አንድ አገር እንደ አገር ለመቀጠልም ሆነ፤ ለዜጎች የተሻለች የመኖሪያ ስፍራ እንድትሆን አገራዊ የፖለቲካ ስክነት እጅጉን ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ፖለቲከኛ ነን ከሚሉ ግለሰቦችና የፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠበቀው ከሁሉም ከፍያለ ነው።
በተለይም እንደኛ አገር የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠርና በዚህ ውስጥ የዜጎችን የዘመናት መሻት እውን ለማድረግ ፖለቲከኞች በራሳቸው ተግዳሮት እየሆኑ ባሉባቸው አገራት ፤ ፖለቲከኞች ራሳቸውንና የፖለቲካ አስተሳሰቦቻቸውን ቆም ብለው ሊመረምሩ ይገባል።
የትኛውም ፖለቲከኛም ሆነ ይዞት የሚነሳው የፖለቲካ አስተሳሰብ በአደባባይ የሕዝብን የነገ ተስፋዎችን የሚጻረር ሆኖ የተገኘበት አጋጣሚ የለም። በታሪክ ዓለምን ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ አምባገነን /ፋሽስት መሬዎች ሳይቀሩ የአደባባይ ዲስኩሮቻቸው የብዙዎችን ቀልብ የሳቡና ከጎናቸው ያሰለፉ ናቸው።
በሕዝቦቻቸው ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋቶችን በመፍጠር፤ ከአለመረጋጋቶቹ ለማትረፍ የሄዱበት የጥፋት መንገድ ለጊዜው ከፍያለ ስኬት ይዞ የመጣላቸው እስኪመስላቸው ድረስ ብዙ ቢያስፈነድቃቸውም በስተመጨረሻ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ያስከፈለሉት ዋጋ ግን የከፋ ነው። የራሳቸውም ፍጻሜ ቢሆን ያማረ አልነበረም ።
በእኛም አገር ላለፉት 60 ዓመታት የሆነው ብዙም ከዚህ የተለየ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። እንደ አገር በነዚህ ዓመታት የተጓዝናቸው ስክነት ያጡ የፖለቲካ መንገዶቻችን ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል። ለታሪካዊ ጠላቶቸችንም እንደ አንድ አቅም ሆነውም ”በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆነውብናል።
አገራዊ የፖለቲካ መድረኩ ስክነት እንዳይኖረው አቅዶ ከመስራት ጀምሮ ፤ በዚህ የጥፋት መንገድ ከሚፈጠሩ ሁከቶችንና ግጭቶች ተጠቃሚ ለመሆን ብዙዎች ወገባቸውን ታጥቀው ረጅም ርቀት ሄደዋል፤ የፖለቲካ መሻታቸውን በንጹሃን ደም ለማወራረድ ያለርህራሄ በጭካኔ ተጉዘዋል።
አንዳንዶች ይህ መንገዳቸው ውጤታማ የሆነ እስኪመስላቸው ድረስ፤ በአሸናፊ እና ተሸናፊ ትርክት ተዘናግተው፤ ይህንኑ የጥፋት መንገድ እንደ አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ አድርገው በመውሰድ አገር ሰላም ነች እየተባለ ሳይቀር ዜጎች የከፋ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርገዋል።
ይህ አገርና ሕዝብን ከነገ ተስፋው ጋር የሚያጋጭ እና እንደ ሕዝብ በነገዎች ላይ ያለውን ተስፋ የሚያቀጭጭ አገራዊ የፖለቲካ ባህል ለመለወጥ የለውጥ ኃይሉ አለመግባባቶችንና ቁርሾዎችን በይቅርታ ለማለፍ የደረሰበት የፖለቲካ ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ አዲስ አገራዊ ተስፋ ሰንቆ መምጣቱ የሚታወስ ነው።
አገራዊ የፖለቲካ መድረኩን በይቅርታ በማስከን የጎደለውን ነገር በውይይትና በንግግር ለመፍታት፤ ይህንንም አገራዊ የፖለቲካ ባህል ለማድረግ የተሄደበት መንገድ ገና ከጅምሩ ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ቀልሎ የሚታይ አልነበረም።
በተለይም በአገሪቱ ሰፍኖ ከኖረው የአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት የፖለቲካ ባህል አኳያ ሊያጋጥመው የሚችለው ተግዳሮት/ፈተና በቂ ጊዜና ዝግጅት መፈለጉ ለጥያቄ የሚቀርብም አልነበረም።
በርግጥም የተፈራው ነገር የአገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ማጣበቡ፤ በጉልበት እንፈታተን የሚል ኃይል መኖሩ ፤አገራዊ ፖለቲካው እንዳይሰክንና ሕዝብን ከሕዝብ እንዲሁም ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ከዚያም በላይ ሕዝብን ከተስፋው ጋር የሚያጣሉ ትርክቶች በዝተው ተገኝተዋል። በዚህም አገራዊ የፖለቲካ መድረኩ ስክነት እንዲያጣ ሆኗል።
በርግጥ አገራዊ ለውጡን ያጋጠሙት ግዳሮቶች ለውጡ ይዞት ከመጣው ከፍ ያሉ የፖለቲካ እሴቶች፤ ከዛም ባላይ በአገሪቱ ተንሰራፍቶ ከኖረው የተዛባ አካሄድና አካሄዱ ሊፈጥረው ከሚችለው የተዛባ አስተሳሰብ አንጻር በቀላሉ ሊገመት የሚችል ነበር።
ይህን ትናንትም ሆነ ዛሬ ላይ ብዙ ዋጋ ያስከፈለን የተበላሸ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለመግራትና ወደጀመርነው አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ /መንገድ ለመመለስ እስከዛሬ የከፈልነው ዋጋ በቂና ከበቂ በላይ ነው። በየዘመኑም በዚህ የፖለቲካ መንገድ የተጓዙ ፖለቲከኞች ከመንገዱ ጥፋት ራሳቸውንም አላተረፉም።
አሁን እንደ አገር ለመቀጠል ሆነ፤ አገራችንን ለራሳችን የተሻለች ለማድረግ አገራዊ የፖለቲካ ስክነት መፍጠር ይጠበቅብናል። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ድርጅቶች ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል ።
ከትናንት ስህ ተት በቅንነት ተምረው ሕዝብንና አገርን ለ መካስ ከራሳ ቸው ጋር ቃል ሊ ገቡም ያስፈልጋል። አገርና ሕዝብን መታደጊያው ተጨባጭ መንገድም ይሄው የሰከነ አገራዊ የፖለቲካ መድረክ መፍጠር ነው!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም