ለፍቶ አዳሪዋ ወጣት ሰብለ
ወጣትነት ውበት፤ ወጣትነት ተስፋ፤ ወጣትነት ጉጉት ነው ይሉት ነገር በግልፅ የሚታይባት ሰብለ ንጉሴ ፈጣን፤ ተጫዋች አይነት ሴት ናት። በሥራዋ ታታሪ የሆነችው ወጣት ማልዳ ወጥታ እስከ ምሽት ስትሠራ ትቆያለች። ኑሮን በወጣትነት ጉልበት እየታገለች ለማሸነፍ የምትታትረው ወጣት ውሃ አጣጯንም ካገኘች በኋላ የነገ ኑሩዋን በፀና መሰረት ላይ ማስቀመጠን ግቧ አድርጋ በሴቶች ፀጉር ቤት ስራዋ ላይ ተግታ ስትሠራ ትውላለች።
የፍቅር አጋሯ ዳግማዊ አራጋው ከንጋት እስከ ሌሊት ድረስ በስራ ላይ መቆየቷ ለሱ ጊዜ ለመከልከል እየመሰለው ብዙም ደስታ አይታይበትም ነበር። ሁልጊዜ “ለምን በጊዜ አትገቢም?” በሚል መነሻ ሲጨቃጨቁ ይውሉ ነበር። ቀናት ቀናትን እየወለዱ ትኩረት ተነፈኩ የሚለው የዳግማዊ ንትርክ እየቀጠለ ሄደ።
ፀቡ ከንትርክ አልፎ ለዱላ መጋበዝን ማስከተል መጀመሩ ሰብለን ቢያሳስባትም ጨክኖ ጉዳት ያደርስብኛል የሚል ሃሳብ አልነበራትም። እንደ አመሏ በስራ ሰትታትር ቆይታ ቤቷ ስትደርስ በኩርፊያ የሚቀበላትን የፍቅር ጓደኛዋን አቅፋ አባብላ የሚያስደስተውን አድርጋ ወደ አልጋዋ ትሄዳለች። በስራ ስትባዝን ስለምትውል እንቅልፍ የሚወስዳት ጎኗ አልጋ እንደነካ ነበር ።
ዳግማዊ ግን በተቃራኒው የሷ ያለ ሃሳብ መተኛት እያናደደው ለእሱ ትኩረት አለመስጠቷ ከስራ ብዛት ሳይሆን ከፍቅር ማጣት እየመሰለው ውስጡ በክፋት ሃሳብ እየታመሰ ሳይተኛ ያነጋ ነበር። ታህሳስ 30/2014 ዓ.ም ላይ ግን ጭንቅላቱን የሞላው ያለመፈለግ ስሜት ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው…
ፍቅርና ስጋት እንቅልፍ የነሳው …
ከልጅነቱ ጀምሮ ያለመፈለግ ስሜት ሲያሰቃየው እንደኖረ ወዳጆቹ ይናገራሉ። ሁልጊዜ “ማንም አይወደኝም” የሚል ቃል ከአፉ አይለየውም። “ እኔ ማንም የሌለኝ ብቸኛ ሰው ነኝ…” የሚለውም ንግግር ሌላው የዳግማዊ መለያው ነው። በዙሪያው በርካታ ሰዎች ቢኖሩም ከሱ የሚፈልጉትን ለማግኘት እንጂ ወዳጅነቱን ብለው የመጡ አይመስለውም።
ይህ አስተሳሰቡ ደግሞ ዳግማዊ አራጋው ብቸኛ እንዲሆን አድርጎታል። ጓደኞች ቢያገኝም ይህ የጥርጣሬ መንፈሱ መልሶ እንዲያጣቸው አድርጎታል። ከእለታት አንድ ቀን ነው፤ አንድ ከሴቶች ፀጉር ቤት ጎን የሚገኝ የጀበና ቡና መሸጫ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ አንድ አይን የምትገባ ወጣት እየሳቀችና እየቀላለደች ቡና ስትጠጣ ይመለከታታል።
በወቅቱ በፈገግታ ሲያያት ቆይቶ ከቡና መጠጫው ቢወጣም ከልቡ ግን ሊያወጣት አልቻለም ነበር። ፈገግታዋና የማያቋርጭ ቀልዷ በጆሮው እያቃጨለ እንቅልፍ ይነሳዋል። እሱ የተለየ የቡና ፍቅር ባይኖረውም ወጣቷን ያየበት ቡና መሸጫ ደንበኛ መሆን ግን ግዴታው ሆኖ ነበር።
እርሷም ምንም እንኳን ስራ ቢበዛባትም በምሳ ሰአት አንድ ሲኒ ቡና ሳትጠጣ አትቀርም ነበር። ልማደኛው አፍቃሪዋም ከቡና ሱስ እኩል እሷን ማየት የሚናፍቀው እግሩ እያመላለሰው ለወራት ያለማቋረጥ ተያይተዋል።
በአይን መለማመዳቸው የአንገት ሰላምታ መሰጣጠትን አስጀምሮ በድንገት ወደ ፍቅር ግንኙነት ተሸጋግረዋል። ለወራትም ደጅ ደጁን ሲገናኙ ቆይተው ሁለቱም የመኖሪያ ቤት ተከራይተው ስለሚኖሩ በአንድ መጠቃለላቸው ወጪ እንደሚቀንስላቸው ተስማምተው በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ሳሬም ሆቴል ጀርባ አካባቢ ባለ ሁለት ክፍል መኖሪያ ቤት ተከራይተው አብረው ይኖሩ ጀመር።
የኑሯቸው መጀመሪያ አካባቢ በሞቀ ፍቅር የተሞላ ነበር። ስራ በዝቶባት ስታመሽም ስራ ቦታዋ አካባቢ ቆሞ ጠብቆ ወደ ቤት ይዟት እየገባ፤ በፍፁም መተባበርና መተጋገዝ ይኖሩ ነበር። ቀናት ቀናትን እየወለዱ ሲሄድ ወጣት ዳግማዊ ከጎኔ አትራቂ በማለት ስራ መሄዷን ትታ ቤት እንደትቀመጥ ያስገድዳት ጀመር።
ስራውን ባትተይው እንኳን ማምሸቱ ይቅር በማለት ዘወትር የሚጨቀጭቃት ፍቅረኛዋ ጭቅጭቅ ሰብለንም እየሰላቻት መጥቷል። ለኑሮዋ ደፋ ቀና የምትለው ይህች ወጣት ከልቧ ያነገሰችው ፍቅረኛዋ ጊዜ ከለከልችኝ በሚል ምክንያት መውጫ መግቢያ ማሳጣቱ ግራ አጋብቷታል።
በተረጋጋ መንፈስ ስትናገረው ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ቢጠይቃትም ሁለት ሶሰት ቀን ቆይቶ ደግሞ ዳግም ወደ ጭቅጭቁ ይመለሳል። የእለት ከእለት ድግግሞሽን አንዴ በፍቅር ሌላ ጊዜ ደግሞ በቁጣ ልታስቆመው ብትፈልግም አለመቻሏ እያበሳጫት ነው። ለውጥ አለመኖሩ ቢያናድዳትም ከልቧ ስለምትወደው በትእግስት ማለፍን ምርጫዋ አድርጋለች።
እሷ መፍትሄ ያላችውን ብትሞክርም ዳግማዊ ግን እሷን የማጣት ፍርሃቱ ሰቅዞ ይዞት የታህሳስ ወር የመጨረሻዋን ቀን እንድታልፍ አልፈቀደላትም ነበር….
ክፉዋ ሌሊት
ታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ ከ9፡ 00 እስከ 10፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። በድካም የዛለችው ወጣት ሀገር ሰላም ብላ እንቅልፏን ትለጥጣለች። የእሷ እንዲህ ራስን ጥሎ መተኛት የሱ እንቅልፍ ማጣት ብስጭቱን ከፍ እያደረገው ሲሄድ ከጉኖ በሰላማዊ እንቅልፍ ውስጥ የነበረችውን ሰብለን ይቀሰቅሳታል። ከእንቅልፏ ነቅታ በእርጋታ ልታዳምጠው ብትሞክርም እሱ በትእግስት ማጣትና በጩኸት ምንም መግባባት እንዳይኖር ያደርግ ጀመር።
ያኔ ድካሙ የማያልቀው ጭቅጭቅ ያሰለቻት ወጣት ሰብለ ብድግ ብላ ወደደጅ ለመውጣት ስትሞክር በጥፊ ይመታና ይጥላታል። በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ሳሬም ሆቴል ጀርባ ባለው መኖሪያ ቤት ውስጥ ፤ በፍቅር የሳለፏቸውን ዓመታት አስረስቶ እንዲህ በጭካኔ እንዲመታት የደረገው ነገር ግራ ቢያጋባትም እንዲረጋጋ እየተማፀነች ለማምለጥ ወደ በሩ ተጠጋች።
ይህ ድርጊቷ ይበልጡኑ ያናደደው አፍቃሪ ያለምንም ርህራሄ የተለያዩ ጉዳቶችን ያደርስባት ጀመረ። በዚህ መካከል ጥቃቱን መቋቋም ያቃታት ወጣት የድረሱልኝ ጩኸት ማሰማት ጀመረች። ጩኸቷን የሰሙት ጎረቤቶችም የተቆለፈውን በር ገንጥለው ሲገቡ ሰብለን በአሰቃቂ ሁኔታ ከባድ ጉዳት ደርሶባት ይመለከታሉ።
ይህን ያዩት ጎረቤቶች ፖሊስ በመጥራት ጥቃት አድራሹን ለሕግ በማቅረብ፤ ሰብለን ወደ ህክምና ቦታ ያደርሳሉ። ተጎጂዋም የህክምና እርዳታ ሲደረግላት ቢቆይም በደረሰባት ጉዳት የተነሳ በተፈጠረ ኢንፈክሽን የሰብለ ሕይወት ሊያልፍ ችሏል።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ በቦታው እንደደረሰ በሕግ ጥላ ሰር ያቆየው ተከሳሽ የወንጀል ድርጊት አፈጻጸሙን በተመለከተም ሲያብራራ ተከሳሽ በዕለቱ በፍቅር ግንኙነት አብራው የምትኖረውን ሟች ሰብለ ንጉሴን በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት በእጁ ይዞት በነበረው የቤት ቁልፍ ደጋግሞ ግንባሯ ላይ እንዲሁም ፊትዋንም በጥፊ በመምታቱ ጉዳት ሊያደርስባት ችሏል።
ከዚህም በተጨማሪም በቢላ የግራ እግሯ የታችኛው ክፍል ወይም መርገጫዋን እና የቀኝ እጅዋን ትንሽዋ ጣቷ ላይ በመውጋት ጥልቀት የሌለው የቆዳ መቆረጥ እንዲደርስባት ካደረገ በኋላ ሳኒታይዘር ሰውነትዋ ላይ በማርከፍከፍ ክብሪት ለኩሶ ፊትዋ፣ አንገትዋ፣ የደረት ሶስተኛ ክፍሏ፣ ሆዷ፣ እጆቿ እና እግሮቿ በእሳት እንዲቃጠል ማድረጉንም የወንጀል አፈጻጸም ድርጊቱ ያስረዳል።
በደረሰባት አደጋ ምክንያትም የተቃጠለው ሰውነትዋ ኢንፌክሽን ፈጥሮ ወደ ሳምባዋ እና አእምሮዋ ተዛምቶ የደም ዝውውሯና የእስትንፋስ ሥርዓቷ ተቋርጦ ሕይወትዋ ሊያልፍ ችሏል።
ይህንን የወንጀል አፈፃፀም በሰውና በሰነድ ማስረጃ ያጠናቀረው ፖሊስ ወደአቃቤ ሕግ ልኮ ክስ እንዲመሰረትበት አድርጓል።
የፍርድ ቤት ክርክር
በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ዳግማዊ አራጋው በተባለው ግለሰብ ላይ በፈጸመው ከባድ የግድያ ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶ የክርክር ሂደቱን ሲያካሂድ ቆይቷል።
ተከሳሽ ታህሳስ 30 ቀን 2014 ከሌሊቱ በግምት ከ9፡00 እስከ 10፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ሳሬም ሆቴል ጀርባ ባለው መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ሲል ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስቀምጧል።
አቃቤ ሕግ በመሰረተው ክስ መሰረት ተከሳሽ ክሱ ተነቦለት ‹‹የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም›› በማለት ክዶ የተከራከረ በመሆኑ፤ ዐቃቤ ሕግ የወንጀሉን መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ሰው ምስክሮች አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ ያሰማ ሲሆን፤ በተመሳሳይም የሰነድ ማስረጃዎችን ከክስ መዝገቡ ጋር አያይዞ አቅርቧል።
የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ 5 የሰው ምስክር ያሰማ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሽ ሟች ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት እራሴን አጠፋለሁ የሚል የጹሁፍ መልዕክት ልካልኛለች በማለቱ፤ የሰነድ ማስረጃው ከኢንፎርሜሽንና መረጃ ደህንነት አስተዳደር እንዲቀርብለት ጠይቋል።
የሰነድ ማስረጃውን ውጤት ለመጠባበቅ ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 13 ቀን 2015 ቀጠሮ በሰጠው መሰረት፤ የኢንፎርሜሽንና መረጃ ደህንነት አስተዳደር በበኩሉ ጉዳዩን በተመለከተ ምንም አይነት የመልዕክት ልውውጥ አለመገኘቱን ለፍርድ ቤቱ በላከው ማስረጃ ላይ አመላክቷል።
ውሳኔ
በክሱም መሰረት ተከሳሽ ተከላከል በተባለበት የወንጀል ድንጋጌ ስር ክሱን ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ነህ በማለት የፍርድ ውሳኔውን አስተላልፏል።
በዕለቱ የተሰየመው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና የወንጀል ችሎትም በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የቀረቡ ማስረጃዎችን እና በተከሳሽ የቀረቡ የመከላከያ ማስረጃዎች መዝኖ ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ በበቂ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ሲል የቅጣት ውሳኔውን ማስተላለፉን ከፍትሕ ሚኒስቴር ድረ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም