ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ አገር ብዙ ችግርና መከራን ለማለፍ ተገደናል። በእርግጥ ይህ ችግርና መከራ በሕዝባችን አንድነትና ርብርብ ፤ በመንግሥት የሰላም አማራጭ መልክ ይዞ አገር አንጻራዊ በሆነ ሰላም ውስጥ ትገኛለች። ይህም ሆኖ አሁንም አንድነታችንን ፤ መደጋገፋችንን እና መተሳሰባችንን የሚፈልጉ በርካታ ችግሮች አሉብን ፡፡
መጪውን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ቀደም ሲል ችግሮቻችንን ለማለፍ ከዳር እስከ ዳር ያሳየነውን አንድነት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ። እያንዳንዱ ዜጋ እራሱን ፣ ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና እውቀቱን ፤ ለአገሩ ያለውን ሁሉ ያለመቆጠብ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ሁለት ዓመታት ለአገራችን ያለንን ሁሉ አንሰስትም ብለው የሚችሉትን ነገር ከማድረግ ጀምሮ የአገራቸውን እውነት በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲሰማ ብዙ ለፍተዋል ብዙ ጥረዋል።
በተለይም ጦርነቱን ያመጣብን ጣጣ ለመመከት በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ የአገርን እውነት በማስረዳት፣ ዜግነቱን ተጠቅሞ ትልልቅ የዓለም ባለሥልጣናት ላይ ጫና በማሳደር ፣ ገንዘቡን በማዋጣት ትልቅ ስራን በመስራት አገሩ ላይ ሊጣሉ የነበሩ ማዕቀቦች ክልከላዎችና ሌሎች እርምጃዎች ሁሉ እንዲቀለበሱ የበኩላቸውን አበርክተዋል። ይህ ልፋትና ጥረታቸውም ፍሬ አፍርቶ እነሆ አገራችን የከፋ ችግር ውስጥ ሳትገባ ጠላቶቿ ወይም የሷን ክፉ የሚያስቡ ሁሉ እንደተመኙላት ሳትበታተንና ዜጎቿ መግቢያ ሳያጡ ዛሬን ለማየት በቅተናል፡፡
ይህ እንዲሆን ለለፉ ሁሉ ደግሞ ምስጋናን መቸር አዋቂነት ብሎም ኢትዮጵያዊነት ነው። ከዚህ አንጻር መንግሥት መላውን በአገርም በውጭም ያለውን ዜጋውን ቢያመሰግንም ፣ በተለየ ሁኔታ ግን አገራቸውን ከፊት አስቀድመው በባዕድ አገር ለተንከራተቱ አደባባይ ወጥተው ስለያዙት እውነት ለማስረዳት ለጣሩና ውጤትም ላመጡ የዳያስፖራ አባላት የሚመጥን የምስጋና ፕሮግራም ማዘጋጀቱ የሚያስመሰግነው ነው።
በአገርና ከአገር ውጪ የነበሩ ኢትዮጵውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ባደረጉት ሁለንተናዊ እልህ አስጨራሽ ትግል ዛሬ ላይ እንደ አገር ያሳለፍነውን አስከፊውን ምዕራፍ ዘግተን ወደ እድገት የታሪክ ምእራፍ ተሸጋግረናል፤ ለዚህም በተለይ በባዕድ ምድር የሚኖሩ እህት ወንድሞቻችን ከከፈሉት ዋጋ በላይ ፣ በጋራ የመቆምንም አስፈላጊነትና ጠቀሜታ አሳይታችሁናል ለዚህም መመስገናችሁ ቢያንሳችሁ እንጂ አይበዛባችሁም።
እንደ አገር ያሳለፍነውን አስከፊው ምዕራፍ ከባድ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ሁሉንም በተባበረ ክንዳችን መመከት ችለናል ፤ ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚገባው ትናንት በችግር ወቅት የጀመርነውን አዲስ የትብብር ምዕራፍ ከፍ ወዳለ ደረጃ በማሸጋገር አገርን የተሻለ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ሥርዓት መፍጠር ነው።
እንደ አገር አሁንም አሮጌውን ምዕራፍ በዘላቂነት ዘግተን ኢትዮጵያን የሚመጥናት(አሁን ያለውን ትውልድ የሚመጥን) አዲስ የታሪክ ምእራፍ ለመክፈትና አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የዲያስፖራው ሁለንተናዊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር ሰሞኑን ለዲያስፖራው ማህበረሰብ የተሰጠውም እውቅና ጤናማ ፉክክርን በመፍጠር የበለጠ ሥራ እንዲሠራ የሚያበረታታ ነው። የሕዝብን ሕይወት ለማሻሻልና የአገርን እድገት ለማረጋገጥ የሚተጉ ሁሉ እውቅና እንደሚገባቸው ያመላከተ ነው።
በእርግጥ አሁን ከባዱን ምዕራፍ ተጋግዘን ያለፍነው ቢሆንም እንደ አገር ዛሬም በጋራ እንድንቆም የሚያስገድዱን በርካታ የቤት ሥራዎች አሉብን ፤ ከነዚህ የቤት ስራዎቻችን መካከል አንድና ዋንኛው የወደሙ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ የመገንባት ስራ ነው። ይህ ስራ የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ከፍያለ ርብርብ ይፈልጋል።
ኢትዮጵያ በየዘመኑ ጀግኖችን ታፈራለች። ባለፉት ዓመታት ያጋጠመንን ችግር ለመሻገር በተደረገው ተጋድሎ የጸጥታ አካላትን ጨምሮ በየዘርፉ ተሰልፈው አገሪቱን ያገለገሉ ሚሊዮን ጀግኖች ተፈጥረዋል። የዲያስፖራ አባላትም በተለያዩ የዓለም አደባባዮች የኢትዮጵያን እውነታ ለማስረዳት ያላቸውን ሁሉ አበርክተዋል። ይህን ለአገር የከፈሉት ዋጋ ደግሞ በወርቃማ ብዕር ተጽፎ የሚኖር ይሆናል።
ዛሬ ላይ ችግሩን በሰላም ስምምነት ለመቋጨት ተስፋ ሰጪ መንገድ ላይ ነው ። ይህ አገራዊ ስኬት በጀግኖች ልጆቿ የተገኘ ውጤት ነው ፤ በቀጣይ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በመሻገር የአገርን ክብር ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው ፣ ለዚህም በጋራ መቆም ወሳኝ ነው ። የዲያስፖራው ማህበረሰብም ለአገራቸው የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው በመቀጠል አካላቸው ባዕድ አገር ልባቸው ግን ሁሌም ከአገራቸው ጋር መሆኑን ማሳየት መቻል አለባቸው።
ዛሬም ያልተሻገርናቸው በርካታ ችግሮች ከመኖራቸው አንጻር ዲያስፖራው በእውቀት ሽግግር፣ የልማት ሥራዎችና በሌሎች መስኮች ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት አገራችንን ከለሙት አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የተጀመረውን ጥረት በበለጠ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል። መንግሥትም ይህንን አቅም ለመጠቀም ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ሁኔታና በተጠና መንገድ የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ማስተባበርና መደገፍ ይጠበቅበታል። ይህንንም በተጨባጭ እየሰራ ማሳየት ይኖርበታል።
በእምነት
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም