የደርግ አመሠራረት እና የአብዮቱ 50ኛ ዓመት

የደርግ ሥርዓተ መንግሥት አመሠራረት በተለይም በዚህ ዓመት በሰፊው ተወርቶበታል:: ብሔራዊውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጨምሮ ብዙ መገናኛ ብዙኃን የታሪክ ምሑራንን እና ፖለቲከኞችን እየጋበዙ ብዙ ትንታኔ አሰርተውበታል:: በተለይም በዚያ ዘመን በተሳታፊነትም ሆነ በነዋሪነት (በታዛቢነት) የነበሩ ትዝታቸውን እንዲያካፍሉ ተጋብዘዋል:: ይህ ሁሉ የሆነበት ምክንያት ዘንድሮ 50ኛ ዓመቱ ስለሆነ ነው:: ለዚህ ዘመናት የኖረው የኢትዮጵያ ንጉሣዊ ሥርዓት ከተገረሰሰ እነሆ ዘንድሮ 50ኛ ዓመት ሆነው:: የአብዮቱ የመጨረሻ ግብ የሆነው የደርግ መንግሥት ምሥረታ እነሆ በዚህ ሳምንት 50 ዓመት ሆነው:: በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ50 ዓመታት በፊት የነበረውን አብዮት እና የደርግን አመሠራረት እናያለን:: ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ::

ከ29 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 19 ቀን 1987 ዓ.ም በአዲስ አበባ የወቅቱ የግብፁ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገ:: ሙባረክ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በወቅቱ ስያሜው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 31ኛውን መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ለመታደም ነበር:: በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 2፡00 አካባቢ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱት የግብፁ መሪ ከወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ ጋር ፕሮቶኮላዊ አቀባበል ተደርጎላቸው ጥይት በማይበሳው ተሽከርካሪያቸው ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉዞ ተጀመረ::

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ገና 110 ሜትር ወጣ እንዳሉ ለረጅም ጊዜ ሁኔታውን ሲያጠና እና በዕለቱም ሲጠባበቅ የነበረው አሸባሪ ኃይል የግብፁ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ ተኩስ ለመክፈት በተሽከርካሪ መንገዱን ዘጋ:: ይህኔ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች እንዲቆም ተጠየቀ:: ለሽብር የተዘጋጀ ነበርና አንድ የኢትዮጵያን የፀጥታ ኃይል ተኩሶ ጣለ:: ቀጥሎም እየተጠጋው ያለው የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ተሽከርካሪ ላይ አከታትሎ ተኮሰ:: በዚያው ቅጽበት ግን አንደኛው አሸባሪ ያነጣጠረውን ሳይተኩስ ከኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይል በተተኮሰ ጥይት ጭንቅላቱ ሲበተን ታየ:: ቀጥሎም ሌላኛው አሸባሪ አሁንም በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይል በተተኮሰ ጥይት የእግረኛው መንገድ ላይ ሲወድቅ ታየ:: የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ሙባረክ ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ የአሸባሪዎቹን ዒላማ አከሸፉት:: ሙባረክም ወዲያውኑ በሠላም ወደ ሀገራቸው ሄደው፣ የኢትዮጵያን መንግሥትና የፀጥታ ኃይል አመስግነው በሠላም መድረሳቸውን አሳወቁ:: ብዙ የሴራ ትንታኔዎች የተደረጉበት ሲሆን፤ እነሆ ያ ክስተት በተለያዩ አጋጣሚዎች ይታወሳል::

ከ79 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 19 ቀን 1937 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ላይ፣ በሳንፍራንሲስኮ የጦር መታሰቢያና ኪነ ጥበብ ማዕከል ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የቃል ኪዳን ሰነድ (የመመሥረቻ ስምምነት /ቻርተር) ፈረመ:: ቻርተሩ ከሚያዝያ 17 ቀን 1937 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወራት ያህል ውይይት ሲደረግበት ከቆየ በኋላ ለመጨረሻ የፊርማ ስምምነት ክፍት ሆኖ ፊርማው የተጀመረው በዚሁ ቀን (ሰኔ 19 ቀን 1937 ዓ.ም) ነበር::

ከ100 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 20 ቀን 1916 ዓ.ም ሁለገቡ አርቲስት ተስፋዬ ሳሕሉ (አባባ ተስፋዬ) ተወለዱ:: በልጆች ፕሮግራም የታወቁት እና ለልጆች ፕሮግራም አርዓያ የሆኑት አባባ ተስፋዬ፤ ከ59 ዓመታት በፊት ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም የልጆች ጊዜ የተሰኝ ፕሮግራም እንዲኖር ሀሳቡን አቅርበው በማፀደቅ የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተዋወቃቸውን ዝግጅታቸውን ለ42 ዓመታት በአባትነት መርተዋል:: ፕሮግራማቸውን ሲጀምሩ ‹‹ጤና ይስጥልኝ ! … የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምናችሁ ልጆች!›› እያሉ አቅርበዋል። በበርካቶች ዘንድ የሚታወስና የልጆች ፕሮግራም አርዓያ ሆኖ ቀጥሏል::

ከ88 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 20 ቀን 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ወጣት አርበኞች የመሠረቱት ‹‹የጥቁር አንበሳ ጦር›› ነቀምት፣ ወለጋ አካባቢ ሰፍሮ በነበረው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር አየር ኃይል ላይ ጥቃት ከፍቶ በእሳት አወደመው። የጥቁር አንበሳ ጦር በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት በአርበኝነት የተሳተፉ የሆለታ ገነት ጦር ምሩቃን እና በውጭ የተማሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የመሠረቱት ፀረ ፋሽስት እንቅስቃሴ ነው። በጣሊያን ላይ ዘመናዊ የጦር ውጊያ በማሳየት ብቻ ሳይሆን በጥንታዊ መንገድ ለሚዋጋው የኢትዮጵያ ገበሬ አርበኛ ዘመናዊ የውጊያ ስልትን በማስተማር የጥቁር አንበሳ ጦር ያደረገው አስተዋፅዖ ቀላል አልነበረም። የሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት ፋሽስት ጣሊያን ከሀገራችን ተባሮ ንጉሠ ነገሥቱ ተመልሰው ከመጡ በኋላ በ1935 ዓ.ም እንደገና ተመሠረተ። የጦር ትምህርት ቤቱ በአፍሪካ አንጋፋው በዓለማችንም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት ከተመሠረቱ ጥቂት የጦር ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው።

ከ4 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት 3፡00 አካባቢ የአርቲስት ሃጫሉ መገደል ተሰማ:: ከእናቱ ወይዘሮ ጉደቱ ሆራ እና ከአባቱ ከአቶ ሁንዴሳ ቦንሳ በ1978 ዓ.ም በአምቦ የተወለደው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፤ በሙዚቃዎቹም የኦሮሞን ትግል የሚገልጹ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ የኖረ ነው:: ሃጫሉ ከዘፈን ባሻገር ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ነፃነት በመታገሉ ለኦሮሞ ሕዝብ ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን እንደ ታጋይ ይታያል:: አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን፤ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ለብዙዎች ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ተገሏል:: እነሆ ሥራዎቹና ታሪኩ ግን ሲታወስ ይኖራል:: የአርቲስት ሃጫሉን ድንገተኛ ግድያ ክስተቶች በተመለከተ ዝርዝሩ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በታተመ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይገኛል::

ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን ለዓለም መንግሥታት ማህበር (League of Nations) ተወካዮች አሳወቁ:: ንጉሠ ነገሥቱ ጀኔቫ (ስዊዘርላንድ) በሚገኘው የመንግሥታቱ ማኅበር ተወካዮች ፊት ቀርበው የፋሽስት ወረራ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት የደፈረ ተግባር እንደሆነ በአማርኛ ቋንቋ አስረድተዋል:: በወቅቱም ወደ ስብሰባ አዳራሹ ገብተው የነበሩ የኢጣሊያ ጋዜጠኞች የንጉሠ ነገሥቱን ንግግር በጩኸትና በጭብጨባ ለማቋረጥ ጥረት አድርገው ነበር:: ይህ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለመንግሥታቱ ማኅበር ማሳወቅ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ በጉልህ ሲጠቀስ ይኖራል::

አሁን ወደ ደርግ አመሠራረት እና የአብዮቱ 50ኛ ዓመት ጉዳዮች እንሂድ ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት፣ በተለይም ለግማሽ ክፍለ ዘመን የኖረውንና በኢትዮጵያ የመጨረሻ የሆነውን የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ንጉሣዊ ሥርዓት ያስወገደው ወታደራዊው ደርግ የተመሠረተው በዚህ ሳምንት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ነው::

የታሪክ ባለሙያዎች ደርግ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን ያስወገደበትን መንገድ ‹‹አዝጋሚው መፈንቅለ መንግሥት›› ይሉታል:: ምክንያቱም አንድ ጊዜ አይደለም ያስወገዳቸው:: የደርግ ምሥረታ ራሱ አንድ ጊዜ አይደለም:: ሰኔ 21 ቀን በይፋ የተመሠረተበት ይሁን እንጂ ወታደሮቹ ሀሳቡን ከጠነሰሱትና የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴውን ከጀመሩት ቆይተዋል::

ከታሪክ ባለሙያው ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983››፣ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› መጽሐፎች እና ከተለያዩ ድረ ገጾች ባገኘናቸው መረጃዎች ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የተመሠረተውን የደርግ መንግሥት ታሪክ እንዲህ እናስታውሳለን::

ደርግ የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ቡድን ወይንም ኮሚቴ ማለት ነው። ይህን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ለሥርዓቱ መገለጫነት የተጠቀመው ግለሰብ ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ ሲሆን ቀኑም፤ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ነበር።

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአራተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር መምሪያ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ መለዮ ለባሾች በየካቲት ወር ስለፈነዳው አብዮት ከሰኔ 19 ጀምሮ ውይይት ማካሄድ ጀመሩ:: ደርግ በዝቅተኛ መኮንኖች (ከኮሎኔል ማዕረግ በታች የሆኑት ማለት ነው) ከተመሠረተ በኋላ በዚያው ቀን ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም የደርግ ሊቀመንበር በመሆን ተመረጡ::

በ1953 ዓ.ም የተሞከረበትን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ፤ የንጉሡ ሥርዓት የተለያዩ ጥገናዎችን ሲያደርግ ቢቆይም በ1966 ዓ.ም አብዮቱ ፈነዳ:: አብዮቱን የጀመረው የወታደሩ መደብ ሲሆን፤ ነገሌ እና ሲዳሞ ላይ ሰፍሮ የነበረው የምድር ጦር ሠራዊት አዛዥ መኮንኖቻቸውን ሲያግቱ ይጀምራል። ጉዳዩ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚኖሩ የሠራዊቱ ክፍሎች ድጋፍን በማግኘቱ በወታደሩ መደብ ከመዛመቱም ባሻገር ወደ ተቀረው ዜጋም በመዝለል አብዮቱ ተቀጣጠለ:: አሁንም የንጉሡ መንግሥት ብዙ ጥገናዎችን እያደረገ ነው::

የዘውዱ መንግሥት አብዮቱን ለማርገብ የተለያዩ ለውጦችን አድርጓል:: ለምሳሌ አክሊሉ ሃብተወልድን አንስቶ እንዳልካቸው መኮንንን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጓል:: ለወታደሩ ልዩ ደመወዝ ጭማሪ አድርጓል፤ ሊተገበር የነበር የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ለውጥን በተነሳበት ተቃውሞ ምክንያት አስቁሟል:: ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ሞክሯል። ይሄ ሁሉ ግን የወታደሩን አዝጋሚ መፈንቅለ መንግሥት ማስቀረት አልቻለም::

ሰኔ 21 ቀን በአራተኛ ክፍለ ጦር የተመሠረተው ደርግ የቀድሞውን ባለሥልጣናት ማሰር ጀመረ:: ከሐምሌ 2 ቀን 1966 ዓ.ም ጀምሮ እስረኞቹ ጋዜጣና ራዲዮ እንዳያስገቡ ተከለከሉ:: ጠያቂዎች እስረኞችን የሚጎበኙት በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ጧት ብቻ ነበር:: ከሐምሌ 9 ቀን 1966 ዓ.ም በኋላ እሥረኞች ከነበሩበት የጎፋ ሠፈር ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ተዛወሩ::

እንዲህ እንዲህ እያለ የቆየው ደርግ፤ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሡን ገርስሶ መንግሥት መሆኑን በይፋ አወጀ:: አሁን ደርግ የሀገሪቱ መንግሥት ሆኗል:: ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን መውረዳቸውን፣ ሕገ መንግሥቱ መሻሩን፣ ፓርላማው መዘጋቱን አወጀ::

አላግባብ የበለፀጉ፣ ፍርድ ያጎደሉ፣ አስተዳደር የበደሉ የተባሉ የቀድሞ የንጉሡ ባለሥልጣናት ሁሉ በጦር ፍርድ ቤት የሚዳኙ መሆኑን ደርግ በአዋጅ አስታወቀ:: በዚሁ ዕለት የንጉሡ የልጅ ልጅ እና የባሕር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ ተይዘው ከእሥረኞቹ ጋር ተቀላቀሉ:: እንዲህ እንዲህ እያለ ደርግ የታሳሪዎችን ቁጥር እያበዛው መጣ:: በመጨረሻም፤ ደርግን ክፉኛ ያስወቀሰው 60 የጦር መኮንኖችንና ባለሥልጣናትን የረሸነበት ድርጊት ተፈጸመ::

ደርግ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር በይፋ ተመሥርቶ፣ መስከረም 2 መንግሥት መሆኑን አውጆ፤ ሀገር ባስተዳደረበት ዘመን በጨካኝነት የተገለጸውን ያህል፤ የሀገር ዳር ድንበር በማስከበርና የውጭ ወራሪን አፈር ድሜ በማስበላት ይታወቃል:: ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ታሪካዊ አዋጆችን አውጇል::

የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም «የገጠር መሬት አዋጅ» እና ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ.ም «የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ» በመባል የሚታወቁት ሁለት አዋጆች ተጠቃሽ ናቸው።

1966 ዓ.ም ተከትሎ የመጣው ለውጥ ቀደም ሲል የነበረውን የርስት ጉልት ግንኙነት በመሻር በመሬት ላይ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል:: የደርግ ሥርዓት ይከተል በነበረው የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም በመመራት ኢኮኖሚውን የሚመሩትን ዋና ዋና ነገሮች ከግል ባለቤትነት ወደ ሕዝብ ባለቤትነት አሸጋግሯል:: መሬትም የገጠር መሬትን የሕዝብ ሀብት ለማድረግ በሚል አዋጅ ቁጥር 31/67 የሕዝብ ሀብት በሚል ታወጀ:: አዋጁም መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለውን ጥብቅ የሆነና የመሬት ጉዳይን ከሌሎች ንብረቶች የሚለየውን ገደብ ይዞ ብቅ ብሎ ነበር::

የገጠር መሬትን የሕዝብ ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 31/67 አንቀጽ 5 አንድ የመሬት ተጠቃሚ በይዞታ የያዘውን መብት መሸጥ፣ መለወጥ፣ በስጦታ ማስተላለፍ፣ በማስያዝ፣ በወለድ አግድ ወይም በሌላ ሁኔታ ማስተላለፍ እንደማይችል ገደብ ያስቀምጣል:: ደርግ፤ ንጉሣዊ ሥርዓቱን ከመገርሰሱ ባሻገር በእነዚህና በሌሎች አዋጆች ይታወሳል::

የአብዮቱን 50ኛ ዓመት አስመልክቶ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የአብዮቱ መነሻ ምክንያቶች ነባራዊ ሁኔታዎች እና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታዎች ናቸው:: ነባራዊ ሁኔታዎች ማለት በንጉሣዊ ሥርዓቱ አገዛዝ ዘመን የነበሩት ኢ-ፍትሐዊ አሠራሮች ማለት ነው:: የጭሰኛና ባላባት ሥርዓት መኖሩ አንዱ ነው:: ‹‹መሬት ለአራሹ›› የሚለውን የተማሪዎች እንቅስቃሴ የፈጠረውም ይሄው አሠራር ነው:: አገዛዙም ፍጹም ንጉሣዊ ብቻ መሆኑ አብዮቱን ወለደ::

የሥነ ማኅበረሰብ ተመራማሪው የራስ ወርቅ አድማሴ (ዶ/ር) ‹‹አብዮት›› የሚለውን ቃል ሲያብራሩ፤ የግብርና አብዮት ነበር፣ የኢንዱስትሪ አብዮት ነበር፤ አብዮት ሲባል ለፖለቲካ እንዳልሆነ ገልጸው፤ የ1966ቱ አንድ የአብዮት አይነት እንደሆነ ይናገራሉ::

የአብዮቱ 50ኛ ዓመት ሲታወስ ዋናው ነገር ምን እንማር? የሚለው እንደሆነ ብዙዎች አስተያየት ሲሰጡበት ነበር:: የአስተያየቶች ይዘት ሲጠቃለል፤ የ1966 አብዮተኞች ለትምህርት ወደ ውጭ ሀገራት ሲሄዱ የሠለጠኑ ሀገራትን ተመለከቱ፤ ከሀገራቸው ሁኔታ ጋር ሲያነፃፅሩት ሰማይና ምድር ሆነባቸው:: ለውጡን ቢመኙትም ዳሩ ግን የሀገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነበርና ድንገተኛ ንቃት ሆነ:: ከአብዮቱ በኋላ የመጣው መንግሥትም የተፈለገውን ዴሞክራሲ ሳያስገኝ ቀረ:: በመሆኑም ከዚያ ስህተት በመማር ከእርስ በእርስ መጠላለፍና መጠፋፋት በመላቀቅ ወደ ሠላምና ዴሞክራሲ መሄድ እንደሚያስፈልግ ብዙዎች መክረዋል::

ወደ ታሪክ ትውስታችን ስንመለስ፤ የኢትዮጵያን ንጉሣዊ ሥርዓት ለማስወገድ የተጀመረው አብዮት እነሆ 50 ዓመት ሆነው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You