ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ሀገራዊ ስክነት ወሳኝ ነው። በተለይም ከለውጥ ዋዜማ ጀምሮ ያሉ ወቅቶች ለለውጡ ስኬት ካላቸው ሁነኛ አስተዋጽኦ አንጻር በሰከነ መንፈስና አዕምሮ ሊቃኙና ከስሜታዊነትና ከግብታዊነት በጸዳ መንገድ ሊገሩ ይገባል። ይህን ማድረግ ደግሞ ለተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍል የሚሰጥ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።
የለውጥ ወቅት በባሕሪው በገፊ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የተዋቀረ ነው። ከዚህ የተነሳም በራሱ/ለውጡ/ ሊያመጣቸው የሚችላቸው ወቅታዊ ምስቅልቅሎች ብዙ ናቸው። ይህንን ምስቅልቅል እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ የፖለቲካ መሻታቸውን እውን ለማድረግ ባልተገባ መንገድ ለመጓዝ ወስነው የሚንቀሳቀሱ ብዙ ናቸው።
እነዚህ ኃይሎች ቀደም ሲል ለለውጡ ገፊ የሆኑ ምክንያቶችን ጨምሮ አዳዲስ ለግጭትና ለሁከት ምክንያት የሚሆኑ አጀንዳዎችን በመቅረጽ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በስፋት በማሰራጨት ለውጡ የተነሳበትን ሕዝባዊ ዓላማ ስቶ ወዳልተገባ መንገድ እንዲጓዝ ጫናዎችን ያሳድራሉ። በለውጡ ኃይልና የለውጡ ባለቤት በሆነው ሕዝብ መካከል አለመተማመን እንዲኖር በትጋት ይሠራሉ።
በለውጡ ኃይልና በለውጡ ባለቤት መካከል ለመፍጠር የሚፈልጉትን አለመተማመን እውን ለማድረግም፤ ከተራ አሉባልታ ጀምሮ ከውጪ ኃይሎች ጋር ጭምር በመናበብ የስም ማጥፋት ዘመቻን ያካሄዳሉ። ከዚያም አልፈው መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋል ብለው የሚያምኑበትን ወንጀል ሳይቀር በአደባባይ በመከወን በንጹሐን ደም የመጨረሻ ዕድላቸውን እስከ መሞከር የሚሄድ ድፍረትና ጭካኔ የተሞሉ ናቸው።
የለውጥ ኃይሉ በእነሱ እልህ አስጨራሽ ትንኮሳና ያልተገባ የአደባባይ ባሕሪ እልህ ውስጥ ገብቶ አላስፈላጊ እርምጃዎችን በመውሰድ ፤ሀገራዊ የፖለቲካ መድረኩ ወደሚፈልጉት የሁከትና ግጭት መድረክ እንዲሆን ፤በግልጥም በስውርም ይንቀሳቀሳሉ። ለዚህ ዓላማቸው ንጹሐንን ከፊት አሰልፈው ለአደጋ ተጋላጭ ማድረግ ደግሞ ዋነኛ መገለጫቸው ነው።
በእኛም ሀገር አሁን ላይ የለውጥ ኃይሉን ከሁሉም በላይ እየተፈታተነው ያለው ፤በለውጡ ማግስት ለሕዝቡ የገባውን ቃል ተግባራዊ የማድረግ ቁርጠኝነት ሳይሆን እነዚህ ኃይሎች በየወቅቱ የሚፈጥሯቸው ተግዳሮቶች ናቸው። ለዚህ ደግሞ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደሀገር ያጋጠሙንን የለውጥ ወቅት ፈተናዎች መለስ ብሎ ማየት በቂ ነው ።
በለውጡ ማግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ የተቃጣው የአደባባይ የግድያ ሙከራ፤ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በሀገሪቱ የመከላከያ ዋና ኤታማዦር ሹም ላይ የተካሄደው ግድያ ፤በሕዝብ ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት በነበረው የሙዚቃ ባለሙያ /ሃጫሉ ሁንዴሳ/ላይ የተፈጸመውን ግድያ ወዘተ ማስታወስ ተገቢ ነው።
እያንዳንዷን ክስተት ለፖለቲካ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ ለማድረግ የሄዱበት ርቀትና በዚህም ሀገርና ሕዝብን ያስከፈሉት ዋጋ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም። ያሰቡት ቢሳካላቸው እንደሃገር ሊያጋጥመን የሚችለው ፈተና የቱን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም። ፈተናዎቹን ተሻግረን እንደ ሃገር በዛሬ ቁመናችን እንገኝ ነበር ወይ ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው ።
እነዚህ ኃይሎች ዛሬም ቢሆን ያገኟቸውን አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ፤ ለጥፋት ዓላማቸው ስኬት አስቻይ ሁኔታዎችን በንጹሐን ደም ሳይቀር በማመቻቸት በሀገር ውስጥ በሚፈጠሩ ሁከቶችና ብጥብጦች የሥልጣን ጥማታቸውን ለማርካት የአቅማቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው።
ይህ መንገዳቸው እስካሁን ያሰቡትን ባያጎናጽፋቸውም ፤ ሃገርና ሕዝብን ያስከፈለው ዋጋ ግን ብዙ ነው። ይህን የጥፋት መንገዳቸውን እንደ ሃገራዊ የለውጡ ባለቤት/ሕዝብ ፈጥነን ማስቆም ካልቻልን በቀጣይ ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ ካለፈው የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አይሆንም።
በነዚህ ኃይሎች ሀገርና ሕዝብ እየከፈሉ ያለውን ዋጋ ለማስቀረት ከሁሉም በላይ እንደ ሕዝብ መስከን ይጠበቅብናል። ስክነት የእነዚህን ኃይሎች እኩይ ዓላማ በአግባቡ ተገንዝበን ራሳችንን ከጥፋት ወጥመዳቸው ለማራቅ የተሻለ ዕድል ይሰጠናል ።
ከዚያም በላይ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እያጋጠሙን ያሉ ሀገራዊ ፈተናዎች የእነዚህ ኃይሎች ማቆሚያ ያጣ እኩይ ተልዕኮ ውጤት መሆኑን ተረድተንና በለውጡ የሚፈለጉ ፍሬዎች ለመብሰል ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው አውቀን ሃገራዊ የለውጥ ጉዞውን በጽናት ማስቀጠል ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም