ሸማችነት ሰዎች በዘመናቸው የሚከተሉት፣ የሚከተላቸው የሕይወት ክስተት ነው። አንዳንዴም እንደ ጥላ በሉት። ስንሸሸው ሲከተለን፤ ስንከተለው ሲሸሸን ዓይነት ነገር ፤ በሕይወታችን የማይነጠለን ማለት እንችላለን። ሰው በዘመኑ፤ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ ይሻል። ይህንን የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለን አውቀናል። ግን ብላቴና ሳለን ቢያንስ ምግብና ልብስ፤ ሲርበንም ሲበርደንም እንደሚያስፈልገን ሳንማርም በደመነፍስ ተረድተናል። ሰው በደህናው ጊዜ ሸማች፤ በችግር ጊዜ ደግሞ ዘማች የሚሆንበት ጊዜ አለ። ጦርነት ሲኖር ሰው ሸመታውን አቁሞ ለአገሩ ይዘምታል። ሕይወቱንም እስከ መስጠት የደረሰ መስዋዕትነትን ይከፍላል።
በተመሳሳይም በችግርም ሳይሆን ደግሞ፤ ዘማችም ሸማች የሚሆንበት ጊዜው ብዙ ነው። በሌላ አነጋገር ዘማቾች ሁሉ ሸማቾች ናቸው። ሸማቾች ግን አልፎ አልፎ ዘማቾች ይሆናሉ። ወረራ ሲመጣ ደግሞ ሸማቾች ዘማቾች ሊሆኑ ይገደዳሉ። ወደው ፈቅደው ዘማች የሚሆኑ እንዳሉ ሁሉ በተፃራሪው ተገደውም ዘማች የሚሆኑ አሉ። ሸማች በተርታ ዘማች በገበታ ስንልም ሸማች ሰው በሕይወት መሥመር ውስጥ የሚያገኘው ሲሆን፤ ዘማች በገበታ ስንልም ደግሞ ሰው አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው አልያም የሚመርጠው ማለታችን መሆኑ ይሰመርበት።
ሕይወታችን በሙሉ በሸመታና በዘመቻ የተሞላ ነው። ኑሮ ተወደደ፤ የሸቀጥ ዋጋ ናረ፤ የብር ዋጋ ወደቀ የሚሉና መሰል ስሞታዎች ሰርክ የሚነሱት ሸማቾች ስለሆንን ነው። ዘመቻም የሕይወታችን አንዱ አካል ነው። የትምህርት ዘመቻ፤ የእናት አገር ጥሪ ዘመቻ፤ የጽዳት ዘመቻ፤ ወዘተ ሁልጊዜም ሲዘምቱብን የኖሩ ናቸው። ሕይወት እስካለ ድረስም ዘመቻ ይቀጥላል።
ሸማች የሚለውን ቃል የአማርኛ መዝገበ ቃላት ሲፈታው እህልን ለንግድ ሳይሆን ለምግብነት፤ የሚገዛ በላተኛ ይለዋል። በላተኛ ደግሞ አባወራ እማወራ ብቻ ሳይሆን ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው የሚኖሩ ላጤዎች፣ ኮረዳዎች፣ ባልቴቶች ጭምር ናቸው። እህል የማይሸምት ጎረምሳም ቢኖርም ፤ ከምግብ ቤት ምግብ በሳህን ነገር አልያም የታሸገ ገዝቶ ይበላል። የበሰለውን ምግብ ገዝቶ ሸመተ በላ ማለት ነው። ለመሸመት ደግሞ ከነጋዴ ጋር ግንኙነት ይኖራል። ነጋዴ በተራው ሸማች ሆኖ ቀለብ የሚገዛበትም ጊዜ አለ።
ሸመተ የሚለውን የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ሲፈታው ገዛ ገበየ (ብዙውን ጊዜ እህልን) እንዲሁም ያዘ ፣ አተረፈ ፤ ጥንቃቄ ባለማድረጉ በሽታ ሸመተ ይለዋል። እናም ቃሉ አዎንታዊም አሉታዊም ፍቺ አለው። በመሥራት ፤ በመሸመት ራስንና ቤተሰብን የወር በሉት የዓመት አስቤዛ እየገዙ ለማኖር የሚደረግ ጥረት አለ። ተማረ ሲባልም ዕውቀት ጨበጠ ፣ያዘ ወይም ሸመተ ይሆናል። ይህም አዎንታዊ ነው። በአሉታዊ ስንፈታው በሽታ ሸመተ የሚለው ቃል ይገልፀዋል። ሰው በዘመኑ በውጣ ውረድ ሕይወቱን ለማኖር ሲጥር መቼም ገበያ ሄዶ በገንዘብ በሽታን አይሸምትም። ሳያውቀው ሳያስበው በሽታ ከያዛቸው ሰዎች ጋር ፤ በጨዋታ፣ በሰላምታ በሉት በመኝታ ተገናኝቶ፤ ሊይዘው ይችላል። በዚህም በሽታ ሸመተ ይባላል። ድንገት በሽታ ያዘው እንጂ መቼም አስቦ አልሞ ከገበያ በሽታ ሸመተ አይባልም።
ሰዎች በአካል በብርና በምግባር እየጠነከሩ ሲሄዱ ሸማች ሊሆኑ ይገደዳሉ። ሸማች የሚለውን ቃል ከአባወራ እና እማወራዎች ጋር ብቻ የማያያዝ ልምድ አለ። ነገር ግን ከእናትና አባታቸው ርቀው የሚኖሩ የራሳቸው ገቢ ያላቸው ላጤዎች ባልቴቶች (ባል ፈቶች፣ ያረጡ ሴቶች) ሸማቾች ናቸው። ወዛደሩ ፣ወታደሩ፣ መምህሩ፣ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ፣ ባልቴቱ፣ መበለቱ ሸማች ነው። አርሶ አደሩ ደግሞ እያመረተ ምን ይሸምታል? የሚሉ ይኖራሉ፤ መቼም ከዘራውም ሆነ ከጎተራው አተር ፣ባቄላ ሸጦ ምስር፣ በቆሎ ሸምቶ የሚገባ ገበሬ አይጠፋም። ሰው ራቅ ያለ ቦታ ለትምህርት ስት/ሲ/ሄድ በተለምዶ እ/ሱ/ሷ ኮ ዕውቀት ለመሸመት ሄደ/ች ዓይነት ንግግሮች እንሰማለን። መጽሐፍትን በተለያየ ጊዜ የሚሸምትም ዕውቀትን የሚሸምት ነው ብንል የሚቃወመን አይኖርም።
ከመንግሥት ጀምሮ በየተዋረዱ ያሉ ኃላፊዎች ከአለቃ እስከ ምንዝር ሁሉ ሸማቾች ናቸው። ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው የወር አስቤዛ መግዛታቸው፣ ማስገዛታቸው የማይቀር ነው። የወር አስቤዛ ካልበዛ ያላቸው በአንዴ በጅምላ የመንፈቅም ሆነ የዓመት አስቤዛ ይገዛሉ፤ የሌላቸው ደግሞ በችርቻሮ የየዕለቱን ሳምንቱን ይሸምታሉ።
መንግሥትም ሸማች ሆኖ ዜጋውን ይቀልባል፣ ይመግባል። ሰላሙንና ፀጥታውን ይጠብቃል። ልማቱን ያሳልጣል። ቢያንስ በቀጥታ እህል ባይሸምትም በተዘዋዋሪ ለቀጠራቸው ለፀጥታ ተቋማት ፣ ለጤና ማዕከላት ሠራተኞች፣ ለመሠረተ ልማት ድርጅት ለሲቪል ሰርቫንት ሁሉ ደመወዝ ሲከፍል ሸማች ሆነ ማለት ነው። ሰላምና ፀጥታ በማስከበር፤ ዜጎችን በማስገበር፤ ሰዎች ዘርተው እንዲቅሙ፣ ወልደው እንዲስሙ ያደርጋል። ፀጥታን ሲያስከብርም በዘማች ወታደሩ፣ ጦሩና ፖሊሱ ለዜጎቹ ሰላምን ሸማች ሆነ ማለት ነው። ይህንን ስናስበው መንግሥት በአንድ ጊዜ ለዜጎቹ ዘማችም ሸማችም የሚሆንበት መንገድ ሰፊ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።
መከላከያው እና ፖሊስ የሕዝብና የአገርን ሰላምና ደህንነት የሚጠብቁት፣ የሚዋደቁት (ዘማች የሚሆኑት) መንግሥት ስለሚቀልባቸው (ስለሚሸምትላቸው) ነው። ደመወዛቸውንም ሲከፍላቸውም በተዘዋዋሪ እየሸመተላቸው ነው። በአዲስ አበባ ያለውን የትምህርት ምገባ ስናይም መንግሥት እየሸመተ ለተማሪዎች የሚመግበው ነው። ተማሪውም ሲማር ዕውቀት ሸማች ይሆናል ፤መምህሩም ራቅ ብሎ ወገኖቹን ለማስተማር ሲጓዝ ዘማች ይሆናል። መቼም መምህሩ ዕውቀት ሳይሸምት ዘማች ሊሆን አይችልም። አስቀድሞ ከዕውቀት አባቶቹ ተምሮ ዕውቀት ሸማች ሆኖ ብቁ ሲሆን ድንቁርናን የሚያጠፋ ዕውቀትን የሚያስፋፋ ዘማች ይሆናል። መምህር ሕዝብን ለማንቃት፣ ለማብቃት የሚተጋ ነው። ስለዚህ ትምህርት ቤት ዘማችና ሸማች ዕውቀት የሚገበያዩበት አንድ ዐውድ ነው ማለት እንችላለን።
ዘማች ፤ ዘመቻ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ያለ ፤ ወይም የዘመተ ሰው ነው። በግእዝ ዘሚት፣ በትግርኛ ዘማቲ ይባላል። በአፋን ኦሮሞ ዘማች Duulaa ፤ ዘመቻ ደግሞ Dula ይባላል። ዘማች አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ትርጓሜ አለው። በአሉታዊው አገሩን ዳር ድንበሩን ለማፈራረስ የሚተጋ ‹‹ የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ ›› የሆነ ዜጋ፣ አገሩን ለማፍረስ ‹‹የሚተጋ›› ባንዳ ዘማች ነው። ማለትም ለባዕድ አድሮ ባንዳ ሆኖ እናት አገሩን የሚዋጋ ጭንጋፍ ዜጋ ማለት ነው።
ብሔራዊ የውትድርና ዘመቻ ዜጎች ዕድሜያቸው ከፈቀደ የግድ የሚዘምቱበት ነው። የደርግ መንግሥትን መሃይምነት የማጥፋት ዘመቻንም እናስበው። ሰዎች ማንበብና መፃፍ እንዲችሉ የተደረገ ዘመቻ ነበር። ዘማች ለመሆን ሀሞተ ኮስታራ ማለትም ጀግና ቆፍጣና ሰው ይመረጣል። ሀሞተ ቢስ ዘማች ሆነ ማለት በጠላት ድል ሆነ እጅ ሰጠ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ‹‹ሳያውቅ የተረተ፣ ሳይዘራ ያመረተ›› እንደሚባለው ብሂል የተገላቢጦሽ ነገር ተፈጸመ ማለት ነው። ነፍስ ሔር ጥላሁን ገሰሰ በአንድ ሙዚቃው ስለ ዘማች ሲያቀነቅን በዘፈኑ እንዲህ ብሎ ነበር።
‹‹…ዘማች ነኝ ቆራጥ ነኝ ለሀገሬ
አልሻም ማየት ተደፍራ ድንበሬ
አልሳሳም ጭራሽ ምንም በሕይወቴ
ለእናቴ ሲፈልጉ ላካላቴ
ይኸው ልሰዋ ለውዲቷ እናቴ …››
በአዎንታዊው ስናየው ዘማች የአገር ዳር ድንበር የሚያስከብር፣ ዜጎቹን ከወራሪ ጠላት የሚጠብቅ ፤ ለጠላት ባዳና ለባንዳ እጅ ከመስጠት አንገት መስጠት የሚሻ ፤ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የሚዋደቅ ዜጋውን የሚታደግ ወታደር ዘማች ነው። ፖሊሱና ወታደሩ የሰላም ዘማች፣ ሸማች ነው። ዘማች ሆኖ ሰላም ሸማች ወይም ሰላምን የሚያመጣ የሚሸምት ማለታችን ነው። ሠራዊቱ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያካሄደው ዘመቻ ዜጎችን ከጥፋት፤ የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን ንብረትን ከውድመት ለማዳን ነው። እናም ዘማቹ የዘመተው ሰላምንና ልማትን ለመሸመት ነው። በዚህም ዘማቾቹ ሰላምን በመስዋዕት በመሸመት፤ ወደ ሸማቾች ጎራ ሊቀላቀሉ ይገደዳሉ። ዘማች ለአገሩ ለሕዝብና ለራሱ ሰላም ሸማች ሆነ ማለት ነው።
ተማሪን (ዕውቀት የሚሸመትን) ለመማር የሚዘምት ልንለው እንችላለን። ለትምህርት ሲሄድ ዘማች ሆኖ ተምሮ ሲመለስ ደግሞ ሸማች ይሆናል። በሚያገኘው ደመወዝ ለእራሱም ለቤተሰቡም ያሻውን ይገዛል። ስለዚህ ተማሪ ዘማችም፣ ሸማችም ሆነ ማለት ነው። መምህሩም ዕውቀት በማስፋፋት የሚሳተፍ ዘማች ነው። መምህር ቀን እየሠራ ሰርክ እየተማረ ራሱን ለማሻሻል የሚጥር ከሆነ የዕውቀት ሸማች ነው። ለቤተሰቡ ቀለብ መሸመቱ ግድ ነው። እናም ዘማችም ሸማችም ይሆናል። ክፉ ወረርሽኝ ቢከሰት ሀኪም በሽታውን ለማጥፋት (ሰዎችን ለመከተብ ፣ለማከም) ይዘምታል። ገበሬውም መሬቱን ሲያረሰርስ፣ እህሉን ሲዘራ፤ ከብቱን ሲያረባ የልማት ዘማች ነው። ራሱንም ሸማቹንም ለመመገብ ለመቀለብ የሚታገል።
ሀኪሞችም ወይም የሕክምና ባለሙያዎችም ዘማቾች ናቸው። እንደ ኮረና ዓይነት የበሽታ ወረርሽኝ ቢመጣ ብሔራዊ የሕክምና ዘመቻ በመንግሥት ታውጆ ዘመቻ ይደረጋል። ዘመቻው ዜጋውን ከበሽታ ለመታደግ ይሆናል። በየሕክምና ተቋማቱ ሆስፒታልም ሆነ ጤና ጣቢያ የሚታከሙ ሰዎች የጤና ሸማች ይሆናሉ። ከላይ እንደገለጽነው ሐኪሞቹ ደግሞ ዜጋውን ከበሽታ ከወረርሽኝ ለመታደግ ዘማች ይሆናሉ። ወታደሩ፣ መምህሩ፤ ሀኪሙ እና ጋዜጠኛ ዘማች ሲሆኑ በቅደም ተከተል እንደየሥራ ድርሻቸው ወይም ተልዕኮዋቸው ሰላም ለማስከበር ፤ዕውቀት ለማስፋፋት እና ድንቁርና ለማጥፋት እንዲሁም በሽታን ለማጥፋት እና መረጃን ለመስጠት ዘማች ሆኑ ማለታችን ነው። ጋዜጠኛ መረጃ ለመሰብሰብ ወደ መስክ ሲወጣ፣ ባለሥልጣን ቢሮ ሲመጣ መረጃ ለመሰብሰብ ዘማች እየሆነ ነው። መረጃውን ከጋዜጣ ከሬዲዮ ወዘተ የሚገኘው ሰው ደግሞ መረጃ ሲያነብ ሲያዳምጥ ሸማች ሆኖ ነው።
የዛሬ መቶ ዓመት አካባቢ የህዳር በሽታ ተከስቶ በአዲስ አበባ ከተማ ብዙ ሰዎች ሞተው ነበር። በየዓመቱም ህዳር 12 ሰዉ አካባቢውን እያፀዳ ቆሻሻው ማቃጠል ጀመረ። በዚህም ህዳር ሲታጠን ተባለ። ራሱን ችሎ የጽዳት ዘመቻ ሆነ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተጠቀሰው ቀን በአዲስ አበባ በየዓመቱ ቆሻሻ ተጠርጎ የማቃጠል ልምድ እንደነበር ይታወሳል። ከላይ እንደገለጽነው የዘመቻ ዓይነቱ ብዙ ነው። በደርግ ዘመን የነበረው ዕድገት በኅብረት ፣ ብሔራዊ የውትድርና ፣ የመሠረተ ትምህርት ወይም ማይምነትን የማጥፋት ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስን የመከላከል ዘመቻዎች፤ በኢህአዴግ መንግሥት የነበረው ድህነትን የማጥፋት ዘመቻ (አንዳንድ የግል በጋዜጦች በወቅቱ ድህነትን የማስፋፋት ዘመቻ እያሉ ሲያፌዙበት አስታውሳለሁ) ፣ በዘመናችን ያየነው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ፣ እንቦጭንና በጥባጭን የማጥፋት ዘመቻ ይጠቀሳሉ። በቅርቡ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም በጥናት ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ለመውሰድ መታሰቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መነገሩ ደግሞ ሲተገበር ‹‹ሙስናን የማጥፋት ዘመቻ ›› ልንለው እንችላለን።
ዘማች መስዋዕትነት እየከፈለ ጠላትን እየተከላከለ ሰላምንና ደህንነትን ይሸምታል። ሸማች ደግሞ እህልን ከገበሬው ከነጋዴው እየሸመተ ቤተሰቡን እየመገበ ያኖራል። ዘማቹም ቤተሰቦቹን የሚመግበው ከነጋዴው ሲሸምት ነው። ሸማቹ ገበያ የሚወጣው ዘማቹ የአገር ሰላምና ደህንነት ሲሸምት ነው። ዜጋው ሸማች የሚሆነው፤ አገር ሰላም ብሎ ተረጋግቶ ቤቱ የሚገባውም፣ የሚያገባው ሆነ የሚመገበው፣ የሚጽናናውም ሆነ የሚዝናናው ሰላምና ደህንነቱ ሲኖር ነው።እናም አገርን ሸማችና ዘማች ዋልታና ማገር ሆነው የሚያቆዩ ናቸው። ስለዚህ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ጥሩ ዘማችና መልካም ሸማች ያስፈልጋታል። በሌላ አነጋገር ሁላችንም አንድ ጊዜ ሸማች በሌላ ጊዜ ዘማች ነንና በየተሰማራንበት መስክ ለአገራችን ጥሩነ ዘማችና ሸማች ልንሆን ይገባል ።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም