‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም›› አለ ደጉ ያገሬ ሰው፤ እውነቱን ነው፡፡ ከወደ ሀገረ ኔዘርላንድ የተሰማው ወግ አጃኢብ ያሰኛል፡፡ ወሬውን ለጆሮ የበቃው በእለተ ሰኞ በፈረጆቹ አቆጣጠር ሚያዚያ 15 ቀን በ2019 ከሰዓት በኋላ ነበር፡፡ ለማንኛውም ወሬው ከቢቢሲና ከኦድ ኒውስ የተገኙ መሆኑን እናስታውስዎ፡፡
አንዳንዶቹ አስተያየት ሰጭዎች እሰይ ደግ አደረገ። የልጅ አምሮቱ ቆርጦለታል ሲሉ ተሳልቀውበታል፡፡ አያድርሰን ያቀላል ሰው። ሆሆይ እንኳንም በእኛ ሀገር ያልሆነ፡፡ ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድራለን፣ ክልል ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ሌላ የራስ ምታት አይሆኑም ብላችሁ ነው? ኧረ እንደውም እናንተ ከእኛ ወገን አይደላችሁምና ውጡልን፤ አትድረሱብን ቢሉስ? ደግሞም ያደርጉት ነበር። በእኛ ሀገር አይደረግ የለ፡፡ ለነገሩ ለእያንዳንዱ የሚፈጸም ድርጊት እኮ ሰበብ ሞልቷል፡፡ ለእንትን ጀማሪ ሥለሆን እኮ ነው ማለትን ተክነንበታል። ሰውየውም ለእንትን ጀማሪ ሆነው ይሆናላ፡፡ ሆሆይ በሉ ጦሳችሁን እዚያው….፡፡
ነገሩ በገሐድ የሆነ ነው፡፡ ግን ደግሞ በህልሜ ነው? እያሉ የሚሰሙት አለያም የሚያነበንቡት ጎንታ አይነት ወሬ፡፡ በኔዘርላንድስ የሚገኝ አንድ የስነ-ተዋልዶ ሀኪም ነው፡፡ ሥሙም ጃን ካርባት ይባላል፡፡
እናም በርካታ ለእናትነት የሚቋምጡና የእናትነት ወግ የናፈቃቸው ሴቶች ከበጎ ፈቃደኞች የወንድን ዘር ይለገሰን ጥያቄ ያቀርባሉ። እውነትም አጃኢብ ያስብላል። የእኛ ሀገር በጎ ፈቃደኞች በትራፊክ ዜብራ ከማሻገር፣ ክረምት ማጠናከሪያ ከማስተማር፣ ከደሳሳ ጎጆ እድሳት ባሻገር አይናቸውን መግለጥ አለባቸው።ጉድ እኮ ነው፡፡ ሰውየው እውነቱን ባለመተንፈሱ ዋጋ እንዳስከፈለው እያየሁ እዚሁ ላይ እዋሻለሁ፡፡ አሁን ‹‹ደሜን ደሜን….ደሜን ለወገኔ›› ይረሳል፡፡ በእኛ ሀገርም በበጎ ፈቃድ ደም እስከ መስጠት በመደረሱ ሁለቱም እስትንፋስን የሚቀጥል በመሆኑ አልተራራቅንም ለማለት ነው፡፡ እናም ደማችሁን ለግሱና አሁንም ከእኛ ደም ነህ ብላችሁ መንገድ እንዳትዘጉ፡፡ ወደ ወሬዬ ተመለስኩ፡፡
ሴቶቹ ከተለያዩ ፈቃደኛ ከሆኑ የወንድ ዘር ለጋሾች ለመውሰድ ቢስማሙም አጅሬው የሥነተዋልዶ ሀኪም የእራሱን ዘር አሽሯቸዋል/ሰጥቷቸዋል/ ተብሏል፡፡ ለነገሩ ልገሳው የከፋ አልነበረም፡፡ ክፋት የሆነበት፣ የችግር መዘዝ ያስከተለበት እውነታውን አለማሳወቁ ነው። አያችሁ! እውነታን ደብቆ በዋዛ መላቀቅ የለም። ሰውየው እናቶቹ ያለእነሱ እውቅና የስነ-ተዋልዶው ሀኪሙ የእራሱን ዘር ነበር በመጠቀም የልጅ እናት ያደረጋቸው። በዚህም 49 እናቶችን ማስረገዙ በዘረመል (ዲ ኤን ኤ) ምርመራ ተረጋግጧል።
መረጃዎቹ እንዳመለከቱት ግለሰቡ በኔዘርላንድ ውስጥ በሚገኘው ክሊኒኩ ከ30 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት ህይወቱ አልፏል፡፡ ከ49ኙ ልጆች መካከል አንዷ የሆነችው ጆይ ”ከዚህ በኋላ አባቴ ማነው ስለሚለው ማሰብ ማቆም እችላለሁ። አባቴ ከሁለት ዓመት በፊት አልፏል” ስትል እውነታውን ተቀብላዋለች። ”ከ11 ዓመታት ፍለጋ በኋላ አሁን በሰላም ህይወቴን መምራት እችላለው። አሁን ሰላም አግኝቼያለው”በማለት ተናግራለች፡፡
49ኙን ልጆች ወክሎ ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የህግ ባለሙያ ቲም ቡዌተርስ ደግሞ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ ለረጅም ዓመታት በመቆየቱ የአሁኑ የምርመራ ውጤትና የፍርድ ቤቱ ማረጋገጫ አስደስቶኛል በማለት ስሜቱን ገልጿል። አብዛኛዎቹ ልጆች በ1980 ዎቹ የተወለዱ ናቸውም ተብሏል፡፡ ዶክተር ካራባት በፈረንጆቹ እኤአ በ2017 በ80 አመታቸው ክስ ቀርቦባቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት፡፡ በወቅቱም ተከሳሹን የሚመስል አንድ ልጅ ለፍርድ ቤቱ እንደ ማሳያ ቀርቦ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።
እንደ ዘገባው ፍርድ ቤቱ የዘረመል ምርመራ እንዲካሄድ ትእዛዝ አስተላልፎ የነበረ ሲሆን፣ የፍርድ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ግን ውጤቱ ለህዝብም ሆነ ለ49ኙ ልጆች ይፋ እንዳይሆን ተበይኖ ነበር። ባሳለፍነው የካቲት ወር ግን ፍርድ ቤቱ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ ባሳወቀው መሰረት የዘረ መል ምርመራው ውጤት ይፋ ሆኗል። በዚህም 49 ልጆች ከአንድ በጎ ፈቃደኛ መቀዳታቸው ተረጋግጧል፡፡ የአንድ ቀን መዘዝ ያለዘጠኝ ወር ወይንስ የ49 መዘዝ? ሞት ባይቀድመው ፍርዱ ምን ይሆን ነበር? ያጓጓል አይደል?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011
በሙሐመድ ሁሴን