በተለያየ ጊዜ የተለያየ ስም ቢሰጠውም ተቋሙ ግን አንጋፋ ነው። ለ134 ዓመታት አንድ ጊዜ ከሌሎች ተቋማት ጋር እየተቀላቀለ፤ ሌላ ጊዜ እራሱን ችሎ የኖረ ተቋም ነው። ኢትዮጵያ ተቋማትን ከመገንባት አንጻር ረዥም እድሜ ያስቆጠረች ብትሆንም በአሠራር፣ በአደረጃጀት፣ በቴክኖሎጂ፣ ተቋማት በሚሰጧቸው ፍትሃዊ አገልግሎቶች ጠንካራ የሚባል ተቋም ሳትገነባ የኖረች አገር ነች። ታዲያ በዚህ ውስጥ ካለፉት ቀዳሚ ተቋማት መካከል ጉሙሩክ ኮሚሽን አንዱ ነው። የተቋሙን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፡- ኮሚሽኑ በዋናነት የሚሠራቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው? በተለይ ከሪፎርም ጋር ያሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ አንኳር የሚባለቱን ቢያነሷቸው?
ኮሚሽነር ደበሌ፡– የኮሚሽኑ ዋና ዋና ተልዕኮዎች ተብለው የተቀመጡት በርካታ ናቸው። ከተልዕኮዎቹ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል አንደኛው የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ምርቶችን የጉምሩክ አገልግሎት መስጠት ነው። ሁለተኛው የገቢ ንግድ ሥርዓቱ የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት የመፈጸሙ ጉዳይ ነው። ሦስተኛው ደግሞ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድን የመቆጣጠር ሥራን መሥራት ነው። በተለይ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጫና ስለሚታወቅ አስቀድሞ የኮሚሽኑ ትልቁ ተልዕኮ ተደርጎ በሕጉ የተቀመጠ መቋቋሚያ ደንቡ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ኮሚሽን ባደረጋቸው ሪፎርሞች ምን ለውጦች መጡ?
ኮሚሽነር አቶ ደበሌ፡– ኢትዮጵያ በመንግሥት ምስረታ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረች አገር ናት። በዚህ ረገድ ረዥም እድሜ ካስቆጠሩ አገራት ተርታ ትሰለፋለች። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ገና መንግሥት የሚባል አስተዳደርና ተቋማትን ከመሰረተች ጊዜ ጀምሮ ሰባት ቁልፍ ከሚባሉ ተቋማት መካከል አንደኛው ጉምሩክ ነው። እንግዲህ ከዛሬ 134 ዓመት በፊት ቁልፍ የሚባሉ የመንግሥት ተቋማት ሲመሰረቱ አንዱ የጉምሩክ ተቋም ነበር። ስሙ አንዳንድ ጊዜ በጅሮንድ፣ አንዳንዴም ጉምሩክ፣ አንዳንዴም ጉምሩክና ኤክሳይዝ በሚል ተቀያይሯል።
አንድ ሥርዓት ሲመጣ የነበረውን ያፈርስና ከዜሮ ይጀምራል ፤ ሌላው ሥርዓት ሲመጣም ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማል፤ አንዲህ አይነት አዙሪት ውስጥ የኖርን በመሆናችን ምክንያት ጠንካራ ተቋማትን ሳንገነባ ኖረናል። ይህ ደግሞ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የባሰበት ነበር። በሪፎርሙ ምን ተሠራ? የሚለውን ለማየት ዳራዎችን መመልከት ጠቃሚ ስለሆነ ነው ከኋላ የተነሳነው። ኢትዮጵያ ጠንካራ ተቋም መገንባት ያቃታት ለምንድን ነው? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ አድርገን ነው የተነሳነው።
መከላከያን ጨምሮ ከሰባቱ ዋና ዋና ተቋማት ውስጥ ጉምሩክ አንዱ ነው ከተባለ ለምንድነው ጠንካራ የጉምሩክ ሥርዓት መገንባት ያልተቻለው? የሚለውን ጥያቄ በ2010 ዓ.ም መዳረሻ እና በ2011 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ መነሻ በማድረግ ወደ ሪፎርም ገብተናል። ስለዚህ በአንድ ጊዜ በርካታ የሪፎርም አጀንዳዎችን በማከናወናችን ለውጥ መጥቷል።
የኢትዮጵያን የተቋማት ግንባታ ስብራትን ሊጠግን የሚችል ጠንካራ ተቋም መገንባት ካለብን የምንገነባውን ተቋም ራዕይ መንደፍ ያስፈልግ ነበር። በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ ጉምሩክ የተጠቀሱትን ከላይ የተዘረዘሩ ተልዕኮዎች ለመወጣት ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት ተቋም አድርጎ መገንባት በጣም ያስፈልጋል። ስለዚህ በአንድ ጊዜ በጣም በርካታ የሪፎርም አጀንዳዎችን አብሮ ማካተት ነበረብን። በራዕይ ደረጃ ያስቀመጥነው በ2025 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን የሚያምኑትና የሚተማመኑበት በሁለንተናዊ አቅም የተገነባ ፣ ለዜጎች ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት የሚችል፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያረካ የጉሙሩክ ተቋም ገንብቶ ማየት የሚል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በስትራቴጂ እቅዱ ላይ የተቀመጠው ማለት ነው?
አቶ ደበሌ፡- አዎን! ይህንን በሚገባ መለየት አስፈላጊ ነው። ከጎደሉት ጉዳዮች አንዱ ይህ ነበር። ጠንካራ ተቋም እንገንባ ከተባለ የምንገነባው ተቋም በ2025 ዓ.ም በራዕያችን ልንገነባ ያሰብነውን ተቋም ለማየት በሚገባ ትኩረት ለማድርግ ተሞክሯል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያንን ያረካ ፣ በሁለንተናዊ አቅሙ የተገነባ፣ ማለትም በሰው ኃይል፣ በተቋም፣ በስትራቴጂ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተደራሽነት ወዘተ ጠንካራ ተቋም ገንብቶ ማየት የሚል ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ዝርዝር ስትራቴጂዎች ያስፈልጋሉ። የስትራቴጂ ዶክመንት ማዘጋጀትና በግልጽ ማስቀመጥ በራሱ አስፈላጊና አንዱ የጎደለ ነገር ነበር።
ይህን ተከትሎ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቷል። እንግዲህ የተገኙት ውጤቶች ምንድን ናቸው? ከተባለ አንዱ ይህንን ስትራቴጂክ ሰነድ ወደ ሥራ ማስገባት፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ኮሚሽኑን የሚመጥንና እናስገኛለን የተባለውን እድገት የሚመጥን መዋቅር ማስቀመጥ አንዱ የሪፎርሙ አካል ነበር። እናስገኛለን ያልነውን እድገት የሚመጥን እሱን ሊያሳካ የሚችል መዋቅር ማስቀመጥ ነበረብን። ይህ አንዱ የሪፎርሙ አካል ነው።
የጉምሩክ ሥራ በጣም የተወሳሰበ ስለሆነ ይህም ውስብስብ የሆነውን የሥራ አካባቢ ወይም ባህሪን ሊሸከም የሚችል መዋቅር ምን አይነት ነው? ለተገልጋይ ተደራሽ ሊሆን የሚችል፣ በየሥራ ባህሪያት እና አገልግሎቱ ባሕሪያት የሚተነተን ነው። በቅርንጫፍ ደረጃ ከቅርንጫፍ ውጭም ያሉት ምን አይነት አደረጃጀት ይኖረናል የሚለው በደንብ መጤን አለበት። ምክንያቱም በአገር ውስጥ በጣም በርካታ ኢትዮጵያን በሙሉ የሚያካልል አገልግሎት የሚሰጥ ስለሆነ ኬላዎችን ጨምሮ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ በሁሉም አገር ውስጥ ባሉ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እና በድንበሮቻችን ዙሪያ ከኢትዮጵያ ውጭም ባሉን ሁለት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም ወደፊት የሚከፈቱትን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ጨምሮ ይሄንን ግልጽ ማድረግና የተዘረዘረ ሥራ ማስቀመጥ በጣም ጠቃሚ ስለነበር አንደኛው ትልቁ ሥራ ይሄ ነበር። ራሱን ችሎ በጣም ጥልቅ ሥራና ትልቅ ጊዜ የጠየቀ ስለነበረ ሪፎርሙን የሚሸከመው ይሄኛው መሰረት ነው።
መዋቅሩ ካስቀመጥን በኋላ ደግሞ መዋቅሩ ላይ የሚመደበው የሰው ኃይል እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። መቅጠር፣ ማሰልጠን፣ ማብቃት፣ ማሰማራት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ውጤታማነቱን በዛው እግረ መንገድ ስለሚለካ ነው። ስለዚህ መዋቅር መፍጠር ብቻ ሳይሆን መዋቅሩ ላይ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ በሁሉም አቅጣጫ፣ ቦታዎች፣ የጉምሩክ አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ማዘጋጀት የግድ ነው። ኬላዎች፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ድንበሮች በእነዚህ ላይ ደግሞ በመዋቅሩ በተተነተነው መልክ የሰው ኃይሉን መመደብ፣ ማሰልጠን፣ ማሰማራት፣ መከታተል፣ መደገፍ፣ መሸለም፣ መቆጣጠር የመሳሰሉ ሥራዎች ደግሞ የእዚህ ማዕቀፍ አካል ሆነው እየተሠሩ ነበሩ።
ስለዚህ በተቋሙ መዋቅር እና በተቋሙ የሰው ልማት (human development) ዙሪያ የሠራናቸው ሥራዎች በጣም ውጤታማ ነበሩ። አንደኛው ወሳኝ ሥራ ይሄ ነው። ሁለተኛው ጉምሩክ በባሕሪው አገልግሎት የሚሰጥባቸው የስራ አካባቢዎች አንደኛ ከስፋቱ አንጻር እና የሥራ አካባቢው ውስብስብነት በጣም ትልቅ ነው። ስለዚህ ለሁለት ነገሮች በሚገባ መገዛቱን ማረጋገጥ አለብን። አንደኛ የአገር የወደብ (port) ፍላጎት አለ። ጉምሩክ የተሰጠውን አገልግሎት በብቃት እንዲያገለግል የመንግሥት የወደብ (port) ፍላጎቶች አሉ። መንግሥት የሚከተለውን የሪፎርም አጀንዳ (የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል) ስለዚህ ቀጥታ የኢምፖርትና የኤክስፖርት አገልግሎቱ ደግሞ ለእነዚህ የመንግሥት ፖሊሲዎችና የመንግሥት ፍላጎቶች ቀጥታ አወንታዊም አሉታዊም ተጽኖ አለው።
ስለዚህ አንደኛው ይሄንን የሚሸከም አሠራር ሊኖር ያስፈልጋል። ሁለተኛ ይሄ ብቻ ሳይሆን ደግሞ ዓለምአቀፋዊ በሆነ ሁኔታ ዓለም አቀፍ የጉምሩክ ሥርዓቶች ደግሞ አሉ። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጉምሩክ ህብረት አባል ስለሆነች ከዚህ አኳያ የሚፈለግብን ወይም የሚጠበቅብን ሥራ አለ። የምናወጣቸው ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሠራሮች በሙሉ ለዓለም አቀፍ የጉምሩክ ህብረት ሥርዓት (vena convention or revised croton convention) የተገዛ የሕግ ማዕቀፍና ሥርዓቶች ሊኖሩን ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በርፎርሙ ከተሰሩ የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ ዓለም አቀፍ ሕጎች እና ድንጋጌዎችን መጠበቅ አንዱ ነው። ኢትዮጵያን በቀጣናው ወደብ የሌላት አገር ናት። በዚህ ላይ ምን እየተሰራ ነው?
ኮሚሽነር ደበሌ፡- ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከአወቃቀሩ ጀምሮ ለምሳሌ ነገ ኤርትራ ወደቦች ላይ አገልግሎት የምንጀምር ቢሆን ኤርትራ ወደቦች ላይ የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ሊሰጥ የሚችለውን አገልግሎት አስቀድመን እኛ በለውጥ ሂደት ሰርተነዋል። ሊኖረን የሚችለውን የትራንዚት ፕሮቶኮል የሰራነው በ2010 እና 2011 ነው። ስለዚህ ያለው እስትረቴጅክ ዕቅዱ በስፋት ነው። ከሁለቱም ሱዳን እና ከኬንያ ጋር የሚኖረንን ከጅቡቲ ጋር ከሶማሊያ ታሳቢ ተደርጓል።
የኢትዮጵያን ጥቅም እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል፤ ከዛም ባለፈ በዓለም አቀፍ ንግዱ ውስጥ ምንድን ነው? የኢትዮጵያ ጥቅሞች ለምሳሌ ነገ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን የጉሙሩክ አሠራርን ማፋጠኑን በመጨመር ሊያመጣቸው የሚችሉ አገልግሎቶች የተባሉት በሙሉ ኢትዮጵያ በየጊዜው የምትፈራረማቸው ስምምነቶች አሉ። ጉዳዮች በተለያየ መንገድ ይተነተናሉ።
በትራንዚት ሥርዓት ውስጥ አንድ ተጓዥ ከጀርመን ተነስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ የምናስተናግደው ስመጣ እንዴት ነው? የእኛ ከስተምስ ሊያገለግል የሚችለው እንዴት ነው? የዋስትና ጉዳዮች ቢያጋጥሙ ማለትም ድንበር ዘለል የሆኑ የዋስትና ጉዳዮች ቢያጋጥሙ መሰል ነገሮችን አንድ በአንድ ለቅሞ ነው የሰራው። ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት የምታስገባቸውም ሆነ ወደ ውጭ የምትልካቸው ዕቃዎች ጎሮቤቶቻችን ላይ ያሉ ወደቦችን በትክክል በመጠቀም በተለይ የእኛ የማመቻቸት እና የቁጥጥር ሥርዓታችንን የዘመነ የተተነተነ መሆን አለበት።
የዜጎችን መብት የገፋ፤ አንቀጾችን በሙሉ በማስወገድ በአዲስ መልክ ያሻሻልናቸው አሉ። ለአብነት ከስተምስ አዋጅ ማሻሻያ 1160/2011 በዚህ የሪፎርም አጀንዳ ሂደት ውስጥ የሠራነው አንዱ የሕግ ማዕቀፍ ነው። ከዛ በኋላ በጣም የተተነተኑ ስድስት ደንቦችን አንድ ላይ ያጠቃለለ የጉምሩክ ደንብ የተተነተነ ነው።
በጣም በርካታ ፕሮሲጀሮች አሉ። እነዚህ ፕሮሲጀሮች ትራንዚት ለማሳለጥ የመጋዘን አገልግሎትን ለማቀላጠፍ፤ ክሪላንስን ለማሳለጥ ወጪም ገቢን የክሪላንስ ሥርዓቶችን ለማሻሻል የተወሰዱ ናቸው። ይሄን መሥራት ብቻውን በቂ ስላልሆነ የሰው ሃይሉን ማሰልጠን ማብቃት ያስፈልጋል። አሁንም ይሄ ብቻውን በቂ አይደለም። የምንሰጣቸው አገልግሎቶች በጊዜ የተለኩ መሆን አለባቸው።
እያንዳንዱ በኢምፖርትም በኤክስፖርትም የምንሰጣቸው አገልግሎቶች የተለኩ እና ስታንዳርድ ያላቸው መሆን አለባቸው። በዛ መሰረት ደግሞ አገልግሎት የተሰጣቸው ስለመሆኑ እርካታን ያረጋገጠ ስለመሆናችው መለካት አለባቸው። ከአገልግሎት ተቀባዩ አንፃር መለካት አለበት። እንደዛው ደግሞ ከማናችንም ውጭ በሆነ መለኪያ በዓለም ባንክ (ኤልፒአይ or logistics performance index) በሚለው ዓለም አቀፍ መለኪያ ይለካሉ።
በተጨማሪ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ሁሉንም ተቋማት የሚለካበት በጣም በርካታ የተተነተኑ መለኪያዎች አሉት። እነዚህ የሪፎርም ሥራዎች ተቋማትንም ጭምር የሚለኩ ናቸው። አንድም በተገልጋዩ ይለካል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከኛ ውጭ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይለካል።
ሶስተኛ ደግሞ የኢትዮጵያ ተቋማትን የጥራት ደረጃ በሚለካ ተቋም ወይም በኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ይለካል ማለት ነው። በነዚህ ሁሉ የሪፎርም ሥራዎች ይለካሉ። በነዚህ ሁሉ መለኪያዎች ደግሞ ኮሚሽኑ ወደፊት እንደመጣና በየዓመቱ ተሸላሚ እንደሆነ እያየን ነው። ስለዚህ አንዱ የኦፕሬሽን ሥራዎቻችን የምንመራበት የሪፎርም ዝርዝር ወይም አጀንዳዎችን ሠርተናል። እዚህ ውስጥ አንዳንዱን ለመጥቀስ ያህል ቴክኖሎጂን እናንሳ፤ ከስተምስ ያለ ቴክኖሎጂ የትም ሊደርስ አይችልም።
አንዱ ባለፈው ሥርዓት ውስጥ የነበረው ስብራት ለውሳኔዎች ኢ-ፍትሃዊነት ለማጭበርበርም ለሌብነትም ለኢ-ተገማችነትም ለዜጎች የእንግልት ምንጭ ነበር። አገልግሎቶች የሚሰጡት በምን ልክ ነው በየትኛው ቴክኖሎጂ፤ የሚሉት ነገሮች አልተመለሱም ነበር። ሪፎርሙ ይህንን መልሷል። በቴክኖሎጂ ረገድ ከኢትዮጵያ ወደፊት ከሄዱ ተቋማት መካከል አንደኛ ሆኗል። ዛሬ ኦን ላይን ከስተም አገልግሎት ወይም ወረቀት አልባ አገልግሎት ነው የምንሰጠው። ይህም በብዙ አካላት የተመሰከረ ነው። የተመሰከረበት አግባብ ደግሞ ይሄንን ሥርዓት እኛ ነን ያለማነው።
በቴክኖሎጂ ረገድ ብዙ ለውጦች መጥተዋል። ይህ በጣም ትልቅ ነው። የኢትዮጵያን የከስተምስ ማኔጅመንት ወይም አስተዳደር ሥርዓትን ተግባራዊ ስናደርግ አንደኛ ቢፒኤ (business analysis) እራሱ የኛ መሆኑ አንዱ ትልቅ ዲፓርቸር ነው። ሁለተኛ ሁሉንም አገልግሎቶች በዚህ ቴክኖሎጂ መስጠት ችለናል።
ሶስተኛ ይህ ቴክኖሎጂ የከስተምንም የአገልግሎት ሥርዓትንም በማረቅ የተገልጋዮችንም ጊዜ፣ ገንዘብና ሀብት በመቆጠብና የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ አንድ ትልቅ ዲፓርቸር ፈጥሯል። ዛሬም በመላ አገሪቷ በሙሉ ሰው ቤቱ ላይ ሆኖ ኮምፒተርና የእጅ ስልኩን ተጠቅሞ አገልግሎቱን የሚያገኝበት እድል ተፈጥሯል።
ሌላው አንዱ የሚያከራክረው ቴክኖሎጂ ውስጥ ለአብነት ዋጋ ነው። የዕቃዎች ዋጋ በዓለም ደረጃ አከራካሪና አጨቃጫቂ ነው። ከዚህ ቀደም እንደዚሁ በግለሰቦች ፍላጎትና ግምት ይሠራ ነበር። ትንሽ ሻል ባለመልክ ደግሞ ወደ ሲዲ የተቀየረበት (ዋጋዎች ከዓለም አቀፍ የዋጋ ምንጮች የተሰበሰቡ በሲዲ ተደራጅተው በሲዲ ላይ በተገለጸው ዋጋዎች ዋጋ ይወሰን የነበረበት)። ይሄንን በሌላ አሠራር ወይም ሪፎርም መተካት ያስፈልጋል። በዚህም በጣም ተገማች የሆነ ተአማኒና ሕጋዊ የሆነ አንዱ ከደንባችን ስለሚፈልቅ በደንባችን የዕቃዎችን ዋጋ የሚተምነው ጉምሩክ ነው ስለሚል እንዴት ነው። ይሄንን የምንተምነው ዝምብለን ሲዲውን ዲፕሊኬት እያደረግን ነው። የውስጥ ደግሞ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ አለብን የሚል ነው። ይሄ የኢሲቬስ ኢትዮጵያ ሥርዓት (Ethiopian customs variation system) ብለን የምንጠራው ቴክኖሎጂ አልምተን ዋጋዎችን በዚህ የቴክኖሎጂ መረጃ ቋት ላይ አደራጅተን አንድ ጊዜ በሁሉም ቅርንጫፎቻችን ኦን ላይን እነዚህን ዋጋዎች እያየ ባለሙያዎቻችን፣ የሥራ ኃላፊዎች ወዘተ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ የሠራንበት በጣም አንዱ ትልቅ ሪፎርም ነው። ምክንያቱም ዋጋ እጅግ እጅግ መሰረታዊ ነገር ስልሆነ። ይህም በቴክኖሎጂ ከሚካተቱ ሥራዎቻችንና የሪፎርም አጀንዳዎቻችን አንዱ ነው።
ሌላው የአንድ መስኮት አገልግሎት (single window) የሚባለው ነው። በኮርያውያን በባለሙያም እንደገናም ደግሞ በካፒታልም የተወሰነ ድጋፍ ወይም ኢንጀክሽን አለን። ከዛ ውጭ ግን ሙሉ በሙሉ ቢዝነስ አናሊስሱ በኛ ነው የተሠራው። ዛሬ በጣም በርካታ የመንግሥት ተቋማትን በአንድነት ያሰባሰበ ከስተምስን በባለቤትነት የሚመራው የጉምሩክ አንድ መስኮት አገልግሎትን ሥርዓት ተግባራዊ ያደረግንበት ሁኔታ ነው ያለው።
የአደጋ አስተዳደር (risk manegment) ሥርዓት፣ እንደዚሁ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት እያለማን ያለነው በቅርቡም ሥራ ላይ ልናውል የምንችለው የካርጎ ትራፊክ ሲስተም (cargo traffic system) አንዱ ቴክኖሎጂ ነው። ኢአይ (customs artificial intelligent) ቴክኖሎጂዎችን የተለያዩ ዲስትራክቲቨ ቴክኖሎጂዎችን የዚሁ አካል አድርገን ለመጠቀም እየሠራን ያለነው። በአጠቃላይ በቴክኖሎጂ ማዕቀፍ እጅግ እጅግ በሚያስደምምም ሁኔታ ለውጥ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ቴክኖሎጂ በመጠቀማችሁ በቁጥር ሊገለፅ የሚችል የአገር ሀብት ማዳን ተችሏል?
ኮሚሽር ደበሌ፡- በእርግጥ ይህ በየዓመቱ ይለካል። እኛ ብቻ ሳንሆን በኤልፒአይ (Logistics Performance Index) የዓለም ባንክ ባለሙያዎች እና ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች፣ ለምሳሌ ከእኛ ውጭ በሆኑ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሚያስተባብረው አካል ምን ውጤት እንዳመጡ ይለካቸዋል። ባለፈው ዓመት፣ በአንድ ዓመት ብቻ በዋጋ ደረጃ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን የተቻለ መሆኑን በዘርፉ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ባለሙያዎች ያረጋገጡትና ምስክርነት የሰጡበት ነው።
አንደኛ ጊዜ ቆጥቧል። ሰው አገልግሎት ለማግኘት በርካታ የመንግሥት ተቋማትን ያማትራል። ለምሳሌ እስክሪብቶ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚፈልግ አካል የራሱ ስልክ ላይ ሆኖ ድክሌር ማድረግና ፍቃድ እና ማረጋገጫ ለማግኘት ወደ ተለያዩ ተቋማት መሄድ ሊጠበቅበት ይችላል። ስለዚህ ይህን ለማድረግ ከቤቱ ይወጣል፣ መኪና ካለው ነዳጅ ይመድባል፣ ጊዜ ይመድባል፣ እነዚህን ሁሉ አድርጎ በጊዜም ላያገኝ ይችላል። ስለዚህ ለኢምፖርተሮችም ለኤክስፖርተሮችም ከፍተኛ ጊዜ ቆጥቦላቸዋል።
ሁለተኛው ደግሞ በዚህ ምክንያት ያወጡ የነበረውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ቆጥቦላቸዋል ብለን ነው የምናምነው። ሰው ከራሱ ኮምፒዩተር ላይ ሆኖ የሚፈልገውን እቃ ዲክሌር በማድረግ ከጉምሩክ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል አሰራር መንገድ ተፈጥሯል። ይህ ትልቅ ነገር ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ይህ ሪፎርም ከቴክኖሎጂ ወጣ ብሎ በጣም በርካታ ማሻሻያዎችን አድርጓል። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ግልጽ ያልነበሩ እጅግ በርካታ አሰራሮችን በማስወገድ ግልጽነትን ፈጥሯል። ለምሳሌ መረጃን ቀድሞ የማግኘት መብት። አንድ ሰው አንድ እቃ ከመምጣቱ በፊት ቀድሞ መረጃ ማግኘት ካለበት ጉምሩክን ጠይቆ አስቀድሞ መረጃ ያገኛል። ይህ ደግሞ ብዙ ነገር ያስቀርለታል። ‹‹ልግዛው›› ወይንስ ‹‹አልግዛው›› የሚለውን አስቀድሞ ለመወሰን ያስችለዋል።
መቻሉንና አለመቻሉን ወስኖ፣ የሚችል ከሆነ ይገዛዋል፤የማይችል ከሆነ ደግሞ ጊዜ ጠብቆ ይገዛዋል። ይህ አሰራር ከዚህ ቀደም አልነበረም። ምክንያቱም ሰዎች ይህን መረጃ ይደብቁና ይህን መረጃ ለመፈለግ ሲባል አላግባብ ይከፍላሉ። ስለዚህ ግልጽነትን በመፍጠርና ሰዎች የሚፈልጉትን መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ረድቷል። ይህ አንዱ በሪፎርሙ ውስጥ የመጣው ነው።
አዲስ ዘመን፡- የዓለም ገበያ በሚዋዥቅበት በዚህ ወቅት ጉምሩክ ገቢና ወጪ ምርት ላይ በሚሰራው ሥራ የኑሮ ውድነት በማቃለል ላይ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አለው ተብሎ ይታመናል። በዚህ ላይ ኮሚሽኑ ምን እየሠራ ነው?
ኮሚሽር ደበሌ፡- አንዱ ሥራችን አሰራሮችን ማፍታት ነው። ይህ ደግሞ የዜጎችን ጊዜ እና ገንዘብ በመቆጠብ ሚና አለው። በዚህ ላይ ንቁ ሆኖ መስራት ይገባል። አሰራርና ሂደት፣ ደንብና መመሪያ ብሎም እያንዳንዱ ተግባር በዜጎች ላይ የራሱ የሆነ ሚና አለው ብለን እየሰራን ነው። በግልጽ ለመናገር እኛም በዚህ ደረጃ በዝርዝር እየሰራን ነው። ለምሳሌ ከሪፎርሙ በፊት የነበረው አዋጅ 622 ነበር። ይህን ተከትሎ ደግሞ ሌላ አዋጅ ነበር። እነዚህ የየራሳቸው ጥቅምና ድክመት ነበራቸው። በ622 እቃ ደረቅ ወደብ ለይ የሚቆይበት ጊዜ አያስቀምጠውም።፡ በመሆኑም በሪፎርሙ በአዋጁ ያካተትነው 829 ነበር። እቃ ወደብ ላይ ሲቀመጥ በቆየ ቁጥር ጊዜ ይገዛበታል፤ በዚያውም እየተወደደ ይሄዳል። በተጨማሪም የተለያዩ ወጪዎች ስለሚኖሩ በወደብ ላይ ባለው ቆይታ የሚኖረውን ወጪ አስመጪዎች ተጠቃሚዎች ላይ ይጭናሉ። ይህን ገምግመን መፍትሄ አስቀመጥን። በመሆኑም በደረቅ ወደብ ተጓጉዞ የመጣ ዕቃ በ15 ቀናት ውስጥ ወደ ገበያ አሊያም ልማት መግባት አለባቸው።
በካርጎ ተርሚናል ወይም በአየር መንገድ በኩል የመጣው ደግሞ መቆየት ያለበት 10 ቀናት ብቻ መሆን እንዳለበት በአዋጅ ጭምር የተቀመጠ ነው። ይህን ስንወስን ደግሞ የምንሰጠው አገልግሎት መስጠት አለብን። ለምሳሌ እቃ ወደብ ላይ ሲደርስ ጉሙሩክ በኦን ላይን ለባለንበረቱ ያሳውቃል። እንደየስራ ባህሪያቸው ለዚህም ያደረጀናቸው የሥራ ክፍሎች አሉን። ይህ አንዱ ሎጂስቲክስን የምንደግፍበትና የኑሮ ውድነትን የምናቃልልበት መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እዚህ ጋር በደረቅ ወደብ ለሚመጡ 15 ቀናት በአየር ለሚመጡ ደግሞ 10 ቀናት ብለዋል። ነገር ግን ደንበኞች ንብረታችን እየጠፋ ነው ይላሉ። እነዚህን ነገሮች ለማስቀረት የሔዳችሁበትን ቢገልፁልኝ?
ኮሚሽነር ደበሌ፡- ጉምሩክ ጋር እቃ አይጠፋም። ምክንያቱም ዕቃው የሚጓጓዘው በአየር ከሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕቃውን በሰነድ ተረክቦ ያጓጉዛል። በመቀጠል በራሱ መጋዘን ይከታል። አሰራሩ ይሔ ነው። በዚህ መንገድ ላይ ዕቃዎች የሚጠፉ ከሆነ ዕቃውን መክፈል ያለበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። በዚህ ዓይነት ተጓጉዞ አየር መንገዱ ለግምሩክ ካስገባ በኋላ ደግሞ በሰነድ ርክክቡ ይፈፀማል።
አዲስ ዘመን፡- ከተረከባችሁ በኋላ ከግምሩክ ዕቃ አይጠፋም?
ኮሚሽነር ደበሌ፡- በፍፁም አይጠፋም፤ የምንጠይቅበት ጥብቅ ሥርዓት አለ። የምንመዘግብበት፣ ለባለቤቱ የምናስረክብበት ግልፅ ሥርዓት አለ። በየብስ ተጓጉዞ የሚደርስም ካለ ተመሳሳይ ነው። የኢትዮጵያ ባህር ሎጀስቲክ ያጓጉዛል። በተመሳሳይ መንገድ መጋዘን አስገብቶ እርሱም ያስረክባል።
አዲስ ዘመን፡- ሌላኛው የኮሚሽኑ ትልቅ ሥራ ኮንትሮባንድን የተመለከተ ነው። በእርሶ አረዳድ መሠረት ኮንትሮባንድ እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ? ለምን?
ኮሚሽነር ደበሌ፡- ኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ንግድ በጣም ፈተና ነው። እንደአገራዊ ትልቅ ተግዳሮት መታየት ያለበት ነው። ወደ ኋላ ሔደን ማየት ጠቃሚ ነው። ከሪፎርሙ በፊት ኮንትሮባንድ ውስጥ ብዙ እጁን ከቶ የሚሰራ ስለነበር ያዝኩ የሚለውም፣ የሚጠቀመውም ይኸው ወገን ስለነበር ወደ መገናኛ ብዙሃን አይወጣም። ከሪፎርሙ በኋላ ኮንትሮባንድ አጀንዳ የሆነበት ትልቁ ሚስጢር አንደኛ ነባር በሽታ ስለነበር፤ ነባሩ በሽታ ወደ መድረክ መጥቷል። በዚህ ምክንያት በፊት ተሸፍነው የኖሩ ኮንትሮባንዲስቶች በግልፅ መጥተዋል። ከዚያ ፍጥጫ እና ግርግር መጣ። ይህን የመጣውን ግርግር ተከትሎ፤ በዚህ አጋጣሚ እንጠቀማለን ያሉ በከፍተኛ ደረጃ መሰማራት ጀመሩ። ዘርፎ እና አስዘርፎ መክበር የተለመደ እንደነበር ይታወሳል። በመሆኑም ግርግር ለሌባ ያመቻል፤ እንደሚባለው በወጪ ንግድ ኮንትሮባንድም ሆነ በገቢ ንግድ ኮንትሮባንድ ላይ በስፋት መሠማራት ጀመሩ።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ በጠረፍ አካባቢዎች በሱዳን፣ በሞያሌ እና በቶጎ ጫሌ፣ ፍተሻዎች ላይ አፋር እና በሌሎችም አካባቢዎች አሁንም ድረስ ያልጠሩ ነገሮች የሉም?
ኮሚሽነር ደበሌ፡– እመጣበታለሁ። ያለፈውን እንደመነሻ ለመጥቀስ እንጂ ዛሬም ቢሆን ኮንትሮባንድ የአገራችን አንደኛው ጠንቅ ነው። የኢንቨስትመንቱ፣ የንግድ ሥርዓቱ አጠቃላይ ለሕጋዊ ንግድ ሥርዓቱ በጣም ጠንቅ የሆነ ከፍተኛ ተግዳሮት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ምን እየተሠራ ነው የሚለውን ዓይተን እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ ነው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። ከ2011 ዓ.ም ጀምረን በጣም በከፍተኛ ደረጃ የፀረ ኮንትሮባንድ ንቅናቄው ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን እያደገ የመጣበት እና መቆጣጠር የተቻለበት ጊዜ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ያለማጋነን ለውጡን ተከትለን በወሰድናቸው የመቆጣጠር እርምጃዎች ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል።
የተቆጠሩ ውጤቶች መጥተዋል። ይህን በመረጃ አስደግፈን ማቅረብ እንችላለን። ለምሳሌ 2011 ላይ ኮሚሽኑ አጠቃላይ ገቢ ወጪ ሕገወጥ ንግድን እና በህጋዊነት ሽፋንም የነበረውን ኮንትሮባንድ የመቆጣጠር አቅሙ 9 ነጥብ8 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ቁሳቁሶችን ለመቆጣጠር ተችሏል።
2012 ዓ.ም ላይ ግን የመቆጣጠር አቅማችን ወደ 26 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመቆጣጠር ተችሏል። በ2013 ዓ.ም ደግሞ የመቆጣጠር አቅማችን ወደ 36 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር አድጓል። 2014 ዓ.ም ደግሞ 50 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ 2015 ዓ.ም ላይ በስድስት ወር ውስጥ ብቻ 40 ነጥብ 7 ቢሊዮን መቆጣጠር ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ በሁለት እና በሶስት እጥፍ ያደገ ነው። ኢትዮጵያ በኮንትሮባንድ አደጋ ውስጥ ናት ማለት ነው?
ኮሚሽነር ደበሌ፡– ይህ ሁለት ጉዳዮችን ያመለክታል። አንደኛው አገሪቷ በገቢም ሆነ በወጪ ኮንትሮባንድ በከፍተኛ ደረጃ የምትፈተን መሆኑን ያሳያል። ሌላው ደግሞ በርትተን ስንሰራ ውጤት እንደምናመጣበት የሚያሳይ ነው። የኮንትሮባንዲስቶቹ ስፋት እና ጉልበት እንዲሁም አደገኝነቱ በዛው ልክ አለ። ስጋቱ እና ተግባሩ ቢኖርም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሠራው ስራ እያደገ መምጣቱንም የሚያሳይ ነው። ለየብቻ ማየት ይቻላል። ለምሳሌ የገቢ ኮንትሮባንዱን ራሱን አስችለን ማየት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ለየብቻ እንያቸው?
ኮሚሽነር ደበሌ፡- ከላይ የጠቀስነው ገቢ ኮንትሮባንድ፣ ወጪ ኮንትሮባንድ እና በሕጋዊ ንግድ ሽፋን የሚፈፀመውን አጠቃላይ ነው። ከዚህ ውስጥ የገቢ ኮንትሮባንድን ብቻ ስናይ በ2011 ዓ.ም 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም ደግሞ 2 ነጥብ 14 እንዲሁም በ2014 ዓ.ም 4 ነጥብ 284 ቢሊዮን ነበር። ዘንድሮ በ2015 ዓ.ም በግማሽ ዓመት 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስን መቆጣጠር ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ይህቺ አገር ወደብ የላትም። ይህን ያህል ኮንትሮባንድ እንዴት ተስፋፋ? ይህ የአገረ መንግሥት ስጋት አይሆንም፤ የእናንተ ትንተና ምንድን ነው?
ኮሚሽነር ደበሌ፡– የጀመርኩትን ልዘርዝር እና ወደዛ እገባለሁ። ወጪ ኮንትሮባንድ ማለትም ከአገሪቱ ወደ ውጪ ከሚላከው ምርት ማግኘት ያለባትን ገቢ በማሳጣት ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ስግብግብነት ነው። ስለዚህ በ2011 ዓ.ም 334 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወጪ ዕቃን መያዝ የተቻለ ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም 294 ሚሊዮን ብር የተገመቱ በ2013 ዓ.ም ደግሞ 633 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ወጪ ዕቃዎችን የተቆጣጠርንበት ነው። በ2014 ዓ.ም ደግሞ 836 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዕቃ የተቆጣጠርንበት ሲሆን፤ በ2015 ዓ.ም በስድስት ወር ብቻ አንድ ቢሊዮን 184 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ ለምሳሌ የግብርና ምርቶች፣ ማዕድናት እና የቁም እንስሳት እንዲሁም የፋብሪካ ውጤቶች እና አደንዛዥ ዕፅን ጨምሮ ለመያዝ ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ከአገር ደህንነት እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ካላት ታሪካዊ ጠላቶች አንፃር እንዴት ይታያል? ብዙ አገራት በኮንትሮባንድ ንግድ በአሸባሪዎች አደጋ ላይ ወድቀዋል። በዚህ ደረጃ አይተነዋል?
ኮሚሽነር ደበሌ፡- በእርግጥ አይተን ተንትነነዋል። ለምሳሌ በጦርነቱ ወቅት በየአቅጣቸው የተያዙ የጦር መሳሪዎችን ማየት እጅግ የሚያስገርም ነው። ለመሳሪያዎች ብቻ ራሱን የቻለ ትልቅ ሰነድ አለ። በሌላ በኩል አደንዛዥ ዕፁ ብቻውን ራሱን የቻለ ሰነድ አለ። ሌሎችም ለንግድ ሥራ የሚውሉ ዕቃዎችን የያዘ ሰነድ አለ። አደጋው በጣም ትልቅ ነው። የዚህ ዋናው ምንጭ የማይጠረቃ የኮንትሮባንዲስቶች ፍላጎት ነው። ምክንያቱም ኮንትሮባንዲስቶች ከሕጋዊነትን ይልቅ ሕገወጥነትን ይመርጣሉ።
ሕገወጥነትን ለምን ይመርጣሉ፤ ሲባል አንደኛ ቀረጥ እና ታክስ ሳይከፍሉ ትርፍ ለማግኘት ነው። ጤናማ ያልሆነ መስመርን እንደአንድ የመክበሪያ ዘዴ በመቁጠር፤ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ታክቲኮችን ይጠቀማሉ።
አንደኛው ቦርደሩ ሰፊ ሲሆን ተቋማቶቻችን ደግሞ ደካማ ናቸው። ይህ ዕቃዎችን ለማውጣትም ሆነ ለማስገባት ይጠቀሙበታል። የፌዴራል ተቋማት በወረዳም ሆነ በዞን እንዲሁም በክልልም ሆነ በከተማ ያሉ የመንግሥት ተቋማት በዚህ ደረጃ ተከታትሎ ለማስቆም የሚያስችል ብቁነት የላቸውም። ይልቁኑ በተቃራኒው በመረጃ ወይም በማስተላለፍ ኮንትሮባዲስቶችን መመገብ እና እንዳይጠየቁ በማድረግ ይደግፏቸዋል።
ተቋማት አቅማቸውን ተጠቅመውና ተጠናክረው ሥራቸውን መስራት አለባቸው። ይህ አደጋ በመከላከል በኩል ያላቸው ድርሻ ተከታታይነት እና ተመሳሳይነት የለውም። ብቃቱም የለውም። የሚያዙትም ተመጣጣኝ ቅጣት አያገኙም። በስድስት ወር ብቻ 700 ኮንትሮባንዲስቶች ለሕግ አቅርበናል፤ እነዚህ በሕግ በአግባቡ መጠየቅ ነበረባቸው። ግን እዚህ ግባ የሚባል ቅጣት አላረፈባቸውም። የተያዙት እጅ ከፍንጅ፤ ከምስክሮች ጋር ነው። ግን በተገቢው ካልተመረመሩ ገቢ የክስ ቻርጅ አይደርሳቸውም። ክስ ተገቢ ክስ ካልቀረበ ደግሞ ዳኝነቱ ለመቅጣት ይቸገራል። እነዚህ ነገሮች ተዳምረው ኮንትሮባንዲቶች ጥርስ አውጥተዋል ።
ገበያው ደግሞ ክፍት ነው። ወደ ገበያ የምናቀርበው ምርት እጥረት አለ። የኑሮ ውድነት ላይ ኮንትሮባንዲቶች አሉ፤ ያያሉ። እነዚህ አካላት በሕጋዊ መንገድ የሚገባውን ያውቃሉ። ገበያውን የሚያሟላ ባለመሆኑ ይህን ክፍተት ለመጠቀም ቀረጥና ታክስ የማይከፍሉበትን እቃ ወደ ገበያ በቀላሉ ያስገባሉ። በአሻጥር የሚያግዛቸው አካል ፈልገው እና አሳቻ ወቅት ተጠቅመው ወደ ገበያ ይገባሉ። እነዚህ አካላት ሕጋዊ ነጋዴም በመጣል ለራሳቸው በገበያው ላይ ይነግሳሉ። እነዚህ ሁሉ የገበያ ሥርዓቱን ማየትና ማረም አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል።
እፅ በአስደንጋጭ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ነው። በየብስ እና በአየር እየመጣ ነው። በአገር ውስጥ ደግሞ ካናቢስ እየተመረተ ነው። ይህ በጣም በከፍተኛ ደረጃ አደንዛዥ እፅ ወደ ኢትዮጵያ እየተጋዘ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዕፅ ዝውውር ለኢትዮጵያ አደጋ ደቅኗል ማለት ነው?
ኮሚሽነር ደበሌ፡- አዎ! በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ደቅኗል። ሌሎች አካላት ዳታው ቢጠቀሙበት ጥሩ ነው። ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ያመጣል። በተለይ ጤና ላይ የሚሰሩ አካላት ቢሰሩበትና ቢመራመሩበት መልካም ነው። በርካታ ቤቶች በዚህ ጉዳይ ለማህበራዊ ምስቅልቅል ነው። ተሸፍኖ ይሆናል እንጂ በርካታ ቤተሰቦች በዚህ ጉዳይ ታውከዋል። በየትምህርት ቤቱም አደገኛ ሁኔታ ላይ ነው። ይህ ለኢንቨስትመንቱ፤ ለምርታማነትና ለገበያ አደገኛ ሁኔታ ላይ ይጥላል። በአጠቃላይ ሕግ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ ዕጽ ለአገሪቱ በጣም አደጋ ደቅኗል። በመሆኑም ከታችኛው እርከን ጀምሮ የሚመለከታቸቨው የመንግሥት አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት አለባቸው። ቴክኖሎጂ መጠቀም፤ እርምጃ ማጠንከር፤ ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር ለይደር የማይተው ጉዳይ ነው። የሚመለከተን ሁሉ ሥራችን ነው ብለን ካልሰራን ይህ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል፤ ማህበረሰባዊ ቀውስም ያስከትላል። በእኛ በኩል በጣም በትኩረት እየሰራን ነው። በዚህ ሂደት ብዙ ሰው አጥተናል። በርካታ ባለሙያዎችና የፀጥታ አካላት ሞተዋል፤ አካል ጎድሏል።
አንዳንድ ኮንትሮባንዲስቶች ቀላል አይደሉም። በመኪና ሰው ይገጫሉ፤ ተዋግተው ኬላ ይጥሳሉ፤ በርካቶችን ገድለው ያልፋሉ። ይህ ደቡብ አሜሪካ እና ጣሊያን ያየነው ማፊያ ቡድን የበቀለው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው። በመሆኑም አደጋው አሳሳቢ በመሆኑ በጋራና እና በፅናት ልንዋጋው ይገባል።
ለምሳሌ ማዕድንን ብንመለከት ማግኘት ከሚገባን ገቢ 63 በመቶ ቀንሷል። በጫት ላይ ከፍተኛ ትንቅንቅ አለ። በየቀኑ ከፍተኛ የሆነ ጫት መጠን ይቃጠላል። ይህን አደጋ ለመከላል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በቁርጠኝነት ካልሰሩ እና ሁሉም ኃላፊነቱን ካልተወጣ በጣም ፈታኝ ነው። እጅና ጓት ሆኖ የሚሰራ አካል ካለ አገር ትዳከማለች። የአገር የነውጥ አንዱ ምንጭ ይሆናል። ሕገ ወጦች ሲነግሱ ሕግ ይነጥፋል። ስለዚህ ሕግ ትርጉም አልባ ይሆናል። ጉልበተኞች እንደፈለጉ ከሆነ ትውልድ አደጋ ላይ ይወድቃል። ወደዚህ ምዕራፍ እንዳይደርስ በትጋት መሥራት ይገባል። በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ፣ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ መዋቅሮች፣ የአገሪቱ የደህንነት ተቋማት በመናበብ እየሰሩ ነው። ግን በቂ አይደለም፤ ገና ብዙ መሥራት አለብን። መከላከልና መቆጣጠር ሥራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የኮንትባንድ ሥራ በሚዲያ አዋጅ እና በአንድ ቀን ስብሰባና አይፈታም። በፎቶ ሾው ኮንትሮባንድ መካለከል አይቻልም። ኮንትሮባንድ ቀን ከሌሊት ስለሚኖር የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተደራጅተውና ተናበው መሥራት አለባቸው። ገቢ ንግድ ሥርዓታችን በተመለከተ በስድስት ወር የተገኘው 90 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ታስቦ 87 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።
ይህ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 34 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። ኤክስፖርትን በተመለከተም ባለፉት በስድስት ወራት ውስጥ አንድ ቢሊዮን 554 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል። በስራ ሂደት ውስጥ ብልሹ አሰራር ውስጥ የገቡ ሰራተኞችን ከሥራ እስከማሰናበት የተወሰነ ውሳኔ ተወስዷል። በዚህ ስድስት ወራት ብቻ 446 አመራሮችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል።
አዲስ ዘመን፡- ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ኮሚሽኑ ምን እየሰራ ነው?
ኮሚሽነር ደበሌ፡- በዚህ ላይ በስፋት እየሰራን ነው። ለአገር መከላከያ ሠራዊት፤ የአቅመ ደካሞችን ቤትና የምገባ ማዕከላት መገንባት፣ ገበታ ለአገር፤ ሸገር ፕሮጀክት እና ሌሎችም ላይ በሰፊው እየሰራ ነው።፡ በዚህ ረገድ በስድስት ወራት ብቻ 524 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስና በገንዘብ ደረጃ የማህበራዊ ኃላፊነት ተወጥቷል። ከሪፎርሙ ወዲህ ደግሞ ስምንት ቢሊዮን ብር ለማህበራዊ ኃላፊነት ተወጥቷል።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበረው ቆይታ አመሰግናለሁ።
ኮሚሽነር ደበሌ፡– እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2015