መንግሥት ለግንባታው ዘርፍ ቁልፍ የሆነውን የሲሚንቶ እጥረት ለመቅረፍ ሲል በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል:: በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየናረ የመጣውን የሲሚንቶ ዋጋ የተጋነነ ዋጋ እንዳይኖረውና ገበያውን ለማረጋጋት በሚል አማራጮችን በማፈላለግና አዳዲስ መመሪያዎችን በማውጣት ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል:: ይሁን እንጂ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አላስቻለውም::
እንደሚታወቀው መንግሥት የሲሚንቶ ዋጋን ወስኖ በመንግሥት ቁጥጥር ውስጥ በማድረግ ገበያውን ለማረጋጋት ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ምክንያት ሲሚንቶን ከእጁ በማውጣት እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ሲሚንቶ በነጻ የንግድ ሥርዓት እንዲመራ መወሰኑ ይታወሳል:: ይህን ውሳኔ ተከትሎም በተወሰነ መጠን እጥረት ቢኖርም ሲሚንቶ በችርቻሮ መሸጫ ሱቆች መታየት እንደጀመረና የተሻለ ስርጭት እየታየበት እንደሆነ መታዘብ ተችሏል::
ይህን መነሻ በማድረግም በየጊዜው የሚታየውን የሲሚንቶ ገበያ አለመረጋጋት በማስቀረት ብሎም የተረጋጋ ገበያ እንዲፈጠር በሚል ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ ምክክር አድርጓል:: በምክክሩም የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ተቆርጦለታል:: የተወሰነው የመሸጫ ዋጋም ከጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተወስኗል::
በዕለቱ የተገኙት የሲሚንቶ አምራቾች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዱኛ በቀለ የሲሚንቶ ዋጋ ቁጥጥርና ስርጭትን አስመልክተው እንደገለጹት፤ በተያዘው ሳምንት ሲሚንቶ በተወሰነለትና አዲስ በተቆረጠለት ዋጋ የማሰራጨቱና የማከፋፈሉ ተግባር ይከናወናል:: በዚሁ መሠረትም ለመንግሥት ፕሮጀክቶች፣ ለግል ቤት አልሚዎች (ሪልስቴት) ኮንክሪት የማደባለቅ (ሚክስ)የሚሠሩ ድርጅቶችም እንዲሁ ሲሚንቶ በቀጥታ ከፋብሪካው ማግኘት የሚችሉበት የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል::
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የሲሚንቶ ፍላጎት ከ60 በመቶ በላይ በመሆኑ የመሸጫ ዋጋ ተወስኗል:: በዚህ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለው የሲሚንቶ ችርቻሮ ዋጋ ዳንጎቴ ሲሚንቶ በኩንታል 1106 ብር ከ85 ሳንቲም፣ ደርባ ሲሚንቶ 1067 ብር ከ33 ሳንቲም፣ ሙገር ሲሚንቶ 1016 ብር ከ52 ሳንቲም፣ ኩዩ ሲሚንቶ 1065 ብር፣ ካፒታል ሲሚንቶ 1026 ብር ከ35 ሳንቲም መሆኑን መሆኑን የጠቆሙት አዱኛ፣የሁሉም ሲሚንቶ አምራች ድርጅቶች የመሸጫ ዋጋ ከ1200 ብር በታች እንዲሆን እና እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል በተወሰነው ዋጋ ሲሚንቶ ማግኘት የሚያችልበት አሠራር መዘርጋቱን አመልክተዋል:: ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ የክልልና የዞን ከተሞች ጋርም ተደራሽ ለመሆን እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል::
እንደ አቶ አዱኛ ማብራሪያ የሲሚንቶ ምርት እጥረትና የገበያ አለመረጋጋትን ለመከላከል የተለያዩ አማራጮች ሲወሰዱ ቆይተዋል:: በዚሁ መሠረትም የሲሚንቶ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በነጻ ገበያ እንዲመራ በመንግሥት መፍቀዱ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል:: ከጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲሚንቶ በተተመነለት ዋጋ ለገበያ ይቀርባል:: ፋብሪካዎች የማጓጓዣ ወጭን ጨምሮ ያለባቸው ወጪ የተለያየ በመሆኑ ገበያ ላይም የተለያየ ዋጋ ይዘው ነው የሚቀርቡት::
ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ሲሚንቶ እንዲሸጡ የተፈቀደው ትክክለኛ የንግድ ፈቃድ ላለው፣ የሽያጭ ደረሰኝ መቁረጥ ለሚችልና ቋሚ አድራሻ ላለው ነጋዴ ብቻ ነው:: በገበያው ሰንሰለት ውስጥ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎችም ይሳተፋሉ:: አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች በገቡት የውል ስምምነት መሠረት ምርቱን ለሸማች ያደርሳሉ:: ፋብሪካዎች የሚያቀርቡበት እና የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን ለሸማቹ በግልጽ የማሳወቅ ግዴታም ተጥሎባቸዋል:: የመሸጫ ዋጋው ሸማቹ ማየት በሚችልበትና ግልጽ በሆነ ቦታ መለጠፍ ይኖርበታል::
መንግሥት የስርጭቱን ሂደት አስመልክቶ ያወጣውን መመሪያ ያልተገበሩ መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ አዱኛ፤ድርጊቱ አግባብነት የሌለው መሆኑን በመገንዘብ ወደ መደበኛ የገበያ ሥርዓት እንዲመለስ በመደረጉ በሲሚንቶ ግብይት ላይ አሁን እየታየ ያለውን ውጤት ማምጣት ተችሏል ብለዋል:: በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ የሚቻለው አቅርቦትና ፍላጎት ማጣጣም ሲቻል እንደሆነ ጠቁመዋል:: በዚህ ረገድም የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሆነ አንስተዋል:: ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉ አዳዲስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እና የማስፋፊያ ሥራ ውስጥ የገቡ ጥቂት የማይባሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ በምርት አቅርቦትና በዋጋ የሚስተዋለው ችግር ይቀንሰዋል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል::
‹‹ከዚህ ቀደም የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ የተጋነነ ከመሆኑም ባለፈ የምርቱ አለመገኘት ፈታኝ የነበረ ሲሆን፤ ነጋዴው አሁን በተቀመጠው የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ሲሚንቶን ለማኅበረሰቡ የሚያቀርብ ይሆናል:: ለተግባራዊነቱም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቁጥጥር ያደርጋል›› ያሉት አቶ አዱኛ ከመንግሥት በተጨማሪ በዋናነት ፋብሪካዎችም ሆኑ አከፋፋዮች እንዲሁም ቸርቻሪዎች የየራሳቸው ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል::
ከዚህ ቀደም ሲሚንቶን በከፍተኛ መጠን ይፈልጉ የነበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለአብነትም በቤት ልማት ላይ የተሠማሩ በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ሥራ አቁመው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አዱኛ፤ አሁን ላይ በዘርፉ በተደረገው ማሻሻያና የዋጋ ትመና መሠረት ግዙፍ ፕሮጀክቶችና ሌሎችም ሥራ ለመሥራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው የነበሩ የግብዓቱ ተጠቃሚዎች በቀጥታ ከፋብሪካ ሲሚንቶ መግዛት የሚችሉበት ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው አስረድተዋል::
የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋትና ጤናማ የሆነ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር በሚል “በሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር በኩል ይፋ የተደረገው የሲሚንቶ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ድርሻ ምን እንደሆነና ምን ሊሠሩ እንዳቀዱ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ለሆኑት ለወይዘሮ ቁምነገር እውነቱ ጥያቄ አቅርበንላቸው በሰጡት ምላሽ፤የሲሚንቶ ገበያን አስመልክቶ ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር በጋራ በመሆን ወቅታዊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን፣አዲስ በተሻሻለው 940/2015 መመሪያ መሠረት የሲሚንቶ ዋጋ በአምራቹ አንደበት እንዲነገርና አጠቃላይ ያለውን የሲሚንቶ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ይፋ እንዲሆን ተደርጓል::
ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሕግ በተሰጠው ስልጣን፣ተግባርና ኃላፊነት መሠረት አንደኛው የሲሚንቶ ምርት አቅርቦትን መነሻ ያደረገ እንደ አስፈላጊነቱ የግብይትና የስርጭት አሠራር ሥርዓትን መዘርጋት ነው:: ሆኖም በቅርቡ የወጣውና ወደ ሥራ የገባው አዲሱ መመሪያ ለአሠራር ምቹ ባይሆን እንኳን ወደፊት የማሻሻል፣ የመቀየርና ሌላ የተሻለ አሠራር የመዘርጋት ኃላፊነት ተሰጥቶታል::
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ የአሠራር ሥርዓትን ከመዘርጋት ባሻገር አፈጻጸሙን ይከታተላል:: የሚከታተል በተለይም በወጣው መመሪያ መሠረት በትክክል ተፈጻሚ መሆኑን ያረጋግጣል:: በተጨማሪም የፋብሪካ መጋዘን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ መነሻ በማድረግ የጅምላና የችርቻሮ ዋጋ ጣራውን ማውጣቱን መከታተል ሌላኛው ተግባሩ ነው:: ይህንንም ተግብሯል::
በዚህ መሠረትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአሁን ወቅት የሲሚንቶ ምርት አፈጻጸም ስርጭትና የመሸጫ ዋጋ መረጃዎችን በመከታተል ቁጥጥር ያደርጋል:: የክትትልና የግምገማ ሥርዓቱንም እንዲሁ በመዘርጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ይፈታል:: የመፍትሔ ሃሳቦችንም በማምጣት መፍትሔ የመስጠት ሥራም ይሠራል:: ይህ መመሪያ ከተዘረጋ በኋላም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚሁ ሳምንት ከሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፤ የሲሚንቶ ገበያው በተቀመጠው መመሪያ መሠረትና በተቆረጠለት የዋጋ ተመን እየተሸጠ ነው ወይ የሚለውን ክትትል እያደረገ ይገኛል::
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እያደረገ ባለው ክትትልና ቁጥጥርም አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች የተለያዩ ምክንያቶች እያነሱ እንደሆነ የገለጹት ወይዘሮ ቁምነገር፤ ለአብነትም የመሸጫ ደረሰኝ ሕትመት አለመድረስና የቅደም ተከተል ችግር እና ተያያዥ ችግሮች መኖራቸውን እያነሱ እንደሆነ ተናግረዋል:: ይሁንና መመሪያው ከወጣ ገና ሳምንት ያልሞላ ጊዜ በመሆኑ በቀጣይ እነዚህ ችግሮች ተፈተው ሲሚንቶ ያለምንም ችግር በተወሰነለት ዋጋ ሸማቹ ጋር ይደርሳል የሚል ዕምነት ያላቸው መሆኑንና መመሪያው ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮም ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት:: ለክትትልና ቁጥጥሩ የተቋቋመ ግብረ ኃይል መኖሩን በማስታወስም ግብረ ኃይሉ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል::
ክትትልና ቁጥጥሩን በተመለከተ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ይቆጣጠራል:: ግብረ ኃይሉም እንዲሁ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆንም ቁጥጥሩን የሚያደርግ ይሆናል፤ የሚሉት ወይዘሮ ቁምነገር፤ እንደ አዲስ አበባ ከተማ በዋናነት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሚከታተለውና የሚቆጣጠረው ቢሆንም ቁጥጥሩን ለማጥበቅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ይቆጣጠራል ብለዋል:: ክልሎችን በሚመለከትም በየራሳቸው የንግድና የገበያ ልማት ቢሮዎች እንዲቆጣጠሩ አዲሱ መመሪያ የሚያዛቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት::
አስፈላጊውን እና ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ ካልተቻለ መመሪያ ማውጣቱ ብቻ ምንም ፋይዳ የሌለው እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ ቁምነገር፤ ገበያው ላይ ያለውን ሁኔታ በአካል በመዘዋወር በገበያው ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል ብለዋል:: በዚህም በደረሰኝና በትክክለኛው በተተመነው ዋጋ ስለመሸጡ ያረጋግጣል:: ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ካልተቻለ ግን ትርጉም የሌለው ሥራ ከመሆን ባለፈ እንደገና ወደ ነበረበት ዋጋ የሚመለስ በመሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል::
ቸርቻሪዎች ከፋብሪካው በር ሲረከቡ የገቡት ግዴታ ስለመኖሩ በማስታወስም በግልጽ የተቀመጠላቸውን የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በመሸጫ ሱቆቻቸው በሚታይ መልኩ ለሸማቹ እያሳዩ መሸጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል:: ሲሸጡም በደረሰኝ መሆን እንዳለበትና የተሟላ መረጃ በመያዝ ጤናማ በሆነ የግብይት ሥርዓት እንዲመሩ ነው ያሳሰቡት:: በመጨረሻም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለሙያዎችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ዕለት ተዕለት ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል::የሲሚንቶ ገበያን በዋጋ በማሻሻልና ስርጭቱንም ተደራሽ ለማድረግ በተጀመረው የተጠናከረ ሥራ ውጤት ይጠበቃል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2015