ጊዜው 1940 ዓ.ም ነበር፤ የ12 ዓመቱ ወርቁ በቸርችል ጎዳና አድርጎ ከመንገዱ ዳር ወዲህና ወዲያ ሲል ድንገት አንዲት የቆመች መኪና ከዓይኑ ውስጥ ትገባለች:: ትንሹ ልጅም ጠጋ ብሎ መኪናዋን ይመለከታል:: ከተከፈተው የመኪናዋ መስኮት ውስጥም አንድ የተጠቀለለ ወረቀት አይቶ ብድግ ያደርገዋል:: የተጠቀለለውን ወረቀት ሲገልጠውም በውስጡ አንድ የማያውቀው ድቡልቡል ነገር አገኘ:: ይህ ነገር ምን ይሆን በማለት ለማወቅ ጓጓና በእጁ እንቢ ቢለው ጊዜ በድንጋይ መቀጥቀጥ ጀመረ:: ለመፍታት ሲታገለው ግን በእጁ የያዘው ቦምብ ፈንድቶ ሀገር ምድሩን አናወጠው:: አካባቢውን ባመሰው የፍንዳታው ድምፅ ሲሮጥ የመጣው ሰውም ትንሹን ልጅ አፈፍ አድርጎ ከሆስፒታል አደረሰው:: ሁለቱ እጆቹ ክፉኛ ተጎድተው ስለነበረ ሕይወቱን ለማትረፍ የግዴታ መቆረጥ እንዳለባቸው ሐኪሞቹ ተናሩ:: እጆቹም ተቆረጡ:: ሰዓሊ የመሆን ትልቅ ሕልም የነበረው እንቦቃቅላው ወርቁ የሚያሳሱ እጆቹ በቦንብ የእሳት ነበልባል ሳቢያ ድባቅ ተመቱ። ቤተሰቦቹም ጭምር በእርሱ ተስፋ ቆረጡ። ፈተናው መራራ የሕይወት ጽዋ ነበር። ይህ ልጅ ሰዓሊ ለመሆን ይችላል ብሎ የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እንኳን ተስፋ ያደረገ አነበረም። እርሱ ግን ተዓምረኛ ሰዓሊ ሆነ:: የማይቻለውን ችሎ ተፈጥሮንም አሸነፋት:: ገና በ12 ዓመቱ ለመሸከም የማይቻለውን የተሸከመው ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ዛሬ ላይ ትንግርተኛው የስዕል ሊቅ ለመባል በቅቷል:: የኑሮ ችንካር ቢያደቀውም በዕድሜም 90ዎቹን ለመያዝ ተቃርቧል::
አርቲስት ወርቁ ማሞ በ1927 ዓ.ም በቡልጋ ከተማ ነበር የተወለደው:: ነገር ግን ገና ትንሽ ልጅ ሳለ አባቱ ወደ ጦርነት ዘመቻ በመሄዱ ከእናቱ ጋር አዲስ አበባ ገብተው መኖር ጀመሩ:: እንደማንኛውም ልጅ ሲቦርቅና በእጆቹም ሲጫወት ቆይቶ በድንገቴው የቦንብ ፍንዳታ የተመታውም ከዚህ በኋላ ነበር:: በድባቴ አዘቅት ውስጥ ተዘፍቆ ለመኖር ግን ልቡ አልፈቅድም:: በዚያን ወቅት በእርሱ ላይ ተስፋ ያልቆረጡ ምናልባትም እናቱና ውስጡ የሚንቀለቀለው ጥበብ ነበሩ:: እናቱ ማለት በራስ የመተማመን ጥጉ ናት:: በእጆቹ ሳቢያ የሐኪም ቤት ደጅ መርገጥ የዘወትር ሥራው ነበር:: ከዚህ መለስ ቤት ገብቶ ለማድረግ የሚፈልገው የመጀመሪያውን ነገር እርሳስ ለመጨበጥ እየታገሉ ከስዕል ፍቅር ጋር መፋጠጥ ነበር:: አንስቶ ለመሳል በሞከረ ቁጥር ሁሉ ከተቆረጡት እጆቹ መካከል እርሳሱ ወደ መሬት ይወድቅበታል:: ከአጠገቡ የማይጠፉት እናቱ ደግሞ ከመሬት እያነሱ ያስጨብጡታል:: ከልምዳቸው አንጻር ሀሳብ እየሰጡ እንዲህና እንዲያ ብታደርገው ይሉታል:: ደግሞ እየተንፈራፈረ ሲወድቅ እኔን እያሉ በማንሳት እጅ እንዳይሰጥ በብርታት ወኔ ያቆሙታል:: ወርቁ ልጅ ሳለ ጀምሮ የሥነ ስዕል ጥበብን አፍቅሮ እንዲኖር ያደረጉትም ወላጅ እናቱ ስለመሆናቸው ሁሌም ይናገራል። እናቱ የተዋጣላቸው ሰዓሊ ባይሆኑም በቤት ውስጥ ግን በብዙ መንገድ ጥበቡን የሚከውኑ ድንቅ ሴት ነበሩ። ወርቁ በዕድሜ 60ዎቹን እስኪይዝ ድረስ ሁሉ በሕይወት ነበሩና በእያንዳንዱ ሥራዎቹ ውስጥ አሻራቸው አለበት። የእናትነት ምስል ለወርቁ የተለየ ምስልና የሕይወት ጌጥ ነው። “ያለ እናቴ የትም ለመድረስ አልችልም ነበር” ይለዋል ወርቁ:: ለዚህም ይመስላል ከምንጊዜም ምርጥ ሁለት ሥራዎቹ መካከል አንደኛው “እናቶች” የተሰኘው ስዕሉ ቀዳሚው ነው:: ሌላና ሁለተኛው ደግሞ “ተፈጥሮ” የሚለው ውብና ደማቅ የስዕል አበርክቶው ነው። ከእነዚህ በተለየ መንገድ አንድ ኢትዮጵያዊ ተመልክቶ በስሜት ንዝረት ሊገልጸው የሚችለው ሌላኛው ታላቅ ስዕሉ “ዓድዋ” ሲሆን ከሌሎቹ በተለየም በግዙፍ ሸራ ስሎ ለሀገሩ አበርክቶታል::
አንድ ቀን፤ ወደ አንድ ሰው በማምራት “ሰው ሠራሽና ባዕድ እጄን ይዤ ከምቸገር ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገቡኝ” ያላት ነገር የመግባት ዕድሉን አስገኘችለትና የሕይወቱን አቅጣጫ ቀየረችው:: ወደ ትምህርት ቤቱ ካቀና በኋላ ሰዓሊ የመሆን ሕልሙን ለማሳካት ምቹ ሆነለት:: በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አልፎ ድንቅ ሰዓሊ ለመሆን ከበቃ በኋላ ሁሌም የሚለው አንድ ነገር አለው፤ “እጅ ቢኖረኝ ኖሮ ምን ላደርግበት እንደምችል አላውቅም” ይላል:: የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ ሲናገር “እጆቼን በማጣቴ ይገጥሙኝ የነበሩትን ችግሮች ተላምጄዋለሁ:: ፈተናም የሚሆንብኝ አይመስለኝም:: እንደ ልቤ እሠራለሁ፤ እንደልቤም እንቀሳቀሳለሁ:: ያኔ በእጆቼ የተጠቀምኩባቸው ነገሮች ቢኖሩ ምናልባትም ወንጭፍ ወርውሬ ይሆናል:: የገና በትር ይዤ እንደልቤ ሩርንም ለግቼ ይሆናል:: ምናልባትም ደግሞ ከፈረስ ላይ ወጥቼ ጋማውን ይዤ ጋልቤም ይሆናል:: በጊዜውም እነዚህ ሁሉ ነገሮች ቀሩብኝ ብዬ ተስፋ በመቁረጥ አዲስ ነገር ከመልመድ መንገድ አልወጣሁም:: አንዳችም ነገር ሳይሰማኝ የምፈልገውን ለመሥራት አስችሎኛል” በማለት እጅ ቢኖረኝ ኖሮ ምናልባትም ለዚህ ደረጃ ሳልበቃ እቀርም ይሆናል፤ የሚል ሀሳቡን አካፍሎም ነበር:: የእርሱ ችግር ሁሌም ለሥራው ግብዓትና ለሥራ የሥራው የሚሆን ቦታ ማጣት ነበር:: ከ60 ዓመታት በላይ በስዕል ሥራ ውስጥ ሲቆይ የራሱ የሆነ ስቱዲዮ እንኳን አልነበረውም:: በዚህም ከውሃና አቧራው ጋር ሳይቀር ሲንከራተቱ ከጥቅም ውጭ የሆኑ የስዕል ሥራዎቹ ቀላል የሚባሉ አይደሉም::
በኢትዮጵያ የሥነ ስዕል ጥበብ ማኅደር ውስጥ አርቲስት ወርቁ ማሞ በሁለት ታላላቅ መስመሮች ላይ አርፏል። በሰዓሊነቱ ያበረከታቸው የስዕል ሀብቶቹ ከዘመን ዘመን ተሻግረው በየትውልዱ ሁሉ የሚበሩ ላምባ ናቸው። ጎን ለጎን ደግሞ ከመሥራት አልፎ ሠሪዎችንም የሚቀርጽ ታላቅ ቀራጺ ነው። ከቤተሰቦቹ አንስቶ እርሱን የተጠጉ ሁሉ የሥነ ስዕል ጠበበት ሆነዋል። ከግማሽ በላይ የሆነውን ዕድሜውን ያሳለፈው በመምህርነት ነው። አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ረዥሙን የሥራ ዘመን ያሳለፈበት ስፍራ ነው:: ዕድሜው ገፍቶ በጡረታ እስከተገለለባት ዕለት ከዚያው ነበር:: በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ያለውን ጥበብ ሁሉ ለተማሪዎቹ ሲያድል ቆይቷል። በጡረታ ከትምህርት ቤቱ ከወጣ በኋላም አሁንስ በቃኝ ብሎ እጁን አልሰጠም:: በቀጥታ ወደ አቢሲኒያ የሥነ ጥበብና የሙያ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አቀና:: ሁለቱ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በሥነ ጥበብ መምህርነት ከበርካቶች ደጅ ላይ ደርሷል። በገባባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ ከእግሩ ስር ቁጭ ብለው ጥበብን በመቅሰም የራሱን ደቀመዝሙሮች የሚያፈራ ጉምቱ አስተማሪ ነበር። ለተማሪዎቹ ተቀኝቶ የሚቀርበው እንደ መምህር ብቻ ሳይሆን በአባታዊ የመንፈስ ትስስርም ጭምር ነበር። የቱንም አይነት ተማሪ ቢሆን፤ አይችልም ብሎ የሚንቀው አይገባውም ብሎ ችላ የሚለው የለም። ከእድሜው እየቀነሰ በትርፍ ሰዓትም እያስተማረ መድረስ ካለባቸው ደረጃ ላይ ያደርሳቸዋል። በሙሉ አካል ሆኖ ለመሥራት የሚያታክተውን ነገር እርሱ ግን በሁለት የተቆረጡ እጆቹ መሐከል ብሩሹን አሳርፎ ሌት ከንጋት በዚሁ ትግል ውስጥ ነው። በእነዚያ ሁሉ ዘመናት ውስጥ አስተምሮ በታላቅነት ሰገነት ላይ አስቀምጧቸዋል።
እዚህ ጋር ግን አንድ ሳንደነቅበትና ሳናደቀው የማናልፈው ነገር ለማንሳት ይገባናል:: አንድ የ80 ዓመት አዛውንትን ስናስብስ የሚታይን ምስል እንዴት ያለ ይሆን? ያረጀ፣ የጃጃ ሸበቶ…በሰው አሊያም በከዘራ ምርኩዝ ተደግፎ የሚንቀሳቀስ ወይም ደግሞ ከወገቡ ጎብጦ፣ አይኖቹ ሞጭሙጨው፣ ጉልበቱም የከዳው፣ ሁሉን የተሳነው ዓይነት ምስል እንደሚከሰትልን እርግጥ ነው:: ይሁንና ሰዓሊና መምህሩ ወርቁ ማሞ ግን በሰማንያ ዓመቱ ቆሞ ሲስልና ሲያስተምር ነበር:: ሞት ካልሆነ በቀር እንዴትስ ሰዓሊ ጡረታ ይወጣል? ሰዓሊ ጡረታ አይወጣም:: በሙያው ውስጥ ያሉ ሰዓሊያን ችሎታቸውን የምንመዝንባቸው ሁለቱ መሠረታዊ ነጥቦች ሲኖሩ እነዚህም የንድፍ አወጣጥና የቀለም ማቅለም ጥበቦች ናቸው:: ሰዓሊያኑም ከአንዱ ይልቅ በሌላኛው ላይ በይበልጥ የተዋጣላቸው ሆነው ሊገኙ ይችላሉ:: ከሰዓሊ ወርቁ ፊት ቆሞ ሲስል ለሚመለከት አንድ የስዕል አዋቂ ከሁለቱ አንጻር በቀለም ማቅለም ችሎታው ይበልጥ ይደመማል:: ቀለሞቹን የሚያዋሕድበት የኬሚስትሪ ቀመሩ ሳያስደንቀው አያልፍም:: ዕድሜ ዘመኑን ሁሉ ያሳለፈው ጥሩውን በመሥራት፣ መጥፎውንም በማቅናት ነውና አንዲት የተለየች ባሕሪም አለችው:: በጥሩ የሚሠራው ሲያሞግስ ሌላኛውንም ወደ መንገዱ የሚያስገባው በቃላት አይደለም:: ምን ቢያጠፋ አንዱ በንዴትና በተግሣጽ ጩኸት አይቀርበውም:: ስህተቱን ከማሳየቱ በፊት እራሱኑ መስሎ ጠጋ በማለት በቀልድና በሳቅ እያዋዛ ጥቂት ያጫውተዋል:: ያ ሰው ከሁሉም ነገሮች ነፃ ሆኖ በነፃነት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ሲያረጋግጥ ቀስ አድርጎ ያክመዋል:: ተማሪዎቹ የነበሩ ሁሉ አብዝተው የሚወዱት አንድም በዚሁ ባሕሪው ነበር:: ሰውን ብቻ ሳይሆን እራሱን ማከም ይችልበታል:: ይህን ሁሉ ዕድሜ በጤና ለመቆየትህ ምስጢሩ? ሲባል “መሥራቴ ነው፤ ሁሌም በሥራ ላይ መሆኔ ጉልበቴን ይጨምረዋል እንጂ አይቀንሰውም:: እኔም ከእናቴ ተምሬ ረዥም መንገድ በእግሬ መጓዝን አዘወትራለሁ” የሚል ነው ምላሹ:: ታዲያ ወርቁ ምን ቢናደድ እንኳ ንዴቱን የሚያበርደው ረዥም መንገድ በእግሩ በመንቀሳቀስ ነው::
ወርቁ ካለው ጥበብ አንጻር ቅንጣት ታህሏን እንኳን በኑሮው የታደለ አይደለም። በሕይወቱ ውስጥ ጉስቅልና አድፍጦ የኑሮ ኩታው በብዙ ወይቧል። የእርሱ ሀብትና እርካታው በዙሪያው ያሉ ሰዎችና አድናቂ ተከታዮች ናቸው። ሕይወት ለወርቁ ማሞ የምታነድ እሳት እንጂ የምታሞቅ ፀሐይ አልነበረችም። የስዕል ሕይወትም የማትገፋ ቁልል ተራራ ነበረች። ከጫፏ ላይ ለመድረስ ከስር መወጣጫዋን በከመረ ቁጥር ግማሽ ደርሳ እየተናደች ፍዳውን ታበላዋለች። እርሱ ግን ዳግም የፈረሰውን ለመገንባት ይነሳል እንጂ ከፈረሰው ጋር አብሮ የሚፈርስ አይደለም። የሕይወቱ የመጀመሪያ የአጋጣሚ ዱብዳ እጆቹን አሳጥቷት አለፈ። ወርቁ ፈተናውንም ትዕግስቱንም የእዮብን ያህል ለክቶ ሰጥቶታል። አንድ አልፎ ሁለተኛው ታላቅ ፈተና ድንገቴውን አደጋ አጋብሶ መጣበት። ጊዜው 1970 ዓ.ም ወቅቱ ደግሞ የክረምት ነበር። ከሚኖርባት ቤት ውስጥ በርካታ የቤተሰቡ አባላት ነበሩበት። አንድ ቀን ግን ከባዱን የሕይወት ውርጅብኝ ያዘለው የዝናብ ዶፍ ወረደ። የቤቱን ጣራ ግርግዳ በጎርፍ አጥለቀለቀው። ከቤተሰቡ መሐል የሁለት ሕጻናቶችን ነብስ ቀጠፈ። ወርቁ በእርዳታ ጭምር ከውጭ ሀገራት የሰበሰባቸውን ልዩ ልዩ ቀለማትና የሚሠራባቸውን ቁሳቁሶች እያግበሰበሰ አጥረገረገበት። ብዙ ተስፋ ብዙ ሕልሙን አርግፎ ባዶውን ጨለማ አወረሰው። የሕይወት ክምሩ ተንዶ ከላዩ ላይ ተከመረ። ግን የማያልፉት የለም አለፈ። እከክን የሰጠ ጥፍርን አይነሳም … ለረዥሙ መከራ ትልቁን ትዕግስት ሰጥቶታልና አቀርቅሮም ጥርሱን ነክሶ ሁለተኛውንም ፈተና አለፈው። በስተእርጅናው መጨረሻ ሁሉ ይህን ያነሳባቸው አጋጣሚዎች አያሌ ናቸው።
የስዕል ጥበብ ሥራዎቹን በቁጥር ለማንሳት እጅጉን አዳጋችና አታካች ናቸው:: በመምህርነቱ ያበረከተውንም ሰፍሮ በቃላት ለማስቀመጥ ፈጽሞ የሚቻል አይደለም:: ለሀገሩ እንደደከመ በሀገሩ ምንስ ተደረገለት? ካልን ግን የሚያስተዛዝብ ነው:: ይሁንና ለኑሮው ባይሆንም ለሥራዎቹ ያገኛቸው ጥቂት ነገሮች ነበሩ:: በ1994 ዓ.ም በስዕልና በቅርጻ ቅርጽ ጥበብ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ለመሆን ችሏል:: ከመድረኩ ፊት ወጥቶም ከወቅቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል:: በሌላ ጊዜም ካፒታል ሆቴል ሲያዘጋጀው በነበረው ዝግጅቱ በስዕሉ ዘርፍ ላበረከተው ትልቅ አስተዋፅዖ ወርቁን የሕይወት ዘመን ተሸላሚው አድርጎ ሸልሞትም ነበር:: ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም ወርቁ ማሞ በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ውስጥ ተገኝቶ በክብር ተሞሽሮም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ እስከዚያች ጊዜ ድረስ ላበረከታቸው ሥራዎቹ ምስጋናን ለመቸር ታስቦ ነበር። በዕለቱም በተለያዩ ጊዜያት ተማሪዎቹ የነበሩ ታላላቅ ሰዓሊያንና የቅርቡ የነበሩ ሁሉ በቃላት ለመግለጽ እስኪያዳግታቸው ድረስ ተናግረውለታል። ወርቁ በአለ የሥነጥበብ ትምህርት ቤት ውስጥ ካስተማራቸው ሊህቃን መካከል አንደኛው አንጋፋው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ነበር። የዚያን ዕለትም “ወርቁ በጥበብ ዓለም ውስጥ በጀግንነት የተፈጠረ አንድና ብቸኛ ሰው ነው” ሲል ነበር የገለጸው። ከበርካቶቹ ዘንድ የሚቸረው ክብርና የተለየ አድናቆት ግን ለብዙ ጊዜያት ከውስጡ አንድ ጥያቄን እንዳጨረበት ቆይቷል። መጽናኛዬ የሆነውን ይህን ሁሉ አድናቆት ሰዎች የሚሰጡኝ ስለምን ይሆን?…አካል ጉዳተኛ ስለሆንኩ አዝነው ወይንስ የምር በሥራዎቼ ተደንቀው? የሚል ነበር። እናም ከረዥም ጊዜያት በኋላ ምላሽ አገኘለት። አካል ጉዳቱ ለእርሱ ትልቁ ፈተና አልነበረም። ይልቅስ ከዚያ የገዙፉና በዙሪያው እንደ ጅብራ ተገትረው ያሉ ብዙ አሳሮች እንዳሉም ድንቅ ሰዓሊ መሆኑን አመነ። የአድናቆቱ ምንጭም አካል ጉዳቱ ከወለደው አዘኔታ ሳይሆን ችሎታው ከፈጠረው የስዕል ጥበብ መሆኑን ግን ተረዳ።
አርቲስት ወርቁ ማሞ ዛሬ በዕድሜ 90 ሊደፍን ተቃርቧል። ከእነዚህ መሐከልም ከሰባ በላይ የሆኑትን ያሳለፈው በስዕልና በመምህርነቱ ነው። ሲወድቅ ሲነሳ የሠራቸው የስዕል ሥራዎቹ ቁጥር ስፍር የላቸውም። ግን ደግሞ ገቢ ለማግኘት ሲል ለገበያ አያወጣቸውም ነበርና ያቺ ጠመዝማዛ የኑሮ ዱላ እስከዛሬም ድረስ አልተቃናችለትም። በእርሱ ቦታ ይበልጥ ሸብታ ጎብጣለች። መንፈሱ ብርቱው ወርቁ ግን በበርካታ ልጆችና የልጅ ልጆች ተከቦ እየተመለከታቸው አለ። በዚያ ቤተሰብ ውስጥ ከስዕል ሸራ ፊት ቆሞ ብሩሹን በእጁ የማይጨብጥ የለም። ገና ተወልደው በሁለት እግር ለመቆም እንኳን ሳይችሉ በፊት የሚቀላቸው ነገር የአባታቸውን የስዕል ብሩሽ ማንሳት ነበር:: ልጆቹ በተጠየቁ ቁጥር “እኛ ቤት ስዕል የማትስለው ውሻችን ብቻ ናት” ይላሉ። ለወርቁ ማሞ ከዚህ በላይ ምንስ ሀብት ይኖርና…መጀመሪያውኑ የትውልዱን የሥነ ስዕል ጥበብ ለመሥራት እንጂ የራሱን ሕይወት ለመሥራት የመጣ ሰው አነበረም። ጥበብን ከእናቱ ተቀበለ፤ መልሶም ለልጆቹ ሁሉ አወረሰው። ለራሱ ሳይኖርም ሌሎችን አኖረበት። በሥራዎቹ ሁሉ አዋቂም ታዋቂም ነበር፤ ሕይወትና ኑሮው ግን ከአፍ እስከ ገደፍ አስጨናቂ ነበር:: ተረሳሁኝ ብሎ ግን አያውቅም:: አካል እንጂ ስሜትና መንፈስ አያረጅም ካሉ ማሳያው ወርቁ ማሞ ነው:: ከራስ ቆርሶና አሳንሶ ለተሰጡለት ጥበብ ለማድላትም ሰውኛን ገፎ ወርቁ ማሞን መሆን ያሻል:: አሁንም ረዥም እድሜ፣ አሁንም ትልቅ ጥበብ… ትዕንግርቱ ብዙ ነው ተዓምሩም ይቀጥላል::
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም