ሁላችንንም በሚያግባባ መልኩ ሙሰኞች የአገር ጠላቶች ናቸው:: እንደ ነውረኛ ዜጋ፣ እንደ ሙሰኛ ባለሥልጣን አገር የሚጎዳ ነገር የለም:: ከትናንት እስከዛሬ አገራችንን እየተፈታተነ ያለ አንዱና ዋነኛው ሙስና ነው:: ሙስና ገንዘብ መስጠትና መቀበል ብቻ አይደለም:: ሙስና እንደ ቃሉ መከራው በሶስት ቃሎች ብቻ የሚገለጽ አይደለም::
ሙስና በአገርና ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ጫና እጅግ ብዙ ነው:: በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በማህበራዊው በነዚህ ሁሉ ውስጥ ተጽዕኖው አለ:: አንድ ቦታ የሚያበቃ ቢሆን ኖሮ በዚህ ልክ ዋጋ አያስከፍለንም ነበር:: ሙስና ለአንድ አገር የኒውክሌር ያክል አደገኛ ነው:: ሁሉንም ነገር ማውደም ይችላል::
ኢኮኖሚውን፣ ልማቱን፣ ተስፋውን፣ ማህበራዊ መስተጋብሩን ይሄን ሁሉ ሊበጥስ ይችላል:: በጤናው፣ በመማር ማስተማር ሥርዓቱ በሁሉም መስክ ላይ አሻራው አለ:: አገር ደግሞ የነዚህ ሁሉ መሰናሰል ናት:: አንዱ ተበጠሰ ማለት ተያይዞ መልማቱ፣ ተያይዞ መበልጸጉ፣ ተያይዞ ተስፋ ማድረጉ ይስተጓጎላል ማለት ነው:: ለዚህ ሙስናን መዋጋትና ሙሰኞችን ማጋለጥ ተቀዳሚው መፍትሄ ይሆናል::
ሙሰኞች በአስተሳሰባቸው ራስ ወዳዶች ናቸው:: በህልማቸው ውስጥ አገርና ሕዝብ ትውልድም የለም:: የሚጨነቁት ስለራሳቸው ብቻ ነው:: እንዴት አድርጌ፣ እንዴት ዋሽቼ፣ እንዴት አጭበርብሬ ሆዴን ልሙላ እንጂ እንዴት አድርጌ የድሃውን ሆድ ልሙላ አይሉም:: የሚያስቡትና የሚያደርጉት ሰፊውን ማህበረሰብ ባገለለ መልኩ ነው:: ራሳቸውን በመጥቀምና የራሳቸውን የሆነን ብቻ በማገልገል የሚኖሩ ናቸው::
በጣም የሚገርመው ደግሞ የሚሞሉት የሞላ ሆዳቸውን መሆኑ ነው:: በአካውንታቸው ውስጥ ከአገር ተሰረቀ ብዙ ብር እያለ በዛ ብዙ ብር ላይ ሌላ ብር መጨመር ነው:: አንድ ቤታቸውን ሁለትና ሶስት ማድረግ እንጂ ቤት ለሌለው ስለመስራት አይጨነቁም:: ስለራሳቸው በማሰብ፣ ስለራሳቸው በመጨነቅ ወጥተው የሚገቡ ናቸው:: ይሄ አስተሳሰብ በአገር ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመረዳት ጠቢብ መሆን አይጠበቅብንም:: አሁን ላይ አገራችን በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ናት::
ሥልጣን ሕዝብ ማገልገያ እንጂ በሕዝብ መገልገያ አይደለም:: በኢኮኖሚዋ በምትንገዳገድ አገር ላይ፣ ለማደግና ራሷን በምግብ ለመቻል ደፋ ቀና በምትል አገር ላይ ሙሰኞች ታክለውበት ፤ተስፋ ሰንቃ ከዛሬ የተሻለ ነገን ለመኖር በምትታትር አገር ላይ ሌቦችና ራስ ወዳዶች ታክለውበት አስቡት:: እንዴትም ይሁን በአንድ አገር ላይ ሙሰኞች ካሉ የዛች አገር የእድገት ርምጃ ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ውሃ ይበላዋል::
እንዴትም ይሁን በአንዲት ተስፈኛ አገር ላይ ራስ ወዳድ ባለሥልጣናት ካሉ የዛችን አገር ተስፋ ውሃ ይበላዋል:: ይሄ እንዳይሆን መንግሥት እንደመንግሥት በነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ርምጃ ሊወስድ ይገባል:: መንግሥት ብቻ አይደለም ማህበረሰቡም እንደነዚህ አይነት ሌቦችን በማጋለጥ ለአገሩ ውለታ መዋል አለበት:: እንደነዚህ አይነት ድርጊቶች በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በተቀናጀ የጋራ ስራ የሚገቱ ናቸው::
አገር ስትሰረቅ አገር ብቻ ሳትሆን ዜጎቿም ነው የሚጎዱት:: የአገር ሀብት የዜጎች ሀብት ነው:: የአገር ተስፋ የዜጎቿ ተስፋ ነው እናም ሙሰኞችንም ሆነ ሌሎች ለአገር የማይበጁ ድርጊቶችን ማጋለጥ ይጠበቅብናል:: ሙሰኞችን የሚያጠራ ወንፊት ያስፈልገናል:: እነዚህን ግለሰቦች እያጠራ ለሕግ የሚያቀርብ ወንፊት:: ማንነታቸውን፣ የኋላ ታሪካቸውን እያብጠረጠረ ተጠያቂ የሚያደርግ ወንፊት:: ስብዕናቸውን፣ ለአገር ያላቸውን ስሜት የሚመዝን ፍትሃዊ ወንፊት::
አሁን ላይ አገራችን እብቁን ከፍሬው፣ እንክርዳዱን ከስንዴው የሚለይ ወንፊት ያስፈልጋታል:: ሁሉንም በአንድ የሚሰፍር ወንፊት ሳይሆን እንደየስራችን የሚለየን ወንፊት ያስፈልገናል:: በዚህ የእውነት ወንፊት ብላሹን ከጥሩው ካለየን በስተቀር የአገራችንን ተስፋ ማየት አንችልም:: በዚህ የእውነት ወንፊት ነውራቸውን ካላጋለጥን፣ ለፍርድና ለቅጣት ካላበቃናቸው አገራችንን መታደግ አንችልም:: የዚህ ወንፊት አለመኖር ለሙሰኞች የልብ ልብ ይሰጣቸዋል::
ሙሰኞች ነቀዞች ናቸው.. አገር የሚበሉ፣ ትውልድ የሚያመክኑ ነቀዞች:: ነቀዝ ሰብል የሚበላ፣ ምርታማነትን የሚቀንስ፣ የአርሶ አደሩን ልፋት መና የሚያስቀር ተባይ ነው:: ልክ እንደዚህ ተባይ ሁሉ አገር የሚበሉ፣ የአገርን ብልጽግና የሚጎትቱ፣ የትውልዱን፣ የወጣቱን ተስፋ የሚነጥቁ ነቀዞች ናቸው:: እነዚህ ነቀዞች በሃሳባቸው ጽድቅና፣ በተግባራቸው ሚዛናዊነት የላቸውም:: በመስረቅ የሚረኩ፣ በማታለል የሚደሰቱ ናቸው::
አገራችን በነዚህ ነቀዞች ተበልታ ነው ከስፍራዋ የጎደለችው:: አገራችን በነዚህ ነቀዞች ተወራና ተመርዛ ነው ከኋላቀርነት ያልወጣችው:: እነዚህን ነቀዞች መፋለም አለብን:: እንዳይበሉን፣ እንዳያመረቅዙን ልንገታቸው ይገባል:: ሕዝብ የሰጣቸውን ሥልጣን ያላግባብ እንዳይጠቀሙ ከተጠቀሙም ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ አሰራር ያስፈልጋል::
ነቀዝ በመርዝ ነው የሚጠፋው:: የአገራችን ነቀዞችም እንዲጠፉ እንደ መርዝ የበረታ የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል:: እርምጃ መጪውን የሚያስተምር ጥሩ ነገር ነው:: ያጠፉ ካልተቀጡ፣ የሰረቁ ካልተቆነጠጡ፣ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ጉቦ የሚቀበሉ ባለሥልጣናት ካልተጠየቁ መጪው ትውልድ ሙስናን የሚዋጋበት ምክንያት አያገኝም:: ሰርቶ መለወጥን እንጂ ሰርቆ መለወጥን ለልጆቻችን ማስተማር የለብንም::
ቤተሰብ የአገር መሰረት ነው:: ሁሉም ወላጅ ለልጆቹ መልካም ሥነምግባርን በማስተማር ለአገር የሚበጁ አድርጎ ሊያበቃቸው ይገባል:: አሁን ላይ አገር እያበላሹ ያሉ ሙሰኞች በሥርዓት ያላደጉ ናቸው:: እየኮረጀ የተማረና እየሰረቀ ያደገ ልጅ ነገ ላይ በሥልጣኑም ሆነ በማንኛውም ማህበራዊ ሕይወቱ ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ነው የሚፈጽመው::
ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በልጅነታቸው በሥርዓት ያላደጉ ልጆች በሙስናም ሆነ በሌሎች ተያያዝ ጉዳዮች ላይ የመገኘት እድላቸው የሰፋ እንደሆነ ይነገራል:: በባህሪያቸው ብልሹ የሆኑ ባለሥልጣናት ትናንት ላይ ይሄን ካደረክልኝ ይሄን አደርግልሀለው በሚል ቤተሰብ ውስጥ ያለፉ እንደሆኑም ጥናቱ ያክላል::
የልጆቻችን ፈጣሪዎች እኛ ነን:: ለእኛ በጎ ሲሆኑ ነው ለአገራቸውና ለወጡበት ማህበረሰብ በጎ የሚሆኑት:: የሆነ ነገር ስናዛቸው ይሄን አደርግልሃለው ማለት ተገቢ አይደለም:: የሆነ ነገር እየሰጠንና መደለያ እያሳየን ያሳደግናቸው ልጆቻችን ካደጉ በኋላም ከዛ አመለካከት አይርቁም:: ወደሃላፊነት ሲመጡም ያኔ ያደጉበትን ማንጸባረቅ ነው የሚጀምሩት::
ይሄ ደግሞ አንዱና ዋነኛው ሙስናን መለማመጃ መንገድ ነው:: እናም ልጆቻችንን ስናሳድግ መታዘዝ፣ ቤተሰብን ማገልገል ግዴታቸው እንደሆነ በማሳወቅ ይሁን:: ሀገር ብቻዋን በቂ ናት..ሀገር ብቻዋን ለብዙዎቻችን የእውቀትና የጥበብ ቤታችን ናት:: ለልጆቻችን ስለሀግ ፍቅርና ስለታማኝነት ካስተማርናቸው ያ በቂ ነው::
አገር የእኔና የእናተ ሃሳብና ድርጊት ናት:: ይሄ ሃሳባችንና ድርጊታችን ነው ሊያነሳትም ሆነ ሊጥላት የሚገባው:: ሙስና አገር የሚጥል ነቀርሳ ነው:: ሰርተን ለመለወጥ፣ ተምረን ለመቀየር እንጂ በአቋራጭ መበልጸግን እንደ ስኬት ልንቀበለው አይገባም:: ታላላቆቻችን ያለማመዱን ያልተገባ ነገር ብዙ ነው:: አሁን ላይ ብዙዎቻችን የምንማረው አገር ለመጥቀም ሳይሆን ራሳችንን ለመጥቀም ነው::
የሚያበላ ፊልድ/ትምህርት መርጠን የምንማር፣ የሚያበላ ስራ ፈልገን የምንይዝ፣ ሥልጣንና አለቅነትን ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ለመብላት /ለመዝረፍ የምንመኝ ብዙ ነን:: ይሄ አስተሳሰብ ነው የአሁኖቹን ሙሰኞች የፈጠረው:: ይሄ አስተሳሰብ ነው ብዙ ነቀዞችን ወልዶ ያሳደገው:: አስተሳሰባችን መቀየር አለበት:: አገርን ሳንጠቅም፣ ድሀ ማህበረሰባችንን ሳናገለግል የምንገለገለው ነገር የለም::
ለመብላትም ሆነ ለማብላት መጀመሪያ አገር የሚባል ነገር ሊኖረን ይገባል:: በአስተሳሰባችን አገር እያፈረስን፣ በድርጊታችን ተስፋ እየነጠቅን የምንፈጥረው አገርና ሕዝብ የለም:: ከምንም በፊት ለራሳችን ታማኝ መሆን ይኖርብናል:: የራስ እምነት ነው ወደ አገርና ወደ ማህበረሰብ የሚሄደው:: የራስ እምነት ነው ወደ ትውልድ የሚፈሰው:: ሥልጣናችንን ለመብላት ከተጠቀምነው፣ የምንማረው ለመብላት ከሆነ ከእኛ ያለፈች ለልጆቻችን የምትሆን አገር መፍጠር አንችልም::
ሥልጣኔ ለአገር ምርጡን ከማድረግ የሚጀምር ነው:: ሥልጣኔ ለማህበረሰብ ከመልፋት የሚጀምር ነው:: ብዙ ሥልጡን አገራት ሥልጣኔአቸውን ያገኙት ከራሳቸው ቀድመው አገራቸውን በማገልገላቸው ነው:: ዛሬ ላይ የምንቀናባቸው አገራት ልዕልናቸውን ያገኙት ከእኔ በፊት አገሬን በሚል ፍልስፍና ነው:: እኛም ከኔ በፊት አገሬን፣ ከእኔ በፊት ማህበረሰቤን የሚል ሃሳብና በጎ ተግባር ያስፈልገናል::
ለአገራችን ስንለፋ ሰፊ ሃሳብና ሰፊ ድርጊትን አንግበን ነው:: ለራሳችን ስንለፋ ግን በጠበበና ባነሰ ሃሳብና ድርጊት ነው:: ወደሚበጀን ማየት አለብን..የሚበጀን አገር ያለችበት ሰፊ ሃሳብና ድርጊት ነው:: በጠበበ ሃሳብ ሙስናንና ሙሰኞችን ወልዶ ከማሳደግ ባለፈ የምንጠቀመው ነገር የለም:: ከእኔነት የሚሻገር፣ ሩቅ የሚደርስ የሰፋ.. የበረታ ሃሳብና ድርጊት ያስፈልገናል::
በዚህ እውነት ውስጥ ካልቆምን ሙሰኞችን መዋጋትም ሆነ ሙስናን መግታት አይቻለንም:: ሙስና የጠባብ አስተሳሰብ ውጤት ነው:: አስተሳሰባችን ማስፋት አለብን:: በሃሳባችን ውስጥ አገራችንን መጨመር፣ ትውልዱን ማከል ይኖርብናል:: እንዲህ ሲሆን ነው የምንሰፋው::
እየተራመድን ያለነው፣ እየለፋን ያለነው እንደ ሙስና ወደ ኋላ ከሚጎትቱን ነገሮች ጋር ነው:: ወደ ኋላ የሚጎትቱንን ነገሮች ሳናጠራ ከህልማችን መድረስ አንችልም:: የአገር ጠላት የሆኑ ነውሮቻችንን ማስተካከል ስንችል ነው ካሰብነው የምንደርሰው:: በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ እንሁን አገር የማገልገል ልዕልና ሊኖረን ይገባል::
አገር የማገልገል ልዕልና ሲኖረን ነው ከነውር ርቀን በታማኝነት የምንቆመው:: ሙሰኞች አገር የከዱ፣ የገቡትን ቃል ኪዳን ያጠፉ ነውረኞች ናቸው:: በቀን ሶስቴ መብላት በማይችል ማህበረሰብ ውስጥ ሆነው ከድሀ ጉሮሮ የሚቀሙ አረመኔዎች ናቸው:: ሙሰኞች አገር የማገልገል ሞራል የላቸውም:: በሃሳባቸው ውስጥ ለትውልድ የሚሆን አንዳች የለም::
ራሳችንን እንጠይቅ.. ለአገራችን የሚሆን ምን አለን? በድህነት ላስተማረን ማህበረሰብ የሚሆን ምን አለን? ራሳችንን እንጠይቅ.. ከድሃ አገርና ከድሃ ሕዝብ ላይ እየሰረቅን የምንሰራው ቤት፣ የምንነዳው መኪና ነገ እኛን ይዞ ከመጥፋት ባለፈ በረከት የለውም:: ሕይወቱን እንድንቀይርለት እድል ከሰጠን ማህበረሰብ ላይ የምናጎድለው ማንኛውም ነገር ነገ ላይ ሕይወታችንን ከማጉደል ባለፈ ጸጋ ይዞልን አይመጣም::
ሥልጣኔአችንን አገርን ከማገልገል፣ ለማህበረሰባችን በመታመን መጀመር አለብን:: ብዙ ነገሯ ሰጥቶ መቀበል የሆነባት ሀገር ላይ ነው:: እከክልኝ ልከክልህ በሚል ነውረኛ ፈሊጥ አገራችን መድረስ ካለባት ቦታ ሳትደርስ ቀርታለች:: ለአገር የሚጠቅሙ፣ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት አቅም ያላቸው እያሉ ግን ባልተገባ አካሄድ ያልተገባ ነገር እያደረግን ብዙ በረከቶቻችንን ሰውረናል:: ሙስና አገር ከማውደም ባለፈ ሌላ ትርጉም የለውም::
ሙሰኞችን እየቀጣን አገር እንስራ:: የአገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ሌቦችን እያጋለጥን ትውልድ እንቅረጽ:: ዓላማችን አገር ማሻገር ከሆነ አገር በማሻገር ሂደት ላይ ዓላማ የሌላቸውን ነውረኞች ለፍርድ እያቀረብን ይሁን:: ከነውሮቻችን ጋር አብረን እየተጓዝን አገር አንገነባም:: መንግሥት ሙስናንና ሙሰኞችን ለመቆጣጠር ኮሚቴ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: የእኛ ድርሻ የሚሆነው ሙሰኞችንና ብልሹ አሰራሮቻቸውን በማጋለጥ ከመንግሥት ጎን መቆም ነው:: በጠራ ሃሳብ፣ በጠራ ድርጊት ተስፋ ያላት የጠራች አገር ታስፈልገናለች:: አገራችን እንድትጠራ ደግሞ ሙሰኞች መጥራት አለባቸው::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም