ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 በፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉአላዊነትንና የግዛት አንድነትን ባስከበረ መልኩ ዕልባት አግኝቷል። የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ ርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመርና የአገሪቱን የድንበርና የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲከበር የማድረግ ዓላማ አለው።
የፕሪቶርያው ስምምነትን ተከትሎ በኬንያ ናይሮቢ ሁለት ተከታታይ ውይይቶች ተካሂደዋል። እነዚህ ውይይቶች በፕሪቶርያ የተካሄደውን የሰላም ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ ያስቻሉና መተማመንን ለመፍጠር የማዕዘን ድንጋይ ሆነው ያገለገሉ ናቸው። ለሁለት ጊዜያት ያህል የተካሄዱት የናይሮቢ ስምምነቶች መተማመንን የፈጠሩና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ ያጸኑ ናቸው። ስምምነቶቹ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችንና ሰብአዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ለማድረስ መሠረት ጥለዋል። ከስምምነቶቹ በኋላም በትግራይ፤ በአማራና አፋር ክልሎች ተቋርጠው የነበሩ የቴሌኮሙኒኬሽን፤ የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎቶች መልሰው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ አስችሏል።
የናይሮቢዎቹን ውይይቶች ተከትሎም በአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ የልዑካን ቡድን በመቀሌ ተገኝቶ የተቋረጡ አገልግሎቶች መልሰው በሚጀመሩባቸው ነጥቦች ዙሪያ ውይይት አድርጓል። ከውይይቱ ማግስት ጀምሮ መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የአየር በረራ እንዲጀመር ተደርጓል። ባንክ፤ ቴሌኮሙኒኬሽን፤ የሕክምና አገልግሎትና የመሳሰሉት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲቀርቡ አስችሏል።
ከሰሞኑ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የፌዴራል መንግሥቱና የሕወሓት የሰላም ተደራዳሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኘው ሃላላ ኬላ በተባለው ስፍራ ተገናኝተዋል። የሰላም ሂደቱ በአስተማማኝ መልኩ እየተከናወነ መሆኑም የፌዴራልና የሕወሓት የሰላም ተደራዳሪዎች በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ወደ ክልሉ የሚደረጉ በረራዎች እንዲጨምሩ፣ የባንክ አገልግሎት እንዲፋጠን እና ሌሎች የእርስ በርስ መተማመንን የሚያጎለብቱ እና የዜጎችን አኗኗር የሚያቀሉ አገልግሎቶች እንዲፋጠኑ መመሪያ ሰጥተዋል።
ሁለቱ አካላት እንዳረጋገጡት በተከታታይ የተካሄዱት የሰላም ስምምነቶች በሂደት መተማመንን እየፈጠሩ መጥተዋል። ጥላቻና ቁርሾንም ማለዘብ ችለዋል። ለዜጎች ሰብአዊና ቁሳዊ አገልግሎቶችን በስፋት ለማቅረብ አስችለዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በጦርነት የሚጎዱ ወገኖችን ሕይወት መታደግ ተችሏል፤ እንደአገርም ሰላምን ማስፈን አስችሏል።
በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃም የፕሪቶርያውን ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያ በሰፈነው ሰላም ምክንያት ሰብአዊ ዕርዳታዎች በስፋት ወደ አማራ፤ አፋርና ትግራይ ክልሎች መግባት ችለዋል። በአጠቃላይ ሰብአዊ ዕርዳታዎችን የጫኑ 3ሺ901 ተሳቢ መኪናዎች ወደ ትግራይ የገቡ ሲሆን 142ሺ 969 ምግብ ነክ ድጋፎች እንዲሁም 16ሺ 96 ሜትሪክ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ለተጎጂዎች ማቅረብ ተችሏል። 1ነጥብ 6 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅም ቀርቧል። በአጠቃላይም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከ4 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሰብአዊ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆኗል። የአማራና የአፋርን ሲጨምር ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከ8 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በአጠቃላይ ሰላም የዜጎች ዋስትና ማስጠበቂያ የአገር ካስማና ዋልታ መሆኑን ከፕሪቶርያው ስምምነት ጀምሮ ያሉ ሁነቶች ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በየጊዜው እየተካሄዱ ያሉ ስምምነቶች በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከማስቻላቸውም ባሻገር በጦርነቱ ምክንያት ላልቶ የነበረው መተማመንና አንድነትን ወደ ቀድሞ ቦታቸው መመለስ የሚያስችሉ ናቸው። ስለሆነም በፌዴራል መንግሥቱም ሆነ በሕወሓት በኩል የሚታየው ለሰላም ጸንቶ የመቆም አቋም አበረታች ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም