የአራራት – ኮተቤ- ካራ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት የአካባቢውን ነዋሪዎች ለከፍተኛ እንግልት እንደዳረገ በተለያዩ የዜና አውታሮች ተደጋግሞ ተነግሯል። ግንባታው ሳይጠናቀቅ ከስድስት ዓመታት በላይ የቆየውን ይህን መንገድ በተመለከተ በዚሁ ጋዜጣችን ላይ አንድ ተስፋ የሚሰጥ ዘገባ ተሰርቶበታል። ዜናው እንዲህ ይላል “የመንገዱ ግንባታ በየካቲት ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል”። ይህን ያለው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ነው። እንዳፋችሁ ያድርግልን።
አራራት – ኮተቤ- ካራ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም ከአራራት ሆቴል በተለምዶ 02 አለፍ ብሎ እስከ ደጃዝማች ወንድራድ ትምህርት ቤት ድረስ በከፊል ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ቆይቷል። ይህ በመጠኑም ቢሆን የትራንስፖርት ፍሰቱን ያቃለለ ቢሆንም ከመንገድ ደህንነትና ከትራፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች ወይም ስጋቶች እየተስተዋሉበት ነው።
መንገዱ ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ስፋት የተሰራ ቢሆንም ከዲዛይን ጋር በተያያዘ ብዙ ሰው ጥያቄ ያነሳበታል። ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡም ከትራፊክና መንገድ ደህንነት ጋር በተያያዘ በሚያቀርቡት የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ የዚህን መንገድ ዲዛይን በተመለከተ ችግሮች እንዳሉበት ሲናገሩ እንደነበር አስታውሳለሁ። በእርግጥ በዚህ መንገድ ላይ ከዲዛይን አኳያ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች እንዳሉ ለመረዳት የግንባታ መሃንዲስ መሆን አያስፈልግም። ማንም ሰው ተመልክቶ የሚረዳው ነው።
በዚህ መንገድ ላይ በዋናነት የሚስተዋለው ስጋት በመንገዱ አካፋይ ላይ የተገነባው ሰፊ የትራፊክ ደሴት ነው። ይህ ደሴት ሙሉ በሙሉ በኮንክሪት የተገነባ ሲሆን እንደሌሎቹ አካባቢዎች አበባ ወይም ሳር ተተክሎበት ከውበት አኳያ የሚሰጠው ፋይዳ እንደሌለ ያየ ሰው ሁሉ ሊመሰክር ይችላል። ይልቁንም ደሴቱ አልፎ አልፎ ከመንገዱ ያልተናነሰ ስፋት ያለው በመሆኑ መንገዱ የተሻለ ስፋት እንዳይኖረው ማድረጉ በጉልህ ይታያል። እሺ ይሄም መሃንዲሶቹ በራሳቸው ሙያዊ እይታ አስቀምጠውት ነው ብለን ብናልፈው እንኳን እያስከተለ ያለውን አደጋ በዝምታ ማለፍ አይቻልም።
ይህ የትራፊክ ደሴት ሲገነባ ከዋናው አስፓልት በመጠኑ ከፍ ተደርጎ ነው። ይህም በተለይም ምሽት ላይ በርካታ ተሽከርካሪዎች ዋናውን መንገድ ስተው እየወጡበት የመገልበጥ ወይም ከተቃራኒ አቅጣጫ ከሚመጣ ተሽከርካሪ ጋር እንዲጋጩ እያደረጋቸው እንደሚገኝ በብዙ አጋጣሚ መመልከት ይቻላል። ይህ ከአሽከርካሪው ችግር ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ማለት አይቻልም። የትራፊክ ደሴቱ ከዋናው አስፓልት ጋር ያለው ልዩነት በትንሽ ሜትሮች ርቀት በግልጽ ካለመታየቱ ጋር በተያያዘና ከሌላኛው አካፋይ መንገድ ጋር ያለው ስፋት አንድ ተሽከርካሪ ብቻ ማሳለፍ የሚችል በመሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት አደጋዎች እየተከሰቱ በመሆኑ ደሴቱ ከርቀት እንዲታይ ለማድረግ ምልክቶች እየተቀመጡ ቢሆንም ሁሉንም ስጋቶች የሚያስቀሩ አልሆነም።
በዚህ በከፊል ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ በሚገኝ መንገድ ላይ ሌላም የሚስተዋል ችግር አለ። ይህ ችግር በእርግጥ ሙሉ በሙሉ ከመንገዱ ዲዛይን ጋር የተያያዘ ባይሆንም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህም አንድ ተሽከርካሪ ከሚጓዝበት በተቃራኒ አቅጣጫ ዞሮ ለመመለስ ረዘም ያለ ርቀት መጓዝን ግዴታ ማድረጉ ነው። የዚህች አገር ብዙዎቹ አሽከርካሪዎች ባህሪ ደግሞ ይታወቃል፣ ረዘም ያለውን ርቀት ሄደው ከመዞር ይልቅ በሚኬድበት መንገድ ዞረው መመለስን ይመርጣሉ። ይህም የትራፊክ ፍሰቱ ላይ ጫና ከማድረግ ባሻገር ግራና ቀኙን አይቶ በሚሻገር ሰው ላይ ሳይቀር አደጋ እንዲፈጠር እያደረገ ነው።
ሌላው በዚህ መንገድ ዙሪያ ትልቅ ችግር የሆነው ጉዳይ ከዋናው አስፓልት ወደ ሶስት ሜትር ገደማ ከፍ ተደርጎ ወደተሰራው ሌላኛው መንገድ ለመሄድ የተገነባው የእግረኞች መሻገሪያ ነው። ይህ ሁለት ሜትር የማይሞላ ስፋት ያለው ጠባብ መሻገሪያ ከሚጠቀመው የሰው ቁጥር ጋር ፈጽሞ የተመጣጠነ አይደለም። በዚህ ላይ የሚለምኑ ሰዎች እንዲሁም መንገድ ላይ ንግድ እየተካሄደበት ይገኛል። መሻገሪያው ሶስት ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው ቢሆንም ምንም አይነት የብረት ድጋፍ አልተበጀለትም።
ይህም የሚሻገረው ሰው ቁጥር መብዛት ከጥበቱ ጋር ተዳምሮ ትንሽ መገፋፋት ቢፈጠር ማንኛውም ሰው ከዚያ ከፍታ ላይ በቀላሉ እንዲወድቅ የማድረግ እድሉ ሰፊ ነው። ከዚያ ከፍታ መውደቅ በራሱ ቀላል አደጋ ባይሆንም የወደቀውን ሰው የሚቀበለው ከስር ያለው አስፓልት ብቻ ሳይሆን አገር ሰላም ነው ብሎ የሚጓዝ ተሽከርካሪ መሆኑ ሲታሰብ ያሳቅቃል። እዚሁ ከፍታ ያለው መሻገሪያ ላይ ህጻናትን ይዘው የሚለምኑ እናቶች፣ አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞች ብዙ ናቸው። የሚሻገር አንድ ሰው ድንገት አደናቅፎት ትንሽ ቢነካቸው እነዚህ ምስኪኖች እጣ ፋንታ አሰቃቂ እንደሚሆን አላፊ አግዳሚው ሳያስብ ቀርቶ አያውቅም።
በቅርብ የተካሄዱ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአስፓልት መንገድ ሽፋን 14 በመቶ መሆኑን ይጠቁማሉ። 80 በመቶ የሚሆነው አደጋ የሚደርሰውም በአስፓልት መንገድ ላይ ነው። ለዚህም የአሽከርካሪዎችና መንገደኛች ግንዛቤ ማነስ፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ደካማ መሆን፣ ያረጁ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መበራከት፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ክፍተት፣ የቁጥጥር ሥርዓቱ ደካማ መሆን፣ የመንገድ ዲዛይንና ጥራት የችግሩ መንስኤዎች ናቸው። እነዚህ ችግሮች የበለጠ እየገዘፉ እንጂ እየቀነሱ እየሄዱ እንደማይገኙ በየጊዜው የሚወጡ ሪፖርቶች አመላካች ናቸው።
ከአሽከርካሪና ከተሽከርካሪ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ያህል ከመንገድ ጥራትና ዲዛይን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመቀነስም የበለጠ ትኩረት መስጠት ለነገ የማይባል የቤት ስራ ነው። ለዚህም የመንገድ ደህንነትን አስቀድሞ በመረዳትና ለጉዳቱ አሳሳቢነት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የሚመለከተው አካል ቢያንስ እንደ ኮተቤው አይነት መንገዶች ለአደጋ መንስኤ የሚሆን ችግራቸውን የማስተካከል እድሉ በእጁ ነውና ያስብበት።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም