ከያዝነው ከጥር ወር መግቢያ ጀምሮ የአፈርና ጥበቃ የተፋሰስ ልማት ሥራ በመላ ሀገሪቱ ተጠናክሯል:: ከሁለት ወራት በኋላ ለሚጀመረው የበልግ ግብርና ሥራ ዝግጁ ለመሆን ከወዲሁ የተፋሰስ ልማት ሥራ በርብርብ መጠናከር እንዳለበትም የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ:: በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ችግሮች በአፈር መሸርሸርና ለተለያየ ጉዳት ተጋላጭ የሆነ መሬትና ተዳፋታማ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ማድረግ የሚቻለው የተፋሰስ ልማት በማከናወን እንደሆነም ይገልጻሉ:: ወቅቱን ጠብቆ በሚከናወነው በዚህ የተፋሰስ ልማት ሥራ ውጤት የተመዘገበባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ለዚህም በሰው ሰራሽና በተለያየ ምክንያት ለድርቅ ተጋልጦ የነበረውን ሐሮማያ ሐይቅን መጥቀስ ይቻላል::
በውሃ መሳቢያ (ፓምፕ) ከሐይቁ ውሃ በመሳብ የአካባቢው አርሶአደር ለግብርና ሥራ ይጠቀምበት የነበረው ይህ ሐይቅ የመድረቁ ዜና ሲሰማ ከማሳዘንም ባለፈ ለሀገርም እንደውድቀት ታይቶ እንደበር አይዘነጋም:: ችግሩ ከተከሰተ ጀምሮ በተከናወነው በጥናት የተደገፈ የርብርብ ሥራ በተለይ ደግሞ አካባቢ ጥበቃ ላይ የተፋሰስ ልማት የተጠናከረ እንደነበር በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ:: በዚህ የርብርብ ሥራ ላይ አንዱ ባለድርሻ በሆነው ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በደረቀው ሐይቅ አካባቢ ለተከታታይ አስር ዓመታት በተከናወነው የተፋሰስ ልማት የእርከን እና የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃግብር ተከናውኗል::
ይህን መረጃ የሰጡት በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ዳይሬክተር ዶክተር አድማሱ ቦጋለ በ2012 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ መርሃግብር በሐይቁ ዙሪያ 358 ችግኞች መተከላቸውን እንዲሁም ለልማቱ ከዩኒቨርሲቲው ከአምስት ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጭ ይደረግ እንደነበርም ለመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸው ይታወሳል:: በተከናወነው ሥራም ሐይቁ እንዲያገግም በማድረግ የነበረውን የሐዘን ስሜት ወደ ደስታ መቀየር ተችሏል:: ሐይቁን ወደነበረበት ይዞታው ለመመለስ የተጠናከረ ሥራ የሚጠበቅ ቢሆንም ተስፋ ሰጪ ውጤት ማየት መቻሉ በስኬት ተጠቅሷል:: የተፋሰስ ልማት ሥራ ውጤት እንደሆነም ተደርጎ ተወስዷል::
ለሐሮማ ሐይቅ መድረቅ በምክንያትነት ይጠቀስ የነበረውና ችግሩንም ለመቅረፍ ትልቅ ዋጋ ያስከፈለውን ደለል፣ አካባቢው ላይ የነበረው ዛፍ መመናመን፣ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት፣ እንዲሁም ለመሥኖ የግብርና ልማት ሥራ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው የውሃ አጠቃቀም ለማስተካከል በተሰራው ሥራ በተለይም የተፋሰስ ልማት መጠናከር ያስገኘውን ውጤት በመቀጠል በዚህ ወቅትም በሐይቁ እና በሁሉም ምሥራቅ ሐረርጌ እየተሰራ መሆኑን የምሥራቅ ሐረርጌ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ ገልጸውልናል::
እንደ አቶ ጌታሁን ማብራሪያ በሐሮማያ ሐይቅ ዙሪያ በተከናወነው የተፋሰስ ልማት ደርቆ የነበረውን ሐይቅ ወደ ቀድሞ በመመለስ በአሁኑ ጊዜም ሐይቁ 61 በመቶ ውሃ መያዝ እንደቻለ በጥናት ተረጋግጧል:: ቀሪ 39 በመቶ ለመመለስ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጽህፈት ቤቱ በቅንጅት እየሰራ ይገኛል:: በ2014 በጀት አመት የክረምት ወቅት ዝናብ ባለመኖሩ የተገኘውን ለውጥ በመጠኑም ቢሆን ወደኋላ በማስቀረት ተጽእኖ አሳድሯል::ይህንንም ክፍተት ለማካካስ ጭምር በተጀመረው የተፋሰስ ልማት ሥራ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው::
ጥር ወር 2015 ዓ.ም መግቢያ ላይ በተጀመረው የተፋሰስ ልማት ሥራ በሐይቁ ዙሪያ በሚገኙ ወረዳና ቀበሌዎች በተፋሰስ ልማት አሰራር ውጫዊ የሚባለው የእርከን ሥራ ተከናውኗል:: ቀሪው የዛፍ ችግኝ ተከላ ሥራም ይቀጥላል::በምሥራቅ ሐረርጌ በሚገኙ 20 ወረዳዎችና 543 ቀበሌዎች ጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ንቅናቄ ፈጥሮ ወደ ሥራ ከገባ ከ14 ቀናት በላይ ሆኖታል:: በዚህ ጊዜ በ515 አካባቢዎች ላይ የእርከን ሥራዎች እየተከናወነ ነው:: ይህን ጨምሮ ተያያዥ ሥራዎች ለ60 ቀናት ይቀጥላሉ::
ከአቶ ጌታሁን መረጃውን የሰጡን ወደ መስክ ስራ እየወጡ ስለነበር ለምን ሥራ እንደወጡም ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ እርሳቸውን ጨምሮ የጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎች የተፋሰስ ልማቱን ሥራ በስፍራው በመገኘት ድጋፍ ያደርጋሉ::ክፍተት ካለም የማረም ሥራ ይሰራሉ:: ልማቱም በአግባቡ መከናወኑን መረጃዎች ይሰበስባሉ::
የማህበረሰብ ንቅናቄው ምን ያህል የተሳካ እንደሆነና ስለ ሕዝቡም ተሳትፎ አቶ ጌታሁን እንደገለጹት፤ ምሥራቅ ሐረርጌ በመሬት አቀማመጡ ምክንያት ለአፈር መሸርሸር ተጋላጭ በመሆኑ የተፋሰስ ልማት ሥራ ካልተሰራ ልማት ማከናወን እንደማይችል ማህበረሰቡም ስለሚያውቅ ቅስቀሳ ሳያስፈልገው በራሱ የመነሳሳት ባህል አዳብሯል:: ሆኖም ግን የንቅናቄ ሥራው አይቀርም:: በዚህ መልኩ በጥር እና የካቲት ወራት የተፋሰስ ልማቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል:: መጋቢት ወር ላይ የሚጀመረው የበልግ ግብርና ሥራ ውጤታማ የሚሆነው ቀድሞ በተሰራው የተፋሰስ ልማት እንደሆነም አቶ ጌታሁን አመልክተዋል::
ለበልግ የግብርና ሥራ ዝግጁ በሚደረው በዚህ የተፋሰስ ልማት ሥራ ትኩረት በተሰጠው የሐሮማያ ሐይቅ ዙሪያም ከሚከናወነው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በተጨማሪ በአካባቢው የመስኖ ልማት በማከናወን ላይ የሚገኙ አርሶአደሮችም ከሐይቁ የሚጠቀሙትን ውሃ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ሥርዓት መዘርጋቱንና ተጨማሪ ተግባራት መከናወናቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታሁን፤ የውሃ ኩሬዎች በየአካባቢው እንዲመቻች በማድረግ በሐይቁ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ እንዲሁም በአስተዳደር ቁጥጥር የአጠቃቀም ችግርን ለመቅረፍም ጥረት መደረጉን፣ከዚህ ቀደም ከከተማ ተወግደው ቀጥታ ወደ ሐይቁ ይገባ የነበረውን ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ለማስቀረት፣ ደለልን ለመከላከል አስፈላጊ የግንባታ ሥራ በተፋሰስ ልማቱ ተካትቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል::
ምሥራቅ ሐረርጌን ጨምሮ በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ ስላለው የተፋሰስ ልማት ሥራ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የተፈጥሮ ጥበቃ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር እንደሚከተለው አስረድተዋል:: የ2015 በጀት አመት የተፋሰስ ልማት የዝግጅት ምእራፍ ሥራ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲና ምሥራቅ ሐረርጌ ግብርና ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን የተጀመረ ሲሆን፣ በጋራ በተከናወነው የቅንጅት ሥራም አንድ ሺህ 900 ለሚሆኑ የዞን፣ ወረዳና ከተሞች ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል:: ሥልጠናውን የወሰዱት ባለሙያዎችም ሐሮማያ ሐይቅ አካባቢ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል:: ‹‹የልምድ ልውውጡ ዓላማም ሐሮማያ ሐይቅ ደርቆ የልጆች ኳስ መጫወቻ ሆኖ ነበር:: ግን ደግሞ ያጠፋ እጅ መመለስ እንደሚችል፣ በተለይም ሐይቁ አገግሞ መልሶ ለልማትና ለቱሪስት መስህብ ለመዋል እንዴት ዝግጁ እንደሆነ እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ በአሣና በተለያየ መንገድ ሐይቁን የገቢ ማስገኛ አድርጎ መጠቀም ስለመጀመሩና ለሰልጣኞቹ ከዚህ ግንዛቤ አግኝተው ስኬታማ የተፋሰስ ልማት ሥራ እንዲሰሩ ነው::›› ብለዋል::
የተፋሰስ ዝግጅት ምዕራፉም ከሐሮማያ ሐይቅ እንዲሆን የተፈለገው ሐይቁ ለበጋ መስኖ ልማት በመዋል እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብም የሥራ ዕድል የሚፈጥርበት ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ከፍተኛ ተምሳሌት መሆን የሚችል የተፈጥሮ ሀብት ተምሳሌት በመሆኑ እንደሆነም አቶ ኤልያስ ገልጸዋል:: በዚህ ስፍራ ሥልጠና የተሰጣቸው ባለሙያዎች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ለአርሶአደሮች፣አርብቶአደሮችና የልማት ሰራተኞች ሥልጠና መስተጠታቸውንና በአጠቃላይ ሥልጠናው አልሚውንም በልማት የሚደግፈውንም አመራሩንም ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል::
እንደ አቶ ኤሊያስ ገለጻ፤ ‹‹ዓላማው ተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅና መንከባከብ የትውልድ ግዴታ ነው በሚል መርህ በክልሉ ካለፈው ሳምንት ጀምሮም ወደ ትግበራ ሥራ ተገብቷል:: በዚህ መንፈስ በመነሳት 6 ሺ465 ተፋሰሶችን ለማልማት ታቅዷል:: በእቅዱ መሠረትም ወደ 3 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተፋሰስ ልማት ሥራ ይሸፈናል:: ከዚህ ውስጥም አንድ ሚሊዮን 35 ሺህ ኪሎ ሜትር የእርከን ሥራ የሚከናወን ሲሆን፣ በተለይም ድርቅ በሚያጠቃቸው የክልሉ ምሥራቅ ኦሮሚያ ያሉ አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቷል:: ውሃ በብዛት በሚገኝባቸው ምዕራብ ኦሮሚያ ደግሞ ተስማሚ የሆነ የልማት ሥራ ይከናወናል::በተፋሰስ ልማትና በአምስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ወደ 97 ሚሊየን ሕዝብ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል::
በጅምሩም የሕዝብ ተሳትፎ የሚያበረታታ ሆኖ ተገኝቷል:: በበጋው በሚከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃው እና የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ላይ የማህበረሰብ ተሳትፎ በገንዘብ ቢተመን 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ይገመታል:: ለአምስተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ ለአካባቢ ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ 4 ነጥብ 9 በሚሊዮን የተለያዩ የዛፍ ችግኞች ለማዘጋጀት እየተሰራ ሲሆን፣ እስካሁንም 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞች ተዘጋጅተዋል:: ከሚዘጋጀተው ችግኝም ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ፍራፍሬዎችና የቆላና ደጋ ቀርክሃ ልማት ነው::
ከዚህ ቀደም የተፋሰስ ልማቶች መኖራቸውን የገለጹት፣ አቶ ኤሊያስ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይና በተለያየ ምክንያት በክልሉ በተለይም ከሐረርና ወለጋ አካባቢዎች ማህበረሰቡ መፈናቀሉን አስታውሰው፤ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ የአካባቢያቸው በመመለስ ላይ በመሆናቸውንና በየአካባቢዎቹም የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራ አስረድተዋል:: ‹‹በተፋሰስ ማልማት ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ማህበረሰብ በልማቱ ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል:: ቀደም ሲል በተከናወነው የደን ልማት ስራ የደን ሽፋኑ በመጨመሩ የአካባቢው ማህበረሰብ ከዚህ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል ተመቻችቷል›› ብለዋል::
ቀደም ሲል ከነበረው የተፋሰስ ልማት ሥራ የአሁኑን ለየት የሚያደርገውን ምክንያትም እንዳስረዱት አመራሩ ጭምር የተሳተፈበት መሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አርሶአደሩ ከልማቱ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩ በራሱ ለልማቱ መነሳሳቱ፣የመሬት ምርታማነት ብቻ ሳይሆን አርሶአደሩ ከምርቱ ባገኘው ገቢ የአኗኗር ዘይቤውን ለመቀየር አስችሎታል::
የአካባቢው ማህበረሰብ ያለማውን ጠብቆና ተንከባክቦ መልሶ ለራሱ ጥቅም ለማዋል ሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት እንጂ ከአካባቢው እንዲሰደድ መሆን የለበትም ሲሉም አቶ ኤሊያስ ገልጸዋል:: የሰብል ልማት ብቻ ሳይሆን ንብ በማነብ፣ በእንስሳት እርባታ በመሳተፍ ሌሎች የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችንም በመጠቀም ጭምር ኑሮውን እንዲያሻሽል ማድረግ እንደሚገባና በዚህ አቅጣጫ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል:: ሰፊ ቁጥር ያለው የሕዝብ ተሳትፎ እንዲኖር የታቀደውም እነዚህን የልማት ጥቅሞች ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም አመልክተዋል::
በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች አሁንም በስጋትነት የሚነሳ የፀጥታ ጉዳይ ለተፋሰስ ልማቱ ተጽእኖ አያሳድርም ወይ? ለሚለው ጥያቄም አቶ ኤልያስ በሰጡት ምላሽ፤ እቅዱ ሁሉንም የክልሉን አካባቢዎች ያካተተ ሲሆን፣ የፀጥታው ስጋት የልማቱን ሥራ ያደናቅፈዋል የሚል እምነት አለመኖሩንም አቶ ኤሊያስ ገልጸዋል::
ለምለም ምንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም