ኢትዮጵያን ከኦሊምፒክ ሜዳሊያ ያስተዋወቁ ምርጥ አሠልጣኝ

በድንቅ ብቃታቸው ዓለምን ካስደመሙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጀርባ ምርጥ አሠልጣኞች መኖራቸው እሙን ነው:: ከአትሌቱ ጥረት ባለፈ ሩጫን በአግባቡ የተረዱና በውድድር ወቅት አሸናፊ ሊያደርግ በሚያስችል ቴክኒካዊ እውቀት የተካኑ እነዚህ ጀግና አሠልጣኞች በሃገር ባለውለታነታቸው ስማቸው ሁሌም በክብር ሲነሳ ይኖራል:: ከጥንት እስካሁን ኢትዮጵያ ስሟ በክብር እንዲጠራ ያደረጉ በርካታ አሠልጣኞችን ማንሳት ቢቻልም ዘመናትን መለስ ብሎ ከመነሻው የነበሩ ባለሙያዎችንም ማስታወስ ይገባል:: ኢትዮጵያ የሚለው ስም በክብር ከሚጠራባቸው መድረኮች መካከል በሆነው ኦሊምፒክ የመጀመሪያውን የስኬት መሠረት ድንጋይ ያስቀመጠው ሻምበል አበበ ቢቂላ መሆኑን ማውሳት ለቀባሪው አረዱት ያሰኛል::

ቀድሞ በማይታወቀው በዚህ ውድድር እንዲሁም በአትሌቲክስ ስፖርት ከትውውቁ አንስቶ አስከ ስኬቱ ባለው ሂደት ከጀርባው አትሌት ጀርባ ማን ነበር የሚለው ሲፈተሽ ኦኒ ኒስካነን የሚለው ስም ይከተላል:: እኚህ ሰው የውጪ ዜጋ ቢሆኑም ለኢትዮጵያ እና ለአትሌቲክሷ ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማድረጋቸው ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል:: የዛሬው የስፖርት ማኅደር እትምም ሊያስታውሳቸው ወዷል:: ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን ዘመናዊ የአትሌቲክስ ሥልጠና በኢትዮጵያ እንዲዘወተር ያደረጉ ፈርቀዳጅ ባለሙያ ሲሆኑ፤ 37 ዓመታት በአሠልጣኝነት ማገልገላቸውን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው ታሪካቸው ያወሳል:: በሰፊው የአሠልጣኝነት ዘመናቸውም ሻምበል አበበ ቢቂላን፣ ዋሚ ኢትዮጵያን ከኦሊምፒክ ሜዳሊያ ያስተዋወቁ ምርጥ አሠልጣኝ ቢራቱን፣ ማሞ ወልዴ፣ መርዓዊ ገብሩ፣ አበበ ዋቅጂራ፣… የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን ዕንቁዎችን አፍርተዋል:: እአአ በ1903 የተወለዱት ኦኒ ኒስካነን የክብር ዘበኛ ስፖርት ክፍል አሠልጣኝ የነበሩ ሲሆን፤ እንደ አበበ ቢቂላ ያሉ የክፍሉ አትሌቶች ችሎታ በመደመም ሮም ላይ ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶችን አዘጋጅተዋል::

ኦሊምፒኩ እስኪቃረብ በነበረው ጊዜም ከ2 ሺ ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ተራራማ ቦታዎች ላይ እንዲሁም የ1 ሺ 500 ሜትር ተደጋጋሚ የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን ማሠራታቸውም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ በተሳተፈችበት ኦሊምፒክ የመጀመሪያው ሜዳሊያ ሊመዘገብ ቻለ:: በወቅቱ የነበሩ ድንቅ አትሌቶችን በማሠልጠንና ውድድሮች ላይ በመምራትም ከሮም እስከ ሜክሲኮ ኦሊምፒክ ድረስ መዝለቅ ችለዋል:: የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑት የእኚህ አሠልጣኝ እረፍትም መጋቢት 1976 ዓ.ም ከስቶክሆልም ተሰምቷል::

በ73 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም የተለዩት አንጋፋው አሠልጣኝ በሕመም ምክንያት አስቀድመው ወደሃገራቸው ሄደው የነበረ ቢሆንም በዚያው ዓመት ጥር ወር ላይ ወደኢትዮጵያ በመምጣት በሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ የማራቶን ውድድር ላይ ተገኝተው ነበር:: በወቅቱም የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ከአሠልጣኙ ጋር ቆይታ በማድረግ ሰፊውን የአሠልጣኝነት ልምዳቸውን ‹‹የአትሌቶቻችን አምባሳደር በመሆን ሃገራችንን ከሌሎች አስተዋውቀዋል›› በሚል ርዕስ አስነብቧል::

ያሠለጠኗቸውን አትሌቶች ከአብራካቸው እንዳገኟቸው ልጆቻቸው እንደሚመለከቷቸው እና በመካከላቸውም ከፍተኛ መግባባት እንደነበረ አስታውሰዋል:: ውጤታማው አሠልጣኝ ኢትዮጵያን ከኦሊምፒክ ከማስተዋወቅ አልፎ ሁሌም ከስኬት ጋር እንድትነሳም ምክንያት ሆነዋል:: ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳሊያ ያስመዘገበችበት የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ከመደረጉ አስቀድሞ ለመገናኛ ብዙኃን አበበ እንደሚያሸንፍ ሲናገሩ ምላሹ ሹፈት እንደነበረም ከጋዜጣው ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል:: በባዶ እግሩ የሮጠው ሻምበል አበበ ማሸነፉን ሲረዱ ደግሞ አመለካከታቸው በአድናቆት ተተካ:: ራሳቸው ያሠለጠኑት አትሌት ከሁሉም እንደሚልቅ ቀድመው ቢረዱም አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ መመልከታቸው የፈጠረባቸውን ስሜትም ‹‹አያሌ ደስታዎች ገጥመውኛል፤ የአበበ ማሸነፍ የሰጠኝ ደስታ ግን ከአሁን በፊትም ሆነ በኋላ ሊገጥመኝ አይችልም ›› ሲሉ ነው የሚገልጹት::

እዚህ ላይ እንደ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ 7ኛ በመሆን ውድድሩን ያጠናቀቀው ሌላኛው አትሌት የአበበ ዋቅጂራ ገድል ለምን አለመወራቱ እንደሚከነክናቸውም አልሸሸጉም:: ከአጠቃላይ የጽሑፉ ሐተታ ለመረዳት እንደሚቻለውም ኦኒ ኒስካነን ኢትዮጵያን የትውልድ ሃገራቸው ያህል የሚወዷት መሆኑን ነው:: ከአሠልጣኝነት ባለፈ የኢትዮጵያ ቀይመስቀል አባል በመሆን በዋና ጸሐፊነት እንዲሁም በቦርድ አባልነት ያገለገሉ ሲሆን ለዚህም የክብር ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል:: በስዊድንም ታሪካቸውን የሚያወሳ ዘጋቢ ፊልም ተሠርቶላቸዋል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You