ለውጡን ተከትሎ እየተመዘገቡ ካሉ አበረታች ውጤቶች አንዱ ገቢ በማሰባሰብ ሄደት በአገር አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው እመርታ ነው። ይህ በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥታት በኩል እየታየ ያለው ውጤታማ የገቢ አሰባሰብ አገራዊ ለውጡን ለማፋጠን የሚኖረው ጠቀሜታም ከፍ ያለ እንደሆነ ይታመናል።
በአገራችን የገቢ አሰባሰብ የአገረ መንግሥት ግንባታ ታሪካችንን ያህል ረጅም ዕድሜ ቢኖረውም ፤ የእድሜውን ያህል ውጤታማ እንዳልሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህንኑ ችግር ለመፍታትም በየወቅቱ የተለያዩ አዋጆችና መመሪያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። የተገኘው ውጤት ግን የታሰበውን ያህል አልሆነም።
በሕዝቡ ዘንድ አንድም በመንግሥት ደረጃ /በፌዴራል ሆነ በክልል/ በሚሰበሰቡ ገቢዎች ምንነትና ዓላማ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ አለመኖር ፤ ከዚያም ጎን ለጎን በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተለያዩ ጊዜያት የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ ዋነኛ የፈተና ምንጭ ሆነዋል።
ይህንን የገነገነ አገራዊ ችግር ለመፍታት በለውጡ ማግስት ጀምሮ መንግሥት በገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች (በፌዴራል ሆነ በክልል)ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ አድርጓል፤ እያደረገም ነው። ይህንንም ተከትሎ እየተመዘገበ ያለው ውጤት የሚያበረታታ ነው።
ይህም ሆኖ ግን እንደ አገር አሁንም ቢሆን ያለው የገቢ አሰባሰብ ሊሰበሰብ ከሚገባው ጋር ሲነጻጸር ገና ብዙ ርቀት በቁርጠኝነት መጓዝን የሚጠይቅ ነው። በተለይም ገቢ በማሰባሰብ ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በመንግሥት በኩል የሚወሰዱ ርምጃዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
በተለይም ገቢ ሰብሳቢ ተቋማትን ሆነ የገቢ አሰባሰብ ሂደቶችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የተጀመሩ አገር አቀፍ ፕሮጀክቶች በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው በዘርፉ ለተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ስኬት አቅም የሚሆኑበትን አስቸኳይ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።
አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ከግልፅ ሌብነት (ይህን ያህል ክፈል) ጀምሮ በመንግሥት ገቢ የሚደራደሩ የገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮች ጥቂት አይደሉም፤ እነዚሁ አካላት ገቢ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እና በግልጽ እንዳይሰበሰብ እየፈጠሩት ያለውም ተግዳሮት ቀልሎ የሚታይ አይደለም።
መንግሥት የሚያስተዳድረው የሕዝብ ሀብት ከመሆኑ አንጻር የራሱ የሆነ ሀብት የለውም። እነዚህ ኃይሎች በአንድም ይሁን በሌላ የሚደራደሩት በሕዝብ ሀብት ነው። ከዚህ አንጻር በመንግሥት ገቢ ላይ የሚደረግ የትኛውም ድርድር ሁሉንም ዜጋ የሚመለከት ነው።
የሚሰበሰበው ገቢ ዋንኛ ዓላማ መንግሥት እንደ መንግሥት ያለበትን ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኃላፊነቶች በአግባቡ በመወጣት ለዜጎች የተሻለች ሀገር ለመፍጠር መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ጉዳዩ የበለጠ የሁሉንም ትኩረት የሚስብ ይሆናል።
በዘርፉ ያሉ የጥፋት ኃይሎች (ሌቦች) እየሄዱበት ባለው መንገድ እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸው እድል ካገኙ ሊያስከትሉ የሚችሉት ጥፋት የቱን ያህል የከፋ እንደሆነ መገመት የሚከብድ አይደለም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ማኅበራዊ ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎች የሚፈጥሩም ናቸው።
አሁን ላይ (ዛሬ) ሆነን ካሰብነው ደግሞ አገር በዘርፉ እያገኘች ያለችውን ስኬቶች በመናጠቅ የአገር ስጋት ምንጭ መሆናቸው የማይቀር ነው። ይህ ደግሞ መዘዙ ለአገርና ለሕዝብ የሚተርፍ ፤ ከዚያም አልፎ መጪውን ትውልድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው።
ከዚህ አንጻር በገቢዎች አሰባሰብ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመንግሥት ብቻ የሚተውና መንግሥት እንዳደረገ ያድርጋቸው የሚባሉ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የመላውን ሕዝባችንን ንቁ ተሳትፎ የሚፈልጉ፤ እንደ ማንኛውም ሕዝባዊ ትግል ራስን አዘጋጅቶ መታገልን የሚጠይቁ ናቸው!
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም