ይህችን ዓለም ተቀላቅለው እራሳቸውን አይደለም ገና ስማቸውን እንኳን በቅጡ በማያውቁበት በለጋ እድሜያቸው ከፊት ለፊታቸው ድንቅር ካለው ድንግዝግዝ የሕይወት ጨለማ፣ በእጅና እግራቸው እየዳሁ ወጥተው የጥበብን ላምባ አበሩ። ብርሃንም ወገግ አለችላቸው። ላምባዋን ይዘው የጥበብን መንገድ እየተከተሉም ብዙዎችን አስከትለው መሩ፤ የጥበብን ባሕር ከፍለውም ጠቢባኑን እንደ ሙሴ አሻገሩት። ከግጥም እስከ ልቦለድ፣ ከትወና እስከ አዘጋጅነት፣ ከዳዊት እስከ አስኳላ ደግሞም እስከ ረዳት ፕሮፌሰርነት፣ ከትንሿ መንደር እስከ ባሕር ማዶ፣ እንዲሁም ከንጉሥ እጅ ሽልማትን እስከመቀበል ደርሰዋል። ጣፋጯን ፍሬ ለመብላትም፣ ሁሉንም መራራ መንገዶች በትዕግስትና በተስፋ የተጓዙት ተስፋዬ ገሠሠ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ቲያትር እርሾ ለመሆኑ በቁ። ባበርከቷቸው ዕንቁ የኪነ-ጥበብ ሥራዎቻቸው ታሪክ ያነሳቸዋልና እኛም የዛሬው የዝነኞች ገጽ ባለታሪክ ልናደርጋቸው ወደድን።
ከውስጣቸው የነበረውን የጥበብ ሀብት አንዳችም ሳያስቀሩ ለሀገራቸው የቸሩት እኚህ ታላቅ ሰው መስከረም 17 ቀን 1929 ዓ/ም በሐረርጌ፣ ጎረጎቱ በሚባለው ስፍራ ነበር የተወለዱት። ታዲያ በተወለዱ ገና በስምንተኛው ወርም እናታቸውን ወ/ሮ በለጠች ያየህይራድን በሞት በማጣታቸው የእናታቸውን ታላቅ እህት ጡት እየጠቡ ነበር ያደጉት፡፡ ታላቁ የጥበብ ሰው ተስፋዬ ገሠሠ፣ የሁለት ዓመት ሕጻን ሳሉ ደግሞ አባታቸውን በሞት በማጣታቸው የወላጆቻቸውን መልክ እንኳን አያውቁም ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ሕይወትን በአሳዛኝ ሁኔታ በዚህ መልኩ ጀመሯት። ለቤተሰቦቻቸው ብቸኛ ልጅ የነበሩት ተስፋዬ ገሠሠ እስከ ስምንት ዓመታቸው ድረስ ከዚያው ከሐረርጌ የቆዩ ሲሆን ወደ ቤተ-ክህነት በመሄድም ዳዊት ደግመዋል። ስምንት ዓመት ከሞላቸው በኋላ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት በተፈሪ መኮንን አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የቀለም ትምህርታቸውን ጀመሩ። ወደዚያ የገቡበት ምክንያትም ወላጆቻቸውን ያጡት በጣሊያን ጊዜ በመሆኑ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የተወለዱበት ወቅት የጣሊያን ፋሽስት ኃይል እና ሀገራችን ኢትዮጵያ በሩን ክፈች አልከፍትም! እየተባባሉ የነበረበት ወቅት ነበርና ወደ ፈረንጅ የሚያደላውን መልካቸውንና ሀር መሳይ ፀጉራቸውን የተመለከቱ ብዙ ሰዎች የኋላ ኋላ አባታቸው ከወደጣሊያን ሳይሆን እንዳልቀረ ይጠረጠሩና ይጠይቋቸው ነበር። ተስፋዬ ገሠሠ ግን ስለዚህ ጉዳይ በተጠየቁ ቁጥር የአዕምሮ እረፍት ይነሳቸው እንደነበረ የቅርብ ወዳጆቻቸው ይናገራሉ።
ሁለገቡ አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ወደ ቲያትር ሙያ የገቡት በልዩ አጋጣሚ ነበር። በ1951 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከአንድ የቲያትር መድረክ ላይ ተገኝተዋል። ከመድረኩ ላይ ደግሞ “እዮብ” የተሰኘ አንድ ቲያትር በመታየት ላይ ነበር። ታዲያ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በድንቅ ብቃት እየተወነ ከነበረው ወጣት ላይ አይንና ቀልባቸው ያርፋል፤ በውስጣቸውም ‘የሚበስል እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል’ ሳይሉ አልቀሩም። ታዲያ በአድናቆት ብቻ ማለፍ ያልፈለጉት ንጉሡ ወጣቱን አስጠርተው የእጅ ሰዓት ከሸለሙት በኋላ ቁጭ አድርገው አወሩት። ወጣቱ ሕልሙ የሕግ ሙያ ላይ ነበርና ይህንንም ሲሰሙት “የምን የሕግ ሙያ ነው ያንተ ትክክለኛው ቦታ ቲያትር ላይ ነው” በማለት የተሻለ ዕውቀት ይቀስም ዘንድ ወደ አሜሪካን ሀገር ሄዶ የተውኔት ሙያ እንዲማር አዘዙ። ያ ወጣትም ታላቁ የጥበብ ሰው ተባባሪ ፕሮፌሰር አርቲስት ተስፋዬ ገሠሠ ነበሩ።
ለሁለት ዓመታት ያህል በአሜሪካን ሀገር በኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በመከታተል በተውኔት ዘርፍ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀው ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የቲያትር ትምህርትም የመጀመሪያው ምሩቅ ሆኑ። ከዚያ በኋላ ብዙ ሳይቆዩም በኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት ወይም ደግሞ በአሁኑ ብሔራዊ ቲያትር ለትምህርት ያቆሙትን የቲያትር ሥራ አዳብረው በመጡት አዲስ ክህሎት እንደገና ቀጠሉ። በኢትዮጵያ ቲያትርን ለማዘመን ሰይታክቱ ብዙ ሥራ ሠርተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ክፍል የረዥም ዘመን መምህር ሆነው አገልግለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትርና ሀገር ፍቅር ቲያትር ሥራ አስኪያጅ በመሆን ቲያትሩን የማዘመን በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ጭምር የመዝናኛ መሰናዶዎችን የጀመሩ የጥበብ ሰው ናቸው። በቅርብ ጊዜ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመዝናኛ ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ስለነበረው አጋጣሚ ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ ይህ ነበር “የቲያትር ኬጂ እንድማር የሕይወቴን የጥበብ በር የከፈቱት እሳቸው ናቸው። የኢትዮጵያን ቴአትር ማስፋፋት ደግሞ ትልቁ አደራዬ ነበር”።
ሌላው በሕይወት ዘመናቸው ለሀገራቸው ካበረከቷቸው ትልልቅ ሥራዎች መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘውን ቤተ ኪነ ጥበባት ወቴአትር የሚባለውን ማዕከል ከዶክተር ፊሊፕ ካፕላን ከሚባሉ የቲያትር ሰው እና ከግብጻዊ አሜሪካዊው የሙዚቃ ምሑር ሐሊብ ኤልድሃብ ጋር በመሆን መመሥረታቸው ነው። በወቅቱ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ ወካይ በመሆን የማዕከሉ ዳይሬክተር ነበሩ። ይህ ማዕከልም ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሕል ማዕከል ተብሎ የሚጠራውና ብዙ ደራሲያን እና ከያኒያንን ያፈራ እያፈራም ያለ ማዕከል ነው።
ተስፋዬ ገሠሠ፣ እሳቸው አንድ ቢሆኑም ሙያዊ ተሰጦአቸው ግን እልፍ ነው። ከትወና ሥራዎቻቸው ባሻገር በርካታ መጽሐፍትን ጽፈው ለንባብ ማብቃት ችለዋል። ለምሳሌ ያህልም በአሜሪካን አገር እያሉ በ1953 ዓ.ም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ላቀችና ማሰሮዋ እንዲሁም በ1965 ዓ.ም መተከዣ፣ ጥንወት፣ ይሉኝታና ፍቅር እና ሽልማት፣ ዑመር (የኻያም ልቦለዳዊ የሕይወት ታሪክ)፣ ሩብ አያቶቹ የተሰኘውን የትርጉም ሥራ ጨምሮ የመጨረሽታ መጀመርታ(ታሪክና ሕይወት ቀመስ) ልቦለዶችን፣ እንዲሁም ጎህ ሲቀድ የተሰኘው የግጥም መድብል ተጠቃሽ ናቸው።
በእድሜ ብቻ ሳይሆን በትወናና በድርሰት ሥራቸውም ጭምር አንቱ የተባሉት እኚህ ታላቅ ሰው፣ የሼክስፒርን ሐምሌት የተሰኘውን ተውኔትን ጨምሮ ለመድረክ ካበቋቸው ሥራዎች መካከል የሺ 1954፣ አባትና ልጆች 1958፣ እቃው 1961፣ ማነው ኢትዮጵያዊ በ1966፣ ፍርዱን ለእናንተው 1970፣ ተሐድሶ 1972፣ እንዲሁም 1979ዓ.ም ደግሞ ሰኔና ሰኞ የተሰኙ ተውኔቶች ላይ በብቃት መተወን ችለዋል። ከትወና ባሻገር በዝግጅትና ዳይሬክቲንግ የጥበብ አሻራቸውን ካሳረፉባቸው ተውኔቶች ዕቃ2፣ አስናቀችና ድስቷ፣ ኡኡኡ!፣ ቲያትር ሲዱዳ፣ ባሮች አንሆንም፣ ሰለሞንና ሳባ፣ ሸርሸላፋም እና መንገደኞች የተሰኙ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
አርቲስት ተስፋዬ አበበ(ፋዘር) እና ተስፋዬ ገሠሠ ለአስር አመት ያህል በቅርብ ወዳጅነት አብረው አሳልፈዋል። ሁለቱ ተስፋዬዎች ትውውቃቸው የሚጀምረው ከ1965 ዓ.ም ተስፋዬ አበበ የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤትን ሲመሠርቱ ተስፋዬ ገሠሠ ደግሞ የቲያትር ቤቱ ኃላፊ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ነው። “ተስፋዬ ገሠሠ ልዩና ጨዋ ሰው ነበር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበብ መምህር ሆኖ ሲሠራ ወደፊት ተተኪ የሚሆኑ ተዋንያንን ማፍራት ችሏል። በሙያውም ሆነ በባሕሪው እጅግ በጣም ተወዳጅና ሁሉም ቆሞ የሚቀበለው ሰው ነበር” በማለት ተስፋዬ አበበ ይመሰክራሉ።
ተስፋዬ ገሠሠ ሙያቸውን ማዕከል በማድረግ የሀገሪቱን የገሀድ ዓለም እውነታ ለማሳየት በመሞከራቸው በተለያዩ ጊዜያት ለእስርና ለእንግልት ተዳርገዋል። “ጋሻ ዳምጤ” የወሎ ረሀብን የሚያሳይና በወቅቱ የሳንሱር ሕግ የተከለከለ ሙዚቃዊ ተውኔት ሲሆን የትወና ብቃታቸውን ፍንትው አድርጎ ማሳየት የቻለ ነበር። የዚህ ተውኔት ሙዚቃ በተስፋዬ አበበ የተሠራ ሲሆን፣ ተስፋዬ ገሠሠ ደግሞ ዳይሬክት አድርገውታል። “ዕቃው” የተሰኘውን ተውኔት ግሩም በሆነ መልኩ ጽፈው ለመድረክ ቢያበቁትም ይህም ሥራ የደርግ መንግሥትን የሳንሱር ገደል መዝለል ባለመቻሉ ለእስር ተዳርገዋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ‘ደማችን ትግላችን’ የተሰኘ ሙዚቃዊ ተውኔት ላይ በትወናና በዝግጅት በመሥራታቸው የምን ደማችን ትግላችን ነው፣ የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው፤ ተብለው በድጋሚ ለጥያቄ ቀረቡ።
ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ በሆነው ውጥንቅጡ በወጣው እንደ ሀገሬ ሰው ተረት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተስፋዬ ገሠሠ ግን ዝምታቸውን ሰብረው ሀገራዊና ሕዝባዊ በሆኑ ሥራዎች ውስጥ በድፍረት ገብተው በድፍረት ወጥተዋል። ለኪነ ጥበብ ዘርፉ እንደየዘመኑ ዋጋ ከፍለዋል። ለተጠሩበት የጥበብ ዓለም፣ ከዓላማቸው ዝንፍ ሳይሉ መኖር የቻሉና ለማንኛውም መስዋዕትነት ዝግጁ የነበሩ ስለመሆናቸው የሚያውቋቸው በልበሙሉነት ይናገራሉ። አንዳንድ ነገሮች ከበላይ አካል ሲመጡም ‘ይህን አልሠራም!’ የማለት አቅም የነበራቸው ሰው ናቸው።
የተስፋዬ ገሠሠ የቅርብ ወዳጅ የነበሩት ገጣሚና ፀሐፊ ተውኔት አያልነህ፣ በወቅቱ ከነበሩት አስቸጋሪ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ስለነበረው አንድ አጋጣሚ ደግሞ እንዲህ ያስታውሱታል “በደርግ ዘመነ መንግሥት የሱዳን መሪ ኢትዮጵያ መጥተው ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም ሙዚቃ ለማየት ትያትር ቤት ገብተው ሳለ፣ ማን እንዳደረገው ሳይታወቅ በመሐል መብራት ጠፋ። የዚያን ጊዜ ‘ሆነ ተብሎ ነው የተደረገው’ በሚል ወቀሳ ቀርቦባቸው ነበር። በዚህ ምክንያትም በወቅቱ የነበሩት የባሕል ሚኒስትር ከሥልጣናቸው ተነስተዋል” በማለት ተስፋዬ ገሠሠ ምን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪና መንግሥት ከእይታው እንዳይጠፉ በንቃት የሚከታተላቸው ሰው እንደነበሩ ይናገራሉ።
ተስፋዬ ገሠሠ የአፍሪካ ሀብት፣ የኢትዮጵያ ኩራት ነበሩ። ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ ካፈራቻቸው ቀደምት የትያትር ባለሙያዎች መካከል ተጠቃሽና ሌሎች በርካታ የኪነ ጥበብ ሰዎችን በማፍራት ስመጥር ናቸው። ያለፉበት መንገድ ሁሉ መዓዛው እያወደ ይጠራልና ብዙዎች የእሳቸውን የጥበብ ዳና እየተከተሉ ወደ ትክክለኛው የሕይወት መስመር ለመግባት ችለዋል። የተከተላቸው ይቅርና በሩቁ ሆኖ የተመለከታቸውም እንኳን ስለ ታላቅነታቸው ተናገሮ ሳያመሰግናቸው አያልፍም።
ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከልጅነት ሕይወት እስከ ነጭ ሽበት በመውደቅና መነሳት ብዙ ታላላቅ ሥራዎችን ማበርከት የቻሉት አንጋፋው የጥበብ ሰው፣ በእድሜ መግፉትና መሰል ድካሞች ቢያዙ ጊዜ፣ በጅምር የለኮሱትን ላምባ በስተመጨረሻም በአደራ ለትውልዱ አስረክበው፣ ታኅሣሥ 6 ቀን 2013 ዓም በ84 ዓመታቸው ለዘለዓለሙ አሸለቡ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም