበለጠ ምርት ሊገኝ ይችላል። በቤተሰብ ደረጃ ቢመረት አሁን ባለበት ደረጃ አይወደድም።

በከተማ ብዙ ሰው መሬት ስለማይኖረው፤ ላያመርት ይችላል። ነገር ግን መሬት ያላቸው ሁሉ እንዲያመርቱ የከተማ ግብርናን ማበረታታት ላይ የሚሠራበት ሁኔታ ይኖራል። ለዛ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የከተማ ግብርና ክፍል ተዘርግቶ እየተሠራበት ነው።

የፋይናንስ ችግር መኖሩን በመተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ሰዎች ሥራ ሲጀምሩ ማስፋት ይፈልጋሉ። ለእዛ የብድር አቅርቦት ይጠይቃሉ ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የብድር አቅርቦት ውስን ነው። ያሉትም ዋስትና ይጠይቃሉ። ብድር የሚፈልጉ ሰዎች ደግሞ የሚያስይዙት ዋስትና ላይኖራቸው ይችላል። ያንን ለማሻሻል በመንግሥት ደረጃ እየተሠራ ይገኛል፤ ይህን ተከትሎም የብድር አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው።

የግንዛቤ እጥረትን በተመለከተም፤ በዶሮ እርባታም ሆነ ሌሎች የእንስሳት ምርቶችን ከማምረት ጋር ተያይዞ ብዙ ሰዎች አመለካከታቸው ተቀይሯል። ብዙዎች በዚህ ልማት ተጠቃሚ ሆነው እየታዩ በመሆናቸው የሕዝቡ ግንዛቤ በማደጉ አያሌ ሰዎች ወደ ዘርፉ ገብተው ለመሥራት ተነሳሽነት እያሳዩ ናቸው። ይህም ተነሳሽነት እያደገ መጥቷል፡፡

ለእዚህም በቢሾፍቱ በየቦታው የሚታየውን የዶሮ እርባታ በአብነት ጠቅሰዋል። ዶሮ የሚያረባው ወጣቱ ነው። በሌላ መስክ ተምረው ሳይሰለጥኑ ወደ ሥራው ቢሰማሩ ላያዋጣቸው ይችላል። ብዙዎቹ የሰለጠኑ ወጣቶች ሥራው ቢዝነስ መሆኑን እየተረዱ እና ወደ ሥራው እየገቡ እየተሳካላቸው ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You