– ትምህርት ቤቱ የችግሩ መንስኤ የበጀት ውስንነት ነው ሲል ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የችግሩ መንስኤ የአመራር ነው ብሏል
አዲስ አበባ፡- የመማሪያ ግብዓት አቅርቦት እጥረት መኖሩ ተወዳዳሪ እንዳንሆን እንቅፋት ሆኖብናል ሲሉ በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዓይነስውራን ተማሪዎች ገለጹ። የዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ችግሩን ለመቅረፍ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ብሠራም ተደራሽነቱን ማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ችግሩ የአመራር እንጂ በቂ በጀት መድቤያለሁ ይላል። የዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ዓይነ ስውር ተማሪ አብዩ ገብረሚካኤል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጸው፤ ለዓይነ ስውራን ተማሪዎች የጽሕፈት፣ የመንገድ መምሪያ መሣሪያ፣ የመቅረፀ ድምፅና የብሬል ተደራሽነት እጥረት በትምህርት ቤቱ አለ።
ትምህርት ቤቱ ማየት ለተሳናቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚያግዛቸውን የትምህርት ቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ ባለመሟላቱ ከተማሪዎች ጋር በውጤት ለመፎካከር እንቅፋት ሆኖብናል ሲል አብራርቷል። በተጨማሪም በክፍል ውስጥ የሚሰጡ ትምህርቶችንና ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ የሚሰጡ የተለያዩ ትምህርቶችን እንደ መደበኛ ተማሪዎች መከታተል አለመቻሉንና ፈተናውን ጥሩ ውጤት አስመዝግቦ ከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማትን ለመቀላቀል ስጋት እንደፈጠረበት ተናግሯል ።
የዓይነ ስውራንን የመማሪያ ግብዓቶችን ለማሟላት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባና ትምህርት ቤቱም ያለውን ችግር በመረዳት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ችግሮቻችንን ሊቀርፍልን ይገባል ሲል ተማሪ አብዩ ጠይቋል።
የዘጠኛ ክፍል ዓይነ ስውር ተማሪ የሆነችው ሃና ደጀኔ በበኩሏ፤ በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለዓይነ ስውራን ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚገለገሉባቸው የመማሪያ ግብዓት የተደራሽነት እጥረት መኖሩን ተናግራለች።
በትምህርት ቤቱ ለሚገኙ ዓይነስውራን ተማሪዎች የመማሪያ መሣሪያዎች ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ባለመሆናቸው በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ ጉዳት እየደረሰባቸውና ተወዳዳሪም ለመሆን ፈተና እንደሆነባቸው ተማሪ ሀና ገልጻለች። ለዓይነ ስውራን ተማሪዎች የሚያገለግሉ የትምህርት ግብዓቶችን የሚመለከተው አካል በሰፊው በማቅረብ ተደራሽ ያድርግልን ስትልም መልዕክት አስተላልፋለች።
በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የልዩ ፍላጎት ባለሙያ የሆኑት መምህርት ከበቡሽ ብሩክ በተመሳሳይ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ የተደራሽነት እጥረትን ለመፍታት ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ድጋፍ ቢያደርግም ተደራሽነቱ በቂ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል ።
ተማሪዎች በራሳቸው ለትምህርታቸው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን አሟልተው ትምህርታቸውን ለመከታተል የዓይን ስውራን የጽሕፈት መሣሪያዎችና ሌሎች መገልገያዎች ውድ መሆናቸውን የገለጹት መምህርት ከበቡሽ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች እራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩ በመሆናቸው አቅሙ የላቸውም ብለዋል።
የዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመምህራን ልማትና ትምህርት አመራር ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ዓለምዘውድ ደመላሽ በሰጡት ምላሽ ችግሩ መኖሩን አምነዋል። በትምህርት ቤቱ የነበሩትን የልዩ ፍላጎት የመማሪያ ግብዓቶች በሙሉ ለተማሪዎች ማከፋፈላቸውን ገልጸው፤ ለሁሉንም ተማሪዎች ለማዳረስ እጥረት መግጠሙን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ መቀበል ካለበት ውጭ ተማሪዎችን መቀበሉና የበጀት ውስንነት በመኖሩ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የትምህርት ግብዓት የተደራሽነት እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን እንደምክንያት አንስተዋል። ችግሩን ለመፍታት ለተለያዩ ድጋፍ ሰጭ አካላት በማሳወቅ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው ብለዋል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎት መምህርና አካቶ ትምህርት ባለሙያ አቶ ዳንኤል አሥራት፤ ከመንግሥት የሚበጀተው በጀት የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸው፤ የተበጀተው በጀት አፈፃፀም ላይ የትምህርት ቤቶች አመራሮች ላይ ጉድለት መኖሩን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ከታቀደው በጀት በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው የግብዓት እጥረት ሲገጥማቸው ከድጎማ በጀት ላይ ድጎማ የሚደረግ ቢሆንም የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ የተደራሽነት እጥረት አጋጥሞናል ብለው አላሳወቁንም ሲሉም አብራርተዋል።
በተጨማሪም በመዲናዋ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የትምህርት መማሪያ ግብዓት የአቅርቦት እጥረት ሲገጥማቸውና ከክፍለ ከተማ ትምህርት ቢሮ አቅም በላይ የሆኑትን ለከተማ አስተዳድሩ ትምህርት ቢሮ በማሳወቅ ፈጣን ምላሽና መፍትሔ ማግኘት እንደሚችሉ አቶ ዳንኤል አመላክተዋል።
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም