
በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች የምርጥ ዘር ፍላጎት ከፍተኛ እንዲሆን እንደሚያደርጉት ይታመናል። ይህን ፍላጎት ለመመለስ ደግሞ በምርጥ ዘር ላይ የሚደረግ ምርምርንና የምርጥ ዘር አምራቾች፣ አባዥዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል።
ቀደም ሲል ምርጥ ዘርን በማምረትና በማዘጋጀት በኩል የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት ሲሠራ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፍላጎቱ መጨመሩን ተከትሎ ክልሎችም የራሳቸውን የምርጥ ዘር አምራቾችና አዘጋጆች አቋቁመው ወደ መሥራት ገብተዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እንዲሁ በምርጥ ዘር ላይ ምርምር በማድረግ፣ በማባዛትና በማሰራጨት ላይ የሚገኙበት ሁኔታ ይስተዋላል። ምርጥ ዘር በአርሶ አደሮች ማሳ እንዲመረት የሚደረግበት ሁኔታም እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በምርጥ ዘር ምርታቸውና ዝግጅታቸው ውጤታማ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በተለይ በስንዴ ምርጥ ዘር ምርምርና ማልማት ውጤታማነቱ የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ይጠቀሳል።
ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት አካባቢ ስንዴ በስፋት የሚመረትበት እንደ መሆኑ በአርሶ አደሮች ዘንድ ያለውን የስንዴ ምርጥ ዘር ፍላጎት በማጥናት በስንዴ ላይ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያመለክታል። በአሁኑ ወቅትም ሁለት የስንዴ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ዝግጅቱን አጠናቅቋል።
የዩኒቨርሲቲው የተቀናጀ የግብርና ምርምር ማዕከል አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ገመቹ እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ከማማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ በምርምር ሥራዎቹ ለግብርናው ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ ይሠራል። ዩኒቨርሲቲው ሰፊ የግብርና ሥራዎች ለሚሠራባቸው ለምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ቦረና፣ ምስራቅ ባሌና ባሌ አካባቢዎች ቅርበት ያለው ሲሆን፣ ግብርናው ዘርፍ ላይ አተኩሮ ምርምሮችን ያካሂዳል።
ዩኒቨርሲቲውም የስንዴ ኩታ ገጠም የእርሻ ፕሮግራም በሀገር ደረጃ ሥራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አራት ዓመታት በግንባር ቀደምትነት ፕሮጀክት በመቅረጽ በምዕራብ አርሲ፣ በባሌና በምስራቅ ባሌ አካባቢዎች ሰፋፊ ሥራዎችን ሠርቷል።
የምርምር ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎ ጂዎችንና ዝርያዎችን ለማውጣት ይመራመራል። ምርታማነት ላይ ማነቆ ሊሆኑ በሚችሉ የግብዓት አጠቃቀሞች እንዲሁም በሽታዎች ላይ ምርምሮችን ይሠራል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ለስንዴ ሰብል ምርምር ትኩረት በመስጠት ባከናወነው ተግባር አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎች ማውጣት መቻሉን አቶ ጥላሁን ጠቅሰዋል። የአካባቢውን የምርጥ ዘር እጥረት ለመቅረፍ የዘር ማባዛት ሥራንም እንዲሁ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ከኩታ ገጠም የእርሻ ፕሮግራም ጋር ተያይዞ ከምዕራብ አርሲ፣ ከባሌና ምስራቅ ባሌ ዞኖች ዘጠኝ ወረዳዎችን በመምረጥ ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ዘር፣ ማዳበሪያና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን ያቀርባል። ይህም የኩታ ገጠም እርሻን ለማስፋፋት እንዲሁም አርሶ አደሩን ስለቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማስተማር ያግዛል። በዚህም በየዓመቱ በ180 ሄክታር ማሳ ላይ ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ሥራዎችን እየሠራ ነው።
ዩኒቨርሲቲው የምርጥ ዘር እጥረትን ለመቅረፍ ምርምር ብቻ አይደለም የሚያካሂደው። የዘር አባዥነት ፈቃድ በማውጣት በራሱ የእርሻ መሬትና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ዘር በማባዛት አስፈላጊውን የጥራት ደረጃ ያሟሉ ዘሮችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ያደርጋል።
በተለይ ስንዴ በመስኖ በሚያለሙ አካባቢዎች ዘር በማቅረብና የሙያ ድጋፎች በማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የምርምር ሥራዎቹን በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ጭምር እንደሚያካሂድም አስታውቀዋል። በምስራቅ ቦረና ለቆላማ አካባቢዎች ፣ በምስራቅ ባሌ ለወይናደጋ እና ለደጋ አካባቢዎች የሚሆኑ ምርጥ ዘሮችን እንደሚያለማም ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው ዋና ካምፓስ በባሌ ሮቤ የምርምር ጣቢያዎቹ ከስንዴ በተጨማሪ በተለያዩ ሰብሎችና የእንስሳት መኖዎች ላይ ምርምሮችን እንደሚያካሂድ ገልጸዋል።
የምርምር ውጤቶቹ ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩ እንደሚደረግ አቶ ጥላሁን ጠቅሰው፣ ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር እየተዋወቀ እንዲጠቅም እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በስንዴ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ በዚህም ከሚሰራቸው መካከል አንደኛው አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር ማውጣት መሆኑን ጠቁመዋል። አንድ ዘር በጥቂቱ ከ6 እስከ 12 ዓመት የሚፈጅ ምርምርን እንደሚፈልግ ጠቅሰው፣ ባለፉት ጊዜያት ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ምርምር የተገኘ አንድ ዝርያ መለቀቁንም አስታውቀዋል።
ሌሎች የምርምር ማዕከላት የሚለቋቸውን አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎች በማላመድና በማባዛት እንዲሁም የተባዙትን ደግሞ በማስበጠርና በማሳሸግ የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር እጥረት ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ተግባር እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል።
የማዕከሉ አስተባባሪ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ሁለት ዓይነት የስንዴ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል። አንዱ የስንዴ ምርጥ ዘር ‹‹ቦኩ ዝርያ›› የሚባል ሲሆን፣ ይህም ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቀ ገና አርሶ አደሩ እጅ ያልደረሰ ነው። ምርጥ ዘሩ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ተባዝቶ ለሌሎች ተደራሽ እንዲሆን ዝግጁ ተደርጓል።
በሦስት ዞኖች ዘጠኝ ወረዳዎች ለአርሶ አደሮች ዘርና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በመስጠትና ሙያዊ ድጋፎችን በማድረግ አርሶ አደሩ ያገኘውን ዘር መልሶ ለአካባቢው አርሶ አደሮች እንዲያሰራጭ ይደረጋል ብለዋል። ይህ ምርጥ ዘር በ180 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተባዝቶ የተገኘ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሌላው አዲስ የተለቀቀው ምርጥ ዘር ‹‹መደወላቡ ዝርያ›› የሚባለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በዩኒቨርሲቲው እርሻ ማሳ ላይ ተባዝቶ ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል። 1000ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርጥ ዘር በዩኒቨርሲቲው እርሻ ተባዝቶና ታሽጎ ሊሰራጭ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ዘር የበለጠ ምርታማ የሚሆነውና ጥሩ ውጤት የሚሰጠው በአርሶ አደሮች ማሳ ተሞክሮ እንዲበዛ ሲደረግ ነው የሚሉት አቶ ጥላሁን፤ ቀበሌዎች ላይ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ዘር እንዲያባዙ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሥራት ችሏል ብለዋል።
ለአብነትም ሁለት ወረዳዎች ላይ አርሶ አደሮች ወደ ዘር አባዥነት የተሸጋገሩበት ሁኔታ እንዳለም አመልክተው፣ አርሶ አደሮቹ የዘር ማበጠሪያ ማሽንና የዘር ማከማቻ መጋዘን እንዲኖራቸው ተደርጎ ወደ ዘር አባዥ ማህበር እንዲሸጋገሩ መደረጉንና በዚህም ጥሩ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲውም የተገኘው የስንዴ ምርጥ ዘር በምርምር ማዕከሉ መሞከሩን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በአርሶ አደሮች ማሳ በተለያዩ አግሮኢኮሎጂዎች ላይ ሙከራ ተደርጎ ተግባር ላይ እንዲውል እንደሚደረግ ጠቁመዋል። በባሌ ደሎመና አካባቢ ባለው የስንዴ መስኖ ልማት /ዌል ሜል የተሰኘ ፕሮጀክት ስላለ/ በሶስት መቶ ሄክታር ማሳ ላይ ምርጥ ዘሩን ለማባዛት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።
‹‹የዘር የማባዛት ሥራው ይቀጥላል፤ አዳዲስ ዝርያዎች እያወጣን ነው፤ በእጃችን ያሉ ዝርያዎችንም እያባዛን ለአርሶ አደሮች እያሰራጨን ነው›› ሲሉ ያብራሩት አቶ ጥላሁን፤ ዝርያው በሽታ የሚቋቋምና ምርታማነቱ በጣም ከፍተኛ በሆነ ምርጥ ዘር ላይ እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በምርምር ማዕከሉ ላይ እየተከናወነ ባለው በዚህ ሥራ አጥጋቢ ውጤት ታይቷል። ዝርያው በተለያየ አግሮኢኮሎጂ ተሞክሮ በሄክታር ከ60 ኩንታል በላይ ምርት መስጠት እንደሚችል ተረጋግጧል። ይህ ዘር በዩኒቨርሲቲው የእርሻ ማሳና በአርሶ አደሮች ሰፊ ማሳ ተሞክሯል፤ አርሶ አደሮቹም ምርጥ ዘሩን በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ።
ዩኒቨርሲቲው በምርጥ ዘር ጥራት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በመውሰድ እንደሚሠራም አስታውቀዋል። የፌዴራል የግብርና ባለሥልጣን እና የኦሮሚያ ግብርና ግብዓቶች ቁጥጥር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ምርጥ ዘር የጥራት ሂደትን እንደሚቆጣጠሩ አስታውቀው፣ ምርጥ ዘሩ ሲፈቀድ ብቻ ገበያ ላይ እንዲውል እንደሚደረግ ያመላክታሉ። ተቋማቱ ዘሩ ሲባዛ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ያለውን ሂደት ሲከታተሉ እንደነበር ጠቅሰው፤ የመመዘኛውን ሂደት ያለፉት ዘሮች ብቻ ለአርሶ አደሮች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው በምርምር ሥራው ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራው ዝርያዎችን ማበዛትና አዳዲስ ዝርያዎች በማውጣት ለአርሶ አደሮች ማስተዋወቅ ላይ ነው ሲሉ ገልጸው፣ ዝርያዎችን በብዛት በማባዛት ተደራሽነት የማስፋት ሥራ የበለጠ ውጤታማ የሚሆነው በመንግሥት በኩል ሲሆን ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የዩኒቨርሲቲው ሥራ አዳዲስ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በአነስተኛ ቦታዎችና አርሶ አደሩ ማሳ ላይ በመሞከር ምርጥ ዘር ማቅረብ ነው። በመሆኑም አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪ የሚሆን ጥራት ያለው ምርት እንዲያቀርቡ ያደርጋል። ሌሎቹ ደግሞ ምርጥ ዘር አባዥ ሆነው በተሻለ ዋጋ መሸጥና የዘር አቅርቦት ችግርን እንዲቀርፉ ማድረግ ላይ የበለጠ ይሠራል።
ዩኒቨርሲቲው በስንዴ ላይ ጥሩ ውጤት ማግኘቱን ጠቅሰው፣ ከስንዴ ባሻገር አካባቢው በሚመረቱ የቅመማቅመም ምርቶች ላይም ይሠራል። በተለይ ለኤክስፖርት የሚሆኑ እንደ ሰሊጥ፣ ማሾና ጥቁር አዝሙድና የመሳሰሉትን የተሻሉ ዝርያዎች በማቅረብ አርሶ አደሩ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል። አርሶ አደሩ የአፈር ለምነትን የሚያሻሽሉና በሽታ የሚከላከሉ ዝርያዎችን እያፈራረቀ እንዲዘራ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገም ነው።
የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የዘር ብዜት አስተባባሪ አቶ ድሪባ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ባለበት አካባቢ በጣም ተፈላጊ በሆነው ስንዴ ላይ ትኩረት አድርጓል ሲሉ ጠቅሰው፣ አግሮኢኮሎጂው ለስንዴ የተመቸ በመሆኑ በአካባቢው ስንዴ በተለየ ሁኔታ በብዛት ይመረትበታል ብለዋል።
በአካባቢው የተደረገውን የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ዋቢ አድርገው ሲያብራሩ እንዳሉትም፤ አርሶ አደሩ የስንዴ ምርጥ ዘር በመጠቀም ማሳውን በስንዴ የመሸፈን ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ዩኒቨርሲቲውም ወደ እዚህ ሥራ የገባው የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሠረተ በማድረግ ነው።
የዘር ብዜት አስተባባሪው እንዳብራሩት፡- በዩኒቨር ሲቲው ተባዝተው ለአርሶ አደሩ ሊቀርቡ የተዘጋጁት የስንዴ ምርጥ ዘሮች ምርት በመስጠት እንዲሁም በሽታ በመቋቋም አቅማቸው አርሶ አደሩ እጅ ላይ ካለው ከነባሩ ዘር ይበልጣሉ። አካባቢውንም በደንብ የተላመዱ የተሻሉ ዝርያዎች ናቸው።
በዩኒቨርሲቲው የተሞከረው አዲሱ የምርጥ ዘር ብዜት በ25 ሄክታር ማሳ ላይ ተካሂዷል። ይህ ምርጥ ዘር በሄክታር ከ40 እስከ 60 ኩንታል ምርት ይሰጣል። የምርጥ ዘር ብዜቱ በሚመለከታቸው አካላት ከታየ በኋላ ለአርሶ አደሩ ሊቀርብ ተዘጋጅቷል።
ምርጥ ዘሩ የጥራት ጉደለት እንዳይገኝበት የሚቆጣጠር አካል እንዳለ አቶ ድሪባም ጠቅሰው፣ ጥራቱ ተረጋግጦ ሰርተፊኬት ሲሰጥ ብቻ ለአርሶ አደሩ እንደሚደርስ አስታውቀዋል። ምርጥ ዘሩ ተፈትሾ ማረጋገጫ እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረው፣ ዩኒቨርሲቲው እነዚህን ምርጥ ዘሮች ቀደም ሲል ከሚሠራባቸው ወረዳዎች በተጨማሪም ከዞኑ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።
ለአርሶ አደሩ ተግዳሮት የሚሆነው አንዱ የምርጥ ዘር እጥረት ነው፤ አርሶ አደሩ ምርጥ ዘር ሲያጣ እጁ ላይ ያለውን ይጠቀማል ሲሉ አቶ ድሪባ አመልክተው፤ ዩኒቨርሲቲውም ለሁሉም ተደራሽ መሆን ባይችልም በተቻለ መጠን ተደራሽነቱን ለማስፋት ጥረት እንደሚያደርግ አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉትም ዩኒቨርሲቲው ምርጥ ዘር በማባዛት ብቻ ሳይሆን በምርምርም አዳዲስ ዝርያዎችን የማፍለቅ ግዴታም አለበት። ቴክኖሎጂ ዘርን ከማፍለቅ ስለሚጀመር አንድ ዘር ከተለቀቀ በበሽታ ሊጠቃ፣ ምርታማነቱ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል፤ ከሦስትና አራት ዓመታት በላይ አያገለግልም፤ አዳዲስ ዘሮችን ከሥር ከሥር መተካት ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድም ዩኒቨርሲቲው አዲስ ከሚወጣው ስንዴ ጋር በሚስማሙ ማዳበሪያ፣ ፀረ ተባይ እና በመሳሰሉት ላይም እየተመራመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጊዜውን የሚመጥን ቴክኖሎጂ በማዘጋጀት አቀናጅቶ እያስኬደ መሆኑን ያስረዳሉ።
የዚህ አካባቢ አብዛኛው አርሶ አደር የሚጠቀመው ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው ሰብሎችን ነው ሲሉ አቶ ድሪባ ገልጸዋል። ይህም የአፈር ለምነትን የሚጎዳና በሽታ የማይከላከል መሆኑን አስገንዝበው፣ አርሶ አደሮች ይህ ግንዛቤ ኖራቸው የአፈር ለምነት የሚጨምሩ ዝርያዎችን አፈራርቀው እንዲጠቀሙ ማድረግ ላይም መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም