የዛሬው የሕይወት ገጽ እንግዳችን አንጋፋው ድምፃዊ አርቲስት አያሌው መስፍን ነው። ድምፃዊው የተወለደውም ሆነ ያደገው በቀድሞው አጠራር ወሎ ክፍለ-ሃገር በየጁ አውራጃ ወልዲያ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ጣይቱ ብጡል ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ተከታትሏል። ከልጅነቱ ጀምሮ የሙዚቃ ፍቅር ያደረበት እንግዳችን ይህንን የልጅነት ራዕዩን ለማሳካት ያስችለው ዘንድ 12 ዓመት ሲሞላው ግን ትምህርቱን ርግፍ አድርጎ በመተው የተወለደበትና ያደገበትን ቀዬ ለቆ አዲስ አበባ ገባ። ይሁንና አዲስ አበባ እንዳሰበው ሕልሙን ለማሳካት ምቹ አልሆነችለትም፤ እንደተመኘውም ቶሎ ዘፋኝ መሆን አልቻለም። ይልቁኑም ‹‹ጅቡቲ›› በተባለ ቡና ቤት ውስጥ ሳህን አጣቢ ሆኖ በአስር ብር ተቀጠረ።
ጥቂት እንደሠራ ግን 1956 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ብሔራዊ ቲያትር የቅጥር ማስታወቂያ መውጣቱን ይሰማና ምዝገባው ሊጠናቀቅ ሲል ይደርሳል። ጥበቃን ለምኖ ሲገባ በወቅቱ ተወዳዳሪዎቹን ይፈትኑ የነበሩት እነመርዓዊ ስጦታው አዝነውለት ዕድሉን ይሰጡታል፤ እሱም ውድድሩን በብቃት ተወጥቶ አንደኛ ይወጣል። ይሁንና ዘፋኝ ሆኖ ድምፁ በሬዲዮ ከተሰማ አባቴ ልጄ ‹‹አዝማሪ ሆነ›› ብለው ይቀየመኛል በሚል ስጋት ወደ ቲያትር ቤቱ ተመልሶ ሳይሄድ ይቀራል። ይሁንና ከሥራው ጎን ለጎን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በማታው ክፍለ ጊዜ ገብቶ ትምህርቱን መከታተሉን ቀጠለ።
በዓመቱ ደግሞ በክቡር ዘበኛ ውስጥ የልጅ ወታደር ሆኖ ተቀጠረ፤ በክብር ዘበኛ ውስጥ ደግሞ ከልጅነቱ ጀምሮ ሲሰማቸው ያደገውና ከልቡ የሚያደንቃቸው እነክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ፣ ተፈራ ካሳ፣ እሳቱ ተሰማ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ መሐሙድ አሕመድና አሊ ቢራ ሙዚቃ ይሠሩ ስለነበር በልቡ ተዳፍኖ የቆየውን የልጅነት ሕልሙን ለማሳካት ዳግም ብርሃን ያየ መሰለውና እጅግ ተደሰተ። አሁንም ቢሆን ወደኪነ-ጥበቡ ለመግባት ነገሮች ቀላል አልሆነለትም፤ ቅጥሩ ውትድርና ስለነበር ዕድሉን ማግኘት አልቻለም። በዚያ ላይ ደግሞ በሠራዊቱ ውስጥ ይሰጥ የነበረው ከባድ ወታደራዊ ስልጠና ያልጠነከረው የልጅ ሰውነቱ መቋቋም አቃተው።
በተለይም በቤተሰብ እንክብካቤ ውስጥ ያደገ መሆኑ በሠራዊቱ የሚሰጠው ሥልጠናም ሆነ ቅጣት ምሬት ውስጥ ከተተው። ይህም ብሶት ታዲያ ‹‹ማሩኝ ዘመዶቼ›› የሚለውን የመጀመሪያ ዜማውንና ግጥሙን ወለደ። ይህንን ሥራውን በክብር ዘበኛ ውስጥ ላሉ ኃላፊዎች ሲያሳያቸው ግጥሙን ወደዱለት፤ ግን ደግሞ ‹‹እዚህ ቤት ውስጥ ማሩኝ ተብሎ አይዘፈንም›› አሉት። ከዚያ ይልቅም ቁመናው ስለሚያምር ተወዛዋዥ እንዲሆን መከሩት። እሱ ግን በምላሻቸውም ሆነ ምክራቸውን ስላላስደሰተው በእልህ ተነስቶ ጄኔራል ደበበ ኃይለማርያም የተባሉ ሰው ጋር ዩኒፎርሙን እንደለበሰ ይሄዳል። እንደደረሰም እግራቸው ላይ ወድቆ ጉዳዩ አጫወታቸው። ወላጆቹ እንደናፈቁትና መመለስ እንደሚፈልግ ነገራቸው። የልጅ እግሩ ወታደር ሁኔታ ክፉኛ ልባቸውን የነካው ጄኔራሉ ሰባት መቶ ብር እንዲሰጠው አደረጉና ከሠራዊቱ እንዲሰናበት አደረጉት። ከዚያ እለት ጀምሮም ማንኛውም ወታደር ከ18 ዓመት በታች እንዳይቀጠር ትዕዛዝ አስተላለፉ።
ከሠራዊቱ ከወጣ በኋላም አንድ ቀን ከታላቅ ወንድሙ ጋር በአጋጣሚ በአርበኞች ሕንፃ አካባቢ ሲያልፉ እነጌታቸው ካሣ አዲስ ባንድ አቋቁመው ሙዚቃ ሲሠሩ ያዳምጣል። ወንድሙን መጣሁ ብሎት በተከፈተው በር ሰተት ብሎ ገብቶ ‹‹ጋሼ ልዝፈን?›› ብሎ በቀለ ወዳጆ ለሚባል ሰው ይጠይቃል። ሰውየውም የልጅ እግሩን ወጣት ድፍረት ተመልክቶ ‹‹ትቺያለሽ›› በማለት ፈቀደለት። ያቺ አጋጣሚ ታዲያ ታዳጊውን አያሌው የተፈጥሮ ችሎታ በሚገባ አሳየችለት። የድምፁ ለዛና ውበትም እነዚያን እውቅ ዘፋኞችን ቀልብ ገዛ። የመጀመሪያ ሥራውን ደብረዘይት በሚገኘው ሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት አዳራሽ አቀረበ። ይሁንና በብዙ ሕዝብ ፊት ሙዚቃ ሲያቀርብ የመጀመሪያው በመሆኑ ሙዚቃው በፍርሃትና በሃፍረት የታጀበ ነበር። በመቀጠል ግን ከባንዱ ጋር ሆኖ ጅማ ከተማ ተጓዘ፤ የወይዘሮ ጥሩነሽ ደባልቄ ‹‹ብርችምችም›› ምሽት ቤት መሥራት ጀመረ።
ስለጅማ ሕዝብ ሲያነሳ ‹‹የጅማ ሕዝብ ያልተከፈለ የፍቅር እዳ አለብኝ›› በማለት ይናገራል። በዚያ እድሜው ልጅነቱንም ሆነ ጀማሪነቱን ሳይንቅ ሥራዎቹን በማድነቅና በመደገፍ በሙያው ገፍቶ እንዲሄድ ትልቅ አቅም እንደሆነው ይመሰክራል። ወርቅና ቡና ከመሸለም ጀምሮ ድጋፍ ያደርጉለት እንደነበርም ያስታውሳል። የተለያዩ ምሽት ቤቶች ከባንዱ ጋር እየሠራ የጅማ ሕዝብ ከፍተኛ እውቅና ማግኘት ሲጀምር የባንዱ አባላት ከሙዚቃ ቤቱ ባለቤት ጋር በመደራደር ተወዛዋዦችን ከአዲስ አበባ እናስመጣ በሚል አያሌውን ጥለውት ይሔዳሉ። ወጣቱ ሙዚቀኛ የባንዱ አባላት ከነገ ዛሬ ይመጣሉ ብሎ ለሦስት ወራት ቢጠብቅም እነሱን የበላ ጅብ አልጮህ አለ። ቆይቶ ግን እንዳታለሉት ሲገባው ወደአዲስ አበባ ተመለሰ።
በቀጥታ ክቡር ዘበኛ ለነበሩት ለእነ ካሣ ተሰማ ጉዳዩን አጫወታቸው፤ እነሱም ደብዳቤ ለፓርቲስ ሉቡንባ ምሽት ቤት ወይዘሮ አሰገደች አላምረው ፅፈው ላኩት። ዝንጥ ብሎ በመሄድ ለወይዘሮ አሰገደች የታሸገውን ፖስታ ሰጣቸው፤ በደብዳቤው የተገረሙት ሴት ‹‹መልክና ቁመናው የሚያምር ዘፋኝ ተልኮልናል፤ ድምፁን እንስማው›› በማለት እድሉን ሰጡት። ያን ጊዜ ደግሞ የመድረክ ልምዱ ዳብሮ ስለነበር ኮለል ያለ ሙዚቃውን በነፃነት አሰማቸው። በዚያው እለት ብቻ ሦስት ሺ ብር ተሸለመ። ከዚያ ወዲህም ልምድ የሙዚቃ ሕይወቱ በጠንካራ መሠረት ላይ ተጣለ።
በወቅቱ አባ ዳገት ዘሪሁን የተባሉ የጎጃም ማር ነጋዴ ወጣቱ ድምፃዊ የሰዎች ዘፈን ከመዝፈን ወጥቶ የራሱን ዘፈን እንዲዘፍንና ራሱን እንዲመስል ከፍተኛ እገዛ አደረጉለት። የገንዘብ ድጋፍ አደረጉለትና በአንድ ወር ውስጥ የራሱን ሙዚቃ ሠርቶ በሬዲዮ ሲሰሙት ብቻ ዳግመኛ እንደሚያገኙት ነግረውት ይሄዳሉ። እናም በእኚህ ነጋዴ አነሳሽነት 16 የራሱን ግጥምና ዜማ አዘጋጅና ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ሰጠ። በሚያስገርም ሁኔታ ሙዚቃው በተለቀቀ እለት በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘ፤ እሱ በሚገኝባቸው መድረኮች ሁሉ ጠጠር መጣያ ቦታ እስኪጠፋ ድረስ ሥፍራው በታዳሚዎች ይሞላ እንደነበርም በትዝታ ፈረስ የኋሊት ተጉዞ ያወጋል።
‹‹ባልጠበኩት ሁኔታ እግዚአብሔር አነሳኝ፤ ብዙ ዓመታት ከዘፈኑ ታዋቂ ድምፃያኖች እኩል አሰለፈኝ›› ሲል ለአምላኩ ምስጋናውን ይሰጣል። ‹‹በእውነት ለእውቅና ያበቃኝ ያሰገደች አላምረው ክለብ ነው›› ሲልም ያክላል። ክለቡ እነክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ፤ ታምራት ሞላ፤ አለማየሁ እሸቴና ሌሎችም ታዋቂ ዘፋኞችን ያፈራ ትልቅ ባለውለታ እንደሆነም ይመሰክራል። ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት ከፍተኛ ጥረት ያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆመው።
በወጣትነቱ ስሙ እየገነነ የመጣውን ሙዚቀኛ አያሌውን በ1962 ዓም ብሔራዊ ቲያትር በከፍተኛ ደመወዝ ቀጠረው። ይሁንና ቀድመው የተቀጠሩ አርቲስቶች ደመወዝ አነስተኛ ስለነበር ብዙዎቹ በሱ ከፍተኛ ደመወዝ ተካፋይነት ቅር ተሰኙ። ውሎ ሳያድርም ቅሬታው ወደለየት ጦርነት አመራ። አለመግባባቱ ተካረረና ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሥራውን ለመልቀቅ ተገደደ። ይሁንና የልቡን ያየው ፈጣሪ ብዙም ሳይቆይ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ጄኔራል ይልማ ሺበሺ የተባሉ ሰው የአያሌውን ‹‹ቻለው ሆዴ›› የተሰኘውን ሙዚቃ በሬዲዮ ያዳምጡና ፈልገው አፈላልገው አገኙት፤ የሠራዊቱ ሙዚቃ አድርገው ከአምስት ሺ ብር ሽልማትና በጥሩ ደመወዝ ቀጠሩት። በተሰጠው ሽልማትም ቮልስ ቫገን መኪና ገዛ። እናም የፖሊስ ሙዚቀኛ ሆኖ እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ አብሮ ዘለቀ።
ሠራዊቱን ከለቀቀ በኋላ የራሱን ‹‹ጥቁር አንበሳ›› የተባለ ዘመናዊ ባንድ ከጃፓን 47 ሺ ብር የሙዚቃ መሣሪያ በማስመጣት መሠረተ፤ በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ሙዚቃውን መሥራት ጀመረ። የነበረውን ዞን 66 ክለብ በመተው ስቴሪዮ ክለብ ከፈተ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ አብዮቱ ፈነዳና ሀገርና ሕዝብ መቅደም አለበት በሚል ባንዱን ይዞ በየበረሃው ከሠራዊቱ ጎን መሰለፉን ቀጠለ። ሕይወቱን የሰጠበትና ብዙ ዋጋ የከፈለለት አብዮት ግን የተነሳበትን ራዕይ ወደጎን ትቶ አፈሙዙን ወደ ንጹሐን ሲያዞር ሙዚቀኛውም ትግሉን ገታ፤ መንገዱንም ለየቅል አደረገ። ከደርግ መንግሥት ጋር የተቃቃረበትን ሁኔታ ሲያስረዳም ‹‹ኅዳር ወር ላይ እነዚያ የኢትዮጵያ እንቁዎች አላግባብ ሲጨፈጨፉ ደርግና እኔ ተለያየን›› ይላል። ደርግ ሲመጣ ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበርም የሚያስታውሰው ድምፃዊው ‹‹’እነመለዮ እጥላለሁ እና ጉንፋን’ የመሳሰሉት ዘፈኖቼ ሠራዊቱን ለማገዝ የዘፈንኳቸው ናቸው›› በማለት ይናገራል።
ደርግ ሲመሠረት ለጭቁኑ ማኅበረሰብ ዘብ ለመቆም እንጂ ሕዝብ ለመጨፍጨፍ እንዳልነበር የሚናገረው አርቲስት አያሌው ሲጀምር ‹‹ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› ብሎ መነሳቱን በሂደት ግን ‹‹ያለደም የለም ስርየት›› ወደሚል መርሆ መቀየሩ ልቡን እንደሰበረው ያመለክታል። እናም ወታደራዊው መንግሥት ከነበረበት ወደ አልነበረበት በመሄዱ የተወደደውን ያህል መጠላቱን፤ የተመሰገነውን ያህል መዋረዱን ያወሳል። ያን ጊዜ ታዲያ አርቲስቱ ‹‹እፍ እፍ ያሉት ፍቅር ጭቅጭቅ አያጣም
መንቀዥቀዥሽ በዛ ጠረጠርኩሽ በጣም፤
መጀመሪያ ጣፋጭ ቆይተሸ መራራ
መሆንሽነው መሰል በጣም ልቤ ፈራ…›› ሲል በማቀንቀን የሆዱን ብሶት አውጥቷል። በዚህም ብቻ ግን አላበቃም፤ ‹‹አልሰማም ወገኔ የደርጎችን ጭካኔ
በመላው ኢትዮጵያ በደጋ በቆላ
ወጣት ሽማግሌው በጥይት ሲቆላ
ምነው የሃገሬ ሰው አንጀቱ ጨከነ
እንደጥንቱ አልሆነም ልቡ ደነደነ…›› በማለት አዚሞ ሕዝቡ በድፍረት ጨካኙን መንግሥት እንዲቃወም መቀስቀሱን ቀጠለ። ይህንንም ተቃውሞውንም የሚገልፁለትን 12 ሙዚቃዎችን አዘጋጀ፤ አራት ሺ ካሴት አሳትሞ ለወዳጆቹ ሰጥቶ ከሃገር ለመውጣት ሲል ተያዘ። ‹‹የሚገርምሽ የራሴ ሰዎች ናቸው ያስያዙኝ›› ሲልም ሃዘኑን ይገልፃል። ማስፈራሪያና ዛቻው ያልገደበው አርቲስቱ ፈጣሪ በሰጠው ጥበብ ተጠቅሞ ደርግ በሕዝብ ላይ የሚፈፅመውን በደል በድፍረት መቃወሙን ቀጠለ፤ ይህም ሁኔታ ያበሳጫቸው ባለሥልጣናት ለሦስት ወራት ወህኒ አወረዱት። ሙዚቃው በሰዎች እጅ ሳይደርስ ከነሙዚቃ መሣሪያውና መኪናው ጭምር እንዲወረስ ተደረገ። ከሦስት ወራት በኋላም ዳግመኛ መድረክ ላይ ላይወጣ፤ በማንኛውም ሙዚቃ ሥራ ላይሳተፍ፤ ከሃገር ውጭ እንዳይወጣ ፈርሞ ከእስር ተለቀቀ።
ያመነበትን ሁሉ ከመናገርና ቅሬታውን ለማሰማት የማይሰጋው ይኸው ብርቱ አርቲስት በተለይ የሕዝብ ወገን ነኝ ብሎ ያስብ ስለነበር ሕዝቡን የሚበድሉ አሠራሮች ሲመጡ ለመቃወም ወደኋላ እንደማይል ነው ያጫወተን። ‹‹ነፃነት ከሌለው ሕዝብ ጋር እየኖርኩ እኔ በነጻነት ልመላለስ አልችልም፤ ኢትዮጵያ ሃገሬ ዜጎቿ በሰላም ወጥተው በሰላም ካልገቡ፤ እኔ ፈፅሞ ሰላም ሆኜ ልኖር አልችልም›› ይላል። በንጉሡ ዘመንም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ በሚያቸው ያልተገቡ አሠራሮች ላይ ግጥም ፅፎ፤ ዜማ ሠርቶ ተቃውሞውን ይገልፅ እንደነበርም አልሸሸገንም። በወቅቱ ከሠራቸው ሥራዎች መካከልም ለአብነት
‹‹ወጥ በከሰል በእንጨት እየተቀቀለ
እንጀራ በአቋራጭ በምላስ በሰለ
ከአናፂውም አይደል ወይንም ከገንቢው
አቀባዩ ሆኗል የተጠቀመው
መቆየት ደግ ነው አየን ብዙ መላ
እጅ ሳያቀብል በምላስ ሲበላ…›› ሲል በሐቅ ከሚሠራው ይልቅ ወሬ አቀባዩ እንዴት ተጠቃሚ እንደሆነ ያነሳል። ይህ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ ባለስልጣናት ሕዝቡን በሙስና እንዴት ያስጨንቁት
እንደነበር ለመግለፅ ሲልም ‹‹አላጎበድድም ለራሴም
አልበቃሁ ለእለት ጎሮሮዬ
የእጅ መንሻም የለኝ ተወኝ አለቃዬ
እኔ ሽሮ አሮብኝ አንጀቴ ተርቦ
ለእጅ መንሻ ብዬ ለአንተ አልሰጥም ጉቦ… ››ሲል የፃፈውን ግጥም በአማረና ልብን በሚነካ ዜማ አዚሞታል።
ታጋዩ አርቲስት ለሕዝብ ዘብ በመቆሙ ምክንያት ብቻ መታሰሩ አልበቃ ብሎ በደርግ መንግሥት በርካታ ሃብትና ንብረቱ ተወርሶበታል፤ ከነቤተሰቡ እንግልትና ስቃይ ደርሶበታል። ወታደራዊ መንግሥት አብቅቶ ኢሕአዴግም ሲመጣ ነገሮች ለአያሌው መልካም አልሆኑም። ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ ከአዲሱ መንግሥት ተፋጠጠ። በተለይም ደግሞ ከፋፋይ ሥርዓቱ ለሃገር ወዳዱ ሙዚቀኛ የሚቀበለውም፤ የሚዋጥለትም ጉዳይ አልሆነለትም። እናም እንደተለመደው ተቃውሞውን በዜማ ለመግለፅ አልዘገየም። አዲሱ መንግሥት ስልጣን ከያዘ አንድ ዓመት ሳይሞላው ‹‹አንድ ናት ኢትዮጵያ›› የሚለውን ዜማውን ከሕዝብ ጆሮ አደረሰ። ቀጠለናም
‹‹አይ ጊዜ አይ ዘመን ተው አታተዛዝበን
ሥልጣን በዘር ሃገር ጋብቻም በጎሳ
ሆነና ነገሩ አንድነት ተረሳ
የአንድነቱን ጉዳይ ማን ሰጠና ዋጋ
መክነፍ ይዟል እንጂ ዘር ዘሩን ፍለጋ
የትላንት ለዛሬ ትምህርት ካልሆነ
ይበጀናል ያልነው ይሄም ከጨከነ
ሃጂም መጪውም ከተመሳጠረ
ፍትሕ ደህና ሰንብት ሕዝብ ተበደለ፤ ፍርድ ተጓደለ›› ሲል የጊዜውን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ጭምር ርዕይ ያሳየ ድንቅ ሙዚቃ አቀንቅኗል። ከሁለቱ ሙዚቃዎች መለቀቅ በኋላ በነበረው መንግሥት ለግድያ ይፈለግ ስለነበር እየተሳደደ መኖር ያዘ። ግን ደግሞ በዜማው መታገሉን አላቆመም፤ በ1991 ዓ.ም ‹‹በል በለው›› እና ‹‹ያንቺ ነገር›› የተባሉ ሌሎች ዜማዎችን ለቀቀ። በተለይ የአንቺን ነገር የምትለው ነጠላ ዜማ በቀጥታ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ይነካ ስለነበር በደህንነት ሰዎችና ባለስልጣኑ ዘንድ ቀንደኛ ጠላት ተደርጎ ተፈረጀ። በዚህም ሳያበቁ ግጥሙን ጽፈው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀረቡላቸው፤ እሳቸው ግን ‹‹ዲሞክራሲ ብለን ፈቅደንለታል፤ የእኔን ጭንቅላት እስካልነካ ድረስ መብቱ ነው፤ ተዉት›› የሚል ምላሽ ሰጧቸው። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ በውስጥ ታዋቂነት ‹‹ከንብረት ጀምሮ ሕይወት እስከማጣት ድረስ ስውር ግፍ ተፈፀብኝ›› ሲል በኃዘን የኋሊት ያስታውሳል።
ከእነዚህም መካከል ከሙዚቃ ቦታ ድረስ ሰዎችን በመላክ የ950 ሺ ብር የሙዚቃ መሣሪያ ለመግዛት እንደሚፈልጉ ገልፀውለት 250 ሺ ብር ቀብድ ሰጡት። እሱም መሣሪያውን ከውጭ አስመጥቶ በነገሩት መሠረት መሣሪያውን ከተረከቡ በኋላ ቀሪውን ገንዘብ በቼክ ይሰጡታል። ሆኖም ቼኩ ስርዝ ድልዝ ያለው በመሆኑ ባንክ እንደማይቀበለውና እንዲቀይሩለት ይነግራቸዋል። እነሱም አብሯቸው ታጠቅ ጦር ሰፈር ድረስ ተከትሏቸው እንዲመጣና ቼኩን እንደሚቀይሩለት ይነግሩታል። ‹‹የሚገርመው አብረን እንሂድ ሲሉኝ አዕምሮዬ እየነገረኝ፤ ልቤ እየፈራ መኪናዬን አስነስቼ ተከትያቸው ታጠቅ ጦር ሰፈር ድረስ ተከተልኳቸው፤ እነሱ ግን ‹‹አሁን መጣን›› ብለው አንድ ቦታ ላይ አስቀምጠውኝ ጠፉ፤ እኔም ከአሁን አሁን ይመጣሉ እያልኩ ለሰዓታት ጠበኳቸው፤ አመሻሽ ላይ ግን የዘብ አለቃው መጥቶ ምን እንደምፈልግ ጠየቀኝ፤ እኔም ሁኔታውን ሳስረዳው በጣም አዝኖ ሁሉም ከቢሮ እንደወጡ ፤ማንም በጊቢ ውስጥ አለመኖሩን አረዳኝ›› ሲል ነው በደህንነቱ ሰዎች የደረሰበትን ግፍ ዛሬ የተከሰተ ያህል ሲቃ በተሞላበት አንደበት ያጫወተን።
ግፍና በደሉ ግን በዚህ እንዳላበቃ የሚናገረው አርቲስት አያሌው የቀድሞ የጦር ጉዳተኞችን ለማቋቋም ከሌሎች አርቲስቶች ጋር በመሆን ‘ሰው ለሰው’ የተባለ ባንድ ያቋቁማል፤ የሙዚቃ ድግስ በማዘጋጀትም ለጉዳተኛ የሠራዊት አባላት ድጋፍ የሚውል ገንዘብ ማሰባሰብ እንደጀመሩ ይናገራል። አንድ ቀን ግን ለነበረው መንግሥት ቅርብ በሆኑ ሰዎች አዛዥነት እሱ በሌለበት የባንዱ አባላት የካቲት 11 የሕወሓትን የምስረታ በዓል ለማክበር በግዳጅ ሙዚቃ ለማቅረብ እየተዘጋጁ ያገኛቸዋል። የባንዱ አባላት ያለእሱ እውቅና ለመሄድ መዘጋጀታቸው ያበሳጨው አርቲስቱ በወቅቱ የነበሩ የተሐድሶ ኮሚሽነር የነበሩት ኮሚሽነር ሙሉጌታ ጋር ቅሬታውን አቀረበ፤ እነሱም ባልጠበቀው መልኩ በተለያዩ ወንጀሎች ከሰሱት። ኮሚሽነሩ ግን በእሱ ላይ የቀረበበትን ክስ ሳይቀበሉ፤ እሱ በሚሠራው ሥራ ጣልቃ መግባት እንደማይችሉ ቁርጣቸውን ይነግሯቸዋል። እናም በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ባንዱም ወደመቀሌ ሳይሄድ ይቀራል።
ያሰቡት ያልተሳካላቸው ባለስልጣናቱ ናዝሬት(አዳማ) ባንዱ በነበረው የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ ‹‹ሰላም ለኢትዮጵያ›› የተባለውን ዘፈኑን ማይክራፎኑን ጨብጦ እየዘፈነ ሳለ ሆን ተብሎ 350ሺ ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል በአንድ ጊዜ በመልቀቅ አዳራሹ በእሳት እንዲቀጣጠል ተደረገ። በብዙ ሺ ብር የተገዛው የሙዚቃ መሳሪያ በሙሉ ነደደ። ይሁንና እንደእድል ሆኖ ታላቁ ሙዚቀኛ ማይክራፎኑን ቶሎ መሬት በመጣሉ ምክንያት በኤሌክትሪኩ ሳይያዝ ቀረ፤ በከተማው ሕዝብ ትብብርም እሱም ሆነ መላው የባንዱ አባላት ቶሎ አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ በመደረጋቸው የከፋ ጉዳት ሳይደርስባቸው ከታሰበላቸው የሞት ሴራ ማምለጣቸውን ይናገራል።
ይሁንና ከኃላፊዎች በተፃፈ ደብዳቤ ከዚህ በኋላ በባንዱ ላይ ለሚደርስበት ጉዳት ኃላፊነቱን ራሱ እንዲወስድ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው። እናም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ባንዱ ፈረሰ፤ ለመላው የጦር ጉዳተኛ የተሰበሰበውንም ገንዘብ አዲግራት ይገኙ ለነበሩ የኢሕዴግ ሠራዊት አባላት ብቻ እንዲውል መደረጉን ያወሳል። ‹‹እውነት በመናገሬና ኢትዮጵያ በማለቴ ብቻ ገፉኝ፤ አደኸዩኝ፤ ደክሜ እንዳልደከምኩኝ ሆንኩኝ፤ በተረኛ ሁሉ የምደበደብ ሆንኩኝ› ሲልም ነው በደሉን ሃዘንና ቁጭት በተቀላቀለበት ስሜት የገለፀው። ይሁንና ያ ሁሉ አልፎ ዛሬም በሕይወት ቆይቶ በነበር ማውጋት በመቻሉ ፈጣሪውን ያመሰግናል።
ድምፃዊው ከሙዚቃ ሥራው ባሻገር ያለውን ሁሉ በማካፋል፤ መሬት የወደቁ እና ለልመና የተዳረጉ የቀድሞ ሠራዊት አባላትን ከማንሳት ጀምሮ ሙዚቃ ቤቱ አጠገቡ የሚለምኑ ሕፃናት ፤ ወጣቶችና አዛውንት ነዳያንን በመደገፍ ይታወቃል። በሕመምና በጡረታ የተገለሉ፤ ጧሪ ቀባሪ ያጡ በርካታ የኪነ-ጥበብ ሰዎች በተለይም የመሐል አራዳ ወጣቶች ማኅበር የተባለ ድርጅት በመክፈት ላልተገባ ሱስና ሌብነት የተዳረጉ ወጣቶችን በማሰባሰብና አቅፎ በመያዝ ፤ ከልመናና ካልተገባ ተግባር እንዲወጡ ይልቁንም ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ብርቱ ርብርብ አድርጓል። ይሁንና ይህም ቢሆን በነበሩት ባለስልጣናት ዘንድ ይህ በጎ ተግባሩ አልተወደደለትም።
አርቲስቱ ጫናውና ዱላው ሲበረታበትና የመኖር ሕልውናው ጨርሶ መሟጠጡን ሲረዳ የሚወዳትን ሃገሩን ጥሎ ወደ አሜሪካ ለመሰደድ ተገደደ። ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ የሃገርና የሕዝቡ ናፍቆት አላስችል ይለውና የኢትዮጵያ ሚሊኒየም በተከበረበት ዓመት ለጥየቃ ብሎ ወደ ሃገሩ ይመጣል። እዚህ ሲመጣ ግን ያላሰበው ሌላ አደጋ ገጠመው፤ ቂም ቋጥረው የነበሩ ባለስልጣናት ፓስፖርቱን ቀምተው ለሦስት ዓመታት ከሃገር እንዳይወጣ በማገዳቸው ምክንያት አሜሪካ የመኖሪያ ፍቃዱ ተቃጠለበት። ‹‹እግዚአብሔር ቸር ነው፤ ከሦስት ዓመታት ጥረት በኋላ ተመልሼ አሜሪካ መሄድ ቻልኩኝ ›› ሲል ያስታውሳል። በ15 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታው የራሱን ድርጅት ከፍቶ ከመሥራት ባለፈ አልፎ አልፎ በሚዘጋጁ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ላይ መሳተፉን አላቆመም ነበር። በተለይ ነጭ አባላት ባሉት አንድ የኢትዮጵያ ባንድ ጋር አብሮ በመሥራት ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል።
የ67 ዓመቱ አንጋፋ የጥበብ ሰው በሙዚቃ ሥራ አምስት አስርተ ዓመታት ውስጥ 27 ካሴቶችን እንዲሁም 27 ሙዚቃዎችን በሸክላ አሳትሟል። እሱ በመሠረተው ጥቁር አንበሳ ባንድ አማካኝነት ኤፍሬም ታምሩ፣ ጋሻው አዳል፣ ፍቃደ አጥላው፣ ታምራት ፈረንጅ ፣ አሰፋሽ አንዳርጌ፣ ተክሌ ተስፋእዝጊ፣ ውብሸት ፍስሐ የተባሉ ሙዚቀኞች እውቅና አግኝተዋል። ዜማና ግጥም ከሠራላቸው ሰዎች መካከልም በተለይ የጋሻው አዳል ሥራዎች በሙሉ የእሱ መሆናቸው ብዙዎችን የሚያስገርም ነው። በተጨማሪም ኤፍሬም ታምሩ ‹‹ገና ልጅ ነኝ ጋሜ እና ተጠራጠርሽ እንዴ?›› የሚሉትና፤ ለሒሩት በቀለ ‹‹ስሞት ብቻ አልቅሱ እና ሃሳብ እሽሩሩ›› የተባሉ ሥራዎችን አበርክቶለታል። ለሃገር አንድነት ብዙ ዋጋ የከፈለው ይህ የኪነ-ጥበብ ሰው በሙዚቃ ሕይወቱም ሆነ በሌሎች በጎ አድራጎት ሥራዎች ላበረከተው አስተዋፅኦ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ አስተዳደር ከፍተኛ እውቅና ተሰጥቶታል፤ በተወለደበት ወልዲያ ከተማም በስሙ መንገድ ተሰይሞለታል።
የመላው ኢትዮጵያውያንን ውለታና ፍቅር አንስቶ፤ አመስግኖ የማይጠግበው ይህ አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ሰው በነበሩ መንግሥታት በደል ቢፈፀምበትም ዛሬ የሕዝቡን ውለታ የሚመልስ ሥራ ለመሥራት ማቀዱንም አጫውቶናል። በተለይ ‹‹ክብር ለሰው›› በሚል ድርጅት በማቋቋም በተጨባጭ ችግረኛ የሆኑ ሰዎችን ለመደገፍ ዓላማ ሰንቋል። በተጨማሪም 34 የሚሆኑ የተሠሩ አዳዲስ ሙዚቃዎች እንዳሉት የሚናገረው ድምፃዊው፤ ከዚህም ባሻገር ሃገሪቱ በቅርቡ ከነበረው ጦርነት ተላቃ ወደ ሰላም መምጣቷን ተመርኩዙ ሌላ ነጠላ ዜማ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ነው የጠቆመው።
በጦርነት የወደሙ ከተሞችን ዳግም ለመገንባት በሚደረጉ ጥረቶች የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የሚገልፀው ድምፃዊ አያሌው ከሁሉ በላይ ችግሩ የከፋ በመሆኑ መንግሥትም ሆነ ሌሎች በጎ አድራጊዎች የነዋሪውን ሕይወት ለመታደግ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስቧል። የሠራውን ሥራ በሚመጥንና የልፋቱን ያህል ተገቢውን እውቅና እና ክብር ያላገኘው ይህ አንጋፋ አርቲስት ትውልዱ ዋጋ ከፍለው ይህችን ሃገር ያስረከቡትን ሰዎች ታሪክ ሊያውቅና ሊያከብር እንደሚገባም ተናግሯል። ሕዝቡም ከየመንና ከሶሪያ ልምድ ቀስሞ አንድነቱን እንዲያስጠብቅ፤ የሃገሩን የቀድሞ ገናና ዝና እንዲመልስ ነው አንጋፋው ድምፃዊ አያሌው መስፍን ጥሪ ያቀረበው።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም