ኢትዮጵያ በወራሪ ቅኝ ገዢዎች እጅ ባለመውደቋ ከጠቀሟት ነገሮች አንዱ ባህሏንና ቋንቋዎቿን ጠብቃ መኖር መቻሏ ነው። አሁን አሁን ግን የባእድ አገር ቋንቋና ባህል መልኩን ቀይሮ በተለያዩ መንገዶች ተገዢ እያደረገን እንደመጣ ብዙ መከራከሪያ ነጥቦች አሉ። ከነዚህ መካከል አንዱ በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ የአገራችን ከተሞች የንግድ ድርጅት ስሞች ዋነኛ ማሳያ ናቸው።
በበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ከሚሰጡት አገልግሎትና ከሚኖሩበት ማህበረሰብ አኳያ አንጀት አርስ የሆኑ ምስጉን ስያሜ ያላቸው ድርጅቶች ጥቂት አይደሉም። የዛሬው ትዝብታችን ግን ከነዚህ በተቃራኒ ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡን ከሕግም ከአመክንዮም የተጣሉ የንግድም ይሁን ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስያሜዎች ላይ ትኩረት አድርጓል።
እውነት ለመናገር የአንዳንድ ድርጅት ስሞች ከሚሰጡት አገልግሎትና ከሚያገለግሉት ማህበረሰብ አኳያ ምንም ትርጉም የሌላቸው ከመሆናቸው ባሻገር ለባለቤቱ ራሱ ትርጉም ያላቸው አይደሉም። መቼም ለአንድ ነገር ስም ወይም ስያሜ ሲሰጥ ካለምክንያት አይደለም። በአገራችን ለልጆች እንኳን ሳይቀር ስም ሲወጣ በምክንያት ነው።
ስም መጠሪያ ከመሆኑ ባሻገር በማንነት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል የሚል አመለካከትም አለ፡፡ ስም አንድ ነገር ካለፈም በኋላ ይኖራል፡፡ በዚህ ምድር የአንድ ዘመን ነዋሪነት አሻራ ነው፡፡ ሰዎች ሲተዋወቁ፣ ስለእነሱ ሲወሳ፣ የእነሱ የሆኑ ነገሮች ሲገለጹም መጠሪያቸው ቦታ አለው፡፡ መለዮም ነው፡፡ በከተሞቻችን ብዙዎቹ በተለይም የንግድ ድርጅቶች ስያሜ በምክንያት የተሰጠ መሆኑ አከራካሪ ነው።
ትርጉም የለሽ የድርጅት ስያሜዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ሌሎች አገራት ቋንቋ በተለይም እንግሊዝኛ በብዙ እያዘነበለ መምጣቱን ትንሽ በከተሞች ዞር ዞር ብሎ መመልከት በቂ ነው። አስገራሚው ነገር በርካታ ድርጅቶች ስያሜያቸው እንግሊዝኛ መሆኑ አይደለም። ስማቸው በእንግሊዝኛ ሆኖ ትርጉሙም ከሚሰጡት አገልግሎት ጋር አለመገናኘቱ ግራ አጋቢ ነው።
አንዳድ ድርጅቶች በተለይም ትልልቅ ሆቴሎች ስያሜያቸው በእንግሊዝኛ መሆኑ ምናልባትም በብዛት አገልግሎት የሚሰጡት የውጭ ዜጎችን በመሆኑ በቀላሉ እንዲያዙ ሊሆን ይችላል ብለን እናስብ። ያም ሆኖ ትልልቅ ሆቴሎች ሁሉ የግድ ስማቸው በውጭ ቋንቋዎች ይሁን የሚል መከራከሪያ በራሱ ብዙ ርቀት ሊያስጉዝ አይችልም። እሺ ትልልቆቹን ወይም ዓለም አቀፍ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን እንተዋቸው፣ ትንንሽ ሻይ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች አገልግሎት የሚሰጡት ለእኛው ሆኖ ሳለ የውጭ ቋንቋዎች ላይ መንጠልጠላቸው ምን የሚሉት ነው?
ሌላው አስገራሚ ነገር ከአገር ውስጥም ከውጭም ቋንቋዎች በተውጣጡ ሁለት ቃላት የሚሰየሙ ድርጅቶች ናቸው። በዚህ መንገድ ስም የወጣላቸው አብዛኞቹ ድርጅቶች የበለጠ ትርጉም የለሽ ከመሆናቸው በላይ ከሕግም የተጣሉ ናቸው። ከሁለት አንዱን ቋንቋ ቢጠቀሙ እንኳን የተሻለ ነው። እንዲያውም የአገር ውስጥ ቋንቋውን ብቻ ቢጠቀሙ ከትርጉምም ከስያሜው ውበትም አኳያ የተሻለ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ለምሳሌ ያህል “ሲስተር፣ ብራዘርስ” ተብለው የሚሰየሙ በርካታ ድርጅቶች አሉ። አሁን እንዲያው ሲስተርስ ወይም ብራዘርስ የሚለው ስያሜ ትርጉሙ ሳይለወጥ በአገራችን ቋንቋ እህትማማቾች ወይም ወንድማማቾች ተብሎ ቢሰየም የተሻለው የትኛው ነው? በሚገርም ሁኔታ ይህንኑ ሲስተርስ ወይም ብራዘርስ የሚል ስያሜ ከሌላ ቋንቋ ከተመነተፉ ቃላቶች ጋር አዳብሎ የሚሰይሙም አልጠፉም። ሲስተርማማቾች ወይም ብራዘርማማቾች የሚሉ ግራ የገባቸው የድርጅት ስያሜዎች ገጥመውኝ ያውቃሉ።
የቋንቋውን ነገር እንተወው፣ በማህበረሰባችን ፊት ለፊት የማይጠሩ (ታቡ) ቃላትን ጭምር የሚጠቀሙ የድርጅት ስሞች አሉ። እነዚህን ድርጅቶች ለምሳሌ መጥቀሱ በነፃ ማስታወቂያ መስራት እንዳይሆንብኝ ትቼዋለሁ። ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ሕጉ ምን ይላል የሚለውን እንመልከት። ከንግድ ሚኒስቴር የድርጅት ስያሜ መመሪያ ጥቂቶቹ ይህን ያስቀምጣሉ “ ከሌሎች አገራት፣ዓለምአቀፍ ወይም አህጉራዊ ድርጅቶች ጋር የተያያዙ ስሞች መሆን የለባቸውም፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ ድርጅት ወይም ማህበረሰብ፣ ጎሳ፣የሰራተኛ ማህበራትና የህብረት ስራ ማህበራት ጋር የተያያዘ መሆን የለበትም። የአገር መሪዎች፣ የታላላቅ ታዋቂ ሰዎችና ዓለም አቀፍ ትልልቅ ከተሞች ስሞች ለንግድ ስም ሊውሉ አይችሉም። የንግድ ስም የሁለት አገሮችን ስሞች በአንድ ላይ የያዘ መሆን የለበትም ለምሳሌ (ኢትዮ ካናዳ)”።
ከነዚህ መመሪያዎች አኳያ የድርጅት ስሞችን ከታዘብን በርካታ ድርጅቶች እንዴት ፍቃድ ሊያገኙ እንደቻሉ አስገራሚ ነው። ለምሳሌ ያህል ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታዎችን ታከው በፖለቲካ ፓርቲ ወይም በታዋቂ ፖለቲከኛ ስም የሚሰየሙ ትንንሽ ድርጅቶች በየቦታው መፈልፈላቸውን በሆነ አጋጣሚ ሳንታዘብ አንቀርም። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በሌሎች አገር መሪዎች ስም ሻይ ቤቶች፣ ቁርስና ምግብ ቤቶች ሳይቀሩ ተሰይመው ሲሰሩ መመልከት የተለመደ ነው።
በዚህ ረገድ እንደ ቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በርካታ ትንንሽ የንግድ ድርጅቶች የተሰየመለት የአገር መሪ ያለ አይመስለኝም። እዚህ ጋር አንድ ፈገግ ያደረገኝን ስያሜ ላንሳ፣ “ቢዮንሴ ቁርጥ ቤት” ይላል ስያሜው፣ ቁርጥን ከዝነኛዋ አሜሪካዊት አቀንቃኝ ቢዮንሴ ጋር ምን እንደሚያገናኛቸው ራሱ ሰያሚው ምክንያት ይኖረው ይሆናል ብዬ ባወጣ ባወርድ ሊገለጥልኝ አልቻለም።
የሆነው ሆኖ እንዲህ አይነት ከሕግም ከምክንያታዊነትም የተጣሉ የድርጅት ስያሜዎች ሲወጡ የአውጪው ብቻ ሳይሆን የፈቃጁም አካል ችግር ገዝፎ እንደሚታይ ማንሳቱ ተገቢ ነው። አንድ ድርጅት ወደ ስራ ከመግባቱ አስቀድሞ የንግድ ፍቃድ ሲያወጣ የድርጅት ስያሜ ጉዳይም አብሮ መነሳቱ አይቀርም። በዚህ ረገድ ከሕግ አኳያ መመሪያው የማይፈቅድላቸው ስያሜዎች የሚሰጡት በችልተኝነት ወይም በዘፈቀደ ነው ማለት ነው። ካልሆነ ደግሞ ብዙ ድርጅቶች ከሕግ እውቅና ውጪ ነው የሚሰሩት እንደማለት ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም