ቴክኖሎጂን መጠቀም ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ ነው። የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በማቅለል ዘመናዊ የአኗኗር ዘዴ እንዲኖር፣ ሥራ እንዲቀላጠፍ፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል እና ሕይወት እንዲሻሻል በማድረግ ቴክኖሎጂ ጉልህ ድርሻ አለው። ሕይወትን ቀለል በማድረግ ቀዳሚ የሆነው ቴክኖሎጂን ተደራሽነት ለማስፋት ታዲያ አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በመዘርጋት አቅርቦቱን ማሟላትና በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያም ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ባለመው እቅዷ ውስጥ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ትኩረት እንዲያገኝ ሆኗል። ዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤታማ እንዲሆን ደግሞ በቴክኖሎጂ የዳበረ እውቀት ያለው ማህበረሰብ መፍጠርን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነና ማህበረሰቡን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ ሥራዎች ላይ ውስንነት መኖሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ምን ይመስላል? ቴክኖሎጂው አድጎ የተፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርስ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? ስንል ላነሳነው ጥያቄ የባለሙያ ምክረ ሀሳብን አክለን የማህበረሰቡን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበናል።
እንደ አገር በቴክኖሎጂ ተደራሽነት የሚፈለገውን ያህል እየተሠራ ባለመሆኑ ገና ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች አሉ በማለት ሀሳቡን ያካፈለን የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ብሩክ መላኩ ነው። እሱ እንዳለው በቴክኖሎጂ መጠቁ የሚባሉ አገራትን ስንመለከት ገና ከሙዓለ ሕፃናት ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች በየደረጃቸው ከቴክኖሎጂ ጋር እራሳቸውን እንዲያስተዋወቁና እንዲለማመዱ ይደረጋሉ። በዚህም ተማሪዎቹ ለቴክኖሎጂ ቅርብ ሆነው ያድጋሉ። ከሚያዩት ተነስተው የተሻለ ነገር ለመፍጠር ለሚያደርጉት ጥረት ሰፊ ዕድል ይፈጥርላቸዋል። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ አገራት አይደለም በሙዓለሕፃናት ደረጃ በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ከቴክኖሎጂ ጋር መተዋወቅ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የለም ይላል።
ይሁንና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እየሰፋ በመጣበት በዚህ ወቅት እንኳ፤ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ አልተቻለም። ለዚህም የመጠቀሚያ መሣሪያዎች የዋጋ ንረት እንዲሁም መሣሪያዎቹ በቀላሉ አለመገኘታቸውና የራስ ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ነው።
‹‹ቴክኖሎጂን መጠቀም ከመነካከት ይጀምራል›› የሚለው ተማሪ ብሩክ፤ በእኛ አገር አንድ ተማሪ እጁን የሚያፈታታበት ኮምፒዩተር ይቅርና የረባ ስልክ እንኳን ሳይኖረው ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት መድረሱ የተለመደ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ ቴክኖሎጂው የሚጠይቀውን መጠቀሚያ ቁሳቁሶች (ዲቫይሶች) ኪስን በማይጎዳ ተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እጅግ ፈታኝ በመሆኑ ነው። በተለይ አሁን ላይ እንደ ዘመናዊ ስልክ፣ ላፕቶፕ፣ ኮምፒዩተር እና ታብሌት የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመግዛት አዳጋች እየሆነ መጥቷል። እንኳን በተማሪ አቅም ሥራ ያለውም ሰው ቢሆን ሊደፍረው በማይችለው ደረጃ ዋጋቸው በየቀኑ እያሻቀበ በመምጣቱ ገዝቶ ለመጠቀም የማይቻል መሆኑን አብራርቷል።
እንደምንም ብለው ኮምፒዩተር ሆነ ላፕቶፕ የገዙ ሰዎችም፤ እንዳይበላሽባቸው እንደክት ዕቃ አስቀምጠው በጥንቃቄ በመያዝ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ብቻ የሚጠቀሙበት እንደሆነ ያነሳው ተማሪ ብሩክ፤ እነዚህ መጠቀሚያዎች በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ከአስፈላጊነታቸው ይልቅ እንደቅንጦት ቁስ እንደሚታይ ነው የተናገረው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት ጥሩ የሚባል ስልክ እንዳልነበረው ያስታወሰው ተማሪ ብሩክ፤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት አገልግሎት ላይ የዋለ ላፕቶፕ በብር 11 ሺ ቤተሰቦቹ ገዝተው የሰጡት መሆኑንም አጫውቶናል።
አሁን ባለንበት ዘመን እንኳን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ይቅርና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የሚሰጡ ትምህርቶች በሶፍት ኮፒ ያሉ በመሆናቸው ያለ ኮምፒዩተር፣ ላፕቶፕ እና ታብሌት የመሳሰሉት መሣሪያዎች ለመማር ከባድ ነው። «ላፕቶፕ ባይኖረኝ ኖሮ ምን እሆን ነበር ብዬ ሳስብ እጅግ ይጨንቀኛል» የሚለው ብሩክ፤ ሌሎች እነዚህ የቴክኖሎጂ መጠቀሚያ መሣሪያዎች የሌላቸው ተማሪዎች አገልግሎቱን ለማግኘት ሲፈልጉ ኮምፒዩተር ላብራቶሪ በመሄድ ወይም በስልካቸው የሚጠቀሙ መሆኑን ይገልጻል። ለዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ የተማሪዎችን የመግዛት አቅም ባገናዘበ መልኩ የሚቀርቡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባለመኖራቸው ከገበያ ላይ ባለው ዋጋ ለመግዛት አቅምን የሚፈትን መሆኑን ነው ያብራራው።
ቴክኖሎጂ ለአገር ዕድገት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደ ላፕቶፕ፣ ታብሌት እና ሌሎችንም የቴክኖሎጂ መገልገያ መሣሪያዎች በአገር ውስጥ ማምረት ቢቻልና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርበበት ሁኔታ ቢመቻች ተማሪ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ሰው ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ያነሳው ተማሪ ብሩክ፤ የሚመለከታቸው አካላት በተለይ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ተቋማት እውን ቴክኖሎጂው አድጎ ማህበረሰቡ ከቱሩፋቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ካሰቡ በዚህ ዙሪያ በደንብ ሊሠሩበት ይገባል ባይ ነው።
ተማሪ እምነት ፈይሳ በበኩሏ አሁን ያለው የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ጥሩ የሚባልና እያደገ የመጣ እንደሆነ በመግለጽ፤ ቴክኖሎጂ ሲያደግ ግን እኛ አብረን ለማደግ የሚያስችሉን የግብዓት አለመሟላት ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሳለች። ‹‹የአንድ አገር ቴክኖሎጂ የሚያድገው የማኅበረሰቡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምም አብሮ ማደግ ሲችል ነው›› የምትለው እምነት፤ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ኢንተርኔት መጠቀም የሚያስችሉ ዘመናዊ ስልኮችን (ስማርት ፎን) የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ውስን መሆኑን፤ ስልኩን ፈልገውትም ይሁን በአጋጣሚ እጃቸው የገባ ሰዎችም ቢሆንም ስልካቸውን በአብዛኛው የሚጠቀሙበት ስልክ ለመደወል እንጂ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሲገለገሉባቸው አይታይም ብላለች። ለዚህም ስልኮቹ ጥንቃቄ የሚሹና በቀላሉ የሚበላሹ በመሆናቸውና አንዴ ከተበላሸ ዳግም መልሶ ለማግኘት ወይም ለመግዛት አቅሙ ስለማይኖር መሆኑን በምክንያትነት አንስታለች።
ዘመናዊ ስልክ ይህንን ያህል ብርቅ ከሆነብን እንደላፕቶፕና ኮምፒዩተር ያሉ የቴክኖሎጂ መጠቀሚያ ቁሳቁሶችን ገዝቶ ለመጠቀም ምን ያህል አዳጋች እንደሆነ ማሰብ አይከብድም የምትለው እምነት፤ እርሷ ተማሪ እያለች ወላጆቿ የመሣሪያዎቹን አስፈላጊነት ተረድተው ስልክም ሆነ ላፕቶፕ እንዲገዙላትና በአንድ አጋጣሚ ሌባ እንደሰረቃት አስታውሳለች። በወቅቱ ታዲያ ስልኩን መልሳ መተካት ብትችልም ላፕቶፑን ግን በድጋሚ መግዛት የሚያስችል አቅም አላገኘችም በመሆኑም በእጅ ስልኳ ብቻ በመጠቀም ትምህርቷን ለመቀጠል ተገዳለች።
ትምህርቱም ሆነ ተግባቦቱ የግድ ኢንተርኔት መጠቀምን የሚያስገድድ እንደሆነ የጠቀሰችው እምነት፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀሚያ መሣሪያዎች የግድ አስፈላጊ እንደሆኑ ነው ያነሳችው። ይሁንና አሁን ባለው የገበያ ዋጋ የመሣሪያዎቹ ዋጋ በየቀኑ እየጨመረ በመሆኑ ቁሳቁሶቹን የራስ ማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ከሁለት ወር በፊት ሳምሰንግ አይፎን ስልክ 15ሺ ብር ጓደኛዋ መግዛቷን በማስታወስ ይህ ስልክ ቢሰረቅ ለመተካት እጅግ ከባድ መሆኑን ተናግራለች።
«የዋጋው ንረት በዚሁ ከቀጠለ ለቴክኖሎጂ እየቀረብን ሳይሆን እየራቅን ወደኋላ መሄዳችን አይቀርም» የምትለው እምነት፤ መንግሥትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የግሉ ዘርፍ ትኩረት አድርጎ መሥራት ቢችሉ መልካም ነው። በተለይም በአገር ውስጥ የሚመረቱበት ሁኔታ ቢመቻች አልያም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበት አማራጮች ቢፈጠሩ መልካም ነው ብላለች።
እንደ ተማሪ ብሩክ ሁሉ፤ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መደረግ ያለበት ከታችኛው የትምህርት ደረጃ መሆን እንዳለበት እምነት አንስታለች። ይህ ማድረግ ሲቻልም ቴክኖሎጂ እያደገ አዳዲስ ፈጠራዎች እየታከለበት ይሄዳል። ኅብረተሰቡም ቴክኖሎጂን የሚሞክርበትና የሚለማመድበት ምቹ ሁኔታ በቀላሉ በመፍጠር ከቴክኖሎጂው ጋር ተዋህዶ በመሥራት ውጤታማ እየሆነ ሥራ መሥራት ይችላል።
ሌላኛው የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት አቶ ተሾመ በፍርዱ በበኩላቸው፤ ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸው ቀርቤታ ሩቅ እንዳልሆነ ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ኮምፒዩተር ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት የወሰዱ ቢሆንም የተግባር ትምህርቱ ላይ ብዙ ልምምድ ሳያደርጉ ከዩኒቨርሲቲ መውጣታቸውን ይገልጻሉ። በሥራ ዓለም ከተቀላቀሉ በኋላ ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን ኮምፒዩተር ለማግኘት ብዙ ወራት መቆየታቸውን ያስታወሳሉ። ኮምፒዩተሩን ከተሰጣቸው በኋላ በራሳቸው ጥረት ያላቸውን የኮምፒዩተር እውቀት እያሳደጉ መምጣታቸውን ነው ያስረዱት።
አሁንም ቢሆን በመስሪያ ቤታቸው ያሉት ኮምፒዩተሮች በቂ አለመሆናቸው ያነሱት አቶ ተሾመ፤ በተለይም አዳዲስ ሠራተኞች ሲቀጠሩ ኮምፒዩተር ለማግኘት የወራት ዕድሜ እንደሚያስቆጥሩም አልሸሸጉም። በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ለሚታየው የእውቀት ክፍተት ሠራተኛው በተገቢው መልኩ የሚለማመድባቸው ኮምፒዩተሮች እንዲሁም ላፕቶፖች እንደልብ ማግኘት አለመቻሉን ገልጸው፤ ኅብረተሰቡም በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የሚፈልገውን አገልግሎት ለማግኘት ቴክኖሎጂ ተደራሽ እንዲሆን የሚረዱ መሣሪያዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የግሎባል ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ አበበ በቀለ በበኩላቸው ቴክኖሎጂ በብዙ መልኩ የሚገለጽ መሆኑን ገልጸው፤ የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂው ተደራሽነት ሰፊ እንደሆነ ያነሳሉ። ለአብነትም ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ ውስጥ እ.ኤ.አ 2021 ከ54 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ማለት የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በየዓመቱ 21 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ በተመሳሳይም የኢንተርኔት አገልግሎት ፈልገው የሚመዘገቡ ተጠቃሚዎች ቁጥር አራት በመቶ ያህል እየጨመረ መምጣቱን ነው ያስረዱት።
አሁናዊ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ኢትዮጵያ ውስጥ 24 ሚሊዮን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ነው ቁጥራቸውም በየዓመቱ ሦስት በመቶ ያህል መጨመሩ የቴክኖሎጂ እድገት ፈጣን እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል። አሁን ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ የሰላም እጦትና የሙስና መስፋፋትና ሌሎች ነገሮች ተደማምረው ወደኋላ ባይጎትቱ ኖሮ ከዚህ በበለጠ ማደግ ይቻላል የሚሉት አቶ አበበ፤ ‹‹ኢትዮጵያ በጣም በጥቂት ጊዜ ውስጥ በቴክኖሎጂ እድገት በሁሉም መስኮች የተሳካላት አገር ትሆናለች›› በማለት ያላቸውን ዕምነት ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እየሰፋ ቢሆንም ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚያስችሉ መሣሪያዎች በቀላሉ ማግኘት የማይቻል መሆኑን ያልሸሸጉት አቶ አበበ፤ የማህበረሰቡን አቅም እየፈተነ መሆኑንም ተናግረዋል። ለዚህም አንደኛ መንግሥት እነዚህ የቴክኖሎጂ መጠቀሚያ መሣሪያዎች አገር ውስጥ የሚመረቱበትን ወይም የሚገጣጠሙበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይገባዋል። ሁለተኛው ከውጭ አገር ሲገቡ ያለውን የቀረጥ ዋጋ በማጥናት ለመቅረፍ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሥራት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል እነዚህ መሣሪያዎቹ ተሟልተው ቢሆንም እንኳን በገጠር አካባቢ ያለው የማህበረሰብ ክፍል ከመብራት አለመኖር እና ከኃይል መቆራረጥ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ችግሮች ለመጠቀም ስለማይችል ይህንን ለመቅረፍ በፀሐይ ብርሃን (በሶላር) የሚሰሩ ላፕቶፖችን መጠቀም የሚቻልበት ዘዴ ከወዲሁ መቀየስ ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በግለሰብ ደረጃ ጥሬ ዕቃውን ከውጭ በማምጣት ታብሌቶችንና ስልኮችን የሚገጣጥም የግል ኢንዱስትሪ እንደነበር አስታውሰው፤ እነዚህ መሣሪያዎች ቢበላሹ ግን አገር ውስጥ መጠገን የሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዳልተሠራ ገልጸዋል። የሌሎች አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራ ብዙም ሳይሰሩ የሚጣሉ ኮምፒዩተሮችን እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻል ነው አቶ አበበ የገልጹት፤ አሁን ላይ ችግር ቢሆንም ወደፊት ከኮምፒዩተር በተጨማሪም ሌሎች ትልልቅ መሣሪያዎችን መገጣጠም የሚያስችል ብዙ እውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና ዕድሎች መኖራቸውን ነው የጠቀሱት።
ለዚህም መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ኅብረተሰቡ በጋራ ተባብሮ ስልኮች፣ ላፕቶፖች እና ኮምፒዩተሮች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ቢቻል የቴክኖሎጂ እድገት ይፋጠናል፤ የእውቀት ደረጃ እያደገ ኅብረተሰቡን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም