የኮንግረሱ መመሥረት የሲቪል ማኅበራት በሀገራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ተሳትፎ ያሳድጋል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሲቪል እና የሙያ ማኅበራት የጋራ ኮንግረስ መመሥረቱ ማህበራቱ በሀገራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ሲቪል እና የሙያ ማህበራት ኮንግረስ ሰሞኑን ተመሥርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪልና የሙያ ማህበራት ኮንግረስ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን ምሥረታውን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ ኮንግረሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የሙያ ማኅበራት በሀገራዊ ጉዳዮች ንቁና ሁለተናዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንዲሁም የእርስ በርስ መደጋገፋቸውን እንዲያጠናክሩ ይረዳል።

ኮንግረሱ 11 ዝርዝር ዓላማዎች እንዳሉት ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊ የሆኑ የሲቪል እና የሙያ ማኅበራት ድርጅቶች መብትና ግዴታቸውን ተገንዝበው እንዲንቀሳቀሱ፤ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፤ ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የሚያግዝም ነው ብለዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ኮንግረሱ የኅብረቱ አባላት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ አሠራራቸው ሕግና ደንብን በጠበቀ መንገድ እንዲሆን እንዲሁም በነጻነት እንዲሠሩ ይሰራል፡፡ ተሳትፏቸውም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሆዎችን ባከበረ መልኩ እንዲሆን የበለጠ አቅም ይፈጥራል።

ኮንግረሱ የልምድ ልውውጥ መድረኮችን በማመቻቸት የክህሎት፣ የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በማድረግ ከወቅቱ ጋር ሊያራምዱ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን የሚያስችል መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ የግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ ሥራዎችን የሚያበረታቱ ተግባራትን ለማከናወን ያለመ ነውም ብለዋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የሙያ ማኅበራት አባላት በበኩላቸው፤ የኮንግረሱ ምስረታ የሚበረታታና ከዚህ ቀደም ተነጣጥለው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ማህበራትን ወደ አንድ የሚያመጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በርካታ የሲቪል ማህበራት ቢኖሩም የሚጠበቅባቸውን ያክል ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል ያሉት የሲቪል ማህበራት አባላቱ፤ በዚህም ምክር ቤቱ የከዚህ ቀደሙን ተሞክሮ በመውሰድና ያሉ ችግሮችን መለየት ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በምሥረታ መርሃግብሩ ኮንግረሱ እንዲመሠረት አስተዋፅኦ ላበረከቱ የሲቪል ማህበራት እውቅና የተሰጠ ሲሆን፤ የኮንግረሱን ዓላማ የሚደግፉ ሕጋዊ የሲቪል እና የሙያ ማኅበራት የኮንግረሱ አባል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You