በዛሬ ጽሁፌ አዲስ ትምህርት፣ አዲስ አገር፣ አዲስ ትውልድ ስል መጥቻለሁ። ትምህርት አገርና ትውልድ የሚቀረጹበት ቁልፍ ነው። እንደሚታወቀው አገራችን ጥሩ የትምህርት ሥርዓት ከሌላቸው የዓለም አገራት ውስጥ ቀዳሚዋ ናት። ይሄ ለምን ሆነ ብለን ስንጠይቅ ከመማር ማስተማር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ነው የምናገኘው።
የመማር ማስተማር ሥርዓታችን ለኩረጃ የተጋለጠ ከመሆኑም ባለፈ ለትምህርት ጥራት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር አይደለም። ለበርካታ ዓመታት በአንድ አይነት መንገድ ስንማርና ስናስተምር ቆይተናል። ይሄ ለውጥ የሌለው የመማር ማስተማር ሥርዓት ደግሞ አዲስ አገር፣ አዲስ ትውልድ መፍጠር ተስኖት በትምህርት ረገድ ጎስቋላዋን ኢትዮጵያ አስታቅፎናል፡፡
በርግጥ አገራችን ውስጥ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ብዙ ኮሌጆች አሉ እኚህ ሁሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ግን ለአገራችን የሚገባውን እውቀትና ሽግግር አልሰጧትም። ጥራትና ብቃት ካልታከለበት የዩኒቨርሲቲ መብዛት ብቻውን ዋጋ የለውም። አሁን አገራችን ያጣችው ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ሳይሆን እውቀትን መሰረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓት ነው፡፡
አሁን እንደ አገር ያጣነው ከኩረጃ የራቀ አንብቦና ተረድቶ ለራሱም ሆነ ለሌሎች የሚተርፍ ተማሪን ነው። አሁን አገራችን ያጣችው ሃላፊነት የሚሰማው፣ ተምሮና አውቆ ለአገር የሚጠቅም ዜጋ ነው ። ተማሪዎች ኮርጀው ካለፉ፣ ኮርጀው ስራ ከያዙ አገር የምታተርፈው ትርፍ የላትም። እንደ አገር ትርፋችን ያለው እውቀትን መሰረት ባደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓታችን ውስጥ ነው። እንደ አገር ትርፋችን ያለው ለውጥ በሚያመጣ፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ በታገዘ የተማሪና መምህር መስተጋብር ነው፡፡
እንደመንግሥት የያዝናቸው የእድገትና የልማት እቅዶች የሚሰምሩት አስተማማኝ የትምህርት ሥርዓት ሲኖረን ነው። በእውቀት የሚመራ የትምህርት ሥርዓትን ሳንገነባ አገርና ትውልድ መፍጠር አይቻለንም። አሁን ላይ ተምረን ሥራ የምንጠብቀው፣ ሥልጣን ይዘን አገርና ሕዝብ የምንዘርፈው ጥራት በሌለው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ስላለፍን ነው።
እውቀት ሁልጊዜም ከመፍትሄ ጋር የተቆራኘ ነው። በእውቀት የታገዘ ትምህርት ሥራ ፈጥሮ ይሰራል እንጂ ጠባቂ አይሆንም። በእውቀት የተገኘ ሥልጣን ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ ይሆናል እንጂ ከማህበረሰቡ አይሰርቅም። በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው እያየናቸው ያሉ ነውሮች ደካማ ከሆነ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የተወለዱ ናቸው፡፡
አገራችንን ከዘመናዊው ዓለም ጋር ለማስተዋወቅ ያለን አማራጭ አንድ ብቻ ነው። እርሱም ጥራት ያለውን ትምህርት ለማህበረሰቡ ማዳረስ ነው። በሁሉም መስክ የተሻለችውን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ከኩረጃ ነጻ የሆነ እውቀትን መሰረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓት ያስፈልገናል፡፡
እስኪ እንጠይቅ እስካሁን የመጣንበት የትምህርት ሥርዓታችን ምን አተረፈልን? በየአመቱ የሥራ አጥ ቁጥር እየጨመረ ነው። በየአመቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር የትየሌለ ነው። ተምረን ለማህበረሰቡ ለውጥ ካላመጣን፣ ተምረን የማህበረሰቡን ችግር መፍታት ካልቻለን የመማር ጥቅሙ ምንድ ነው?። እውቀት አገራዊ ችግሮችን መፍቻ ትልቁ አቅም ነው።
ታላላቆቹን አገራት እንዴት ሰለጠኑ ብለን ስንጠይቅ መጀመሪያ የምናገኘው እውቀት መር የሆነ የትምህርት ሥርዓት ስለነበራቸውና ስላቸው ነው። እኛም አገርና ትውልድ የሚፈጥር እውቀት መር የሆነ የትምህርት ሥርዓት ያስፈልገናል። የምናሽሞነሙነው ነገር የለም። ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ያስፈልገናል። እንደ አገር ከኩረጃ የጸዳ ትውልድና እውቀት ያሻናል፤ አውቆና ተረድቶ ፈተና ያለፈ ተማሪ ያስፈልገናል። እንደ አገር ኩረጃን የሚጸየፍ ማህበረሰብ መፍጠር አለብን፡፡
ያለፍንባቸውን ሰላሳ የመማር ማስተማር ዓመታት መለስ ብለን ብናያቸው በትምህርቱ ዘርፍ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ አላመጣንባቸውም። ለውጥ በሌለው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ነበርን ማለት ይቻላል። ይሄ ብቻ አይደለም በየአመቱ ከፈተና ጋር በተያያዘ የምንሰማቸው የስርቆት ወሬዎች በተማሪዎቹም ላይ ሆነ በትምህርት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡
አሁን ላይ ትምህርት ሚኒስቴር በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሄደባቸው ርቀቶች ውስጥ የመጀመሪያው የተለመደውን የተማሪዎች የአፈታተን ዘዴ መቀየር ነበር። በዚህም መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ጊቢ ውስጥ እንዲፈተኑ ተደርጓል። ይሄ መሆኑ እንደአገር የሚጠቅመው ብዙ ነገር አለ።
በመጀመሪያ ደረጃ የተማሪዎችን መኮራረጅ ከማስቀረቱም ባለፈ በትምህርት ጥራት ላይ የጎላ ድርሻ ያመጣል። ልክ እንደዚህ አገራችን የአቅጣጫ ለውጥ ነው የሚያስፈልጋት። በአንድ አቅጣጫ ተጉዘን ውጤት ያላመጣንባቸው ብዙ የስራ መስኮች አሉ። ትንሽ ዞር ማለት ይጠበቅብናል፡፡
ተማሪዎች በቅርቡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፈተናቸውን ወስደው ውጤታቸውንም አይተዋል። ከውጤት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙዎችን ያስደነገጠ ውጤት ይፋ ተደርጓል። ፈተናውን ከወሰዱ ስምንት መቶ ዘጠና ስድሰት ሺ አምስት መቶ ሃያ ተማሪዎች (896‚520) ውስጥ ከግማሽ በላይ ያመጡት ሃያ ዘጠኝ ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠኝ (29‚909) ተማሪዎች ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሃምሳ በመቶ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በሚቀጥለው አመት በቀጥታ ወደዩኒቨርሲቲ ገብተው የአንደኛ ዓመት ተማሪ የሚሆኑበትን አዲስ አሰራር ዘርግቷል። ከዚህም ባለፈ ከሃምሳ በታች ያገኙ ተማሪዎች ውጤት ባላመጡባቸው ውጤቶች አካባቢያቸው በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ ተሰጥቷቸው በቀጣይ ማለፍ ከቻሉ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሆነው እንደሚቀጥሉ አመልክቷል።
ከዘንድሮ ውጤት ጋር በተያያዘ የተስተዋለው ሌላው አስገራሚ ነገር በአገሪቱ ከሚገኙ ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ዘጠኝ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንድ ሺ አንድ መቶ ስልሳ አንድ (1161) መደበኛ ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸው ነው። በዚህ አያበቃም ከአጠቃላዩ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንድ ሺ ሰባት መቶ ዘጠና ስምንት (1798) የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪ ብቻ ያሳለፉ ሆነው ተገኝተዋል።
ከዚህ በተጻራሪም ሰባት የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ማሳለፋቸውን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ተገልጿል። ከዚህ እውነት በመነሳት የአገራችንን የትምህርት ሥርዓት ምን እንደነበረ በድፍረት መናገር ይቻላል።
ከአዲሱ የትምህርት ሥርዓት በፊት እጅግ ብዙ ተማሪዎች የብሄራዊ ፈተናን አልፈው ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ነበሩ። ይሄ እንዴት ሆነ ብለን ስንጠይቅ እጅግ የቀለለ መልስ ነው የምናገኘው። ያም ተማሪዎች በመኮራረጅ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ውጤት ሲያገኙ እንደነበር መረዳት አይከብድም፡፡
አዲሱ የትምህርት ሥርዓት የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ከመወሰኑም ባለፈ እውቀትን ብቻ መሰረት ያደረገ የትምህርት ሥርዓትን ይፈጥራል፤ በራሳቸው የሚተማመኑ ተማሪዎችን ከማፍራት ረገድም የላቀ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት አለ። ሌላም መጥቀስ ይቻላል። አዲሱ የብሄራዊ ፈተና አሰጣጥ መንገድ ተማሪዎች ለመኮራረጅ እድል የማያገኙበት ስለሆነ በእውቀትና ራስን በመቻል ተገንብተው ወደ ፈተና ክፍል እንዲገቡ በማድረግ በኩረጃና በትምህርት ጥራት ማነስ የሚታማውን የትምህርት ሥርዓት ይቀይረዋል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል ።
አንዳንዶች ዝቅተኛ ውጤቱ የተመዘገበው ተማሪዎች ከቤተሰብ ርቀው በአዲስ ቦታ፣ በአዲስ አካባቢ በመፈተናቸው ነው ሲሉ ይሰማል። የትምህርት ሚኒስቴር አሰራሩ አዲስ ከመሆኑ አንጻር የተማሪዎችን ውጤት ከግንዛቤ አስገብቶ የመቁረጫ ነጥብን ዝቅ ቢያደርግ መልካም ነው የሚሉና ሌሎችንም አስተያየቶች እየሰጡ ነው። ጉዳዩንም የፖለቲካ ይዘት ለማላበስ የሚሞክሩም አሉ።
በዚህች አገር ባህል እየሆነ የመጣው ጥሩ ሲሰራ፤ ጮኸን መጥፎ ሲሰራም ጮኸን ፤ለትችትና ለአሉባልታ የመፍጠናችን እውነታ ልጓም የሚያስፈልገው ነው። ለብዙ ጊዜ በትምህርት ጥራት ማነስ ስትጎሳቆል የነበረችው አገራችን መፍትሄ መጣላት ባልን ማግስት እንዲህ አይነት ያልተገባ አሉባልታ ተገቢ አይደለም ።
ለሀገራችን እድገትና መሻገር ሁላችንም ከመንግሥት እኩል ድርሻ አለብን። በጎ ነገር ማዋጣት ባንችል እንኳን ተስፋ አስቆራጮች መሆን የለብንም። በየትኛውም ሚዛን ብንመዝነው አሁን ላለችውም ሆነ ነገ ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ የሚበጃት እንዲህ ያለው ከኩረጃ ነጻ የሆነ የትምህርት ሥርዓት ነው፡፡
ተማሪ ለምን ጥሩ ውጤት አላመጣም ብሎ መንግሥትን መጠየቅ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። እርግጥ አገራችን የነበረችበት ሁኔታ ይታወቃል። ያ ሁኔታ ግን ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ብቸኛው ምክንያት ነው ብዬ አላሰብም። በቃ የለመድነውና ስንኮርጅና ስናስኮርጅበት የነበረው መንገድ ተዘጋብንና ውጤት ማምጣት አልቻልንም፡፡
በአዲስ የትምህርት ሥርዓት የቻልነውን እንድንሰራ አስገዳጅ ሥርዓት በመፈጠሩ የሚገባንን ውጤት አገኘን። ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም አይነት ምክንያት የለውም። ሁልጊዜ አዲስ ነገር የሚያስፈራን ሕዝቦች ነን። ድህነትን እንጠላለን፣ ኋላ ቀርነትን እንጸየፋለን፤ መፍትሄ የሚሆን ነገር ስናመጣ የመፍትሄው አንድ አካል ከመሆን ይልቅ ለትችትና ለወቀሳ የምንፈጥን ነን፡፡
በየትኛውም ሁኔታ ቢታይ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ለመታደግ የትምህርት ሚኒስቴር አካሄድ እጅግ አዋጪ አካሄድ ነው። የእኛ ጥያቄ ሊሆን የሚገባው ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች እጣ ፈንታ ምንድነው? ውጤታቸውን አሻሽለው የተሻለ የትምህርት እድል የሚያገኙት እንዴት ነው? ብሎ መጠየቅ እንጂ ተማሪዎች ለምን ወደቁ፣ ለምን ጥሩ ውጤት አላመጡም ብሎ ወቀሳ ማቅረብ አይደለም፡፡
ገና በአዲሱ የትምህርት ሥርዓት የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተና አለ። ተማሪዎች ከኩረጃ ነጻ በሆነ መንገድ ተፈትነው ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ በመውጫ ፈተና ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ ያኔ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በሚያስተማምን መንገድ ላይ እንሆናለን። ወደሚበጀን ማየት አለብን፡፡
አዲሷ ኢትዮጵያ የሚበጃት እንዲህ ያለው ከኩረጃ ነጻ የሆነና በእውቀት የተመራ ትውልድን ማፍራት ነው። ለበርካታ ዓመታት በአንድ አይነት መንገድ ላይ ስንጓዝ ነበር። በአንድ አይነት ሥርዓት አንድ አይነት ተማሪ አስተምረን ስናስመርቅ ነበር። በአንድ አይነት ሥርዓት አንድ አይነት አገር፣ አንድ አይነት ትውልድ ስናፈራ ነበር። የአቅጣጫ ለውጥ ያስፈልገናል፤ በእውቀት አገርና ትውልድ የተቆራኙበት ለውጥ፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም