የኦካላሆማ ግዛት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲሠጥ አዘዘች

የአሜሪካዋ ኦክላሆማ ግዛት በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲሠጥ ወስናለች።

ግዛቷ በሁሉም የመማሪያ ክፍል ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲቀመጥ ያዘዘች ሲሆን ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን ተማሪዎች መጽሀፍ ቅዱስን እንዲያውቁ አስተማሪዎች እንዲቀጠሩ መመሪያ አውርዳለች።

ውሳኔውን ያሳለፉት የትምህርት ባለሥልጣናት ተማሪዎች ከሰዎች ጋር እንዴት መኖር እንደሚችሉ፣ አገልጋይነትን፣ ርህራሄን ፣ መልካምነትን እና ግብረገብነትን እንዲማሩ መጽሐፍ ቅዱስ ወሳኝ መሣርያ ነው ብለዋል።

ባለሥልጣናቱ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ለመቅረጽ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመርያ ምንጭ ነበር ያሉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ተማሪዎች ሕግን መከተል እና ማክበርን ያውቁ ዘንድ አስርቱን ትእዛዛት እንዲማሩ ወስነዋል።

በግዛቷ የሚገኙ ሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከአምስተኛ እስከ 12ኛ ክፍል በሚገኙ ተማሪዎቻቸው ላይ መመሪያውን በፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉም አዘዋል።

በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነት የሚጥስ ነው ያሉ የሲቪል መብት ተሟጋቾች በውሳኔው ላይ ትችት ሰንዝረዋል።

ከዚህ ባለፈም በአሜሪካ ሕገ መንግሥት የሃይማኖት ነጻነትን እንዲሁም በሃይማኖችና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነት የሚጠቅሰውን ድንጋጌ በማንሳት ውሳኔ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።

የግዛቷ አንዳንድ የመምህራን ህብረት በበኩሉ ሥነ

ምግባርና ለሕግ መገዛትን ማስተማር መጥፎ ባይሆንም ተማሪዎችን ከአንድ ሃይማኖት ጋር ብቻ እንዲተሳሰሩ ማስገደድ ተገቢ አይደለም ብለዋል። በቅርቡ የአሜሪካዋ ሊውዚኒያ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ 10ቱ ትዕዛዛት እንዲለጠፉ ማዘዟ ይታወሳል።

በዚህ ውሳኔ መሠረት በአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ በሚደረግላቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ እ.አ.አ. ከ2025 ጀምሮ በሁሉም የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ 10ቱ ትዕዛዛት የተጻፉባቸው ፖስተሮች እንዲለጠፉ ተወስኗል።

እ.አ.አ. በ1980 የአሜሪካዋ ኬንታኪ መሰል ሕግ አውጥታ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት የሃይማኖትና መንግሥትን መለያየት ይቃረናል በሚል ውድቅ አድርጎት ነበር።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You