ለሰው ልጆች ትልቅ የሕይወት ምዕራፍ ከሆኑ ሁነቶች መካከል አንዱና ቀዳሚው ዘጠኝ ወራትን አርግዞ ልጅን ያህል በረከት ማግኘት ነው። ይህንን በረከት ለማየት ግን ቤተሰብ በተለይም ደግሞ እናት የምትከፍለው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚገለጽም አይደለም። ዘጠኙን የእርግዝና ወራቶቿን ለእሷ ብቻ ሳይሆን በሆዷ ውስጥ ላለው ሕጻን ጭምር ተመግባ፣ ከጉዳት ራሷንም ጽንሱንም ጠብቃ ፣ሕመሙን ድካሙን ችላ ብቻ ብዙ ብዙ ነገሮችን አሳልፋ ቀኗ ደርሶ ከሕመሞች ሁሉ በላይ ከባድ የሆነውን የምጥ ሕመምን ታግሳ ልጇን በሰላም ወደዚህች ምድር ታመጣለች።
ዛሬ ይህንን ለማለት ያነሳሳን ነገር የወይዘሮ ዘቢባ መሐመድ አሳዛኝ አጋጣሚ ነው። ወይዘሮ ዘቢባ ለእርግዝናም ሆነ ልጅ ወልዶ ለማሳደግ አዲስ አይደሉም። ሦስት ልጆችን በሰላም ወልደው አሳድገዋል። ያን ያህል ያማረ የሰመረ ኑሮን ይኖራሉ ባይባልም እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ያገኙትን ሠርተው ቤት ኪራይ ከፍለው ልጆቻቸውን አብልተው ያሳድሩም ነበር። የእግዚአብሔር በረከት ከእሳቸው ጋር ነበርና አራተኛ ልጃቸውን በድንገት አረገዙ። በዚህ እርግዝና እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ቅሬታ አልተሰማቸውም፤ የአላህ ስጦታ ነው ብለው በጸጋና በደስታ ነው የተቀበሉት።
ወይዘሮ ዘቢባ የአራተኛ ልጃቸው እርግዝና ከቀደሙት እርግዝናዎቻቸው ምንም የተለየ ነገር አላዩበትም፤ የሕክምን ክትትላቸውንም በአግባቡ ጊዜውን ጠብቀው ሲያደርጉም ነበር። ቀናቶች እየጨመሩ ወራት እየተቆጠረ የወይዘሮ ዘቢባ እርግዝናም እየገፋ ሄደ፤ አሁን ቀናቸው ደርሷል የውሸት የሚመስሉ ምጦችም መጣ ሄደት ይሉባቸዋል።
አንዱን ቀን ጠዋት ግን ከወትሮው የተለየ ሕመም ተሰማቸው በልምዳቸው ሄደው ሲያስቡትም ምጥ መሆኑን ተረድተዋል ፤ ስለዚህ ቀጥታ ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለባቸውና ጊዜ ሳያጠፉ ያስፈልጉኛል ያሏቸውን ነገሮች ሰባስበው ጉዟቸውን ሲከታተሉበት ወደነበረው ጤና ጣቢያ አደረጉ።
“……እኔ የሚሰማኝ ሕመም የምጥ መሆኑን በእርግጠኝነት አውቄዋለሁ፤ ነገር ግን የተቀበለችኝ የጤና ባለሙያ ምጥ እንዳልሆነና ቤቴ እንድሄድ ነገረችኝ፤ ብለምናትም አልሰማችኝም፤ እኔ ግን በሁኔታው እርግጠኛ ስለነበርኩ ወደቤቴ ከመሄዴ ይልቅ እዛው መቆየትን መረጥኩ” በማለት ይናገራሉ።
ወይዘሮ ዘቢባ እንዳሰቡትም ሕመማቸው ምጥ ነበር ፤ከሰዓታት ቆይታ በኋላ አፋፋማቸው እሳቸውም የድረሱልኝ እሪታቸውን አቀለጡት ቆይ ቤትሽ ሂጂ ያለቻቸው ነርስም በጥድፊያ መጥታ ወደማዋለጃው አስገባቻቸው። ከዛ በኋላ ወይዘሮ ዘቢባ የሆነውን ለማስታወስ ይከብዳቸዋል። ምኑን ልንገርሽ ብለው አይናቸው በእንባ ይሞላል። ልጁ ፋፍቶ ስለነበር ሲወለድ ወይዘሮ ዘቢባን በጣም ነው የጎዳቸው፤ ማህጸናቸው እስከሚወጣ ድረስ ታመሙ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ በጣም ብዙ ደም ፈሰሳቸው እነዚህ ሁሉ ተዳምረው ወይዘሮ ዘቢባ የወለዱት ልጅ ቀይ ይሁን ጥቁር ወንድ ይሁን ሴት ሳያዩት ራሳቸውን ሳቱ።
አሳዛኟ እናት ከቀናት በኋላ ሲነቁ ራሳቸውን ያገኙት በሌላ ሆስፒታል አልጋ ላይ ነበር። በርካታ ደም ስለፈሰሳቸው እሱን የሚተካ ሕክምና ተደረገላቸው ማህጸናቸውም በመውጣቱ ምክንያት ቀዶ ጥገና መሠራት ነበረባቸውና እሱንም ተሰሩ። ብቻ እንዲህ እንዲህ እያሉ የወለዱትን ልጅ ሳያዩ ሁለት ወራት ተቆጠሩ።
“ልጄ የታለ”? ብለው ሲጠይቁ እሱም ባጋጠመው የመታፈን ችግር ምክንያት ሕክምና እያገኘ እንደሆነ ተነገራቸው።አሁን ወይዘሮ ዘቢባ የራሳቸውን ሕመም ትተው ስለ ልጃቸው መጨነቅ ጀመሩ። አምጡልኝና ልየው ጡቴን ልስጠው ቢሉም ቆይ አንቺ አገግሚ በሚል የሚሰማቸው አላገኙም።
ሁለት ወራቱን በዚህ መልኩ ካሳለፉ በኋላ ወደ ጤንነታቸው በመመለሳቸው ልጃቸውን እንዲያገኙ ሆኑ፤ ልጁን ሲያገኙት አዘኑ፤ አለቀሱ ፤አነቡ ።በአፍንጫው በኩል በተተከለለት ቱቦ መሳይ ነገር ነበር ወተትና መድኃኒት የሚሰጠው። እናም ኅዘናቸው ልባቸውን ቢሰብረውም እኔ እናቱ ሳላቅፈው ይድንልኛል በሚል ተስፋ ልጃቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው ሄዱ። ለሁለት ወራት ከተለዩቸው ልጆቻቸውም ጋር ተቀላቀሉ።አዲሱ እንግዳ ወንድማቸውም ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ባይሆንም ወንድም ይሆናቸው ዘንድ ቤተሰቡን ተቀላቀለ፤ እህት ወንድሞቹም አዩት።
ወይዘሮ ዘቢባ ለልጄ እንደዚህ ለመሆን የበቃው ምጤ መጣ ብዬ ወደ ጤና ተቋም ስሄድ ያገኘሁት ፈጣን መስተንግዶ አለመኖሩ ነው።ወዲያው አይተውኝ አስፈላጊውን እርዳታ ቢያደርጉልኝ ኖሮ እኔም ሆንኩ ልጄ እዚህ ፈተና ውስጥ አንገባም ነበር ይላሉ።
ወይዘሮ ዘቢባ ልጃቸው አሁን ዓመት ከስምንት ወሩ ቢሆንም እንደ እኩዮቹ አይጫወትም፣ አይሮጥም፣ ምግብ በሥርዓት አይበላም፣ አይናገርም ከሁሉም በላይ ደግሞ እናቱን እንኳን ለይቶ አያውቅም፣ አንገቱን ቀና ማድረግ ያቅተዋል። ይህ ሁኔታው ደግሞ እናት ለሆኑት ወይዘሮ ዘቢባ አይደለም ላዩት ሁሉ የሚያሳዝን ልብ የሚሰብር ነገር ነው።
አሁን ወይዘሮ ዘቢባ ጠዋት ማታ ሀሳብ ትካዜ ልምዳቸው ሆኗል። ሁሌም ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት የነበረውን ሕይወት በትዝታ ያስባሉ። እንደዛሬው ሳይሆን ከሦስት ልጆቻቸውና ከባለቤቷ ጋር ያገኙትን ሠርተው በሰላም ይኖሩ ነበር። ‹‹አይዞሽ፣ አለሁሽ›› የሚላቸውም አላስፈለጋቸውም ነበር።
ዛሬ ወይዘሮ ዘቢባ መሐመድ እንደልባቸው ወጥተው ወርደው ሠርተው ልጆቻቸውን ማብላት ቤታቸውን መደጎም ተስኗቸዋል። ሁሉም እንዳለፈው ክረምት ተሰናብተዋቸው ሄደዋል። ወይዘሮ ዘቢባ የወለዱትን ልጅ ሲያዩት ውስጣቸው አብዝቶ ያዝናል። የነበረው እንዳልነበረ፣መሆኑን እያሰቡ ይተክዛሉ፣ያዝናሉ። የዛሬን አያድርገውና ከባለቤታቸው ጋር በነበሩበት ወቅት ቢለፉም እንኳን እራሳቸውንም ልጆቻቸውንም ማስተዳደር ይችሉ ነበር። ዛሬ ግን በልጃቸው ምክንያት እጅና እግራቸው ተሳስሯል።
እናትና ልጅ
ወይዘሮ ዘቢባ ብዙ ያቀዱበት ሕፃን አቡበከር ኑረዲንም እንደ እህት ወንድሞቹ ይሆንልኛል፤ በጥሩ ሁኔታ አሳድገዋለሁ ያሉት ልጃቸው በጠበቁት ልክ አልሆነላቸውም። ቢከፋቸው፣ቢቸግራቸውም የመጣውን መቻል እንዳለባቸው አውቀዋል። ጠዋት ማታ ለእሱ መኖር ይፈልጋሉ ፣እንደ እናት ስለጤናው፣ ስለዕድገቱ ያስባሉ። ዛሬ ላይ ዓመት ከስምንት ወር ሆኖታል፤ ቤት ኪራዩ፣ የእለት ወጪው፣ የሕጻኑ ሕክምና የዳይፐር እንዲሁም የወተት ወጪውን መሸከም ከብዷቸዋል።ይህ የሆነው ደግሞ ሕጻን አቡበከር እንደ እድሜ እኩዮቹ መሆን ባለመቻሉ ነው። ሌሎቹን ባሳደጉበት መንገድ ለሚይዝላቸው ሰው ሰጥተው አልያም አዝለው ሥራ መሥራት አለመቻላቸው ያመጣው ጣጣ ነው።
አቡበከር ከጡጦ ሌላ ምንም አይመገብም። ራሱን ችሉ አይቆምም። እንቅልፍ በሥርዓቱ አይተኛም፣ አይንቀሳቀስም፣ አያወራም፣ እናቱንም አያውቅም። ይህ ደግሞ ለወይዘሮ ዘቢባ ፈታኝ የሕይወት ምዕራፍ ሆኖባቸዋል ።
ወይዘሮ ዘቢባ ኑሮን ለመግፋት የፋብሪካ ሥራ ላይ ይውሉ ነበር። ዛሬ እሱን ጥሎ መሄድ አይቻልም። ባለቤታቸው ደግሞ ብቻውን ተሯሩጠው ሠርተው የሚያመጡት ገንዘብ እሷቸውን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ የማስተዳደር አቅም የለውም።አቡበከርን ጨምሮ ሌሎቹም ልጆቿ ከፍ ሲሉ የሚያስፈልጋቸው ነገር ብዙ ነው። አሁንም ቢሆን በዕድሜያቸው የሚያሻቸውን ማግኘት አለባቸው፣ እናት ናቸውና ከእሳቸው ይልቅ ልጆቻቸውን ያስቀድማሉ፣ እየራባቸው የእጃቸውን ለእነሱ ያጎርሳሉ።
አሁን ወይዘሮ ዘቢባ ልጁ እያደገ ቢሆንም ጭንቅላቱን መሸከም አይችልም። እናት ዘቢባ ልጃቸውን ይዘው ያልሄዱበት ሆስፒታል የለም፤ ሁሉም የሚሏቸው ልጅሽ የነርቭ ችግር አጋጥሞታል፤ በአእምሮው ክፍል ላይም ጠባሳ ይታያል ነው። ይህንን ሁኔታ አስተካክላለሁ ብለው በተለይም ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በጣም ተመላልሰዋል፤ አሁን ግን ከአቅማችን በላይ ነው በማለታቸው የሰው እርጥባን እየለመኑ ልጁን በግል ሆስፒታል ለማሳየት እየሞከሩ ነው። ግን ሁሉም ነገር ከአቅማቸው በላይ ሆኗል።
ኑሮ ከባድ ነው። ጎጆ ጣጣው ብዙ ነው ፣ ሕመምተኛ ልጅን መያዝ ደግሞ ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ ዋጋን የሚያስከፍል ነው ፤ ይፈትናል። ወይዘሮ ዘቢባ በዚህ እውነታ እያለፉ ነው። ሕመምተኛ ልጃቸውን ጠዋት ይዘው ወጥተው በየሆስፒታሉ ሲንከራተቱ ምንም ጠብ ያለ መፍትሔን ሳያገኙ የማታ ማታ ቤታቸው ይመለሳሉ።
ወይዘሮ ዘቢባ ይናገራሉ
በእርግዝና ጊዜዬ አራት አምስት ጊዜ አልትራሳውንድ ተነስቼ ምንም ችግር የለበትም ተብዬ ነበር። ነገር ግን በወሊድ ወቅት የመታፈን አደጋ አጋጠመው። እኔም ወልጄ ባጋጠመኝ ከፍተኛ የደም መፍሰስና የማህጸን መውጣት ምክንያት ለሁለት ወራት ያህል በሌላ ሆስፒታል እርዳታ እየተደረገልኝ ስለነበር ልጄ ቀይ ይሁን ጥቁር ጤናማ ይሁን አይሁን አላውቅም ነበር።
ሁለቱን ወራቶች በአፍንጫው በኩል ከሚሰጠው ጉልኮስና ወተት በቀር ጡት አልጠባም።እቤት ከመጣሁ በኋላ እንደምንም ብዬ ጡጦ አለማመድኩት። አሁን ዓመት ከስምንት ወሩ ቢሆንም ከጡጦ በቀር የሚታኘክ ምንም ነገር አይበላም።
አሁን ዶክተሮቹ እያሉኝ ያለው ነገር ልቤን እየሰበረው ነው።አብዛኞቹ ምንም ተስፋ እንደሌለው ይነግሩኛል፤ እኔ ግን አላህ አለምክንያት አልሰጠኝምና የከፈልኩትን ዋጋ ከፍዬ ልጄን አድናለሁ ባይ ነኝ። ዛሬ ላይ ቀን ጨልሞብኛል ልጄ እኔን እናቱን እንኳን አያውቀኝም።ይህ ደግሞ እንደ እናት ቀን ከሌሊት ያስለቅሰኛል።ድህነቴን እንድጠላ ያደርገኛል።ገንዘብ ኖሮኝ ቢሆን ልጄን የትም ገብቼ አድነው ነበር እላለሁ። አሁንም ግን ተስፋ አልቆርጥም ልጄን የትም ገብቼ አድነዋለሁ።ደጋግ ኢትዮጵያውያንም ያግዙኛል በዚህ ምንም ጥርጣሬ የለኝም።
የኑሮ ጫና በቤተሰቡ ላይ
ወይዘሮ ዘቢባ ይቀጥላሉ። ኑሮን እንዴት እንደምገልጸው ራሱ አላውቅም በጣም ከባድ ነው። እሱን ከመውለዴ በፊት ፋብሪካ እየሠራሁ ልጆቼን አሳድግ ነበር። አሁን ሥራ ትቻለሁ። እንዲሁ አለን ማለቱ ይሻል ይሆነል እንጂ ኑሮ በሽተኛ ልጅ ይዞ ዳይፐር ወተት በእኛ አቅም እየገዛን መኖር በጣም ከባድ ነው። ለጥያቄም የሚበቃ አይደለም።
እኔ ባልበላ፤ ባልጠጣ ምንም ችግር የለውም። የእሱን ፍጆታ እንኳን የሚሸፍንልኝ ወገን ባገኝ ሌሎቹ ልጆች ጤነኛ ናቸው ያገኙትን በልተው ካጡም ጦማቸውን ያድራሉ። የእነሱ አያስጨንቅም የእሱን ወተትና ዳይፐር ብቻ ነው የምፈልገው።
ሕክምናውን በተመለከተ 3 መቶ ሺ ብር ይጠይቃል። ይህም በእኔ አቅም የሚሆን ስላልሆነ የደጋግ ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ እየጠበኩ ነው።በማለት ነገን በተስፋ እየጠበቁ መሆኑን ይናገራሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም