
በዓለም አቀፍ ደረጃ በእንስሳት ጤና ላይ ተቋማዊ ይዘት ኖሮት መሥራት የተጀመረው እ.አ.አ በ1924 አካባቢ መሆኑን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ። ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጀ የእንስሳት ጤና እንዲጠበቅና እንዲሻሻል አተኩሮ ይሠራል።
በእንስሳት ሀብታቸው የታደሉ እንዲሁም እንደ ቆላ ዝንብ፣ የዕብድ ውሻ በሽታና የመሳሰሉት የእንስሳት በሽታዎች ለሚያስጨንቋቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች በዚህ በእንስሳት ጤና ላይ በትኩረት መሥራት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና እና እንክብካቤ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ውብሸት ዘውዴ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ትልቅ የእንስሳት ሀብት አላት። ይህ ሀብቷ የሕብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። የእንስሳት ሀብቱ መኖሩ ብቻውን ግን የሚፈለገውን ውጤት አያስገኝም። ይህ ሀብት የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ በእንስሳት ጤና ላይ መሥራት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው።
የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የህብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ በእንስሳት ጤና ላይ መሥራት ወሳኝ መሆኑንም መሪ ሥራ አስፈጻሚው አስገንዝበው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ያላቸው ሀገሮች የሕብረተሰቡን ጤና ያለ እንስሳት ጤና ማረጋገጥ ይቻላሉ ብሎ ማሰብ ዘበት መሆኑን አመላክተዋል።
በእንስሳት ጤና ላይ መሥራት የእንስሳት በሽታዎችን ከመከላከል በተጨማሪ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚያግዝ አስታውቀው፤ የጠናከረ የእንስሳት ጤና አገልግሎት በሌለበት፤ የጠናከረ የሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት እንደማይኖርም አስገንዝበዋል።
ይህንንም ምሳሌ ጠቅሰው ሲያስረዱ እንዳብራሩት፤ ሕብረተሰቡ እንስሳትን ሲመገብ በሽታው ይተላለፍበታል። ይህ በጥናት የተረጋገጠ ነው፤ በርካታ የሕብረተሰብ ጤና ችግሮች በተለይ በወረርሽኝ ደረጃ ከሚነሱት በሽታዎች ወደ 75 በመቶዎቹ ከእንስሳት የሚመጡ ናቸው።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው ያልበሰሉ የእንስሳት ተዋፅኦዎችን የሚጠቀሙ ሰዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ ሕብረተሰቡ የእንስሳት ጤናን በመተለከተ የተወሰነ ግንዛቤ ቢኖረውም አሁንም ክፍተቶች አሉበት ብለዋል። አንዳንዶች የታመሙ እንስሳትን ቅርጫ ተከፋፍለው እስከ መብላት የደረሰ ስህተት እንደሚፈጽሙም ጠቁመዋል።
‹‹በየሜዳው እያረዱ ቅርጫ እየተካፈሉ ስጋ መብላት የሚደገፍ አይደለም›› የሚሉት ውብሸት (ዶ/ር)፤ በሬው ጤናማነቱ በቄራ ባለሙያዎች ያልተረጋገጠ ሥጋ መብላት አይደገፍም ብለዋል። የእንስሳት በሽታዎች ወደ ሰዎች ተላልፈው ሞት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መታወቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በእንስሳት ጤና ላይ በስፋት አለመሥራት ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፤ ከእንስሳት ንግድ ጋርም በፅኑ ይያያዛል፤ በተሻለ ገንዘብ ሊሸጡ የሚችሉ የእንስሳት ተዋፅኦዎች በሽታ ሲኖር በአነስተኛ ገንዘብ ሊሸጡ ይችላሉ። ያ በራሱ የሚያመጣው ችግር ቀላል የሚባል አይደለም።
በሽታ ሲስፋፋ እንስሳትንም ሆነ በሽታው የተላለፈባቸውን ሰዎች ለማከም የሚያስፈልገው ወጪ መታሰብ እንዳለበት አመልክተው፣ በዚህ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደ አንድ ዋነኛ ክፍል ተወስዶ እየተሠራበት ነው ብለዋል።
ገበያም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚቻለው ጤናው የተጠበቀ የእንስሳት ሀብት ወደ ውጪ መላክ ሲቻል ነው ሲሉ አስገንዝበው፣ የኢትዮጵያን የእንስሳት ተዋፅኦዎች ወደ አደጉት ሀገሮች ለመላክ በእንስሳት ጤና ላይ የሚሠራው ሥራ በከፍተኛ መጠን መጠንከር አለበት ብለዋል። የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት በቂ መረጃ ማግኘት እንደሚገባ አስታውቀው፣ በተለይ እንስሳቱን መመዝገብ የግድ መሆኑን ገልፀዋል።
የእንስሳት ሀብት ለሕብረተሰብ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው፣ እንስሳቱ ሲያልቁ በእነሱ ላይ ጥገኛ የነበሩ ቤተሰቦች ተጎጂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። አንድ የወተት ላም ብትሞት፤ የአንድ ቤተሰብ ልጆች የሚጠጡትንም ሆነ ቤተሰቡ ለገበያ የሚያቀርበውን ወተት እንደማያጣ ገልጸዋል። እንስሳቱ በበሽታ ተይዘው ባይሞቱ እንኳ ምርታቸው መቀነሱ በራሱ ሌላኛው ችግር ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ይህንን መሠረት በማድረግ የእንስሳት ጤና እንክብካቤን ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር ከመሥራት በተጨማሪ መንግሥት ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ካለው የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ጋር በማስተሳሰር ብዙ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የመጀመሪያው ከእንስሳት በሽታ ጋር ለተያያዙ ችግሮች ትልቅ መፍትሔ ያመነጫል የተባለለት፤ የእንስሳት በሽታ ዳሰሳ እና ቅኝት ሥራ ዋነኛው መሆኑን ያመለክታሉ። በሀገር ደረጃ ይህንን ሥራ ተደራሽ ለማድረግ ከመሥራት በተጨማሪ የእንስሳት ምዝገባ መጀመሩንም ገልጸዋል።
የእንስሳት በሽታ ዳሰሳ እና ቅኝት በሀገሪቱ የእንስሳት በሽታዎችን እና በሽታዎቹ የደረሱባቸውን ደረጃዎች ለማወቅ እንደሚያግዝ በማመላከት፤ በሽታው ከተከሰተ በኋላ ለማከምና ለማስቆም እንዲሁም በአጠቃላይ የሚፈለገውን ርምጃ ለመውሰድ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል። የዳሰሳ እና ቅኝት ሥራው በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል እንደሚረዳ አመላክተዋል።
ውብሸት (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ እንስሳቱን ከመመዝገብ ጀምሮ፤ በእንስሳቱ ምገባ እና አጠቃላይ አገልግሎት ላይ በደንብ ካልተሠራ የሚፈለገውን የምግብ ደህንነት ማረጋገጥ አይቻልም። በምዝገባው የሚገኙ መረጃዎች በምግብ ደህንነት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።
አንድ እንስሳ አዲስ አበባ ሲገባ ከየት መጣ? ከሚለው ጀምሮ መረጃ መኖር አለበት። በምዝገባ መረጃ ይገኛል፤ ምዝገባው የእንስሳትን በሽታዎች አስቀድሞ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን የሚጠቅመው፣ የእንስሳት ጤና እንክብካቤን በማሳደግ ምርት እና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እና ከውጪ ገበያ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል።
ዳሰሳ እና ቅኝት ማድረግ እንዲሁም ምዝገባ ማካሔድ ብቻ ሳይሆን፤ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል ላይም እየተሠራ ነው ሲሉ የሚናገሩት ውብሸት (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል ከሚሠሩ ሀገሮች መካከል ግንባር ቀደም መሆኗንም ጠቅሰዋል። የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ክትባት ለክልሎች ያሠራጫል ብለዋል።
በጎች እና ፍየሎች በስፋት ወደ ውጪ እንደሚላኩ ጠቅሰው፣ በዓለም ላይ መጥፋት አለባቸው ተብለው አቅጣጫ ከተሰጠባቸው የእንስሳት በሽታዎች መካከል በጎች እና ፍየሎች የሚያጠቁ በሽታዎች እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል። በሽታዎቹን ለማጥፋት ከስድስት ዓመት በፊት ጀምሮ በተለይ በአርብቶ አደር አካባቢ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኑሮ መሠረታቸው ዝቅተኛ የሆነ አርብቶ አደሮች በጎቻቸው እና ፍየሎቻቸው ትልቅ ሀብታቸው በመሆናቸው፣ እንስሶቻቸውን ደስታ እና መሰል በሽታዎች እንዳይጎዱባቸው በዓለም ደረጃ እ.አ.አ በ2030 ይህ በሽታ መጥፋት አለበት ተብሎ እየተሰራ ነው፤ ግብርና ሚኒስቴር ግን እ.አ.አ በ2027 ወይም በ2019 ዓ.ም ለማጥፋት እየሠራ ይገኛልል። ለእንስሳት ጤና በሚፈለገው ደረጃ ትኩረት በመሰጠቱ ቢያንስ ዓለም ባቀደው ጊዜ የደስታ በሽታ ይጠፋል ብለው እንደሚያምኑ አመላክተዋል።
በእዚህ በኩል እስከ አሁን ሲሠራ የቆየው፤ ከሃያ ዓመት በፊት በወጣ አዋጅ ላይ በመመስረት እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፈው ሳምንት ለእንስሳት ጤና ምቹ የሆነ አዋጅ መውጣቱን አስታውቀዋል። እንደ ሀገር በእያንዳንዱ የእንስሳት ጤና ዙሪያ ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።
የሌማት ትሩፋትን የተሳካ ለማድረግ ዶሮ ርባታ ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመት በዶሮ ርባታ ትልቅ ስኬት መገኘቱንም አመልከተዋል። የዚህ ምክንያቱ ቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን ሀገር ውስጥ ማራባት መጀመሩ መሆኑን በመጠቆም፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም የሥነ ሕይወት ደህንነት በሽታን ለመከላከል ትልቅ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በእንስሳት ጤና ላይ ከሚሠሩት መካከል የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ አንደኛው ሲሆን፣ ዶሮ እጅግ አዋጭ ሥራ ቢሆንም፤ የሥነሕይወት ደህንነት በአግባቡ የማይተገበር ከሆነ በትንሽ በሽታ ርባታውን የሚያጠፋ ሊፈጠር ይችላል፤ በተለይ ከአዋጁ መጽደቅ በኋላ ሥነሕይወት ላይ ለመሥራት የሚያግዙ ሰነዶች እና መመሪያዎች እየተዘጋጁ ናቸው።
ውርጃን የሚያስከትለው በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ተናግረው፣ ለእዚህም ስትራቴጂ ተቀርፆ እ.አ.አ በ2032 በሽታውን ለማጥፋት እየተሠራ ነው ብለዋል። ሌሎችም መጥፋት ባለባቸው በሽታዎች ላይ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በግመሎች ላይ የሚከሰት በሽታ እንደነበረም አስታውሰው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ግመሎች ሞተዋል ብለዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት የአቡዳቢ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ጤና ድርጅት የግመል በሽታ የላብራቶሪ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ ናሙና ሰብስቦ ምርመራ ማድረጉን ተናግረዋል። አሁንም ምርመራው ቀጥሏል ብለዋል። ድርቅ ለብዙ እንስሳት ሞት ምክንያት ቢሆንም፤ ግመሎች ግን በአንፃራዊነት ድርቅን ይቋቋማሉ ሲሉ ጠቁመዋል።
‹‹ሴት ቡችላን ሰዎች አውጥተው ይጥላሉ፤ ይሄ ችግር እየፈጠረ ይገኛል›› ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ ባለቤት ያላቸው በየጊዜው ሊከተቡ ይችላሉ፤ ባለቤት የሌላቸው የመንገድ ላይ ውሾች አይከተቡም። ያልተከተቡ ውሾች ሰዎችን በመንከስ በሽታ ያስተላልፋሉ። በእዚህ ዓይነት መንገድ የእብድ ውሻ ሕብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ሰዎች በታመሙ ውሾች ተነክሰው በሽታው ቀድሞ ከተደረሰበት መቶ በመቶ መከላከል ይቻላል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ከግንዛቤ ማነስ በውሻ ሲነከሱ ሳይመረመሩ ውሻው ጤነኛ ነው ብለው ይዘናጋሉ። ቆይተው ወደ ሕክምና ሲሔዱ ምንም ሊረዱ የሚችሉበት መንገድ አይኖርም፤ ለሞት ይዳረጋሉ፤ ይህንንም ለመከላከል ስትራቴጂ ተቀርፆ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የእንስሳት ጤና ባለሙያ እጥረት ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፤ ችግሩ አሳሳቢ አለመሆኑን ገልጸዋል። ቀደም ሲል የእንስሳት ጤናን በተመለከተ የሚያስተምረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ ነበር። አሁን ግን 15 ዩኒቨርሲቲዎች እያስተማሩ ናቸው፤ በመሆኑንም የእንስሳት ጤና ባለሙያ ችግር የለም ሲሉ ገልጸዋል።
በችግርነት ይነሳ ከተባለ ከሕግ ማሕቀፍ ጋር የተያያዘው ችግር እንደነበር ጠቅሰው፣ እርሱም ቢሆን የሚፈታበት ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል። ከየሜዳው መድሃኒቶችን የመውሰድ ችግሮች እንደነበሩም ጠቅሰው፣ ከሕግ ማሕቀፍ ጋር ተያይዞ የእንስሳትን ደህንነት ጨምሮ የነበሩ ችግሮች እየተፈቱና ነገሮች እየተስተካከሉ መምጣታቸውን አስታውቀዋል። ባለፈው ሳምንት የጸደቀው የእንስሳት ጤና እና ደህንነት አዋጅ ትልቅ መፍትሔ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የሀገሪቱ የእንስሳት ሀብት የሕበረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፣ የምግብ ሥርዓትን ለመጠበቅ እንዲሁም የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ ሚና ይጫወታል። መንግሥትም በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ በስፋት እየሠራ ነው። በዝርያ ማዳቀል፣ በእንስሳት ጤና ክብካቤና በመሳሰሉት በስፋት ይሠራል። ከአካባቢው ሀገሮች ጋር በመሆን የሚሠራበት ሁኔታ እንዳለም ይታወቃል። እንደ ሌማት ቱሩፋት ባሉት ኢንሼቲቮች በእንስሳት ላይ እየተሠራ እንደመሆኑ በእንስሳት ጤና ላይም በስፋት መሥራት ያስፈልጋል።
ይህ ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በእንስሳት ጤና ላይ እየተከናወነ ያለው ተግባር ሰፊ ትኩረት ሲሰጠው ነው። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም፤ እንስሳቱን ከበሽታ መጠበቅ ሲቻል ነው። ይህን ማድረግ እንስሳቱን ከመታደግ በተጨማሪ የማህበረሰብን ጤና መታደግ፣ የሀገር ኢኮኖሚ ማሳደግም ነው።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም