ከመደበኛ ባላይ ዝናብ ሊያጋጥም ስለሚችል ጥንቃቄ እንዲደረግ ኢንስቲትዩቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ክረምት ከመደበኛ ባላይ ዝናብ ሊያጋጥም ስለሚችል አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።

በኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ከባድ የክረምት ዝናብ በሚፈጥረው “ላሊና” ምክንያት በቀጣይ ጊዜያት ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ሊፈጠር ይችላል።

ከባድ የዝናብ ስርጭቱ ሊያስከትል የሚችለውን ጎርፍና መሰል ጉዳት ለመከላከል ተቋማት የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን አጠናክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አስረድተዋል።

የዘንድሮው ክረምት በላሊና ተጽዕኖ ሥር እንደሚሆን አመላክተው፤ ላሊና በክረምት ወቅት ሲያርፍ በተለይም የክረምት ዝናብ ተቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንዲያገኙ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በዘንድሮው የክረምት ወቅት በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በአብዛኛው ኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በአዲስ አበባ ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እንደሚኖር ገልጸዋል።

የዝናብ ስርጭቱ የመኸር የግብርና ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያስችል፤ እንዲሁም በሀገሪቱ የሚገኙ የ12 ተፋሰሶችን የውሃ መጠን ለመጨመር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ከዚም ባሻገር የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ አስረድተዋል።

በአንጻሩ ካለፈው የበልግ ወቅት ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናብ ተስተውሎ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር አሳምነው፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ 40 በሚደርሱ አካባቢዎች ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡

አሁንም በከተሞችና ለጎርፍ ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጎርፍ እንዳይከሰት ከወዲሁ ማህበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት የቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪ በምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍል፣ በምዕራብና ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች ላይ የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችል ገልጸው፤ ማህበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት በተለይም ለትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን ለመከላከል አካባቢያቸውን ውሃ ያቆሩ ሥፍራዎችን ማጽዳት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በከተሞች አካባቢ ድንገታዊ ጎርፍ እንዳይከሰት ማህበረሰቡ በየአካባቢው ያሉትን የውሃ መፍሰሻ ቱቦዎችን ማጽዳትና መንከባከብ እንዳለበትም ዶክተር አሳምነው አመላክተዋል፡፡ ተቋማት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ተግባራትን አጠናክረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You