ለውጥ በብዙ ገፊ ምክንያቶች የሚከሰት ማኅበረሰባዊ ክስተት ነው። በአግባቡ እና በጥንቃቄ ካልተገራ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ከተስፋው በላይ የከፋ እንደሚሆን በታሪክ በብዙ አጋጣሚዎች ታይቷል። ለዚህ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ያሳለፍናቸው የለውጥ ታሪኮች ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው ።
በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይ ከ1950ዎቹ ጀምሮ( በታሪክ የጄነራል መንግሥቱ ግርግር ከሚባለው) እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦችን ታሳቢ ያደረጉ አገራዊ የለውጥ ንቅናቄዎች ተካሂደዋል።
የ 1950ዎቹ የለውጥ መሻት መፈንቅለ መንግሥትን ታሳቢ ያደረገውም ሆነ በ1960 ዎቹ ፣ አጠቃላይ አገራዊ የሥርዓት ለውጥን መሰረት አድርጎ የተካሄደው የለውጥ ንቅናቄ የታሰበላቸውን ዓላማ ሳያሳኩ አገርን ሕዝብን ብዙ ዋጋ አስከፍለው አልፈዋል።
በ1983 ዓ.ም በትጥቅ ትግል ፍጻሜ ያገኘው የኢህአዴግ የለውጥ ንቅናቄም የተከፈለለትን ከፍ ያለ ዋጋ ያህል አገርና ሕዝብን በተጠበቀውና በታሰበው መልኩ ተጠቃሚ ሳያደርግ በሌላ ሕዝባዊ የለውጥ ማእበል ተወግዶ ዛሬ ላይ በሌላ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ እንገኛለን ።
በመሰረታዊነት ለውጥንና የለውጥ ንቅናቄዎች በብዙ ገፊ ምክንያቶች ከመከሰታቸው አንጻር ፤ የለውጥ ኃይሉ ለእነዚህ ምክንያቶች ትኩረት በመስጠት ለለውጡ ስኬት ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስና ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
ይህ የለውጡን ገፊ ምክንያት ከመረዳት የሚነሳው፤ ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ፣ የሕዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎ መሰረት ባደረገ መልኩ የሚከናወነው የለውጥ ስራ በብዙ መልኩ ለፈተና የተጋለጠ እንደመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ነው።
በአንድ በኩል ለውጡ በጥቅማችን ላይ መጥቷል ብለው የሚያምኑ፤ በሌላ በኩል በለውጥ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ብዥታዎችን የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርገው ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች የለውጡ ዋነኛ ፈተና የመሆናቸው ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
እነዚህ ኃይሎች ፍላጎታቸውን በራሳቸው ማስፈጸም የሚያስችል አቅምም ሆነ ሕዝባዊ መሰረት የሌላቸው በመሆኑ፤ ለለውጡ ፈተና የሚሆነውን ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም አድርገው የሚወስዱት የለውጡ ኃይል የሆነውን ሕዝብ የለውጥ ተስፋ ከልቡ በማውጣት ወይም በመስረቅ ነው።
ይህ እውነታ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በተጨባጭ በአደባባይ የሚታይ እውነታ ከሆነ ውሎ አድሯል። እነዚህ ኃይሎች አገር ስለ ብልጽግና ተስፋ ሰንቃ መንቀሳቀስ መጀመሯን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ዕድገት መሰረት የሆነውን አገራዊ ሰላም በመናጥ ዜጎች በለውጡ የሰነቁትን ተስፋ ለማስጣል ረጅም ርቀት ሄደዋል።
በዚህም ሕዝባችን እንደአገር ለሰነቀው ተስፋ ከፍያለ ዋጋ ለመክፈል ተገድዷል፤ በገዛ ህልሙ ፈቺ ሳያጣ ግራ እንዲጋባና ህልሙ ቅዠት ፤ተስፋው ደግሞ እርግማን እስኪመስለው፤ ዛሬ ብቻ ሳይሆን መጪውም ጊዜ እንዲጨልምበት ብዙ ተሰርቶበታል።
ሕዝባችን እንደ ሕዝብ ከመጣበት የለውጥ ወቅት ተሞክሮ አንጻር አሁን እየሆነ ያለው አገራዊ እውነታ መልኩና አካሄዱ የተለየ ቢመስልውም፤ ዋነኛ የአስተሳሰብ መሰረቱ ለውጡን በመቀልበስ ወደ ትናንቶች ሕዝባችንን መመለስ መሆኑ ብዙም የሚሰወር አይደለም።
አሁን ላይ እንደ ሕዝብ እየከፈልነው ያለው ከፍያለ ዋጋም ቢሆን በለውጡ ለሰነቅነው ተስፋ ስኬት ልንከፍለው የተገባ፤ አገርን ከትናንት ወደ ዛሬ ከማሻገር ባለፈ ትውልዶችን ከተንሰላሰሉ ትናንቶች በመታደግ፤ ዛሬያቸውን በአግባቡ እንዲኖሩ የሚያስችል ነው።
ታሪክ እንደሚዘክረው በየትኛውም ወቅት እና የዓለም ክፍል የተካሄዱ የለውጥ ንቅናቄዎች ያለ መስዋእትነት ስኬታማ አልሆኑም። የለውጥ ንቅናቄዎቼ ለስኬታቸው የጠየቁት መስዋእትነት ክብደትና ቅለት የሚመዘነውም ለውጡ በባለቤቱ በሕዝቡ ዘንድ በነበረው ግንዛቤ ነው።
ስለለውጡ የተሻለ ግንዛቤ የነበረው ሕዝብ በተሻለ መልኩ የለውጡ ባለቤት በመሆን ያለ በብዙ ዋጋ የለውጡ ትሩፋት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ከዚህ አንጻር መላው ሕዝባችን የለውጡ ባለቤት ከመሆኑ አንጻር ፤ለውጡ ከተገዛበት መርህና እንደ አገር ይዞት ከመጣው ተስፋ ላይ ዓይኑን ሳያነሳ ፤ ከሚነፍሱ አሳሳችና አዘናጊ የጥፋት ንፋሶች ከመወሰድ ተቆጥቦ እያንዳንዷን የለውጥ እንቅስቃሴ መከታተልና መደገፍ ይኖርበታል።
አሁን ላይ እንደ አገር ከለውጡ ጋር በተያያዘ እየከፈልነው ያለውን ዋጋ ለመቀነስ ፤ ለውጡም ወደ ስኬቱ እንዲፈጥን፤ ተስፋነቱም የሚጨበጥ እውነታ ሆኖ ለዜጎች የዜግነት የክብር ምንጭ እንዲሆን ለውጡን በተገቢው መንገድ በአገራዊ አውዱ መረዳት ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2015