ወጣቱ ለሀገሩ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዳማ፦ ወጣቱ ዜጋ ለሀገሩ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

ሦስተኛው የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን መደበኛ ጉባዔ ትናንት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል። በወቅቱ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን እንደተናገሩት፤ ወጣቱ ለሀገሩ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል።

የሀገራችንን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ወሳኝ መሣሪያ ነው ያሉት አፈጉባዔዋ፣ የወጣት አደረጃጀቶች ወጣቱ በልማት ዘርፍ ሚናውን እንዲወጣ በማስቻል ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል።

ፌዴሬሽኑን ጨምሮ ሌሎችም የወጣት አደረጃጀቶች፣ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ፍላጎቱን ለማሟላት በህሕዝብና በመንግሥት መካከል ድልድይ ሆነው እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።

የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በክልሉ ብሎም በሀገራዊ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሠላም ግንባታ ሥራዎች ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ወይዘሮ ሰአዳ፣ በቀጣይም በሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴ ሁሉ ንቁ ተሳትፎው እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የፓን አፍሪካ የወጣቶች ህብረት ዋና ፀሃፊ አቶ መሀመድ ቤንሂን በተወካያቸው በላኩት መልእክት በአህጉራችን ከሚገኙ የወጣት ፌዴሬሽኖት የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን በቁጥር ትልቁ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሀገራችን የክልል የወጣት ፌደሬሽኖች መካከል የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በጣም ትልቅ ቁጥር ያለው መሆኑን አመላክተዋል።

የዛሬ ውሳኔዎቻችሁና ተግባራችሁ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለአህጉራችን እመርታ ያለው በመሆኑ፣ በሚገባ ልታጤኑበት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ እንዲሁም የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታረቀኝ አብዱልጀባር በበኩላቸው፤ ትናንት አባቶቻችን በከፈሉልን መስዋዕትነት ዛሬ በአንድነት መደራጀች ችለናል ብለዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢና መሪ የሆነው ወጣትም ሀገሩን አስከብሮና አልምቶ ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

የወጣቶች በአንድነት መደራጀት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ወጣቱ በማህበራዊና ሌሎችም ዘርፎች የሚጠበቅበትን ለሀገሩ እንዲያበረክትና ለአመራርነት እንዲበቃ ትልቅ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል።

አቶ ታረቀኝ እንዳስታወቁት፤ ወጣቱ በተለይም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በልማት፣ በሠላምና በሌሎችም ማህበራዊ ዘርፎች በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህም ከፍተኛ ውጤትና ለውጥ መጥቷል።

አያይዘውም፣ ወጣቱ ለነገዋ ኢትዮጵያ መፃኢ እድል መሳካት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተረድቶ ሀገራችንን በኢኮኖሚ ሊያሳድጉና ሠላምን በሚያስጠብቁ ተግባራት ላይ በጋራ ሊቆም ይግባል ብለዋል።

በጉባዔው የተገኙት የአማራ ወጣቶች ፌዴሬሽን ተወካይ ወጣት ዘነበ በለጠ፤ ጉልበታችን አንድነታችን ነው ያሉ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑ ከሌሎች ክልሎች ወጣቶች ጋር በአንድነት ለሀገር ሠላም እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በፌዴራሽኑ ጉባዔ የአፍሪካ ወጣቶች ማህበር ተወካይ ወጣት አልዓዛር ሰሎሞንን ጨምሮ የሌሎች ክልሎች ወጣት ፌዴሬሽን ተወካዮችም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን  ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You