የመጽሐፉ ስም፡- እናት
ደራሲ፡- ይሁኔ አየለ (ዶክተር)
የሕትመት ዘመን፡- 2015 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፡- 406
የመሸጫ ዋጋ፡- 500 ብር
ከመጽሐፉ ዋጋ ልነሳ። በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ ‹‹ገቢው ሙሉ በሙሉ የእናቶችን ሸክም ለሚያቃልሉ ተግባራት የሚውል።›› ይላል።
ፀሐፊው ዶክተር ይሁኔ አየለ ይባላሉ። የሥነ ምግብና ጤና ተመራማሪ ናቸው። በሥነ ምግብና ጤና ላይ የሚያተኩሩ መጽሐፎችና የተለያዩ መጣጥፎች አሏቸው።
ይህኛውን መጽሐፍ ግን ለየት የሚያደርገው በእናት እና ከእናት ጋር የተያያዙ የጤና፣ የፍልስፍና፣ የማህበራዊ ሕይወት መስተጋብር… ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መሆኑ ነው። መጽሐፉ በንዑስ ርዕስ ‹‹የሴት ልጅ ስንክሳር፤ ከቤተሰባዊ ሕይወት እስከ ማኅበራዊ ሐለዮመንበርት›› የሚል አለው። የመጽሐፉን ሽፋን እና ሙሉ ይዘቶች ወደኋላ በዝርዝር እንመለስበታለን።
መጽሐፉ የሚሸጠው እንደማንኛውም መጽሐፍ ከመጻሕፍት መደብሮች በመግዛት አይደለም። በሦስት ሰዎች ስም የተከፈተ የባንክ አካውንት አለ። የመጽሐፉ ገቢ ለደራሲው አይደርስም። መጽሐፉን የሚፈልጉ ሰዎች በተከፈተው የጋራ የባንክ አካውንት ከ500 ብር ጀምሮ (የአንዱ መጽሐፍ ዋጋ) የሚፈልጉትን ያህል መግዛት ይችላሉ፤ በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ እናቶችን እየረዱ ነው ማለት ነው።
ወደ መጽሐፉ ይዘት ከመግባታችን በፊት ስለደራሲው ዶክተር ይሁኔ አየለ ጥቂት ልበል።
ዶክተር ይሁኔ አየለን የማውቃቸው በማህበራዊ ትስስር (ፌስቡክ) ገጻቸው ነው። በመድረክ፣ በቴሌቭዥን፣ በጋዜጣ፣ በማህበራዊ ገጾችም ሆነ በየትኛውም የመገናኛ አማራጭ ብዙ ምሁራንን አውቃለሁ። የዶክተር ይሁኔ በተለየ የሚገርመኝ ግን ሳይንስን ያህል ረቂቅና ውስብስብ ነገር እጅግ በጣም ቀላል በሆነ ቋንቋ ማስረዳት መቻል ነው።
ብዙ በአካባቢያችን የሚገኙ የተክል፣ የእንስሳትና የተለያዩ ዘአካላት በአካባቢያዊ መጠሪያቸው ብናውቃቸው እንኳን ሳይንሳዊ ስማቸውን አናውቀውም። የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ በሳይንሳዊ ስማቸው ቢያውቋቸው እንኳን አካባቢያዊ ስማቸውን አያውቁትም። ዶክተር ይሁኔ ግን ‹‹ይሄ ማለት ይህኛው ማለት ነው›› በማለት በብዙ የጥናት ማጣቀሻዎች አስደግፈው ያስረዳሉ።
በልማዳዊ አጠራር የሚጠሩ የተለያዩ የበሽታ ዓይነቶችን በሳይንሳዊ ስማቸው ጠቅሰው ያስረዳሉ። ልብ የማይባሉ አካባቢያዊ የባህል ምግቦችን ሳይንሳዊ ጠቀሜታ ሲያስረዱ ‹‹በርገርና ፒዛ ለምኔ›› ያሰኛል። በአጠቃላይ የዶክተር ይሁኔን መጽሐፍና መጣጥፎች ሳነብ ከሳይንስ ያለን ርቀት ነው የሚታየኝ።
ወደ መጽሐፉ ይዘቶች እንግባ። ይዘቶቹን በጥቂት በጥቂቱ ጥቅል ሀሳባቸውን ለመግለጽ እንጂ ሙሉውን ለመናገር አይደለም። አንዱ ገጽ ብቻ ከአምስት በላይ መጽሐፎች፣ የተለያዩ የጥናት አድራሻዎች የሚጠቀሱበት ነው። መጽሐፉ አንድ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን የቤተ መጽሐፍ ማውጫ ነው ማለት ይቻላል።
የመጽሐፉ የፊት ለፊት ሽፋን ላይ ልጅ ያዘለች አንዲት እናት ትታያለች። ይቺ እናት ልጅ አዝላ ከኋላ ደግሞ የሆነ ትልቅ ቋጥኝ ትጎትታለች። ረቂቅ የሚባል ምስል አይደለም፤ መልዕክቱ ለማንም በቀላሉ የሚገባ ነው። ምክንያቱም ከከተሞች ወጣ ብንል በአብዛኛው የአገራችን አካባቢዎች የምናየው ይህን የእናቶችን ስቃይ ነው። በጀርባቸው ልጅ አዝለው በፊታቸው ደግሞ የሆነ ነገር ይታቀፋሉ። ወይም ልጅ ታቅፈው በጀርባቸው ደግሞ ሌላ ነገር ያዝላሉ።
መጽሐፉ ዘጠኝ ምዕራፎች አሉት። የመጀመሪያው ምዕራፍ ተማጽኖና አዋጅ ነው። የእናትን ውለታ መክፈል ባይቻልም ለእናት ተገቢውን ዋጋ መስጠት እንዳለብን የሚያሳይ ነው።
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሴቶችን በተመለከተ የተጻፉም ሆነ በአፍ የሚነገሩ ልማዶች ሁሉ አልቀሩም። በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ፣ በሕዝብ ሥነ ቃል ውስጥ፣ በተለያዩ ዘፈኖች ውስጥ ሴትና እናትን በተመለከተ ያሉ የግጥም መልዕክቶች፣ ገጣሚያን፣ የልቦለድ ፀሐፊዎች ሴቶችን የገለጹበት ሁኔታ፣ ሃይማኖታዊ ጥቅሶች… በእነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች ሴቶች እንዴት እንደተገለጹ ያሳያል።
የሚገርመው ደራሲው የጠቀሷቸው ማጣቀሻዎች አንዳንዶቹ ሴትን(እናትን) አስመልክቶ የተጻፉ አይደሉም፤ እግረ መንገድ የተገለጹ ናቸው። ደራሲው ዶክተር ይሁኔ ግን አንዲት ዓረፍተ ነገር ብትሆን ራሱ እናትን በተመለከተ የተገለጹ ነገሮችን ልብ ብለዋል።
መጽሐፉን ማንበብ ሳይንስን ማወቅ ነው፣ የሰው ልጅ የጥበብ ሥራዎች ማወቅ ነው፣ ፍልስፍና ነው። የሚገርመው ግን መጽሐፉን ማንበብ መዝናኛም ጭምር ነው። መዝናናት ሲባል ለብዙው ትዝ የሚለው ቀልድ ሳይሆን አይቀርም። የሆነ የማናውቀው ያልለመድነው አስገራሚ ነገር ስናገኝ እንደመማለን፣ ተዝናናን ማለት ነው። የመጽሐፉ አንዳንድ ሳይንሳዊ ገለጻዎች እንደዚያ ናቸው። ይዘነው እየኖርን የማናውቀው ተፈጥሮ አለን። እሱን ሲነግረን እንደመማለን።
በሰው ልጅ ዝግመተ ለውጣዊ የመኖር ሂደት ውስጥ የተፈራረቁ የባህልና አኗኗር አብዮቶችን ይነግረናል። ለምሳሌ በጥንታዊ የኅብረተሰብ ዕድገት ውስጥ የሴት የበላይነት የነበረበት ሥርዓት ነበር። በጎሳ መሰል ሥርዓት ውስጥ የመሪነት ቦታው የሴቶች ነበር። ውርስ የእናት ዘር ሐረግን ተከትሎ ይሄድ ነበር። ባሎች መኖሪያቸውን በሴት አማቾቻቸው ዘንድ ያደርጉ ነበር።
እንግዲህ አሁን ያለው ባህልና ልማድ በተለያዩ የባህል አብዮቶች መፈራረቅ የመጣ ነው ማለት ነው። በሴትና በወንድ መካከል ያለው ልዩነት ሥነ ሕይወታዊ (ባዮሎጂካል) ብቻ ሳይሆን ሰው ሰራሽ የሆኑ ልዩነቶች ናቸው።
የዶክተር ይሁኔ መጽሐፍ እንደሚነግረን፤ ኢምሊ ማርቲን የተባለች የሴታዊት ተሟጋች (ፌሚኒስት) ተፈጥሯዊ የሆነውን የወንድ ነባዛርና የሴት እንቁላል ያላቸውን ሕይወታዊ ተዋፅዖ ተመራማሪዎቹ አድሎ አድርገውበታል ብላ ትሞግታለች። እሷና የዘመኗ ፌሚኒስቶች (ሴት ግዴ ይለዋል የዶክተር ይሁኔ አማርኛ) የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎችን ይሞግቱ ነበር። የተፈጥሮ ሳይንሱን ተመራመርን የሚሉት በብዛት ወንዶች ናቸው፤ እነርሱ ደግሞ የባህል ጫና አለባቸው፤ ስለዚህ የባህል ጫናው በሳይንሱ ላይም ተፅዕኖ አድርጎበታል የሚል ሙግት ነበራቸው።
እነዚህንና የመሳሰሉትን ከጥንት እስከ ዛሬ ያሉ ሳይንሳዊ ጥናቶችንና የባህል አብዮቶችን ጭምር ነው መጽሐፉ የሚነግረን።
አሁን ያለው የሴትና የወንድ የበላይነትና የበታችነት ልማድ ጥንታዊ መሠረት አለው። በተለይም የወንድ የበላይነት ጥንታዊውን የአደን ሕይወት መሠረት ያደረገ ነው። የሰው ልጅ በአደን ይኖር በነበረበት ጊዜ አውሬ መግደል የወንዶች ነበር። ይህ ልማድ እየተወራረደ እዚህ ደርሶ አሁንም በብዙ የአገራችን ክፍል የዱር ሥራዎች የወንዶች ናቸው።
እናት መጽሐፍ እንደምትነግረን፤ ይህ የወንዶች የአደን የበላይነት በሴት ተመራማሪዎች ደግሞ ተቀባይነት የለውም። የሴት ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ የሰውን ልጅ አሁን ወዳለበት ከፍተኛ ለውጥ ያመጣው አደን ሳይሆን የሴቶች ሥራ የሆኑት ናቸው።
እነዚህ የሴቶች ሥራዎች፤ መልቀም፣ መሰብሰብ፣ መፈለግ፣ መለየት፣ መፈልፈል፣ መቀጥቀጥ፣ መፍጨት፣ ተንከባክቦ ማሳደግና የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህን ሥራዎች መጀመር እጅን ለጉዞ ከመጠቀም ነፃ አወጣው። አጎንብሶ ከመሄድ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ መሄድን አስከተለ። ስለዚህ ሴት ተመራማሪዎቹ በሥልጣኔ ሂደት ውስጥ የሴቶች ድርሻ የበለጠ ነው የሚል ሀሳብ አላቸው።
የማህበራዊ ሕይወት ማሰሪያ ነው የሚባለውን በልቶ ማደርን ብንወስድ፤ ሥጋ በቀላሉ የሚበላሽ ነው። ለረጅም ጊዜ የሚቀመጠው በሴቶች ሽምጠጣና ለቀማ የሚገኙት የዕፅዋት ምግቦች ናቸው የሚሉ ተመራማሪዎችም አሉ።
በአደን የጀመረው የወንዶች የበላይነት አመለካከት በእስያም ሆነ አውሮፓ አገራት ውስጥ የነበረ ነው። የሥልጣኔ ቁንጮ ላይ ናቸው የሚባሉት አገራት ብዙ የማይታመኑ የሚመስሉ ኋላቀር የሆኑ አመለካከቶች ነበሩ፤ እንደ ቻይና ባሉ አገራት ሴቶች በባዕድ አምልኮ ይወገዱባቸው ነበር። እንደ እንግሊዝ ባሉ አገራት ውስጥ የነበሩ አመለካከቶችን መጽሐፉ አስቀምጧል። የዴሞክራሲ ፈጣሪ ናት የምትባለዋ ግሪክ ለሴት አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ፈላስፎች ነበሯት።
የልጆች በአባት መጠራት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉት ይነግረናል የዶክተር ይሁኔ መጽሐፍ፤ ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ የሰውን ልጅ የጥንት ዘመን አኗኗር የሚገልጽ ነው። ይሄውም፤ ወንድ ከሴቷ ጋር ሥምረተ ሥጋ (ወሲብ) ከፈጸመ በኋላ ላይገናኙ ይችላሉ። ባለው የዘጠኝ ወር ቆይታ ውስጥ ሊረሳ ይችላል። በዚህ ምክንያት የአባትየው ስም እንዳይረሳ ይደረጋል ማለት ነው። ከዚህ ልማድ የተቀዳ ‹‹አባትነት እምነት ነው›› የሚባል አባባል አለ።
የመጽሐፉ አንዱ ጠቀሜታ ‹‹አሜን!›› ብለን የተቀበልናቸውን ልማዳዊ አስተሳሰቦች በሳይንሳዊ ጥናቶች ውድቅ የሚያደርግ መሆኑ ነው። ለምሳሌ፤ መካንነት ወይም አንድ ዓይነት ፆታ ብቻ መውለድ የሴቷ ችግር ተደርጎ ነው የሚወሰደው። መጽሐፉ ላይ በተቀመጠው መረጃ፤ አንዲት በተከታታይ ሴት ብቻ የምትወልድ እናት ብትኖር ችግሩ የእሷ አይደለም። የወንድነትን ፆታ የያዘው ‹‹y›› የሚባለው ሀብለ በራሂ የሚገኘው በወንዱ ነባዘር ውስጥ ነው። መጽሐፉ እንዲህ ዓይነት ልማዳዊ አስተሳሰቦችን የሚያጠሩ ሳይንሳዊ ማብራሪያዎችን የያዘ ነው።
በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገርሙኝ ነገሮች አንዱ ሰለጠኑ በሚባሉ አገራት ያሉ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ናቸው። ሴትን የሚበድል ነገር የሚፈፀመው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሆነ ነው ብዙ ሰዎች የሚያምኑት። ለምሳሌ በቋንቋችን ውስጥ ለሴቶች አሉታዊ ትርጉም ያላቸው ብዙ ቃላት አሉ። ይህ ግን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሰለጠኑ ናቸው በሚባሉትም አገራት ያለ ነው።
እንዲያውም አንድ ትርጉሙን ልብ ብየው የማላውቀው የእንግሊዝኛ ቃል የላቲን ትርጉሙ ተብራርቶ ሳየው ገርሞኛል። የሴት የመራቢያ አካል የእንግሊዝኛ ቃሉ (ቫጃይና) የላቲን ቃል ነው። ትርጉሙም የጎራዴ አፎት እንደማለት ነው። የጎራዴ አፎት ማለት ጎራዴው የሚቀመጥበት ከቆዳ የሚዘጋጅ ከረጢት ነገር ማለት ነው። ምናልባት የወንዱን የመራቢያ አካል እንደ ጎራዴ በማየት፤ የሴት የመራቢያ አካል ለወንዱ ጎራዴ ማስቀመጫ እንደማለት ነው ብለው ይመስላል። እንዲያ ከሆነ ሴትን ልጅ ዕቃ የማድረግ መልዕክት አለው ማለት ነው።
ወደ አማርኛው ስንመጣ የሥርዎ ቃሉ ትርጉም ስለማይታወቅ ለጊዜው አሉታዊ ትርጉም የለውም። ዳሩ ግን በምሳሌያዊ ንግግሮችና በፈሊጣዊ ቃላት ውስጥ ሴቶችን ዝቅ ያለ ግምት እንዲሰጣቸው የሚያደርጉ ቃላት ብዙ ናቸው። ሴቴ፣ ሴታሴት፣ ሴትላ… በሚሉ መነሻ ቃላት የሚገለጹ ቃላትና ሐረጎች ብዙ ጊዜ ለስድብና የአንድን ነገር ቀላልነት ለመግለጽ የሚያገለግሉ ናቸው።
እንግዲህ የእነዚህ ነገሮች ሁሉ ውጤት ነው እናትን ያህል ነገር ተገቢውን ክብር እንዳታገኝ ያደረገ። በልማድና በዘፈቀደ የሚባሉ ነገሮች ሲወርዱ ሲወራረዱ መጥተው በተፈጥሮ የሆኑ ሁሉ መሰለን። ተፈጥሯዊ ሁኔታውን እንኳን እንዳናስተውል አደረገን።
ለምሳሌ በሰው ልጅ መፈጠር ውስጥ ከወንዱ ነባዘር በላይ የሴቷ እንቁላል ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው ሳይንሱ የሚያሳየው። አብዛኛው የሰውነት ክፍል ቅርጽ የሚሠራው ከሴቷ እንቁላል ነው። ቀደም ሲል በነበረው አመለካከት ደግሞ አብዛኛው የሰውነት ቅርጽ የሚሠራው በወንዱ ነባዘር ውስጥ ነው የሚሉ ሳይንቲስቶች ነበሩ።
መጽሐፉ እንዲህ ተፈጥሮን ከልማድ እያፋጨ አንዴ ያዝናናል፣ አንዴ ያሳዝናል፣ አንዴ ያስደምማል። የሳይንስና የማህበራዊ ሕይወት መስተጋብር መሆኑ ቀርቶ ልክ እንደ ልቦለድ ቀልብ አንጠልጣይ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ‹‹እውነት ይሄ ይደረግ ነበር?›› እያልኩ ለማረጋገጥ የተጠቀሱ አድራሻዎችን ይዤ ወደ በይነ መረቡ ዓለም እገባለሁ። መጽሐፉ ብዙ ነገሮችን ለማንበብ ተንኳሽ ነው።
መጽሐፉ በሳይንሳዊ ጥናቶች የታጨቀ ስለሆነ እንዲህ ባይባል፣ ይሄ ባይጻፍ ለማለት አያስደፍርም። ዳሩ ግን አንዳንድ ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ከተገለጹት በግሌ የማልስማማባቸው ደግሞ አሉ። ምናልባት ፀሐፊው በሴት ልጆች ላይ የሚደርሱ ማህበራዊ ጫናዎች በጣም ስለሚያሳስቧቸው ቢሆንም በሁሉም ጥፋቶች ግን ወንዶች የሚበረታቱ አይደሉም።
ለምሳሌ፤ ሴሰኝነት የሚወገዘው በሴቶች ብቻ እንደሆነ ነው ፀሐፊው የጻፉት። ምናልባት ከአካባቢ አካባቢ ቢለያይም ሴሰኝነት በወንድም በጣም የተወገዘ ነው። ‹‹ሸርሙጣ›› የሚለው ነውር የስድብ ቃል ለሴት ብቻ የሚያገለግል ሳይሆን ለወንድ ጭምር የሚያገለግል ነው። በሚስቱ ላይ የሚማግጥ፣ ብዙ ሴቶችን ለሥምረተ ሥጋ የሚጠይቅ ወንድ በዚሁ ቃል ነው የሚሰደብና የሚወገዝ።
ድንግልናን በተመለከተ ጫናው በሴት ልጅ ላይ እንደሚበረታ ግልጽ ነው። ቢሆንም ግን ወንድ ልጅም ቢሆን ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነት እንዲያደርግ አይበረታታም። በሃይማኖታዊ ሥርዓቱም ካየን (ለምሳሌ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት) በተክሊል የሚጋቡት ሴቷ ብቻ ሳይሆን ወንዱም ድንግል ከሆነ ነው።
ምናልባት በወጣቶች ዘንድ ወንድ ድንግል ሆኖ መቆየት እንደሌለበት ይወራ ይሆናል፤ ከጋብቻ በፊት ግንኙነት ማድረግ እንዳለበት ይገፋፉት ይሆናል። እንደ ባህልና ልማድ ካየነው ግን ከጋብቻ በፊት ሁለቱም ድንግል እንዲሆኑ ነው የሚበረታታው። ችግሩ ግን በተፈጥሮ የሴቶች መለያ ምልክት ስላለው የወንዶች ለማጭበርበር ዕድል መፍጠሩ አልቀረም።
በአጠቃላይ፤ መጽሐፉ ለሴቶች ሙሉ ሰው መሆን የሚታገል መጽሐፍ ነው። ከሰፈር እስከ ጠፈር ያሉ ልማዶችን ከሳይንሳዊ እውነታው ጋር እያመሳከረ የሚያብራራው በሴቶች ላይ የተሠራውን ግፍ ለማሳየት ነው። ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የአገራችንን ሴቶች ታሪክ ፈልፍሎ በማምጣት ሌሎች ሴቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል። እንዲያውም ይህኛው ምዕራፍ (ምዕራፍ 4 የአገራችን ብርቱ ሴቶች በጨረፍታ) የሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ አካላት ብዙ ነገር ሊጠቀሙበት የሚገባ ሰነድ ነው።
በመጨረሻም እናቶችን ካሉባቸው ችግሮች(በልማዳዊ አመለካከት) ለማውጣት ምን መደረግ እንዳለበት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
መጽሐፉን መግዛትና ማንበብ፤ አንድም እናትን መርዳት ነው፤ ሁለትም ዓለምን ማወቅ ነው።
መማራቸው ከጠቀመን ሰዎች አንዱ ዶክተር ይሁኔ አየለ ናቸውና ያሳቡት ይሳካ እንላለን
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 25 ቀን 2015