‹‹የሚደግፈኝ ልጅም ሆነ ዘመድ የለኝም።የምተዳደረው በልመና ነው።ቢሆንም በልመና ባገኘኋት ጥቂት ሳንቲም ጥጥ ገዝቼ እየፈተልኩ ልቃቂት በመሸጥ ኑሮዬን እደጉማለሁ›› ይሄንን የነገሩን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ በር መታጠፊያ ላይ በሚገኘው ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ያገኘናቸው እናት ወይዘሮ ማስተዋል ቁምልኝ ናቸው።ብዙ ልቃቂት ሲሸጡ አልፎ አልፎ ጋቢ በማሰራት ዳጎስ ባለ ብር ሽጠው ይጠቀማሉ።በማህበር የሚያደራጃቸው ቢያገኙ በጥጥ ሥራው ለዘለቄታው ተሰማርተው ከልመና መውጣትም ይፈልጋሉ።
አሁን ላይ እኝህ እናት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ሴቶች ከልመና ጎን ለጎን የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ሲሰሩ መታየታቸው እየተለመደ መጥቷል። ብዙዎቹ ሴቶች እንደነገሩን ተግባሩን የሚያከናውኑት በልመና ቁጭ ሲሉ የሚያጠፉትን ረጅም ጊዜ ለመጠቀም ብቻ ሳይሆን በየቀኑ በልመና የሚያገኙትን ትንሽ ሳንቲም በመደጎም የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈንም ነው።
በዚሁ በስድስት ኪሎ እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት መሶብና ሌሎች የስንደዶ ስፌት ሥራዎችን ሲሰሩ ያገኘናቸው ሌላዋ እናት ወይዘሮ ሩቅያ አሰፋ አምስት ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩት ከልመናው ጎን ለጎን ይሄን የስፌት ሥራ እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። ልጆቻቸው ለምግብ እንጂ ለሥራ ስላልደረሱ ለመንገደኛም እየሸጡ ገቢ ያገኛሉ።የዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑትና የሚደጉሙት በዚሁ ገቢ ነው።የስፌት ግብዓቱን ከልመና በሚያገኙት ገንዘብ ነው የሚሸምቱት። ሆኖም አንደንዴ አንድ ብር ሁለት ብር እየተባለ የሚጠራቀመው የልመና ሳንቲም አልሞላ ሲልና ከሥር ከሥር ለልጆች ዳቦ መግዣ ሲወጣ ቀኑን በሙሉ ጊዚያቸውን ያለስራ የሚያሳልፉበት ጊዜ አለ ። በመሆኑም በቋሚነት የሚያደራጅና በሙያው እንዲሰማሩ የሚያደርጋቸው አካል ቢያገኙ የሰው ፊት ከሚያሳየውና ከሚያፀይፈው ልመና እወጣለሁ ብለው ያስባሉ።
የሰላሳ ዓመቷ ወይዘሮ ዘርትሁን መለሰ ከደራ ከመጣች ዓመታት ማስቆጠሯን ትናገራለች። የሶስት ልጆችም እናት ናት። ልጆቿን ለማሳደግ ስትል ለዓመታትም በልመና ሥራ ተሰማርታ ቆይታለች። በዚህ ወቅት ማንነታቸውን ማታውቀው ሰዎች የምትለምንበት ቦታ መጥተው ከልመናው ጎን ለጎን ያላትን የስፌት፤ የዳንቴልና ሌሎች የእጅ ሥራ ሙያዎች ተጠቅማ ኑሮዋን እንድትደጉም ግንዛቤ ፈጠሩላት።ሁለት ሦስቴም ስንደዶና የዳንቴል ክር እየገዙ ሰጧት።በስንደዶው ይሄን ከመከሯት ለአንዷ የመኪና መቀመጫ ሰፌድ በመሥራት ነው ለመጀመርያ ጊዜወደ ሥራው የገባችው።መሶብ ወርቅ፤መሶብና የዳንቴል ያልጋ ልብሶችና መሸፈኛዎች በመሥራት ደህና ገቢ አገኘች።ይሄን ያዩትና ግንዛቤ ፈጥረውላት የነበሩት ሰዎች ለ15 ቀን ስልጠና እንድትወስድ አደረጓት።ስልጠናው ከዳንቴልና ከክር፤ እንዲሁም ከስንደዶ የተለያዩ የፕላስቲክ ከረጢቶችን በመተካት አካባቢን ሳይበክሉ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቦርሳዎችና ስፌቶች ማምረት የሚያስችል ነበር።አሁን ላይ በእጅ ሥራው ሙሉ በሙሉ ከልመና መውጣት ችላለች።ሽሮ ሜዳ አካባቢ እንዲሁም የንግስ በዓላት በሚሆኑበት ጊዜ ንግሱ በሚከናወንበት ሥፍራ ተገኝታ ምርቶቿን በመሸጥም ትተዳደራለች።አንድ ቦርሳ እስከ 500 ብር ትሸጣለች።በተለይ እንደ ጥምቀት ባሉት በዓላት የውጭ አገር ቱሪስቶች በብዛት ይገዟታል።ልጆቿንም ትምህርት ቤት ማስገባት ችላለች።ከማይመችና በጥገኝነት ትኖርበት ከነበረው የግለሰብ ቤት ወጥታ የራሷን ምቹ ቤት መከራየት ችላለች።ዘርትሁን ‹‹ይሄ አንዲት በልመና ተሰማርታ ለነበረች ሴት ቀላል ለውጥ አይደለም፡ ››ትላለች።አክላም ሌሎችም በተለይም አቅምና ጤና ያላቸው ሰዎች በሙያው ቢሰማሩ በቀላሉ ከልመና መውጣት እንደሚችሉም ተሞክሯን ማሳያ አድርጋ ትመክራለች።
የ‹‹ገላዬ ደያስ ሀንድ ክራፍት›› ድርጅት መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ገላዬ ደያስ ብዙ ሴቶችንና እናቶችን ከልመና የሚያወጣ የተቀደሰ ተግባር እንደ አገርም ሆነ አብዝቶ የልመና ተግባር በሚፈፀምባት አዲስ አበባ በመዟዟር ግንዛቤ እየፈጠሩ የጀመሩ ናቸው። ወይዘሮዋ ከ10 ዓመት በላይ በበርካታ ማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎች ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ ናቸው። ሥራውን ከ2002 ጀምሮ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ በትጋት ሲሰሩት ቆይተዋል።እንደ አገር ከአንድ ሺህ በላይ ሴቶችና እናቶችን ግንዛቤ በመፍጠር በተለያዩ የእጅ ስራዎች አሰልጥነዋል።ከነዚህ አብዛኞቹ ከተለያዩ ክልሎች ፈልሰው ከነልጆቻቸው ወደ አዲስ አበባ የመጡና በጉለሌ፤በአዲስ ከተማ፤እንዲሁም በልደታ ክፍለ ከተሞች በልመና ሥራ የተሰማሩ ነበሩ።ሴተኛ አዳሪ ሆነው ጎዳና የወጡና በልመና ስራ የተሰማሩም ይገኙበታል።አሁን ላይ ካሰለጠኗቸው ሴቶችና እናቶች ከግማሽ በላዩ በጥጥ ፈትል፤ በሹራብ፤ ኮፊያ፤ በቦርሳ፤ በስንደዶ ስፌትና በሌሎች የተለያዩ የእጅ ሥራዎች በመሰማራት የራሳቸውንና የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ ከመሸፈን አልፈው ከልመና መላቀቅ ችለዋል። በሽሮ ሜዳና በተለያዩ ሥፍራዎች ምርቶቻቸውን በመሸጥ በሚያገኙት ገቢም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ አልፈው የተሻለ ሕይወት እየመሩ ይገኛሉ።አሁን ላይም ይሄ ተሞክሮ በተለያየ መንገድ በመስፋቱ እናቶችና ሴቶች ከልመና ጎን ለጎን የእጅ ሥራ ሙያውን ሲያከናውኑት ይታያሉ።
ሥራው ለግለሰቦቹ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች አሉት። በተለይ የሚያመርቱት ቦርሳ ለረጅም ዓመት ሳይበላሽ በመቆየቱ በምርታማነት ላይና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድረውን የፕላስቲክ ከረጢትን የሚተካ ነው።ሆኖም እናቶችን የዕለት ጉርስ፤ መጠለያ የሌላቸው፤ ልጆቻቸውን ማስተማር የማይችሉና ሌሎች ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስላሉባቸው እሳቸው ከዚህ ቀደም በፈጠሩት ግንዛቤ ብቻ በቀላሉ ከልመና ይወጣሉ ብለው አይጠብቁም። በእርግጥ በእጅ ሥራው መስክ ሳይሆን በሌሎች መስኮች በመንግስት ደረጃ እናቶችና ሴቶችን ለመደገፍ የሚሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም በአብዛኛው እነዚህን በልመና የተሰማሩትን አያካትትም። በመሆኑም ከመንግስት ጋር ሥራውን እናቶቹና ሴቶቹ ዘላቂ ለውጥ በሚያመጡበት ሁኔታ በቅንጅት ለማከናወን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፤ለከተማዋ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ አቅርበው ነበር፡ ነገር ግን እስከ አሁን ምላሽ አላገኙም፡፤ እኛም ከልመና ባሻገር ወይዘሮ ገላዬ በፈጠሩላቸው ግንዛቤ ራሳቸውን የሚደጉሙት በቅንጅት ይታገዙ መልዕክታችን ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 25 ቀን 2015