ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት በአካባቢው የሚገኙ ሕዝቦችን ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነት ለማሳደግ የሚኖረው ሚና የላቀ ፤ የቀጣናው ሕዝቦች በጋራ ወደሚፈልጉት ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ለመድረስ ለሚያደርጉት ጥረት ስኬትም ያለው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው። ነገን በተሻለ ተስፋ እንዲጠብቁም የሚኖረው አስተዋጽኦ መተኪያ የሌለው ነው።
በተለይም የብዙዎችን ዓይንና ቀልብ በሚስቡ አካባቢዎች (ቀጣናዎች) ያሉ አገራት ፤ ሊኖርባቸው ከሚችለው የውጭ ጣልቃ ገብነት አንጻር፤ የአካባቢያቸውን ሰላም በትብብር እውን ለማድረግ የሚሄዱበት መንገድ ለሕዝቦቻቸው ዘላቂ ሰላም ማጎናጸፍ የሚያስችል ነው። የልማት ስራዎችን በማስፋፋት የሕዝቦቻቸውን ኑሮ ለማሻሻል ለሚያደርጉት ጥረትም ወሳኝ አቅም ነው።
ሰላምና መረጋጋት በሰፈነባቸው ቀጣናዎች የሚገኙ አገራት ፤ አጋጣሚውን እንደ አንድ መልካም እድል በመጠቀም፤ በመካከላቸው ያለውን አቅም ለጋራ የሕዝቦች ተጠቃሚነት ማዋል ይችላሉ፤ ቀጣይ እጣ ፈንታቸውን በጋራ ወስነው የሕዝቦቻቸውን ነገዎች ብሩህ ለማድረግ የሚያስችሉ የጋራ የልማት ውጥኖችን አቅደው በቀላሉ መፈጸም ይችላሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍሪካ ቀንድ (በምስራቅ አፍሪካ) የሚገኙ አገራት መሪዎች በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት በማስፈን በአገራቱ መካከል የነበረውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ሕዝቦቻቸውን የግንኙነቱ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እያደረጉት ያለው ጥረትና እየተመዘገበ ያለው ውጤት ለዚሁ እውነታ እንደ አንድ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችል ነው።
የአፍሪካ ቀንድ (የምስራቅ አፍሪካ) ቀጣና የብዙዎች ዓይን ያረፈበት ፤ ስትራቴጂክ ጠቀሜታውም ከፍያለ ነው። ከዚህ አንጻር የአካባቢውን አገራት መሪዎች በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እያደረጉት ያለ ጥረት በአካባቢው ሊኖር የሚችለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት መቀነስ የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል። ከዚህም ባለፈ በአካባቢው ዙሪያ በሚነሱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተደማጭነት ያሳድገዋል።
ይህ ደግሞ አሁን ባለንበት ዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፍና የአሰላለፍ ተጠቃሚነት የአካባቢው አገራት ሊኖራቸው የሚችለውን የመደራደር አቅም ከማሳደጉም በላይ፤ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን የጀመሩትን አዲስ የፖለቲካ መንገድ በማጠናከር የሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ማረጋገጥ የሚያስችል እድል ሊፈጥር የሚችል ነው።
ከዚህም ባለፈ ለቀጣናው የሰላም ጠንቅ የሆኑ አልሸባብን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች በአካባቢው መሰረት እንዳይኖራቸው ከማድረግ ጀምሮ፤ ሊፈጥሩት የሚችለውን የሰላም እጦትና ጥፋት ለማስቆም አገራቱ በጸጥታና ደህንነት ዙሪያ የሚያደርጉት ትብብር የሚበረታታና ከፍያለ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።
ትብብሩ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ከማስፈን ባለፈ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ወደ ቀጣናው በመሳብ የአካባቢው አገራት ሕዝቦችን የመልማት ፍላጎት እውን በማድረግ፤ በልማት ዙሪያ የነበረውን የቀደመ ትርክትና ከትርክቱ በስተጀርባ የነበረውን አንገት አስደፊ እውነታ መለወጥ የሚያስችል አቅም የሚገነባ ነው።
በተለይም ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ ፤ የአካባቢውን ሕዝቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግና በአገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት በመተማመን እና በመተባበር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያደረጉት/እያደረጉ ያለው ጥረት ለዚህ ተጠቃሽ ነው።
ይህ የቀጣናው አገራት ሕዝቦች ግንኙነታቸውን በማጠናከር ቀጣይ እጣ ፈንታቸው ላይ የጋራ ግንዛቤ ይዘው፤ በጋራ መንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ታሪካዊ እውነታ ፤ በጸጥታው ዘርፍ ዓለም አቀፉን አሸባሪ ቡድን (አልሸባብን) በጋራ ከመዋጋት ጀምሮ የሶማሊያን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ርብርብ ጎልቶ እየታየ ይገኛል።
ለዚህም ከትናንት በስቲያ የቀጠናው አገራት መሪዎች (የኢትዮጵያ፣ ኬንያ ፣ ሶማሊያ እናጅቡቲ) በተገኙበት በዓለም አቀፍ አሸባሪው ቡድን/አልሸባብ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ አጠናክሮ ለመቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በሞቃዲሾ የተካሄደው መድረክ አንድ ማሳያ ነው።
በወቅቱም የቀጠናው አገራት የሶማሊያን የጸጥታ ኃይሎች ለማሰልጠን ያሳዩት መነሳሳት የዚሁ እውነታ ሌላኛው መገለጫ ነው። ትብብሩ አሁናዊውን ቀጣናዊ ሰላም ከማስፈን ባለፈ፤ በቀጣይም በቀጣናው ሰላም ለማስፈን አገራቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ የታየበት ነው!
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም