ለውጥ እና ለውጥ የሚሸከማቸው አስተሳሰቦች ይዘዋቸው ከሚመጡት ከፍያሉ ተስፋዎች አንጻር ብዙዎች በለውጥ እና በለውጥ ኃይሉ ተስፋ ለማድረግ አይቸገሩም። ከዚህ የተነሳም ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ የለውጥ ኃይል ሆነው የሚሰለፉ ቁጥራቸው የትየለሌ ነው፤ የቁጥራቸውንም ያህል መነቃቃታቸው ረጅም መንገድ መጓዝ የሚያስችል አቅም መስሎ የሚታይ ነው።
በተለይም ለውጡ በብዙ ገፊ ምክንያቶች ወይም ስብራቶች ተጸንሶና ሕይወት ዘርቶ የተወለደ ከሆነ፤ የለውጡ ባለቤት በሆነው በሕዝቡ ዘንድ የሚጣልበት ተስፋ ትናንቶችንና በትናንቶች ውስጥ ተወልደው ያደጉ፤ የገነገኑ ችግሮችን ምንነት ታሳቢ ያደረገ ባለመሆኑ በራሱ ለለውጡ ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑ የማይቀር ነው። ይህ ደግሞ ለውጥ በተካሄደባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ ጎልቶ የተስተዋለና አሁንም የሚስተዋል ክስተት ነው።
ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ የለውጥ ኃይል ሆኖ የሚሰለፈው ሕዝብ፤ በመሠረታዊነት ትኩረት አድርጎ የሚጓዘው የቀደመውን / አሮጌውን የፖለቲካ ሥርዓት ማስወገድ ላይ ነው። ይህ በራሱ ሥርዓቱን በማስወገድ ሂደት ውስጥ የተሻለ አቅም እንዲኖረው የሚያስችለው ቢሆንም፤ ሥርዓቱ የተፈጠረውን ችግር በአግባቡ ተረድቶ ችግሩን በማከም ሂደት ውስጥ ሊያጋጥም የሚችለውን ፈተናና በፈተና ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ጽናት እንዲያስተውል ዕድል አይሰጠውም።
ከዚህ የተነሳም አሮጌው ሥርዓት በተወገደ ማግስት ለለውጡ ገፊ የሆኑ ምክንያቶች /ስብራቶች/ ሁሉ ወዲያው ታሽተውና ተጠግነው ፈውስ እንዲያገኙ የመፈለግ አዝማሚያዎች ጎልተው ይታያሉ፤ ይህ ፍላጎት ሳይሳካ ቀናት እየተቆጠሩ በሄዱ ቁጥርም በለውጡ ተስፋ ማጣት፤ ለፈተናዎች መንበርከክና እጅ መስጠት ጎልቶ መታየት ይጀምራል። ይህ ደግሞ ለለውጡ ኃይል ተጨማሪ ፈተና ከመሆኑም በላይ ለውጡ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይቀጥል ተግዳሮት ይሆናል።
በአገራችን ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ እየሆነ ያለውም ብዙም ከዚህ የተለየ አይደለም። ለውጡ በብዙ ገፊ ምክንያቶች /ስብራቶች/ ሕይወት ዘርቶ አገራዊ የተስፋ ብስራት ይዞ መምጣቱን ተከትሎ መላው ሕዝብ የለውጡ ባለቤት ስለመሆኑ በተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። ለውጡን ለማራመድ ያሳየው መነቃቃት በአጭር ጊዜ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚያስችለው አቅም ሊሆን እንደሚችልም ያሳየ ነበር።
ትናንት ተወልደው ያደጉ፤ የገነገኑት አገራዊ ችግሮቻችን /ስብራቶቻችን የለውጡ ባለቤት የሆነው ሕዝባችን እንዳሰበውና እንደጠበቀው በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ታሽተውና ተጠግነው ፈውስን መጎናጸፍ አለመቻላቸው፤ ከዚህም በላይ ስብራቶቹ በማደንዘዣ ታሽተው የታሸጉበት ፋሻ ሲፈታ እየተፈጠረ ያለው እውነተኛው የስብራት ስሜት የለውጥ ተስፋውን እየተፈታተነው ይገኛል።
ይህ በመሠረታዊነት የለውጡ ባለቤት የሆነው ሕዝቡ አሮጌውን ሥርዓት ከመለወጥ ባለፈ ፤ ለውጡን በማስቀጠል የለውጡን ተስፋዎች/ ትሩፋቶች ባለቤት ለመሆን በቀጣይነት የሚያስፈልገውን የትግል ዝግጁነት በአግባቡ ካለመረዳት፤ ለውጡን የአንድ ጊዜ ትግል አድርጎ ከመውሰድ የሚመነጭ የአረዳድ ችግር ነው።
በርግጥ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እያስቀመጡ ከመጓዝ ይልቅ፤ ችግሮችን እያድበሰበሱና እየሸፋፈኑ የማለፍ ልምምድ በዳበረበትና ይህን እንደ አንድ የችግር አፈታት ባህል ተደርጎ ሲወሰድ ከመቆየቱ አንጻር፤ የለውጥ ኃይሉ እነዚህን አገራዊ ስብራቶች ለማከም የጀመረው መንገድ ፈታኝ መሆን ብዙም ሊያስገርም አይገባም። በለውጡ ኃይል ላይም ተስፋ ሊያስቆርጥ አይገባም።
እንዲያውም የለውጥ ኃይሉ ስብራቶቹን ለማከም፤ የታሹበትን ማደንዘዣ፣ የታሸጉበትን ፋሻ በማንሳት ስብራቱን ለዘለቄታው በማከም፤ ለመጪው ትውልድ የተሻለች አገር ለማስረከብ እየሄደበት ያለው ፈታኝ መንገድ ሊበረታታና ከፍያለ ድጋፍ ሊሰጠው የሚገባ ነው።
አሁን ላይ እንደ አገር እያንገዳገዱን ያሉት ተግዳሮቶች ዛሬን ከትናንት ስብራቶች ለማከም ከምናደርገው ጥረት የሚመነጩ ከመሆናቸውም በላይ፤ ነገን ብሩህ በማድረግ ሂደት ውስጥ ወሳኝ አቅም ገንብተን እንድንሻገር የሚረዱን ናቸው።
ለውጥ በአንድ ወቅት ተጀምሮ የሚያበቃ ትግል ሳይሆን ቀጣይነት ያለው፤ በጊዜ ሂደት ውስጥ እራሱን እያደሰ በትውልዶች መንሰላሰል ማኅበረሰባዊ ተስፋን የሚያጎናጽፍ ከመሆኑ አንጻር፤ ለውጡ በመጪዎቹ ትውልዶች ተጠናቆ ለአገር የተሟላ ትሩፋት የሚሆን እንጂ ትናንት ላይ ተጀምሮ ዛሬ ላይ የሚያበቃ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም