ኢትዮጵያ የዳበረ እና የረጅም አገረ መንግሥት ታሪክ ያላት የበርካታ ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ከመሆኗ ባለፈ የብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አገር ናት:: እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸው መለያ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችና ቅርሶች ባለቤት በመሆናቸው አገሪቱ በሚዳሰሱ (ታንጀብል/ Tangible) እና በማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል/ Intangible) ባህላዊ ቅርሶች ሀብት የበለጸገች እንድትሆን አድርጓታል:: በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ዘጠኝ የሚዳሰሱ እና አራት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን በድምሩ 13 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ናት።
አገሪቱም በዓለም ቅርሶች መዝገብ ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች አንዱ የጥምቀት በዓል ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት የጥምቀት በዓል በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ይከበራል:: በዓሉ በዓለም አራቱ ማዕዘናት ቢከበርም፤ በኢትዮጵያ የሚከበረው በማህሌት ሽብሸባ፣ በያሬዳዊ ዝማሬ፣ በልብሰ ተክህኖ አልባስ በአደባባይ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ሥርዓቱ ተዋዝቶ ይከበራል:: ይህ አከባበር በሌላው ዓለም ከሚከበረው ጥምቀት የተለየ ገጽታ ያላብሰዋል:: በመሆኑም ዩኔስኮ ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም የዓለም ቅርሶችን በተመለከተ በደቡብ አሜሪካ በሀገረ ኮሎምቢያ ባደረገው ጉባኤ ጥምቀትን የኢትዮጵያ አራተኛው የዓለም የማይዳሰስ ወካይ ቅርስ አድርጎ መዝግቦታል::
ዩኔስኮ በዓሉን በዓለም ቅርሶች መዝገብ ያሰፈረው የበዓሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቱ ተጠብቆ ከዘመን ዘመን፣ ከትውል ትውልድ እንዲሸጋገር ብሎም በዓለም ቅርስነት መዝገብ ላይ ሰፍሮ ጥበቃ እንዲደረግለት ነው። ቅርሱ በዩኒስኮ በመመዝገቡ በዓሉ ወይም ቅርሱ የዓለም ቅርስ ሆኖ ስለሚታይ የጐብኚዎችን ቁጥር ይጨምራል:: ለቅርሱ የሚደረግለት እንክብካቤ እና ጥበቃም የተሻለ ያደርገዋል:: እንዲሁም ቅርሱ በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት ጥበቃ (ከለላ) ይሰጠዋል። ለአብነት ከመመዝገቡ በፊት በቅርሱ ጉዳት ቢደርስ ወይም በባዕድ ባህል ተጽዕኖ ውስጥ ቢገባ መክሰስ መከራከር የሚችለው በአገሪቱ ሕግና ፍርድ ቤት አግባብ ብቻ ነው። ነገር ግን የዓለም ቅርስ ከሆነ በኋላ በዓለም አቀፍ ሕግጋትና ፍርድ ቤቶች ጭምር መብቱ ይከበርለታል።
አንድ የሚዳሰስም ሆነ የማይዳስስ ቅርስ በዩኔስኮ ከተመዘገበ ቅርሱ ያስመዘገበው አገር ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለም ነው። ከዚህ አኳያ ቅርሱን መጠበቅም ሆነ የበዓሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቱ መከበር ከቅርሱ ባለቤት ባለፈ የዓለም ሕዝብ ኃላፊነት ነው። በመሆኑም በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ወይም በባዕድ ባህል ተጽዕኖ ውስጥ እንዳይገባ ከማንም በላይ የቅርሱ ባለቤት የሆኑ አገራት ሕዝብ ትልቅ ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለባቸው።
ሆኖም አገሪቱ በዓለም ቅርሶች መዝገብ ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ወይም በባዕድ ባህል ተጽዕኖ ውስጥ እንዳይወድቁ ተገቢው ቁጥጥርና ጥበቃ ሲደረግ አይስተዋልም። ለአብነት ከሰሞኑ አገሪቱ በዓለም ቅርሶች መዝገብ ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች አንዱ የሆነው የጥምቀት ክብረ በዓል በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ በመላ አገሪቱ በድምቀት ተከብሯል።
ይህ በዓል የአደባባይ በዓል በመሆኑ ከሌሎች በዓላት በተለየ ያለሰላም አይደምቅም፤ አያምርም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ በአገሪቱ ክፍል ሲካሄድ በነበረው ጦርነት በመላ አገሪቱ በዓሉ ከመቀዛቀዙ ባሻገር ያልተከበረበት ክልልም (የትግራይ ክልል) ነበር። በመሆኑም የበዓሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቱ መስተጓጎል ገጥሞት ነበር ማለት ይቻላል።
በአንጻሩ አሁን ላይ በሰፈነው የሰላም አየር በዓሉ ከምንጊዜውም በላይ በሕብረ-ቀለማት አሸብርቆ በአብሮነት የከተራ እና ጥምቀት በዓል በመላ አገሪቱ፣ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በድምቀት ተከብሯል። ለክብረ በዓሉ መድመቅ የወጣቶች ተሳትፎ ከሁሉም ይልቃል። ወጣቶች ባህልና ትውፊቱን የጠበቀ ባህላዊና ኃይማኖታዊ አልባሳት ለብሰው በዓሉን በያሬዳዊ ዝማሬ፣ በባህላዊ ጭፈራና በሆታ ከማድመቅ ባሻገር ሰላም በማስከበር፣ ሥርዓት በማስያዝ፣ ታቦታቱ የሚጓዙበትን ምንጣፍ በመሸከምና በማንጠፍ፣ ጎዳናዎችን በመጥረግ በዓሉ የደመቀና ኃይማኖታዊ ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን ትልቅ ሚና ሲጫወቱ ተስተውሏል። በጥቅሉ ወጣቶች በሕብረ ብሔራዊ ባሸበረቀ ቀለም በዓሉን በአንድነትና በፍቅር በማክበር ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ደምቃ እንድትታይ አድርገዋል።
በአንጻሩ “ከስንዴ መካከል እንክርዳድ አይጠፋምና” ከባህሉና ከኃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባፈነገጠ መልኩ አንዳንድ ወጣቶች በዓሉን የቁማር ገበያ ሲያደርጉት ተስተውሏል። እነዚህ ሥነምግባር የጎደላቸው ወጣቶች በክብረ በዓሉ ላይ “ላጥላጥ” የተሰኘውን የካርታ ቁማር ጨዋታ፣ “ቢንጎ” የተሰኘውን ቁማር፣ በውሃ የተሞላ የውሃ መያዣ ላስቲክን በኳስ ኢላማ መምታት፣ ውሃ የሞላበት ሳፋ ላይ በተቀመጠ ሳህን ላይ ሳንቲም ውርውሮ ማሳረፍ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ቁማሮችን 10 ብር አስይዞ 50 ብር፤ 20 ብር አስይዞ 100 ብር ለማገኘት እያሉ ቁማሩን ሲያጧጡፉት ተስተውሏል።
እንዲሁም አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ “ሃርሞኒካ” የተባለውን የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ እየነፉ ከኢትዮጵያዊነት ባህልና ወግ እንዲሁም ከበዓሉ ኃይማኖታዊ ሥርዓት ያፈነገጠ ጭፈራ ከማድረግ ባለፈ በአደባባይ የማያውቁትን ሴት ጎትቶ ወደ ጭፈራው መሀል አስገብቶ ከንፈር እስከ መሳም ድረስ የደረሰ በሕግም በሞራልም የሚያስጠይቅ፣ በየትኛውም ኃይማኖት ተቀባይነት የሌለው አጸያፊ ተግባራት የሚያከናውኑ ወጣቶች ተስተውለዋል።
“ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው” ወጣቶች ይህ አይነት እኩይ ድርጊት ሲያካሂዱ በቸልተኝነት ማለፉ የበዓሉን ኃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔ ከመበረዙ ባሻገር ነገ ላይ እንደ አገር የማንወጣው አዘቅት ውስጥ የሚከቱ መጤ ባህሎች አደባባይ እንዲወጡ በር መክፈት ነው። ስለዚህ በዓሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆኑ የበዓሉን ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓት የማስጠበቅ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ነው። ምክንያቱም እንደአገር እና ህዝብ የበዓሉን ባህላዊና ኃይማኖታዊ ሥርዓት ማስጠበቅ ካልተቻለ ዩኔስኮ ከዓለም የቅርስ መዝገብነት ይሰርዝዋል። ይህም በአንድም በሌላ መንገድ ሁሉንም ማህበረሰብ ይጎዳል።
በመሆኑም የሕግ አካላት ከበዓሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓት ያፈነገጠ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ሊያደርጉ ይገባል። ወላጅና ማህበረሰቡም ልጆቻቸውን “ሀይ” ሊሉና ሊመክሩ ይገባል። ቤተክርስቲያንም ከበዓሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔ ውጭ ያፈነገጡ ድርጊቶችን የሚከውኑ ማንኛውንም አካላት ከክብረ በዓሉ ከማገድ ባሻገር በሕግ መጠየቅ ይኖርባታል።
በተለይ መንግሥት ደግሞ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ከሽብርተኞች ጥቃት፣ ከጦርነት ቀጠና ነጻ ከማድረግ ባለፈ ለቅርሶቹ ልዩ ጥበቃና ጥገና ማድረግ እንዲሁም የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በባዕድ ባህል ተጽዕኖ ሥር እንዳይወድቁ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም